ኢትዮጵያን በአራቱም አቅጣጫ ካሉ የጎረቤት አገራት መንገድን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ለማስተሳሰር ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው:: ኢትዮጵያን ከጅቡቲ፣ ከኬኒያ፣ ከሱዳን እና ከደቡብ ሱዳን ጋር ለማስተሳሰር በርካታ የመንገድ መሰረተ ልማት ስራዎች ተካሂደዋል፤ እየተካሄዱም ይገኛሉ:: ግንባታቸው እየተከናወኑ ከሚገኙ የትራንስፖርት መተላለፊያ ኮሪደሮች መካከል ከአዲስ አበባ እስከ ጂቡቲ የሚዘልቀው የትራንስፖርት ኮርደር አንዱ ነው::
የኢትዮጵያ – ጁቡቲ የትራንስፖርት መተላለፊያ ኮሪደር የሀገራችን ገቢ – ወጪ ንግድ ዋነኛው ማሳለጫ ኮሪደር ነው:: ከሀገሪቱ የወጪና ገቢ ንግድ 90 በመቶ የሚሆነው በዚህ ኮሪደር እንደሚተላለፍ መረጃዎች ያሳያሉ::ይህ መንገድ ከተገነባ በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረ ነው::መንገዱ የኮሪደሩን አስፈላጊነት በሚመጥን መልኩ በዘመናዊ መንገድ የተገነባ አይደለም::
በዘመናዊ መንገድ የተገነባ ባለመሆኑ እና በመንገዱ በብዛት የሚመላለሱን የከባድ ተሽከርካሪዎችን ጫና ለመቋቋም ባለመቻሉ በተደጋጋሚ ጊዜያት ለጥገና ሲዳረግ ቆይቷል:: ይህንን ችግር ለመፍታት 84 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የአዲስ አዳማ የፍጥነት መንገድ በ10 ነጥብ ሶስት ቢሊየን ብር ተገንብቶ የዛሬ ስምንት ዓመት ገደማ ተመርቆ ለትራፊክ ክፍት ሆኗል:: የዚህ መንገድ መጠናቀቅ ለሀገሪቱ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ አስገኝቷል::
ሆኖም ከጂቡቲ አዲስ አበባ ድረስ ካለው ርቀት አንጻር የአዲስ አዳማ የፍጥነት መንገድ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም:: ከአዲስ አበባ እስከ አዳማ የነበረውን የፍጥነት መንገድ ከፍ በማድረግ የረጂሙ የኢትዮ – ጂቡቲ የትራንስፖርት ኮሪደር አካል የሆነ አዳማ – አዋሽ – ሜኢሶ – ድሬዳዋ ኮንታራት አንድ፤ አዳማ አዋሽ የፍጥነት መንገድ ግንባታ የዛሬ ዓመት ገደማ ተጀምሯል:: የአዳማ-አዋሽ ምዕራፍ አንድ 60 ኪሎ ሜትር የፍጥነት መንገድ ፕሮጀክት ግንባታን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የመሰረት ድንጋይ በማስቀመጥ በይፋ ማስጀመራቸው ይታወሳል።
የአዳማ አዋሽ ኮሪደር ለሀገራችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገት ወሳኝ ከሆኑ የመንገድ ኮሪደሮች መካከል አንዱ ቢሆንም፣ ነባሩ መንገድ የትራንስፖርት ፍሰቱን የሚመጥን እና ደረጃውን የጠበቀ ያልነበረ በመሆኑ ፣ በመንገዱ ተጠቃሚዎች እንዲሁም በንብረት እና በህይወት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሲያደርስ ቆይቷል::
የፍጥነት መንገዱን ከነባሩ መንገድ ጋር የሚያገናኙ ሶስት ማሳላጫዎች በአዳማ ፣ ኑራ ኤራ እና በወለንጪቲ ላይ የሚገነባለት ሲሆን፤የምዕራፍ አንድ አዳማ -አዋሽ ኮንትራት አንድ አዳማ-60 ኪ.ሜ የፍጥነት መንገድ 34 ሜትር ስፋት አለው ::
የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ እንደሚሉት፤ እያንዳንዱ የተሽከርካሪ መጓጓዣ መስመር ሶስት ነጥብ ስድስት ሜትር ስፋትና ዘጠኝ ሜትር ሜዲያን (የመንገድ አካፋይ) ያካተተ ነው ::
የመንገድ አካፋዩ ከፍተኛ ስፋት ያለው ሲሆን አካፋዩ በዚህ ደረጃ እንዲሰፋ የተደረገው በተቃራኒ አቅጣጫ ያለን ተሽከርካሪ በመለየት አደጋን ለማስወገድ አልያም ለመቀነስ ነው ተብሏል:: የመንገዱ ትከሻ ስፋት ከአንድ ነጥብ አምስት ሜትር እስከ ሶስት ሜትር ነው:: አራት መኪኖችን በአንድ ጊዜ በግራና በቀኝ በኩል የማስተናገድ አቅምም አለው::
መንገዱ አጠቃላይ 90 ሜትር የወሰን ስፋት ያካተተ ነው:: ይህም በቀጣይ ለሚኖረው የማስፋፋት ስራ በቂ ቦታ እንዲኖር የሚያስችል ይሆናል::በተጨማሪም የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂን መሰረት በማድረግ ችግኞችን በመትከል አካባቢውን የማስዋብ ስራ ይሰራል::በፍጥነት መንገዱ ለመጠቀም የተቀመጠለት የፍጥነት ገደብ በሰዓት ከ100 እስከ 120 ኪ.ሜ ነው::
ከአዲስ አበባ እስከ አዳማ የተገነባው የፍጥነት መንገድ እስከ አዋሽ ከፍ ማለቱ ለሀገሪቱ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥቅምም ያስገኛል:: የመንገዱ መገንባት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ከፍተኛ ፋይዳ ያለው ስለመሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ግንባታውን ባስጀመሩበት ወቅትም አስታውቀው ነበር:: ይህ የፍጥነት መንገድ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ ፣በአሁኑ ወቅት በመንገዱ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍ ፣የትራንስፖርት ፍሰቱን የተሳለጠ በማድረግ እና በትራፊክ መስተጓጎል ሳቢያ ኢኮኖሚው ላይ የሚፈጥረውን ጫና በማቃለል የተሳለጠ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰጥ ያስችላል ::
ከዚህ ባሻገርም የፍጥነት መንገድ ግንባታው በሚካሄድበት አካባቢ የሚኖረው ህዝብ ትስስር ይበልጥ እንዲጠናከር የሚያደርግ ነው:: በተለይም ግንባታው በሚከናወንበት አካባቢ የሚገኘውን የከረዩ ህዝብ ከሌሎች ወንድም ህዝቦች ጋር በማስተሳሰር ረገድ ከፍተኛ ፋይዳ ያለው ፕሮጀክት ነው::
በተጨማሪም፤ የፕሮጀክቱ ግንባታ የሚካሄድበት አዳማና ዙሪያው የትላልቅ ፣ መካከለኛና ቀላል ማኑፋክቸሪንግ፣የአግሮ ፕሮሰሲንግ ፋብሪካዎች እና የኢንዱስትሪዎች መገናኛ እንደመሆኑ እነዚህ ኢንዱስትሪዎች እና ፋብሪካዎች ኢትዮጵያ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ በመሸጋገር ከበለፀጉት ሀገራት ተርታ ትሰለፍ ዘንድ የፍጥነት መንገድ ፕሮጀክቱ ትልቅ አበርክቶ ይኖረዋል::
ፕሮጀክቱ የሀገሪቱን የንግድ እንቅስቃሴን ከማቀላጠፍ እና የአካባቢውን ማህበረሰብ ከማስተሳሰር ባሻገር ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላት ግንኙነት ከመቼውም ጊዜ በተሻለ መልኩ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትስስርን ለመፍጠር ትልቅ አስተዋጽኦ አለው::
የኢትዮጵያ ጂቡቲ የፍጥነት መንገድ አውን መሆን የአካባቢው ሀገራት ከዚህ በፊት ከነበረው በተሻለ መልኩ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትስስራቸው እንዲሳለጥ ያደርጋል::በተለይም ኢትዮጵያ ከጎረቤት ጂቡቲ ጋር ያላት ዘመናትን ያስቆጠረው ግንኙነት ከመቼውም ጊዜ በተሻለ መልኩ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለመፍጠር ፋይዳው የጎላ ነው::
የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር መረጃ እንደሚያመለክተው፤ መንገዱ የሚገነባው በስድስት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር ወጪ ሲሆን፣ በጀቱ የሚሸፈነው በአፍሪካ ልማት ባንክ እና በኢትዮጵያ መንግሥት ነው። ግንባታውንም ጂ. ኤም. ሲ. እና ኤል. አር. ቢ. ሲ. ኤል. የተሰኙ ዓለም አቀፍ ተቋራጮች በጥምረት እያከናወኑት ነው የሚገኙት።
በጂ.ኤም.ሲ. የአዳማ-አዋሽ የፍጥነት መንገድ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ሱባረዲ ባሲረዲ እንደተናገሩት፤ ድርጅቱ መንገዱን በ4 ዓመት ተኩል ጊዜ ለማጠናቀቅ የሚያስችል በርካታ ስራዎች ከወዲሁ እያከናወነ ነው። በኮንትራት ስምምነቱ መሰረት የመንገድ ግንባታው ከተከናወነ በኋላም ለአምስት ዓመታት ተጨማሪ የጥገና ስራ የሚያከናውን ይሆናል::
የአስተዳደሩ የኮሙዩኒኬሽን ሀላፊ አቶ ሳምሶን ወንድሙ እንደገለጹት፤ የፍጥነት መንገዱ ግንባታ በመልካም ሁኔታ እየተካሄደ ይገኛል::ግንባታውን ከተያዘው ጊዜ አስቀድሞ በመጨረስ ለማስረከብ ለግንባታው የሚያስፈልጉትን ባለሙያዎችና መሳሪያዎች በማሟላት ሥራው ተጀምሯል። የካምፕ ግንባታ የስትራክቸር ስራዎች የዲዛይንና መሰል ተግባራትን በተቀመጠው እቅድ መሰረት ለማከናውን ተችሏል።
የፍጥነት መንገዱ ከእንስሳት እና ከሰዎች እንቅስቃሴ ነጻ ተደርጎ የሚገነባ በመሆኑ ለአሽከርካሪ ፍጹም ምቹ የማሽከርከር እድል እና ነጻነትን የሚሰጥ ከመሆኑም ባለፈ በአሁኑ መንገድ በተደጋጋሚ የንጹሃን ዜጎችን ህይወት እየቀጠፈ ያለውን እና የንብረት ውድመት እያስከተለ የመጣውን የትራፊክ አደጋ በመቀነስ ረገድ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል:: ይህም የሀገሪቱ ዋነኛው ችግር የሆነውን የትራፊክ አደጋ በመቀነስ በትራፊክ አደጋዎች ምክንያት የሚፈጠሩ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግር ቀድሞ ለመከላከል የሚያስችል ነው::
አንደ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር መረጃ ፤ ፕሮጀክቱ ለበርካቶች የስራ እድልም ፈጥሯል:: እስካሁን ፕሮጀክቱ መሃንዲሶችን፣ኦፕሬተሮችን፣ሾፌሮችንና የጉልበት ሠራተኞችን ጨምሮ ከ 550 በላይ ለሆኑ ዜጎች የሥራ እድል ፈጥሯል።
የግንባታው ተቆጣጣሪ መሃንዲስ ኢንጂነር ራጁማ ቱር በበኩላቸው፤ የግንባታው ጥራት አስተማማኝ እንዲሆን በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው ማለታቸው የተጠቆመ ሲሆን፤ ለግንባታው ጥቅም ላይ የዋሉት መሳሪያዎች የመንገዱን ጥራት ለማረጋገጥ የሚረዱ መሆኑንም ይገልጻሉ፤ ግንባታውም በከፍተኛ ኃላፊነት እየተካሄደ መሆኑን መናገራቸው ተጠቁሟል::
ይሁን እንጂ የወሰን ማስከበር ችግሮች እና ለግንባታው የሚውል ሲሚንቶ በሚፈለገው መጠን አለመገኘት ግንባታው በሚፈለገው ፍጥነት ለማስኬድ ጫና እያሳደረ መሆኑን ነው አስተዳደሩ ያብራራው:: የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የወሰን ማስከበር ችግር ካለበት ውስጥ 18 ኪሎ ሜትር ቦታ ነጻ በማድረግ ማስረከብ የቻለ ሲሆን፣ ቀሪ ቦታዎችን ለግንባታው ነጻ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ መሆኑን የአስተዳደሩ ኮሙዩኒኬሽን ዘግቧል።
ፕሮጀክቱ ካለው ሀገራዊ ፋይዳ አኳያ ቀሪ ቦታዎቹን ነጻ በማድረግ ግንባታው በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ የሚመለከታቸው አካላት አፋጣኝ ርብርብ እንዲያደርጉም አስተዳደሩ ጠይቋል። በተለይም የክልሉ መንግስት እና የዞን አስተዳደር ችግሩን በአፋጣኝ ለመፍታት በትኩረት መስራት አለባቸው::ፕሮጀክቱ ለአካባቢው ማህበረሰብ ጭምር ያለውን ፋይዳ ከግምት ውስጥ በማስገባት የኦሮሚያ ክልል መንግስት እና ህዝብ ከፌዴራል መንገዶች አስተዳደር ጋር በቅንጅት መስራት አለባቸው::
ከዚህ ቀደም በሀገራችን በአንዳንድ አካባቢዎች የፌዴራል መንግስት የሚያስገነባቸውን የመንገድ ፕሮጀክቶች ሌሎች አካላት እንደሚገነቡት ፕሮጀክት በመቁጠር ከፍተኛ ካሳ የመጠየቅ እና ካሳ ከተከፈለ በኋላ ንብረት አለማንሳት ችግሮች ለመንገዶች መጓተት መንስኤ ሲሆን ቆይቷል:: በእዚህ ፕሮጀክትም መሰል ችግሮች እንዳይፈጠሩ በትኩረት ሊሰራ ይገባል::
ለመንገዱ ግንባታ ሌላኛው ፈተና እየሆነ ያለው የሲሚንቶ እጥረት ነው::ለግንባታው የሚውል ሲሚንቶ በሚፈለገው መጠን አለመገኘት ሌላው ትልቅ ፈተና መሆኑን ተቋራጮቹ መጠቆማቸውን የአስተዳደሩ ኮሙዩኒኬሽን ሰሞኑን ዘግቧል:: ኢመአ አቅርቦቱ በሚሻሻልበት ሁኔታ ላይ ተገቢውን ትኩረት እንዲያገኝ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ መሆኑም ተጠቁሟል::
የሲሚንቶ እጥረት በመንግስት እና በግል ግንባታዎች ላይ እያስከተለ ያለውን ችግር ለመቅረፍ መንግስት በትኩረት እየሰራ መሆኑን በተደጋጋሚ ቢገልጽም፣ አሁንም አዳማ አዋሽ ኮንትራት አንድን የመሳሰሉ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ ሌሎች ፕሮጀክቶች በሲሚኒቶ እጥረት ምክንያት ፈተና ላይ መሆናቸው መንግስት የሲሚንቶ ችግርን ለመቅረፍ ተጨማሪ እርምጃዎችን መውሰድ እንዳለበት አመላካች ነው::
የሲሚንቶ እጥረት ዋነኛው መንስኤ ህገወጥ ደላሎች መሆናቸውን በመግለጽ እነዚህን ህገ ወጥ ደላሎች ከገበያ ሰንሰለቱ ለማስወጣት እርምጃ መወሰዱን መንግስት በቅርቡ መግለጹ ይታወሳል:: ይህም ሆኖ ችግሩ አለመቀረፉ እየተነገረ ነው:: መንግስት አሁንም በጥናት ላይ ተመስርቶ ለእጥረቱ መንስኤ እየሆነ ያለውን ችግር ከስሩ ለመፍታት መስራት ይጠበቅበታል::
የአዳማ አዋሽ 60 ኪሎ ሜትር መንገድ ግንባታ ላይ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን በመፍታት የዚህን ፕሮጀክት ግንባታ በማጠናቀቅ በቀጣይም ኢትዮጵያ ከአዲስ አበባ ተነስቶ ጅቡቲ ድንበር ደወሌ ድረስ የተዘረጋ የዘመናዊ መንገድ ባለቤት የሚያደርጋትን ከአዋሽ – ድሬዳዋ ያለውን ቀጣዩ የጅቡቲ ኮሪደር መንገድ በፍጥነት መንገድ ደረጃ ለመገንባት ርብርቡን ከወዲሁ መጀመር ያስፈልጋል::
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 16/2015