መግቢያ
ከሰሞኑ በአንድ ጠበቆች፣ ዳኞች፣ አቃቢያነ ህግች፣ የህግ ምሁራን እና የሴቶች መብት አቀንቃኞች የተገኙበት የሴቶች እኩልነት እና ሰብዓዊ መብቶች በሚል ርእስ የተዘጋጀ የውይይት መድረክ ላይ ተገኝቼ ሳለሁ፤ አንዲት ተሳታፊ ጠበቂት ሃሳቧን ስታጋራ ለህፃን ስያሜ የመስጠት መብት የወላጆች የጋራ መብት ነው ብላ በደፈናው ተናግራ ስትጨርስ የውይይቱ መሪ ይህን ሀሳብ በህግ የተደነገገ መብት ነው ብላ ስትደግም ከተሳታፊዎች ጉርምምታ ሲበዛ ለምን አላጠራውም በሚል፤ ይህንን ንግግሯን የሚደግፍ የህግ ማዕቀፍ ካለ በሚል ጥያቄ አቅርቤላት ነበር። አወያዪዋም የተሻሻለው የቤተሰብ ህግ እና ሕገ-መንግስቱ ይደነግጋል በማለት ምላሽ ስትሰጥ፤ በዚህ ነጥብ ላይ የጦፈ ክርክር ይነሳል።
በአንድ ወገን ይህንን ስያሜ የመስጠት ቅድሚያ መብት የሚደነግገው የፍትሀብሔር ህጉ ነው እንዲሁም በቤተሰብ ህጉ በግልፅ የተደነገገ አንቀፅ የለም በሚል ሲቃወሙ፤ በሌላ ጽንፍ አወያዩዋን ጨምሮ ሌሎች ተሳታፊዎች ደግሞ የሴቶች እኩልነት በሕገ- መንግስቱ ስለተደነገገ እና በተሻሻለው የቤተሰብ ህግ ስር ቤተሰብን በጋራ የማስተዳደር ኃላፊነት በጋራ መሆን አለበት በሚለው አንቀፅ ስር ይወድቃል በማለት ተከራከሩ። በመጨረሻም ከስምምነት መድረስ ሲያቅተን ጭብጥ ቀይረን ውይይቱን ቀጠልን፤ ነገር ግን እንደ አንድ የህግ ባለሙያ ጉዳዩን የበለጠ ልመረምር ይገባል ብዬ ይህንን ዕልባት ያላገኘ ነጥብ ወደ ማውቃቸው የህግ ምሁራን ወስጄ ሀሳባቸውን ስጠይቅ እዚህም ሁለት ጎራ የያዘ ምላሽ አገኘሁ። በዚህም የተነሳ ይህንን ነጥብ የበለጠ ለማጥራት ከህግ ማዕቀፎቹ፣ ከመሰረታዊ የህግ ፍልስፍና መርሆች እና ከፆታ እኩልነት አንጻር ለመመርመር ወደድኩ። ምንም እንኳ በውይይቱ አንዱን ጎራ ይዤ ስከራከር የነበረ ቢሆንም ለዚህ ፅሁፍ አላማ ሲባል ገለልተኛ ሆኜ የሁለቱንም ጎራ ክርክር አካትቼ እንደሚከተለው አቀርባለሁ።
በመሰረቱ የተሻሻለው የቤተሰብ ህግ ከመምጣቱ በፊት ቤተሰብን በሚመለከት ገዥ ድንጋጌዎችን በስሩ አቅፎ የነበረው የፍትሀብሔር ህጉ ነበር። የፍትሀብሔር ህጉም በንጉሱ ዘመን እንደመውጣቱ ወንድን ከሴት ከፍ ያደረጉ ህግጋትን በውስጡ አቅፎ ይዟል። ለምሳሌ በቤተሰብ አምዱ አባት የቤተሰብ ራስ መሆኑን እንዲሁም ቤተሰቡ የት እና በምን ሁኔታ መኖር እንዳለበት የመወሰን መብት የመሳሰሉት አቅፎ ይዟል።
ከመንግስት ለውጥ ጋር ተያይዞ አሁን የምንጠቀምበት ሕገ-መንግስት ዴሞክራሲን አስተዋውቆ የጾታ እኩልነትን ሲያውጅ፤ ከዚህ ጋር የማይሄዱ ህጎች የቤተሰብ ህጉን ጨምሮ ተሻሽለዋል። በዚህም አግባብ የተሻሻለው የቤተሰብ ህግ ወንድ እና ሴት በትዳር ውስጥ አብረው ሲኖሩ በግላዊም ሆነ በንብረት ላይ እኩል መብት እንደሚኖራቸው ይደነግጋል። ከዚህ በተጨማሪም ከትዳር መፍረስ በኋላም በልጆች አሳዳጊነት እና ንብረት ክፍፍል ላይ እኩል መብት አላቸው በማለት ያትታል። ይህ የተሻሻለው የቤተሰብ ህግ በስራ ላይ ሲውል ከዚህ ቀደም እንጠቀምበት የነበረውን የፍትሀብሔር ህጉ ውስጥ የነበረውን የቤተሰብ ህግ ድንጋጌዎች በሙሉ ሽሯል።
በሌላ በኩል ስለ አንድ ሰው ስያሜ እና ተያያዥ ጉዳዮች(Law of Person) የሚያስተዳድሩት ድንጋጌዎች በፍትሃብሔር ህጉ ከአንቀፅ አንድ ጀምሮ ይገኛሉ። በዚሁ ህግ አንቀፅ 34-35 መሰረት ለአንድ ህፃን ልጅ ስያሜ የመስጠት መብት ቅድሚያ ለአባት መሆኑን ያትታል። በተጨማሪም አባት ሳይኖር የአባት ቤተሰቦች፣ ከሌሉ እናት እና የእናት ቤተሰቦች እያለ ቅደም ተከተሉን ያስቀምጣል፤ በዚሁ ህግ እናት ለልጁ በተለምዶ የቤት ስም የማውጣት መብት ተሰጥቷታል። ይህ ስለ ሰዎች ግላዊ ሁናቴ የሚደነግገው ህግ ስለ ቤተዘመድ ስም ያስቀመጣቸው አንቀፆች ጥቅም ላይ ካለመዋላቸው የተነሳ ተሽረዋል፤ ከነኚህ ስለ ቤተዘመድ ከሚያትቱት አንቀፆች ውጪ ያሉት ድንጋጌዎች ግን በስራ ላይ የሚገኙ ገዢ ህግጋት ናቸው።
አሁን ለዚህ ፅሁፍ መነሻ ወደሆነው የክርክር ነጥብ ስመለስ፤ በመጀመሪያ ስያሜ የመስጠት መብት የጋራ መብት ነው ከሚሉት ወገኖች መከራከሪያ ጭብጦችን
ልዘርዝር፤
- የፆታ እኩልነት በህገ-መንግስት አንቀፅ 7፣25፣35 መሰረት እና በተሻሻለው የቤተሰብ ህግ አንቀፅ 50፣54፣ና 66(1) ስር በመቀመጡ፤ ይህንን ሚቃረኑ ህጎች ውጤት አልባ ናቸው። ስለዚህም ስለ ስያሜ በሚደነግገው የፍትሀብሔር ህግ ስር ለአባት ስያሜ የመስጠት ቅድሚያ የሚሰጠው አንቀፅ ውጤት አልባ ይሆናል።
- ለአንድ ሕፃን ልጅ ስያሜ የመስጠት ጉዳይን የሚመለከተው ህግ የፍትሀብሔር ህጉ ሳይሆን የቤተሰብ ህጉ ነው። ምክንያቱም ጉዳዩ ከልጅ ስያሜ ባለፈ እናትን እና አባት ስለሚያካትት የግል ሳይሆን የቤተሰብ ጉዳይ ስለሚሆን በተሻሻለው የቤተሰብ ህግ ስር ሊካተት ይገባል።
- የተሻሻለው የቤተሰብ ህግ ይህንን የስያሜ ጉዳይ በተመለከተ በቀጥታ የተቀመጠ አንቀፅ ባይኖረውም፤ ቤተሰብን በጋራ ስለማስተዳደር የሚያትተው አንቀፅ 50(2) እንደሚያዘው ‹ባልና ሚስት በማናቸውም ሁኔታ በጋራ ተባብረው የቤተሰባቸውን ጥቅም ማስከበርና ጥበቃ የማድረግ፤ በተጨማሪም ልጆቻቸው ኃላፊነት የሚሰማቸው ዜጎች እንዲሆኑ ለማስቻል በጥሩ ትምህርት እና እንክብካቤ ሊያሳድጉ ይገባል›። በመሆኑም እናትና አባት ለልጆቻቸው አሳዳጊና ተንከባካቢ ‹Guardian & Tutor› ስለሆኑ ይህ ኃላፊነታቸው ደግሞ በተዘዋዋሪ ‹Impliedly› ስያሜ መስጠትን ያካትታል። ስለዚህ አንቀፅ 50(2) በቀጥታ ባይገልፀውም ተለጥጦ ሲነበብ ስያሜ መስጠትንም የሚጨምር ይሆናል።
ከላይ በተዘረዘሩት ምክንያቶች የተነሳ የፍትሀብሔር ህጉ የስያሜ ድንጋጌዎች ከፆታዊ እኩልነት መብት ጋር ተፃራሪ ስለሆነ ሊሻር እንደሚገባው፣ የተሻሻለው የቤተሰብ ህግ አንቀፅ 50(2) በቀጥታ ባይገልፀውም ተለጥጦ ሲነበብ ስያሜ መስጠትንም የሚጨምር ስለሆነ እና ጉዳዩ ከሚያካትታቸው ሰዎች አንፃር ከግላዊ ባህሪ ይልቅ ቤተሰብን የሚመለከት ስለሆነ ስያሜ የመስጠት መብት በሁለቱም ተጋቢዎች የጋራ ስምምነት መሰረት የሚከናወን ይሆናል በሚል ተከራክረዋል።
በሌላ በኩል የዚህ ሀሳብ ተቃራኒዎች በበኩላቸው የሚከተሉትን መከራከሪያ ነጥቦች በማስቀመጥ ስያሜ የመስጠት መብት በፍትሃብሔር ህጉ ድንጋጌ መሰረት ቅድሚያ የአባት ነው በማለት ተከራክረዋል።
- በመጀመሪያ ጉዳዩ የአንድን ሰው ስያሜን የሚመለከት ስለሆነ የግል ጉዳይ ነው። ምክንያቱም ስም ለልጁ መጠሪያ እስከሆነ ድረስ የቤተሰብ ህግ ገዢ ሊሆን አይችልም። በፍትሀብሔር ህጉ በግልፅ ስለ ስያሜ የተደነገጉ ድንጋጌዎች እያሉ በተውሶ ከሌላ ህግ መጠቀም ከህግ ፍልስፍና አንፃር ተገቢ አይደለም።
- ሀገራችን የምትከተለው የህግ ስርዓት ‹Civil Law Legal System› በመፅሀፍ የተደነገጉ ህጎች ስለሚጠቀም አንቀፆች በግልፅ ለታለመላቸው አላማ ብቻ ነው ሊውሉ የሚገባው። በመሆኑም የህገ-መንግስቱ የእኩልነት ድንጋጌዎች እና የተሻሻለው የቤተሰብ ህግ አንቀፅ 50(2) በልኩ ሊተረጉመው ይገባል እንጂ የህግ ስርዓታችን በማይፈቅድ መልኩ እንደ አውሮፓና አሜሪካ ሀገራት ሊለጠጥ አይገባም።
- Ø በተያያዘም አንድ ህግ አንድን ነገር በጋራ ይወሰን የሚል ከሆነ በስሩ ስምምነት ላይ መድረስ ካልተቻለ ምን ሊደረግ እንደሚገባ ያስቀምጣል። ስለዚህ የተሻሻለው የቤተሰብ ህግ አንቀፅ 50(2) ስያሜን ይጨምራል ብንል እንኳ፤ አባት እና እናት መስማማት ካቃታቸው ምን ሊደረግ እንደሚገባ ሊያስቀምጥ ይገባ ነበር። በመሆኑም ከላይ የተጠቀሰው ድንጋጌ የመፍትሄ ሀሳብ አለማስቀመጡ ስያሜን እንደማያካትት ገላጭ ማስረጃ ነው።
- Ø የተሻሻለው የቤተሰብ ህግ መሰረት በአንዳንድ ልዩ በሆኑ ሆኔታዎች እናት እና አባት በህይወት እያሉ የአሳዳጊነት መብት ለሌላ ሦስተኛ ወገን ተላልፎ ሊሰጥ የሚችልባቸው ሁኔታዎች አሉ። ስለዚህ በአሳዳጊነት ‹Guardian & Tutor› መብት ውስጥ ስያሜ መስጠት ከተካተተ ለሦስተኛ ወገኖች መብቱ ሊተላለፍ ሊሆን ነው ማለት ነው።
- Ø አንድ ህግ ከሚሻርባቸው መንገዶች መካከል በሌላ ህግ መውጣት ምክንያት እና ጥቅም ላይ ባለመዋል(ባለመጠቀም) ይገኙበታል። በመሆኑም የተሻሻለው የቤተሰብ ህግ በስራ ላይ ሲውል ሊሽር የሚገባው በፍትሀብሔር ህጉ ስር የነበሩትን ስለ ቤተሰብ የሚደነግጉ አንቀፆች እንጂ ስለግል ህግ ‹Law Of Person› አንቀፆችን ሊሆን አይገባም። እንዲያውም ጥቅም ላይ ባለመዋላቸው የተነሳ ስለ የቤተዘመድ ስም ‹Family Name› የሚያትቱት አንቀፆች ተሻሩ እንጂ እንኳን ለልጁ ቅድሚያ ስም ማውጣት ይቅርና ሚስት ራሷ የአባቷን ስም እንድትቀይር ልትገደድ ትችል ነበር።
- በመሆኑም ስም የማውጣት መብት ለአባት ቅድሚያ መስጠቱ እኩልነትን አይፃረርም። ምክንያቱም የፆታ እኩልነት ማለት በሁሉም ረገድ እኩል ይሁኑ ማለት ሳይሆን እንደ ሁኔታው አንዱ ሌላው ላይ ጫና እንዳያሳድር ለመጠበቅ ነው። እንደሚታወቀው ለሴቶች ከህገ-መንግስቱ ጀምሮ የተሻሻለው የቤተሰብ ህግ እና ሌሎች ህጎች ቅድሚያና ልዩ ጥበቃ ያደርጋሉ። ስለዚህ ለልጅ ስያሜ ቅድሚያ የመስጠት መብት በፍትሀብሔር ህጉ ስር እንደተቀመጠው የአባት ነው።
- ማጠቃለያ
- በእውነቱ ከሆነ ከላይ የተጠቀሱት የህግ ባለሙያዎች ክርክር እንዳለ ቢሆንም በተግባር ስም እኔ ላውጣ በሚል ወደ ፍ/ቤት ያመራ መዝገብ ወይም የሰበር ውሳኔ እስከአሁን ያለ አይመስለኝም(በግሌ አላጋጠመኝም)። በተጨማሪም የማህበረሰባችን የቤተሰብ አወቃቀር እና የቤተሰባዊነት መርህ እንደሚያሳየው አንድ ህፃን ልጅ ሲወለድ በብዛት ስም የሚያወጡት ከወላጆቹ ይልቅ ጓደኛ፣ ጎረቤት እና ዘመድ አዝማድ የመሳሰሉ ሰዎች በመሆናቸው ስያሜ ላይ ብዙም ግጭት አይስተዋልም። ቢያጋጥምም ልጅ ማግኘት ትልቅ የደስታ ምልክት ስለሆነ እዛው በቤተሰቡ ውስጥ የይፈታል እንጂ ወደ ፍ/ቤት የመምጣት ዕድሉ ጠባብ ነው።
- ነገር ግን እንደህግ ባለሙያ ወጥ የሆነ አካሄድ ሊኖር ስለሚገባ እና ጉዳዩ ወደ ፍ/ቤት ቢመጣ እንኳ የተለያየ ውሳኔ እንዳይኖር በሚል ይህን ክርክር ለማሳወቅና ግልፅ ለማድረግ ታሳቢ ያደረገ ፅሁፍ ነው። በመሆኑም እንደ ገለልተኛ ባለሙያ ስመለከተው ሁለቱም ጎራዎች ተገቢ የሆነ የክርክር ነጥብ አላቸው። የመጀመሪያው ጎራ የፍትሀብሔሩ የስያሜ አንቀፆች ከፆታዊ እኩልነት ጋር መጋጨታቸው እውን ነው፤ በሌላኛው ጎራ ደግሞ በግልፅ ያልተሻረ ህግ እያለ በሌላ ህግ መገዛት ተገቢ አለመሆኑ እና አንድን አንቀፅ ከታለመለት አላማ ውጪ መለጠጥ ከመሰረታዊ የህግ መርሆች አንፃር የሚፃረር መሆኑ እውነት ነው። ከዚህ አንፃር የኔ እይታ፤ ምንም እንኳ ህጉ እኩልነት የሚያጠነጥን ባይሆንም በግልፅ እስካልተሻረ ድረስ በደፈናው መሸፋፈን የለብንም። ስለዚህ የትኛው ሃሳብ ሚዛን ይደፋል የሚለው ለአንባቢዎች፤
- ‹ፍርዱን ለናንተው ብያለሁ›
- አቶ አቤል ልዑልሰገድ አበበ- (በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህርና ባለሙያ)
አዲስ ዘመን ሐምሌ 15/2014