የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ በቅርቡ ባደረገው ስብሰባ ለወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ የሚውል የ2 ቢሊዮን ብር ፈንድ አጽድቋል። በዚህም መሠረት ዝርዝር ዕቅዶችን በማዘጋጀት እና በአፋጣኝ ከወጣቱ ጋር ሰፊ የምክክር መድረኮችን በማዘጋጀት የጋራ መግባባት ላይ ከተደረሰ በኋላ ወጣቶቹ በተለያየ ዘርፍ ወደ ስራ እንዲገቡ ካቢኔው አቅጣጫ አስቀምጧል።
በከተማዋ ከ700ሺ በላይ ስራ አጥ ወጣት እንዳለ በስብሰባው የተመላከተ ሲሆን ይህ የሁለት ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ የብድር ፈንድ ያለውን የስራ አጥ ቁጥር ለመቀነስ እና የከተማዋን ኢኮኖሚ በማነቃቃቱ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ይጠበቃል።
ፈንዱን አስመልክቶ አስተያየታቸውን ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ የሰጡት የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች ማህበራት አመራሮች እንደተናገሩት ፈንዱ የወጣቶችን የስራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ እገዛ ይኖረዋል። ፈንዱ በራሱ የወጣቶች ችግር መፍትሄ ስለማይሆን የወጣቶችን ችግር በሚፈለገው ልክ እንዲቀርፍ ከዚህ በፊት የተለቀቁ ፈንዶች አጠቃቀም ላይ ያጋጥሙ የነበሩ ተግዳሮቶች እንዳይደገሙ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል። የፖለቲካ ትኩሳትን ተከትሎ በሚፈቀድ ፈንድ ብቻ የሚፈቱ ባለመሆናቸው ገንዘብ ከማቅረብ ባሻገር ችግሮች በዘላቂነት የሚፈቱበት አሰራር ሊበጅ ይገባል።
የልደታ ክፍለ ከተማ ወጣቶች ማህበር ሰብሳቢ ወጣት ሙከረም ተካ እንደተናገረው የከተማዋ ወጣት በርካታ ችግሮች አሉበት። ከእነዚህ መካከል የስራ አጥነት ችግር አንዱ ነው። በርካታ የከተማው ወጣት በመንቀሳቀሻ ገንዘብ እጦት ምክንያት ስራ አጥ ሆኗል። አልባሌ ቦታዎች ላይ እየዋለ ነው። ችግሩን ለማቃለል የከተማው አስተዳደር ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል። ድጋፉ የወጣቶችን ችግር በማቃለል ረገድ የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት አልቻለም። ይሁን እንጂ እንደገና ሁለት ቢሊዮን ብር ፈንድ መመደቡ ይበል የሚያሰኝ ተግባር ነው ብሏል።
ፈንድ መመደብ በራሱ የወጣቶችን የስራ አጥነት ጥያቄ በሚፈለገው ልክ እንደማይቀርፍ የተናገረው ወጣት ሙከረም፤ ለዚህ ደግሞ ከዚህ ቀደም የተለቀቁ ፈንዶች በተለይም በ2009 ዓ.ም የተለቀቀው ፈንድ የወጣቱን ችግር በሚፈለገው ልክ መቅረፍ አለመቻሉ ጥሩ ማሳያ ነው ይላል።
አዲስ የጸደቀው ፈንድ ወጣቱ ሰርቶ ራሱንና ሀገሩን የመጥቀም ህልም እንዲያሳካ የፈንድ አጠቃቀም መመሪያዎች በተገቢው መንገድ ስራ ላይ መዋል እንዳለባቸው ይናገራል። ከዚህ ቀደም የተለቀቀው ፈንድ በአንዳንድ አካባቢዎች ለሁለት ለተደራጁ ወጣቶች ሲሰጥ በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ ለአምስት መደራጀት የግድ ነበር። በመሆኑም አሁን በተለቀቀው ፈንድ ላይ ተመሳሳይ የአሰራር ጉራማይሌነት እንዳይኖር ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ብሏል።
እንደሙከረም ማብራሪያ፤ ወጣቶች በፈንዱ ዙሪያ ያላቸው ግንዛቤ አናሳ መሆን ወጣቱን ከስራ አጥነት ለማላቀቅ ለሚደረገው ጥረት ሌላኛው ጋሬጣ ሆኗል። ተዘዋዋሪ ፈንድ ሲባል የመንግስትን ገንዘብ ተከፋፍሎ ሄዶ በአልባሌ ቦታ ላይ ማዋል የሚመስላቸው አንዳንድ ወጣቶች አሉ። የመንግስትን ገንዘብ ወስዶ የቤት ዕቃ የሚያሟላ ወጣት አለ። አንዳንድ ወጣቶች ደግሞ በገንዘቡ በሀገራቸው ሰርተው ራሳቸውንና ሀገራቸው መለወጥ ሲገባቸው በወሰዱት ገንዘብ በህገ ወጥ መንገድ የሚሰደዱም አሉ። ይህን የግንዛቤ ክፍተት ለመድፈን የፈንድ ምንነትና አጠቃቀም ላይ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች መሰራት አለበት ሲል መክሯል።
ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ የሚለቀቅ ገንዘብ የሚፈለገውን ለውጥ እንዳያመጣ የሚያደርጉ መሰናክሎች ከላይ እስከ ታች ባለው የመንግስት መዋቅሮች ውስጥ አሉ የሚለው ወጣት ሙከረም፤ የመንግስት አካላት ታች ድረስ ወርደው ፈንዱ ወጣቱ ጋር እየደረሰ መሆኑን በማረጋገጥ ከአጠቃቀም ጋር ተያይዞ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ከስር ከስር ለመቅረፍ ተከታታይ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ እንዳለባቸው ያብራራል።
ወጣት ሙከረም አክሎም፤ ወጣቱም መንግስትና ህዝብ ያቀረበለትን ገንዘብ በአግባቡ መጠቀም አለበት ይላል። በብድር ገንዘብ ማግኘት በራሱ ትርፋማ እንደማያደርገው አውቆ አትራፊ የሚሆንበትን ዘርፍ መርጦ ስራ ላይ ማዋል አለበት። ወጣቱ ገንዘቡን ለመውሰድ ደስተኛ እንደሆነ ሁሉ ለመመለስም ደስተኛ መሆን አለበት።
ወጣቱ ገንዘቡን በአግባቡ ስራ ላይ አውሎ ራሱን ለውጦ በገባው ውል መሰረት መመለስ አለበት። ገንዘቡን የወሰዱ ልጆች የማይመልሱ ከሆነ ሌሎች ስራ አጥ ወጣቶች መስሪያ ገንዘብ ማግኘት አይችሉም። በመሆኑም ወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድን ይዞ መጥፋትና አለአግባብ ስራ ላይ ከማዋል መቆጠብ አለባቸው። ወጣቱ ፈንዱን እንደ ስጦታ ሳይሆን እንደዕዳ ማሰብ አለበት ብሏል።
‹‹የፖለቲካ ትኩሳት ሲከሰት ብቻ በሚጸድቅ ፈንድ የወጣቶች የስራ አጥነትና የኢኮኖሚ ችግሮች ሊፈታ አይችልም›› ያለው ወጣት ሙከረም፤መንግስት የወጣቶች ችግር በዘላቂነት የሚፈታበት አግባብ መፈለግ አለበት ይላል። መንግስት ወጣቱን በቋሚነት ሊለውጡ የሚችሉ ስራዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት ያብራራል። ወጣቶች የሚያጋጥማቸው የመስሪያ፣ የማምረቻና የመሸጫ ቦታ ችግሮችን ለመቅረፍ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል። ለዚህም በህገ ወጥ መልኩ የተያዙ ሼዶች ከህገ ወጦች እጅ ወጥቶ ለወጣቶች የሚተላለፍበት ሁኔታ ሊመቻች ይገባል ሲል መክሯል።
የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች ማህበር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይሁነኝ መሃመድ በበኩሉ እንደተናገረው የወጣቱን የስራ አጥነት ችግር ለመፍታት ከዚህ በፊት ሲሰሩ የነበሩ ስራዎች ከተግዳሮቶች የተላቀቁ አልነበሩም። ስራዎቹ በአመዛኙ የወጣቱን ፍላጎት ያላገናዘቡና ወጣቱን አሳታፊ ባለመሆናቸው የሚፈለገውን ውጤት ሲያስገኙ አይታይም። ግልጸኝነት የጎደላቸውም ነበሩ።
እንደ አቶ ይሁነኝ ገለፃ ስራ አጥነትን ለመቅረፍ የሚመደብ ገንዘብ የሚያስተዳድሩ ባለሙያዎችና በአመራሮች በኩል ግልጸኝነት አለመኖር አንዱ ክፍተት ነው። ስለተመደበው ገንዘብ መረጃው ያላቸው አንዳንድ አመራሮችና ባለሙያዎች በጥቅማ ጥቅም ለተሳሰሩትና ለዘመድ አዝማድ ብቻ ግልጽ በማድረግ ብዙሃኑ እንዳይጠቀሙና ጥቂቶች ብቻ እንዲጠቀሙ ሲያደርጉ ነበር። ከዚያ ባሻገር ወጣቶች ‹‹የተመደበው ገንዘብ ‹የእኔን የስራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ የተመደበ ነው›› ብሎ ገንዘቡን ወስዶ የመጠቀም ክፍተት ነበረበት።
ከዚህ በፊት ያጋጥሙ የነበሩ ችግሮች እንዳይደገሙ በመጀመሪያ የተመደበው ገንዘብ ለምን ተመደበ የሚለውን ሁሉም አካል በግልጽ ማወቅ አለበት ያለው አቶ ይሁነኝ ገንዘቡ የተዘጋጀው ለሚሰሩና ለመለወጥ ዝግጁ ለሆኑ ወጣቶች ብቻ እንደሆነ ሁሉም ሊያውቀው ይገባል። መንግስት ይህንን ግልጽ አድርጎ ማሳወቅ አለበት ይላል። ፈንዱን ለመጠቀም መሟላት ያለባቸው መስፈርቶችም ግልጽ አድርጎ ማስቀመጥ ፈንዱ የሚፈለገውን ፍሬ እንዲያፈራ ሚና ይኖረዋል።
እንደ ይሁነኝ ማብራሪያ ለፈንዱ ስኬታማነት የወጣቶች ዝግጁነት አስፈላጊ ነው። ወጣቶች በተመደበው ገንዘብ ተጠቅሜ ራሴን ለውጬ እመልሳለሁ የሚል ዝግጁነት ሊኖራቸው ይገባል። ፈንዱን የሚያስተዳድሩ ኃላፊዎችና ባለሙያዎችም የማይተካ ሚና አላቸው። መንግስት ሀገሪቱ ካላት ጥቂት ሀብት ለወጣቶች የመደበውን ገንዘብ በትክክል ለታለመለት ዓላማ ውሎ ‹‹ወጣቶች ተጠቅመው እንዲመልሱና በቀጣይም ወጣቶች ወስደው እንዲጠቀሙ የማድረግ ኃላፊነት አለብኝ›› ብለው በኃላፊነት መንፈስ መንቀሳቀስ አለባቸው። መንግስት እያደረገ ያለው ድጋፍ ስራ ላይ ለሚሰማሩት ብቻ መሰጠት እንዳለበት አምነው መስራት አለባቸው ብሏል።
ለወጣቶች የተመደበው ገንዘብ በምንም መልኩ ከፖለቲካ ጋር መያያዝ የለበትም ያለው ወጣት ይሁነኝ፤ የተመደበውን ገንዘብ መንግስትም ሆነ ሃላፊዎች፣ በወጣቶች ዘንድ ከፖለቲካ ጋር ማያያዝ የለባቸውም።
አመራር ላይ ያሉ አካላት ገንዘቡን በሚደለድሉበት ወቅት የፖለቲካ አመለካከትን፣ ብሄርንና ሃይማኖትን መሰረት ካደረገ ድልድል መቆጠብ አለባቸው ብሏል። ለትርጉም አጋላጭ እንዳይሆን አመራሩ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት በመግለጽ ገንዘቡ ሲሰጥ ስራ አጥ ለሆኑና ለመስራት ፍላጎት ላላቸው ብቻ መሆን እንዳለበት መክሯል።
ወጣት ይሁነኝ እንዳለው፤ ሀገሪቱ የበርካታ ወጣቶች ሀገር እንደመሆኗ የወጣቶች ጉዳይ ሁሌም ከሀገሪቱ ትላልቅ አጀንዳዎች መካከል አንዱ ሆኖ መቅረብ አለበት። እንደ አንድ አጀንዳ ሳይያዝ ቀርቶ በዘመቻ መልክ በሚሰራ ስራ የወጣቱ ችግር አይፈታም። የአሁኑ ፈንድም ቢሆን የከተማዋን ወጣት አጠቃላይ ችግር ሊቀርፍ አይችልም። ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ ስትራቴጂና የረጅም ጊዜ እቅድ ሊኖር ይገባል።
አዲስ ወደ ስራ ለሚገቡ ወጣቶች ከሚደረግ የገንዘብ ድጋፍ ባሻገር ወደ ስራ የገቡ ወጣቶችንም መደገፍ ያስፈልጋል ያለው ወጣት ይሁነኝ፤ እነዚያ ወጣቶች ድጋፍ ቢደረግላቸው ወደ ስራ መስመር የገቡ በመሆናቸው ከስራቸው ለሌሎች ወጣቶችም የስራ እድል መፍጠር የሚችሉ ናቸው። በመሆኑም እነዚህ ወጣቶች የሚረዱበት ስትራቴጂ ሊቀረጽ ይገባል ብሏል።
በአጠቃላይ አዲሱ የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት ከዚህ ቀደም ተለቀው የነበሩ ፈንዶች ምን ችግር ነበረባቸው? ምን ውጤትስ አስገኙ? የሚለው በተጨባጭ ሊፈተሽ ይገባል። ምክንያቱም ፈንዶቹ በተለምዶ የሚለቀቁት ወቅታዊ ችግሮችን ተከትሎ በመሆኑ ምን ያህል ጥናት ተደርጎበታል የሚለው በሚገባ ሊመለስ ይገባል። ይህ ደግሞ አዲስ ለተለቀቀው ፈንድ ስኬታማነት ትልቅ ግብዓት ይሆናል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 19/2011
በ መላኩ ኤሮሴ