አምራች ኢንተርፕራይዞች ከ24 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ገቢ አስገኙ

– 1 ነጥብ 32 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ወጪ አድነዋል

አዳማ፦ በ2016 በጀት ዓመት ባለፉት ዘጠኝ ወራት አምራች ኢንተርፕራይዞች 14 ሺህ 190 ቶን ምርት ለውጭ ገበያ በማቅረብ 24 ነጥብ 51 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ገቢ ማስገኝታቸውን የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት አስታወቀ። ኢንተርፕራይዞቹም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከውጭ የሚገባ ምርትን በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት ሀገሪቱ ታወጣ የነበረውን 1 ነጥብ 32 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ወጪ ደግሞ ማዳናቸውን ኢንተርፕራይዙ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት የ2016 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የእቅድ አፈፃፀምና የቀጣይ የሥራ አቅጣጫዎች ላይ የተቋሙ ሠራተኞችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ትናንት በአዳማ ከተማ የግምገማና የውይይት መድረክ አካሂዷል።

በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አለባቸው ንጉሴ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ በ2016 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ውስጥ አምራች ኢንተርፕራይዞች 11 ሺህ 525 ቶን ምርት ለውጭ ገበያ አቅርበው 24 ነጥብ 89 ሚሊዮን ዳላር ለማግኘት ታቅዶ፤ 223 ኢንተርፕራይዞች 14 ሺህ 190 ቶን ምርት ለውጭ ገበያ በማቅረብ 24 ነጥብ 51 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ገቢ ተገኝቷል።

የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ከተያዘው እቅድ አኳያ አፈጻጸሙ 98 በመቶ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመው፤ በዋናነት የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ የቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ የምግብና የመጠጥ፣ የዕደ ጥበብ ውጤቶች፣ የኬሚካልና የኮንስትራክሽን ግብዓቶችን ወደተለያዩ ሀገራት በመላክ የውጭ ምንዛሪ ገቢው እንደተገኘና 223 ኢንተርፕራይዞች ተጠቃሚ እንደሆኑ አስረድተዋል።

ተቋሙ ከክልልና ከፌዴራል ባለ ድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ለአምራች ኢንተርፕራይዞች እያደረገ ባለው የተሟላ ድጋፍ የአምራች ኢንተርፕራይዞች ምርትና ምርታማነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ገልጸው፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት አምራች ኢንተርፕራይዞች 1 ነጥብ 78 ቶን ከውጭ የሚገባ ምርት በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት ሀገሪቱ ታወጣ የነበረውን 1 ነጥብ 32 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ወጪ ማዳናቸውን ገልጸዋል።

በዚህም 1ሺህ 387 አምራች ኢንተርፕራይዞች ከውጭ የሚገባ ምርትን በሀገር ውስጥ በመተካት ሥራ ላይ በመሠማራት ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል በ2016 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ውስጥ አዲስ በተቋቋሙና በተጠናከሩ ነባር አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች ለ138 ሺህ 922 ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ፤ ለ106 ሺህ 441 ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፈጠሩን ዋና ዳይሬክተሩ አክለው ገልጸዋል።

ከተያዘው እቅድ አኳያ አፈጻጸሙ 77 በመቶ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ጠቅሰው፤ ከተፈጠረው የሥራ ዕድል ውስጥ 61 ሺህ 220 በአነስተኛ እንዲሁም 45 ሺህ 221 በመካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች እንደሆነ ተናግረዋል።

የተቋሙ የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ከተቋሙ ሠራተኞችና አመራሮች ባሻገር የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንዱስትሪና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አመራርና አባላት በተገኙበት ቀርቦ ግምገማና ውይይት ተደርጎበታል።

ሶሎሞን በየነ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 22/2016 ዓ.ም

Recommended For You