ለፋሲካ በዓል ሸማቹ በነጻነት እንዲገበያይ ጥምር የፀጥታ ግብረ ኃይሉ ወደ ሥራ ገብቷል

አዲስ አበባ፡- በአዲስ አበባ ከተማ ለፋሲካ በዓል ነዋሪዎች በግብይት ማዕከላት በነጻነት እንዲገበያዩ እና የተለያዩ ወንጀሎችን አስቀድሞ ለመከላከል ጥምር የፀጥታ ግብረ ኃይሉ ወደ ሥራ መግባቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ ቢሮ አስታወቀ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሊዲያ ግርማ ለኢትዮጵያ ፕሬስ እንደገለጹት፤ በመዲናዋ በፋሲካ የበዓል የግብይት ሥርዓት ላይ የፀጥታ ችግር ሳይፈጠር ነዋሪዎች በሰላም እንዲገበያዩ ከወዲሁ ስምሪት ተደርጎ እየተሠራ ነው፡፡

በመዲናዋ ለፋሲካ በዓል በተለያዩ ቦታዎች ግብይቶች ይፈፀማሉ፤ እነዚህ ግብይቶች ላይ ሊፈፀሙ የታሰቡ የተለያዩ ወንጀሎችን አስቀድሞ ለመከላከልና ነዋሪዎች በሰላም እንዲገበያዩ ጥምር የጸጥታ ግብረ ኃይሉ ወደ ሥራ ገብቶ እየተሠራበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመዲናዋ በመደበኛና በበዓላት ጊዜ ማህበረሰቡ ግብይት የሚፈጽምባቸው በርካታ የገበያ ማዕከላት መኖራቸውን ገልጸው፤ የፋሲካን በዓል አስታኮ በእነዚህ የገበያ ማዕከላት ላይ ምንም አይነት የወንጀልና የፀጥታ ችግር ሳይፈጠር ሸማቹና አምራቹ በሰላም እንዲገበያይ ወንጀልን አስቀድሞ የመከላከል ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙ አብራርተዋል፡፡

የመዲናዋ ነዋሪዎች የፋሲካን በዓል ለማከበር በሚያደርጉት ግብይት ላይ በሌቦችና በነጣቂዎች ወንጀል እንዳይፈፀምባቸውና ባሉት የገበያ ማዕከላት በነጻነት እንዲሸምቱ በጥምር የፀጥታ ግብር ኃይሉ በትኩረት እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በከተማዋ በመደበኛ የግብይት ሥርዓትም ሆነ በዓላት ጊዜ ሕገ ወጥ የገንዘብ ልውውጥ፤ በምርቶች ላይ በአድ ነገር መቀላቀል፤ እቃዎች ላይ ከፍተኛ ዋጋ መጨመርና የአላግባብ መከዘን ወንጀሎች በቁጥጥር ሥራ ላይ እንደሚያጋጥሙ ጠቅሰው፤ እነዚህን ወንጀሎች በመጪው የፋሲካ በዓል እንዳይፈጸሙ አስቀድሞ ለመከላከል ጥምር የጸጥታ ኃይል ስምሪት ወስዶ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡

በገበያ ማዕከላት አምራቹ ከሸማቱ ጋር የሚያደርገው ግብይት ሰላሙ የተጠበቀ ለማድረግ ሕግ የማስከበር ሥራ እየተሠራ ነው፤ እየተሠራ ያለው ሥራም እስካሁን ተጨባጭ የሆነ ውጤት አስገኝቷ፤ ለዚህ ውጤትም ማህበረሰቡም ትልቁን ሚና እየተጫወተ ይገኛል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የዘንድሮውን የፋሲካ በዓል ማህበረሰቡ ያሰበውን ምርትና ሸቀጥ በሰላም ገብይቶ እንዲመለስ ወንጀልን አስቀድሞ የመከላከል ሥራ ተግባራዊ በመደረግ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

በተያዘው ዓመት የአደባባይ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ ስኬታማ ሥራ መሠራቱን ያወሱት ወይዘሮ ሊዲያ፤ በመጪው እሁድ የሚከበረው የፋሲካ በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ መጠነ ሰፊ ዝግጅት ተደርጎ ወደ ተግባር ተገብቷል ብለዋል፡፡

በዓላትን ምክንያት በማድረግ በምርቶች ላይ ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪና ሕገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ አካላትን ለመቆጣጠር እየተሠራ ነው ያሉት ኃላፊዋ፤ የፋሲካ በዓልም በሰላም ተከብሮ እንዲያልፍ ከማህበረሰቡ ጋር ሰላም የማስከበር ቅንጅታዊ ሥራ እየተሠራ ነው ሲሉ ጠቁመዋል፡፡

ታደሠ ብናልፈው

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 22/2016 ዓ.ም

Recommended For You