አዲስ አበባ፡- በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች በተከሰተው ድርቅ ለተጎዱ ዜጎች የሚሰጠው ትኩረትና ምላሽ አሁንም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አሳሰበ።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች በድርቁ በከፍተኛ ደረጃ ጉዳት ደርሶባቸዋል ተብለው በተለዩ አካባቢዎች በመዘዋወር ያዘጋጀውን ለተቋሙ በዓይነቱ የመጀመሪያው የሆነውን የማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ዘርፍ ሪፖርት ይፋ አድርጓል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ በበኩላቸው፤ እስካሁን በመንግሥትና መንግሥታዊ ባልሆኑ አካላት በድርቁ ለተጎዱ ሰዎችና አካባቢዎች የተሰጡ ምላሾች አበረታች መሆናቸውን ጠቁመው፤ ለምላሹ ግን ይበልጥ ጥረት መደረግ እንዳለበት ማሳሰባቸው ተገልጿል።
ተጎጂዎች አሁንም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙና ድርቁም ከሁለቱ ክልሎች በተጨማሪ ወደሌሎች አካባቢዎች እየተስፋፋ መሆኑን ኮሚሽነሩ አስታውቀው፤ በተለያዩ ጊዜያት በሚያገረሹ ግጭቶች ምክንያት በድርቁ ሳቢያ የተፈናቀሉ ሰዎችን ለተደራራቢ ጉዳት እየዳረገ ነው፤ ስለሆነም በድርቁ ለተጎዱና አዋሳኝ አካባቢዎች የሚሰጠው ትኩረት ሊቀንስ አይገባም ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
እንደ ኮሚሽነሩ ከሆነ፤ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በሕጉ መሰረት የድርቁን አደጋ በይፋ በማሳወቅ እገዛ ከሚያደርጉ ሀገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ዓለም አቀፍ ትብብር እንዲያደርጉ የማድረግ ግዴታ አለበት።
በድርቁ ሳቢያ ለተፈናቀሉ ድጋፍ ፈላጊዎች ባሉበት ቦታ ቀጣይነት ባለው መልኩ እርዳታ እንዲያገኙ ማድረግ ያስፈልጋል ሲል ኢሰመኮ በሪፖርቱ አመላክቷል።
በሪፖርቱ መሰረት፤ በድርቁ ጉዳት ሳቢያ በተለይ በቂ ውሃና ምግብ ባለመኖሩ ሰዎች ለተለያዩ የጤና እክሎች ተዳርገዋል፡፡ በምግብ እጥረት የተጎዱ ሰዎች አሉ፡፡ የጤና ግልጋሎት መስጫ ተቋማት በአካልም በኢኮኖሚም ተደራሽ አለመሆናቸውንም ክትትሉ አሳይቷል፡፡
በዚህ ምክንያት ተጋላጭ የሕብረተሰብ ክፍሎች በተለይም አረጋውያንና ሕፃናት ሕይወታቸው አደጋ ላይ ወድቋል። በድርቅ ምክንያት ተፈናቅለው በካምፖች የተቀመጡ በቂ የጤና አገልግሎት ሊያገኙ ይገባል ሲል ኢሰመኮ አሳስቧል።
የፌዴራልና የየክልል መንግሥታቱ በአፋጣኝ ሊተገብሯቸው ይገባል ካሏቸው ተግባራት መካከል አንዱ በመረጃና በምዝገባ ሥርዓት የታገዘ፣ አሳታፊ የሆነ፣ የተጠያቂነት ሥርዓት የተዘረጋለት እንዲሁም ከፍላጎት ጋር የተመጣጠነ ምላሽ ማቅረብ ያስፈልጋል ሲል ኢሰመኮ አስታውቋል።
በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን፣ በያቤሎ፣ ተልተሌ፣ ድቡሉቅ፣ ድሬና ሞያሌ ወረዳዎች በሚገኙ 11 ቀበሌዎች፤ እንዲሁም በሶማሌ ክልል፣ ሸበሌ፣ ጀረር እና ፋፈን ዞኖች፣ በጎዴ እና አዳድሌ፣ ደጋሃቡር እና ቢርቆድ እና ቀብሪ በያህ ወረዳዎች በሚገኙ ስድስት ቀበሌዎች ምርመራ መደረጉን ኢሰመኮ ገልጿል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 20/2014