የደረሱ ሰብሎች በፍጥነት እንዲሰበሰቡ ሚኒስቴሩ ጥሪ አቀረበ
አዲስ አበባ፡- በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በመኸር እርሻ ወቅት የደረሱ ሰብሎችን በአግባቡ በመሰብሰብና ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ የሚያስከትለውን ጉዳት በመቀነስ ምርታማነትን ለመጨመር ርብርብ እንዲደረግ የግብርናና እንስሳት ሀብት ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ፡፡
የሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዓለማየሁ ብርሃኑ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፣ የብሔራዊ ሜቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ስርጭት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ትንበያ በማስቀመጡ አርሶ አደሩ የደረሱ ሰብሎችን በፍጥነት መሰብሰብ ይገባዋል፡፡ የደረሱ ሰብሎች ቶሎ እንዲሰበሰቡ ተማሪዎችንና የተደራጁ ወጣቶችን ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ በዘመቻ መልክ ማሰማራት አስፈላጊ ነው፡፡
‹‹ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ጉዳት ያደረሰባቸው አካባቢዎች ስለመኖራቸው እስካሁን በበቂ መረጃና በጥናት አልተለዩም›› ያሉት ዳይሬክተሩ፣ የደረሱ ሰብሎች በፍጥነት ካልተሰበሰቡ ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ሊደርስ የሚችለው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ ሰብሎችን በጥንቃቄ በመሰብሰብ የምርት ብክነትን መቀነስና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡ በተጨ ማሪም ዝናቡ በሚያቆምበት ወቅትም አርሶ አደሩ በመዘናጋት የምርት አሰባሰቡን ችላ ማለት እንደሌለበትም ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት 36 በመቶ የሚሆነውን የመኸር ምርት መሰብሰብ መቻሉንም ጠቁመው፣ እስከ ኅዳር መጨረሻ 80 በመቶ የመሰብሰብ እቅድ ተይዟል ብለዋል፡፡ በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎችም የመከላከያ ሰራዊት አባላት በሰብል ስብሰባ ሥራ ላይ እየተሳተፉ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
በዘንድሮ የመኸር ወቅት 375 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱን የተናገሩት አቶ ዓለማየሁ፣ አቅም በፈቀደ መጠን የቴክኖሎጂ አማራጮችን በመጠቀምና ድህረ ምርት ብክነትን በመቀነስ ምርታማነትን ለማሳደግ ትኩረት እንደሚደረግ ገልፀዋል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 14/2011
በአንተነህ ቸሬ