የሙያ አጋሮቹ ሁሉ ‹‹የትያትር አባት›› ይሉታል። ከጀማሪ እስከ አንጋፋ ያሉ የጥበብ ሰዎች ትያትርን የሚለኩት በእሱ ነው። ከያኒውም ለዚህ ሙያ ብቻ የተፈጠረ ይመስላል። ሕይወቱ እስካለፈችበት ጊዜ ድረስ የነበረው ሕይወቱ ሁሉ ቲያትር ውስጥ ነበር። ይህ ከያኒ አባተ መኩሪያ ነው!
‹‹የትያትር አባት›› እየተባለ የሚጠራው አባተ መኩሪያን ከዚች ዓለም በሞት ያጣነው በዚህ ሳምንት ሐምሌ 13 ቀን 2008 ዓ.ም ነበር። እነሆ በሳምንቱ በታሪክ ዓምዳችን የአባተ መኩሪያን ሕይወትና ሥራዎቹን እናስታውሳለን።
አቶ መኩሪያ አያቱ ናቸው። የልጃቸው የወይዘሮ ውብነሽ መኩሪያ ልጅ ማለት ነው። የአያቱ የአቶ መኩሪያ ምኞት አባተ አድጎና ተምሮ ነገረ ፈጅ እንዲሆንላቸው ነበር። ምኞታቸውን ለማሳካትም አባተ በተወለደ በስድስት ወሩ ‹‹እኔ ነኝ የማሳድገው›› ብለው ከወላጆቹ ወሰዱት። የ‹‹ሀሁ በስድስት ወር›› ገጸ ባሕሪው ‹‹በፊደል ነው የተለከፍኩት›› ሲል የገፀ ባህሪይው አለቃ አባተ ግን ‹‹በጥበብ ነው የተለከፍኩት!›› ብሎ ጥበብን የሙጥኝ አለ። በጥበብ መለከፉ ለበጎ ሆኖለት በጥበብ ጎዳና ተጓዘ፤ ብዙ የጥበብ ክዋክብትንም አፈራ።
አባተ መኩሪያ ከአርባ ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ የቲያትር ጥበብ ውስጥ የራሱን ተፅእኖ ማሳረፍ የቻለና ‹‹የኢትዮጵያ የቲያትር አባት›› የሚል ስያሜን ያተረፈ ተወዳጅና አንጋፋ ባለሙያ ነው። ጸሐፊ ተውኔት፣ የቲያትር አዘጋጅ እንዲሁም የፊልም አዘጋጅ የነበረው አባተ መኩሪያ፤ በኢትዮጵያ የቲያትር ታሪክ ውስጥ ስማቸው በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱትና አሻራቸውን ካሳረፉ ባለሙያዎች መካከል አንዱና ዋኛው ነበር።
አባተ የተወለደው ኅዳር 10 ቀን 1936 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ነው። የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ትምህርት ቤት (የአሁኑ ኮከበ ጽባሕ ትምህርት ቤት) ተምሯል። እርሱና ጓደኞቹ ‹‹በጥበባዊ ስራዎቻችሁ ሹማምንትን ተሳድባችኋል›› ተብለው ከትምህርት ገበታ እስከታገዱበት ጊዜ ድረስም የከፍተኛ ትምህርቱን ደግሞ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ (የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) ተከታትሏል። በእንግሊዝና በጀርመንም የመገናኛ ብዙኃንና የተግባቦት እንዲሁም የሲኒማ ትምህርቶችን አጥንቷል።
በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከፕሮግራም አዘጋጅነት እስከ ዳይሬክተርነት ድረስ በዘለቀ የሥራ ኃላፊነት ሰርቷል። በጣቢያው ‹‹መዝናኛ በክዋኔ ጥበባት›› በሚል ርዕስ በየሳምንቱ ዓርብ የሚቀርብና ለአንድ ዓመት የዘለቀ ፕሮግራም አዘጋጅቶ አቅርቧል። ፕሮግራሙም የአዝማሪ ጨዋታ በኢትዮጵያ ሕዝብና በክዋኔ ጥበባት ውስጥ የነበራቸው ሚና እና ቤተ ክህነት ለጥበቡ ዕድገት ያደረገችው አስተዋጽኦ የተዳሰሰበት፤ የብሄረሰቦች ባሕሎችና መገለጫዎች (የእምነት፣ የደስታ፣ የሐዘን … ስርዓቶች) ከጥበብ አንፃር የታዩበት እንዲሁም የታዋቂ የጥበብ ሰዎች ስራዎችና አበርክቶዎች የሚቀርቡበት መሰናዶ ነበር።
አባተ በቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ቲያትር ቤት (የአሁኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቲያትር) የቲያትር ዳይሬክተር፣ በሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት እና በአዲስ አበባ ባህልና ቲያትር አዳራሽ የቲያትር አዘጋጅ፣ ጸሐፌ ተውኔትና መራሔ ተውኔት እንዲሁም በቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ኪነ ጥበባት ወቲያትር (ባህል ማዕከል) ዳይሬክተር ሆኖ ሠርቷል።
አባተ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቲያትር ጥበባት ትምህርት ክፍል አስተማሪ ሆኖ በርካታ ባለሙዎችን አፍርቷል። አባተ ታሞ የነበረ ቢሆንም በሕይወት እያለ በታኅሳስ ወር 2008 ዓ.ም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባህል ማዕከል ‹‹ዝክረ አባተ መኩሪያ›› ብሎ ባዘጋጀው መድረክ ላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጥበባት ኮሌጅ ባልደረቦች ታላቁ የጥበብ ሰው አባተ መኩሪያ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቲያትር ትምህርት ክፍል በትክክለኛው መሠረት ላይ እንዲገኝ የላቀ ሚና እንደተጫወተና በዩኒቨርሲቲው የኪነ ጥበብ የፈጠራ ማዕከል እንዲቋቋም ደማቅ አሻራውን እንዳኖረ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። ከዚህ ባሻገርም አባተ የተለያዩ የቲያትር ንድፈ ሐሳቦችን በማቅረብ ግንባር ቀደም አርቲስት እንደነበረም ተናግረዋል።
ከአባተ ታዋቂ የተውኔት ስራዎች (ወጥና ትርጉም) መካከል፡-
1. ሀሁ በስድት ወር (1966)
2. አቦጊዳ ቀይሶ (1971)
3. መልዕክተ ወዛደር (1971)
4.የመንታ እናት (1971)
5. መቅድም (1972)
6. ጋሞ (1973)
7. ኦቴሎ (1973)
8. ቴዎድሮስ (1973)
9. ሐሙስ (1978)
10. አሉላ አባ ነጋ (1979)
11. ያላቻ ጋብቻ (1980)
12. ታርቲይፍ (1980)
13. ኤዲፐስ ንጉሥ (1988)
14. በሐምሌ ጨረቃ ጉዞ (1996)
15. አፋጀሽኝ (2003) … የሚሉት ተጠቃሾች ናቸው።
አባተ ካዘጋጃቸው ተውኔቶች መካከል ብዙዎቹ በሎሬት ጸጋዬ ገብረመድኅን የተደረሱ ሲሆኑ ተውኔቶቹ ረጃጅም ቃለ ተውኔትንና ታሪክ ጠቃሽ ዘይቤዎችን ያዘሉ ናቸው። አባተ ረጃጅም ቃለ ተውኔቶችን (መነባንቦች) ተደራሲን በሚማርክ መልኩ እንዲዘጋጁ በማድረግና የድራማን ሥነ ጽሑፍ በምሁራዊ ዓይን አይቶ በማዳበር ችሎታውን አስመስክሯል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሣይንስና የባሕል ተቋም (ዩኔስኮ) አፍሪካዊ የቲያትር ስራ እንዲያዘጋጅ ሲመረጥ የሎሬት ጸጋዬን ‹‹Oda Oak Oracle›› (የዋርካው ሥር ንግርት) አዘጋጅቷል።
አባተ የተውኔት ተመልካቹን በግሩም ሁኔታ መቆጣጠር የሚያስችል ክሂል ነበረው። በሎሬት ጸጋዬ የተተረጐሙት የዊልያም ሼክስፒር ‹‹ማክቤዝ››፣ ‹‹ኦቴሎ›› እና ‹‹ሐምሌት›› ድርሰቶች ተወዳጅ መሆንና ተውኔታዊ ክዋኔዎቹም በታዳሚዎች ዘንድ መታወስ የቻሉት በቃለ ተውኔቶቹ ውበት ብቻ ሳይሆን በአባተ የአዘገጃጀት ጥበብ ጭምር እንደሆነ ዓለም አቀፍ የቲያትር ጥበብ ተቋማትና ሕትመቶች መስክረዋል። ከእንግሊዛዊው ዕውቅ የቲያትር አዘጋጅ ሰር ፒተር ሆል ጋርም የመስራት እድል ስለማግኘቱም መረጃዎች ያሳያሉ።
ከመንግሥቱ ለማ ታዋቂ ሥራዎች አንዱ የሆነው ‹‹ያላቻ ጋብቻ›› የአባተ የአዘጋጅነት እጅ አርፎበታል። አባተ ከሚታወቅባቸው የመድረክ ተውኔቶች ባሻገር በአደባባይ ላይ (ከአዳራሽ ውጭ) ባዘጋጃቸው ተውኔቶቹም ይታወሳል። ‹‹ኤዲፐስ ንጉሥ›› ተውኔትን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ዋናው ግቢ፣ ራስ መኰንን አዳራሽ ፊት ለፊት በሚገኘው ስፍራ ላይ ያሳየውም ይጠቀሳል። በኢትዮጵያ የተውኔት ታሪክ ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሚሰለፈው የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ ‹‹አፋጀሽኝ›› ዳግም የመድረክ ብርሃን ያየውም በአባተ መኩሪያ አማካኝነት ነበር።
አባተ ከተውኔት አዘጋጅነቱ ባሻገር በጸሐፌ ተውኔትነቱም ስሙ ከፍ ብሎ የሚጠቀስ አንጋፋ ባለሙያ ነበር። ራሱ ጽፎ ያዘጋጀው ‹‹የሊስትሮ ኦፔራ›› (1982) የተሰኘው ተውኔቱ በወቅታዊ ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ የተመሠረተና በሙዚቃ የታጀበ ሥራው ነበር። ዓለም አቀፍ ሽልማትም አግኝቶበታል።
አባተ ከታላቁ የዓድዋ ድል ታሪክ ጋር ተያይዞ የሚነሳበት ታሪክም አለው። በርካታ ሰዎች የተሳተፉበትንና አዲስ አበባ ከተማ 100ኛ ዓመት የምስረታ በዓሏን ባከበረችበት ወቅት ተሰርቶ በየዓመቱ በዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓል ላይ በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ‹‹የዓድዋ ጦርነት ዘመቻ›› የተሰኘውን ታሪካዊ ዶክመንተሪ ፊልም ያዘጋጀውም አባተ መኩሪያ ነበር።
አባተ መቀመጫውን በታንዛኒያ ያደረገውን የምሥራቅ አፍሪካ ቲያትር ኢንስቲትዩት በመሥራች አባልነትና በኃላፊነት መምራት አንደቻለም ታሪኩ ያስረዳል። በአዲስ አበባም ‹‹የመኩሪያ ቴአትር ስቱዲዮና መዝናኛ›› የተሰኘ ተቋምን መሥርቶ ‹‹ቲያትር ለልማት›› የሚባለውን የተውኔት አቀራረብ ፈለግ መሠረት በማድረግ በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ብዙ ትምህርት ሰጪ ተውኔቶችን በማዘጋጀት ለመድረክ አብቅቷል። በክልሎችና በአዲስ አበባ ከተማ ለሚገኙ አማተር ከያኒያን የቲያትር፣ የሰርከስና የሙዚቃ ሥልጠና ሰጥቷል፤ ከኢትዮጵያ ውጪም ወደ ተለያዩ አገሮች ተጉዞ ጥበባዊ ትርኢቶችን አቅርቧል። ተቋሙ ለመድረክ ካበቃቸው ተውኔቶች መካከል ‹‹ሕሊና››፣ ‹‹ጠለፋ››፣ ‹‹ጆሮ ዳባ››፣ ‹‹በሐምሌ ጨረቃ ጉዞ››፣ ‹‹ድንቅ ሴት›› ሲጠቀሱ ከዘጋቢ ፊልሞች መካከል ደግሞ ‹‹የፍትሕ ፍለጋ እና ‹‹የመስከረም ጥቃት›› የሚሉት ይገኙበታል።
በአባተ የተውኔት ስራዎች ላይ በተዋናይነት የተሳተፈው ዓለማየሁ ገብረሕይወት ‹‹ከያኒ አባተ መኩሪያ – ስለሱ ከተባለው ያልተባለው›› በሚል ርዕስ ባሰፈረው ጽሑፍ እንዳብራራው፤ አባተ ቲያትር ሲያዘጋጅ መድረክ ላይ ለመውጣት አይጣደፍም። ይልቁኑ ስለሚያዘጋጀው ቲያትርና ስለሚከተለው መንገድ ተዋንያኑ በቅድሚያ እንዲረዱለት ይፈልጋል። ስለዚህም ሃሳቡን ያካፍላቸዋል። እያንዳንዱ የተዋንያን እንቅስቃሴ የታሰበበት፣ በበቂ ምክንያት የሚደገፍና በአእምሮና በሰራ አካላት ጥምረት (Mind and Body Cohesion) የሚመራ መሆን እንዳለበት በጽኑ ያምናል። በዚህ ብቻ ግን አያቆምም። እሱ ከሚፈልገው የዝግጅት ስልት ጋር ይሄዳል ብሎ ያሰበውን ሥራ ተዋንያኑ እንዲመለከቱትና እንዲወያዩበትም ያደርጋል። ‹‹ያላቻ ጋብቻ››ን ሲያዘጋጅ ተዋንያኑ የአሜሪካዊውን ፀሐፌ ተውኔት የአርተር ሚለርን ‹‹የአሻሻጩ ሞት›› በ‹‹ኢዲፐስ ንጉሥ›› ጊዜ ደግሞ ታዋቂው እንግሊዛዊ የቴያትር ባለሙያ ፒተር ብሩክ ያዘጋጀውን ‹‹ዘ ማሀበራታ›› እንዲመለከቱ አድርጓል።
የኢትዮጵያን የቲያትር እድገትና የተመልካቹን ሁኔታ በተመለከተ አባተ መኩሪያ በአንድ መድረክ ላይ የተናገረው ንግግር ‹‹ታሪካዊ መዝገበ ሰብ›› በተባለው መጽሐፍ ላይ እንደሚከተለው ሰፍሯል።
‹‹ … የኢትዮጵያ ሕዝብ የራሱን ባህል አትኩሮ የሚያጣጥምና የሚወድ ነው። ቲያትር ቤቱ ይሞላል። ግን ከቲያትር (ከድርሰቱ) አንፃር ያየነው እንደሆነ ብዙ የሚተቹ ነገሮች አሉ። እንደ ቲያትር አዋቂ ተመልካች ቲያትሮቹን ብናያቸው ብዙ ግድፈቶች እናገኛለን። ተመልካቹ ለዚያ ሁሉ ደንታ የለውም። የራሱን ሕይወት ማየት ይወዳልና ይመጣል። በአሁኑ ጊዜ ጥበቡ ሳይሆን ተመልካቹ ነው የሚፈታተነው። ደግሞ የእኛን አገር ቲያትር እንዳያድግ የገደለው ቲያትር ቤቶች በመንግሥት እጅ መሆናቸው ነው። ቲያትር ቤቶች አንድ ዓይነት ሥራ ነው የሚሠሩት …››
የአባተ የጥበብ ጉዞ ብዙ መሰናክሎችን ያለፈ ነበር። የዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበረበት ወቅት በ‹‹ኪነ ጥበብ ቲያትር›› ማዕከል ሲሳተፉ ጓደኛቸውና የግጥም ጉባኤ ባለቅኔው ዮሐንስ አድማሱ ያቀረበው ‹‹ላም እሳት ወለደች በሬ ቀንድ አወጣ፣ በሥልጣን ሊቅ መሆን ይህም አለ ለካ›› ግጥም ሹማምንቱን የሚሰድብና የሚተች ነው ተብሎ የትምህርት ክፍሉ ተዘጋ፤አባተና ጓደኞቹም ከትምህርት ታገዱ። መንግሥታት በተቀያየሩ ቁጥር አባተና ሙያው ፈተና አልተለያቸውም። ቲያትር ቤቶችም መድረክ ነፍገውት ነበር። ለዚህም ይመስላል አባተ በታኅሣሡ የብሔራዊ ባህል ማዕከል የሽልማትና እውቅና መድረክ ላይ ‹‹ … እባካችሁ መድረክ ስጡኝ ልሥራበት። እኔ ሠርቼ አልጠገብኩም፤ ገና ብዙ መሥራት እፈልጋለሁ፤ ስለዚህ እባካችሁ መድረኩን ስጡኝ›› ብሎ ተማፅኖውን ያቀረበውና ቅሬታውንም በአደባባይ የገለፀው።
አባተ በግል ባህርይው ሰዎችን በክፉ የማያነሳና ነገሮችን የማያካብድ እንደነበር ዓለማየሁ በጽሑፉ ላይ ጠቅሶታል። ‹‹ … ስለጋሼ አባተ ባሰብኩ ቁጥር ቀድሞ ወደ አእምሮዬ የሚመጣው አንድም ቀን ቢሆን – እደግመዋለሁ፣ አንድም ቀን ቢሆን ሰዎችን አጠገቡ ቢኖሩም ባይኖሩም በክፉ ሲያነሳ ሰምቼው አለማወቄ ነው። ይህ ብቻ አይደለም። ከሱ ጋር ሲጠብ ከቲያትር፤ ሲሰፋ ከሥነጥበብ መስክ ውጪ የተጨዋወትኩበትን ቀንም አላስታውስም። ቢቆም፣ ቢቀመጥ፣ ቢያስብ፣ ቢናገር፣ ቢያዝን፣ ቢደሰት ከዚሁ አጥቢያው (ኮምፎርት ዞኑ) አይወጣም። ‹ቲያትር ከመስራት ሌላ ሕይወት የለኝም› የሚለውስ ለዚሁ አይደል!? ሌላው የሚገርመኝ የጋሼ አባተ ባህሪይ ነገር ማካበድ አለመውደዱ ነው። ጠዋት ላይ የተበሳጨበትን ጉዳይ ረፋድ ላይ ሊረሳው ይችላል። አንዳንዴ ደግሞ ሌሎቻችንን እርር ድብን የሚያደርገን ነገር እርሱን ብዙም ላይነካው ይችላል፤ወይም በቀላሉ ያልፈዋል። ጋሼ አባተ እጅግ የሚያስደንቅ ሰብዕና ያለው ባለሙያ ነበር›› ብሏል።
በ2010 ዓ.ም ያረፈው አንጋፋው አርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያም በአባተ መኩሪያ የቀብር ስነ ስርዓት ላይ ‹‹ … ራሴን ፈልጌ እንዳገኝ የገራኝ፣ መንገዱን ያሳየኝ፣ የገሰፀኝ፤ ዛሬ ለደረስኩበት ደረጃ ያበቃኝና ያሳደገኝ የጥበብ አባቴ ነው …›› በማለት ተናግሮ ነበር።
… በኢትዮጵያ ቲያትር ሦስት ሰዎች ጥሩ ቢባል አንዱ አባተ መኩሪያ ነው። በኢትዮጵያ ቲያትር ሁለት ሰዎች ጥሩ ቢባል አንዱ አባተ መኩሪያ ነው። በኢትዮጵያ ቲያትር አንድ ሰው ጥሩ ቢባል ያ ሰው አባተ መኩሪያ ነው …›› ብሏል።
ለረጅም አመታት በኢትዮጵያ የቲያትር ጥበብ ውስጥ ያገለገለውና ‹‹ተንቀሳቃሹ ቲያትር ቤት›› እየተባለ የሚጠራው አንጋፋው አርቲስት አባተ መኩሪያ፣ ባደረበት የጤና እክል በሀገር ውስጥና በውጭ አገር በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ ሐምሌ 13 ቀን 2008 ዓ.ም. አረፈ። ስርዓተ ቀብሩ በማግሥቱ በአዲስ አበባ መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል። አርቲስት አባተ መኩሪያ ከወይዘሮ ምሕረት አረጋ ጋር ትዳር መስርቶ ቴዎድሮስ እና ውቢት የተባሉ ሁለት ልጆችን አፍርቷል፤ የልጅ ልጆችም አይቷል። እነሆ በሥራዎቹም ሲዘከር ይኖራል።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን እሁድ ሐምሌ 17 ቀን 2014 ዓ.ም