ስሜት፤ ጥልቅ እሳቤና ውበት የስነ ስዕል ጥበብ ዋነኛ መቆሚያው ነው። ቀለም አዋህዶ ልዩ ውበት መፍጠር፣ ብሩሽን ከሸራ ጋር አዋዶ ታሪክን መንገር፣ የተለየ እይታን በልዩ ክህሎት በመታገዝ ጥበባዊ በሆነ መንገድ ማሳየት የሰዓሊያን ተግባር ነው። ሰዓሊ በፈጠራ ስራው የተለየ ስሜቱን ይገልፅበታል፣ አስተሳሰቡን ያንፀባርቅበታል ወዲህ ደግሞ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ውበትን ያጎለብታል፤ ያሳይበታልም።
በስዕል ጥበብ ይደምቃል፣ አገርና ባህል ማንነትና ውበት ይተዋወቃል። ዛሬ ላይ እጅጉን የረቀቀው የስዕል ጥበብ ጅማሮው ከስነፅሁፍ ጥበብ የቀደመ መሆኑ ይነገራል። በጥንት ዘመን ሰዎች የጉዳዮችን የቁሳቁስ ውክልና አካባቢያቸው ባፈራላቸው ልዩ ልዩ ቀለማት ተጠቅመው በመሳል አልያም ምስሉን በመቅረፅ ተግባቦት ለመፍጠር ይሞክሩ ነበር።
ሰዎች ውስጣዊ መሻታቸውን፣ አመለካከትና እሳቤያቸውን እንደ ትላንቱ ሁሉ ዛሬም በስዕል መግለፃቸውን ቀጥለዋል። ዛሬ ግን ስነ ስዕል እንደ ትላንቱ ውስን ትርጓሜና ውክልና ብቻ ሳይሆን ውስብስብና ጥልቅ ትርጓሜ የሚሰጥ በኪናዊነቱም የረቀቀበት ጥበብ ሆኗል።
ከሁለተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ኢትዮጵያዊያን በተለያዩ ገዳማትና የእምነት ቦታዎች ላይ የስዕል ጥበብ መጀመራቸውን የተለያዩ ማስረጃዎች ያመለክታሉ። በተለይም ከአምልኮ ጋር የተያያዙ ስዕሎችና የወል መግባቢያ ውክልናዎች በተለያየ ጥበብ ተስለው፣ ተቀርፀውና በጠቢባን ተበጅተው ዛሬ ድረስ ይታያሉ። በልዩ ልዩ ታሪካዊ ቦታዎች አሻራቸው ሳይጠፋ ዘመናት መሻገርም ችለዋል።
ትላንት ጠቢባን አባቶች በራሳቸው ዘመን ፍልስፍናና እሳቤ የተጠበቡበት ስዕል ዛሬ ላይ ያለበት ደረጃ ሲገመገም በተለይ ዕድገቱን ለሚናፍቁት አርኪ አይደለም። የስዕል ማስተማሪያ ተቋማትና ሰዓሊያን ቢበረክቱም እንደ አገር ስዕል ማደግና አገልግሎት መስጠት በሚገባው ልክ አልሆነም።
ለዚህ የበዙ ምክንያቶች ቢኖሩም ህብረተሰቡ ለስዕል ጥበብ ያለው አመለካከት አለመለወጡ፣ ሰዓሊያን ክህሎታቸውን ለማሳደግ የሚችሉበት ምቹ ሁኔታ አለመፈጠሩ፣ እንዲሁም ለስዕል ጥበብ የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ መሆኑ የዘርፉ ባለሙያዎች በምክንያትነት ይጠቅሳሉ።
በዚህ ሁሉ ውስንነት ውስጥ የራሳቸውን አቅም በማጎልበት የዘርፉን ልዩ ልዩ ጋሬጣ ተቋቁመው ስዕልን ለማሳደግ የሚሰሩ ወጣቶች ግን አልጠፉም። ለስዕል ጥበብ ባላቸው ከፍተኛ ፍቅር ዘርፉን ተቀላቅለው እየሰሩ ያሉ ወጣቶችም የኢትዮጵያ የስዕል ጥበብ ያለበት ደረጃና የዘርፉ ተግዳሮቶች በዛሬው የዘመን ጥበብ አምዳችን እንደሚከተለው ተዳሰዋል።
ሰዓሊ ሳሙኤል እንዳለ ይባላል። ከልጅነቱ ጀምሮ ህልሙ የነበረው የስዕል ጥበብ ሙያ ዛሬ ላይ የህይወቱ ዋነኛ መስመር አድርጎታል። ስነ ስዕል ሰዓሊያን ልዩ ክህሎታቸውን በመጠቀም የራሳቸውን እሳቤና ፍልስፍና እንዲሁም ስለ ዓለም ያላቸውን ምልከታ በልዩ መንገድ በመረዳትና በመተርጎም የታያቸውን ለሌሎች የሚያሳዩበት ወይም የሚገልጡበት ጥበብ ነው። ሳሙኤልም እነዚህን ዋነኛ የሰዓሊ ተግባራት ለመወጣት ሌትከቀን ይታትራል። የስዕል ጥበብ ሙያን ከልጅነቱ ጀምሮ ማወቅና እዚያ ላይ በትኩረት መስራት ይፈልግ የነበረው ሳሙዔል፤ ለፍላጎቱ ማሳኪያ የሚሆነው የስዕል ጥበብ መማሪያ ቦታ ማግኘት ግን እጅግ አዳጋች ሆኖበት ቆይቷል።
በመጨረሻም በብርቱ ጥረት አንድ የስዕል ጥበብ ትምህርት ቤት ገብቶ ወደ መሻቱ መቃረብ ችሏል። ኢንላይትመንት የተባለው የእውቁ ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ የስዕል ትምህርት ቤት ደግሞ ሳሙኤል የስዕል ጥበብ ሙያን ሀሁ የቀሰመበት ነው። ያለውን የስዕል ክህሎት በትምህርት ካጎለበተ በኋላ ዛሬ ላይ በተለያዩ የስዕል ማሳያዎች ወይም ጋለሪዎች ውስጥ ስዕሎቹን በማሳየት ከጊዜ ወደ ጊዜ ተቀባይነት ማግኘትም ችሏል። በተለይም እንጦጦ፣ ሂልተንና አዲስ አበባ የሚገኙ የስዕል ጋለሪዎች ውስጥ ለበርካታ ጊዜያት ስራዎቹን አቅርቧል።
እነዚህ የስዕል አውደ ርዕዮች ዘርፉን ይበልጥ መረዳት እንዳስቻሉት የሚገልፀው ሰዓሊ ሳሙኤል፣ የስዕል ጥበብ እጅግ በርካታ ጠቀሜታዎች ያሉት ቢሆንም እንደ አገር ገና ብዙ ያልተሰራበት መስክ መሆኑን ያስረዳል። ኢትዮጵያ የበርካታ ጥበቦችና ጠቢባን አገር መሆኗን የሚናገረው ሳሙኤል፤ የስዕል ጥበብ ሙያ የሚጠበቅበትን ያህል ፋይዳ ይኖረው ዘንድ መሰራት እንዳለበት ይጠቁማል።
ሰዓሊያን ሙያቸውን እንዲያሳድጉና በዚያም ለውጥ እንዲያመጡ ከተፈለገ ህብረተሰቡ ስለ ስዕል ሙያ ያለው ግንዛቤ ማደግና እንደ አገር ለስዕል ጥበብ የሚሰጠው ትኩረት ከፍ ማለት ይኖርበታል። በስዕል ጥበብ ዘርፍ የበዙ ፈተናዎች መኖራቸውን የሚገልፀው ሳሙኤል፤ ሙያውን ልክ እንደሌላ መስክ የተከበረና የዘርፉ ተዋንያን የተለወጡበት ይሆን ዘንድ ብዙ መሰራት እንደሚጠይቅ ያብራራል።
የስዕል ማሳያ ቦታዎች እጥረት፣ ለስዕል ማሳያነት የሚመረጡ ቦታዎችና ሁኔታዎች ለሰዓሊው ምቹ አለመሆን፣ ማህበረሰቡ ስለ ስዕል ጥበብ ያለው አመለካከት የተስተካከለ አለመሆን፣ ሰዓሊው ክህሎቱን የሚያሳድግበት በቂና ምቹ የሆኑ ማሰልጠኛ ተቋማት አለመኖር፣ የስዕል መሳያ ግብአቶች በበቂ ሁኔታ አለመገኘት ለስእል ጥበብ ሙያ ዕድገት ዋነኛ መሰናክል አድርጎም ወጣቱ ሰዓሊ ይጠቅሳቸዋል።
በተደጋጋሚ የስዕል ስራውን አስትቶ ወደሌላ እንዲያተኩር የሚያደርጉ ውጫዊም ውስጣዊም ግፊቶች እንደገጠሙት የሚያስረዳው ሳሙኤል በዘርፉ ላይ ምንም ያህል ምቹ ሁኔታ ባይኖርም ለስዕል ጥበብ ባለው ጥልቅ ፍቅር ምክንያት ግን ፈተናዎቹን እየተጋፈጠ ዛሬ ድረስ በሙያው ቀጥሏል።
ሳሙዔል ነገሮችን በእውነተኛ ቁመናቸው እንዳሉ ለማሳየት በሚሞከርበት ሪአልስቲክ በተሰኘው የስዕል ጥበብ መስክ ትምህርቱን እየተከታተለ እንደሚገኝና አሁን ላይ ስራዎቹ በዚሁ ዘርፍ የተቃኙ እንደሆኑ ይናገራል። ወደፊት በአገር ደረጃ ብሎም በዓለም አቀፍ መድረክ በዘርፉ ትልልቅ ስራዎችን በመስራት አገሩን ማስጠራት እንደሚፈልግ የሚናገረው ሰዓሊ ሳሙኤል፣ እንደሱ ትልቅ ህልም ያላቸው ወጣቶች ካሰቡበት ይደርሱ ዘንድ ዘርፉን መደገፍ እንደሚገባ አስተያየቱን ይሰጣል።
ሰዓሊ ሄርሜላ ንጉሱ በስነ ስዕል ጥበብ የራሷን አሻራ ለማሳረፍ የምትተጋ ወጣት ናት። ከሁለት ዓመት በላይ በተለያዩ መድረኮች ላይ ስራዎቿን አቅርባለች። ይበልጥ የተሻለ የስዕል ጥበብ ክህሎት ይኖራት ዘንድም በኢንላይትመንት የስዕል ጥበብ ትምህርት ቤት በመማር ላይ ትገኛለች።
ሰብለ ሪአሊስቲክ የተሰኘውን የስዕል ጥበብ ዘርፍ ትኩረት አድርጋ የምትሰራበትና እራሷን ለማሻሻልም በትምህርት እየታገዘችበት ነው። በተለያዩ የስዕል ማሳያ ጋለሪዎችና የስዕል ማሳያ አውደ ርዕዮች ላይም ተካፍላለች። ይህም ማህበረሰቡ ስለ ስዕል ጥበብ ያለውን አስተያየትና እንደ አጠቃላይ በስዕል ሙያ ውስጥ ያሉ ችግሮችን ለመለየት አስችሏታል።
ከስዕል መሳያ ቁሳቁሶች ጀምሮ ነገሮችን በተሟላ መልኩ ለማግኘት እጅጉን አስቸጋሪ መሆኑን የምትገልፀው ሄርሜላ፤ ሙያውን በመውደድና በዚያ ውስጥ የሚገኘውን እርካታ ከማጣጣም ባሻገር ከጥቅም አንፃር ዘርፉ ገና ብዙ እንደሚቀረው ታስረዳለች። ‹‹ማህበረሰቡ ለስዕል ያለው አመለካከት እጅጉን ሊለወጥ ይገባዋል›› የምትለው ሄርሜላ፣ የስዕል ጥበብ የግዝፈቱን ያህል ክብር ይጎናፀፍ ዘንድ ስራዎች መሰራት ይኖርባቸዋል ባይ ናት።
እንደ ሰዓሊ ሄርሜላ አገላለፅ፣ አሁን ላይ እየተከፈቱ ያሉ አዳዲስ የስዕል ማሳያ ጋለሪዎች በራሱ ለስዕል ጥበብ እድገት የራሳቸው የሆነ ከፍተኛ ጠቀሜታ አላቸው። ከዚህ በፊት ከነበረው በተሻለ የሚፈጠሩ ምቹ ሁኔታዎች በጎ አስተዋፅዖ ይኖራቸዋል። የስዕል ጋለሪዎቹ ግን በአሰራራቸው ለሰዓሊው ምቹ ሁኔታ መፍጠር ላይ ውስንነት አለባቸው።
ሰዓሊው ስዕሎቹን በተዘጋጁ የስዕል ማሳያዎች ውስጥ አቅርቦ የሚያገኘው ጥቅም በብዙ ምክንያቶች እጅግ በጣም ያነሰ ይሆናል። ሰዓሊው ስዕሉን ለማዘጋጀት የሚወጣው የግብዓት ወይም መስሪያ ቁሳቁሶች ወጪና የስዕል ማሳያ ጋለሪዎቹ የሚጠይቁት የአገልግሎት ክፍያ ከፍተኛ መሆኑን ትጠቅሳለች። እነዚህ ተያያዥ ምንያቶች ደግሞ የስዕሉን ዋጋ ከፍ እንደሚያደርገውና የስዕል ሽያጭ ላይ ትልቅ ተፅዕኖ እንዳለው በማሳያነት ታስቀምጣለች።
በዚህም በሙያው ውስጥ በሚገኝ ሙያዊ ፍቅርና በዚያ ውስጥ በሚገኝ ሀሴት ካልሆነ በቀር ከሚያስገኘው ጥቅም አንፃር ብዙም አጓጊ እንዳልሆነ ታስረዳለች። አንድ ስዕል ለመስራት እስከ ሶስት ወራትና ከዚያ በላይ ሊፈጅ እንደሚችል የምትጠቁመው ሰዓሊ ሄርሜላ፣ አንድ ስዕል ለገበያ ሲቀርብ የወሰደውን ጊዜና ያወጣውን ወጪ ላይሸፍን የሚችልበት እድል ሰፊ መሆኑን ትገልፃለች። ስለዚህም ሰዓሊ የልፋቱን ያህል እየተጠቀመ አይደለም፣ ሙያውም የትልቅነቱን ያህል ክብር እየተሰጠው ባለመሆኑ ለዚህ የጥበብ ዘርፍ ትልቅ ትኩረት እንደሚያሻው ታስረዳለች። ስዕል አገርና ባህልን ለማስተዋወቅ ትልቅ ጠቀሜታ ያለው ዘርፍ መሆኑን የምትናገረው ሰዓሊ ሄርሜላ፣ ከሌሎች አገራት አንፃር በእኛ አገር በስዕል ስራ ላይ ያለው አመለካከት በእጅጉ ያነሰ ነው ትላለች። ያ መሆኑ ደግሞ ዘርፉ እንዳያድግ እንቅፋት ፈጥሯል ብላ ታምናለች።
ስዕል ዛሬ ላይ በሰለጠነው ዓለም በሚሊዮን ዶላር ይሸጣል፤ የትልልቅ መርሀግብር አካል ሆኖ መድረኮችን ያደምቃል። በዚህም ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው እጅጉን የጎላ ነው። እኛ አገር ላይ ግን በተገቢው መልኩ ስላልተሰራበት ይህን መጎናፀፍ አልቻልንም። በአገራችን ላይ ያለው የስዕል ጥበብ ሙያ ማግኘት የሚገባው ክብርና ባለሙያዎቹም ራሳቸውን በዘርፉ መለወጥ እንዲችሉ ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።
በቂ ትኩረት የተነፈገው ይህ አንድ የጥበብ መስክ ለአገር የሚጠበቅበትን ፋይዳ ያበረክት ዘንድ ባለሙያዎቹ በመፍትሄነት የሚያቀርቡት ሀሳብ አለ። በዘርፉ ላሉ ባለሙያዎች ምቹ ሁኔታ መፍጠር፣ የስዕል ጥበብ ማስተማሪያና መስሪያ ቁሳቁሶች ከውጪ ሲገቡ የሚከፍሉት ቀረጥ ላይ ማሻሻያ ማድረግ፣ የስዕል ስራዎችን ጥቅም በመግለፅና የአገርን ባህል እና ማንነት በማንፀባረቅ ረገድ የሚኖራቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ማሳወቅ፣ ሰዓሊያን ሙያውን ለማሳደግ በሚያስችል መልኩ በጋራ መስራት፣ የዘርፉ ባለሙያዎች የስዕል ጥበብን ለማሳደግ የሚያደርጉት ያልተቋረጠ ጥረት መፍትሄዎች መሆናቸውን ያስቀምጣሉ።
ይህ የጥበብ ዘርፍ ባህልና ማንነትን በመግለፅ ያለው ጠቀሜታው የጎላ ነው። ዘርፉ በሚጠበቀው ደረጃ አድጎ አገርና የዘርፉን ባለሙያዎች ተጠቃሚ እንዲያደርግም የሚመለከተው ሁሉ ባለድርሻ አካል ተገቢውን ትኩረት መስጠት ይገባቸዋል።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 21/2014