ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ሰኔ 30/2014 በህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ለቀረቡላቸው በርካታ ጥያቄዎች በየፈርጁ ምላሽ እና ማብራሪያ መስጠታቸው ይታወሳል። በተለይም በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ስለሚስተዋለው የሠላም ሁኔታ በርካታ ምሳሌዎችን በማጣቀስ ማብራሪያ ሰጥተዋል። የሀገሪቱን ሠላምና ደህንነት አስመልክቶ ከሰጧቸው ማብራሪያዎች መካከልም የሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ተጠቃሽ ሲሆን፣ በዚህ ጉዳይ ላይ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፍ ሁኔታዎችን በማጣቀስ አስረድተዋል።
በሰላምና ደህንነት ዙሪያ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር የሰጡት ማብራሪያ ላይ ሐሳባቸውን የሰነዘሩት የዘርፉ ምሁራን በበኩላቸው፤ እውነታውን በግልጽ ይፋ በማድረግ የህዝብን ድጋፍ መያዝና ህዝብ በሠላም ሁኔታ የመኖር መብቱን ማስጠበቅ እንዲሁም ወቅታዊ መረጃዎችን በወቅቱ ለዜጎች በመስጠት ሀገሪቱን ከጫና ማላቀቅና ህዝቡን ከጎኑ ማሰለፍ የመንግስት ኃላፊነት መሆኑን መገንዘብ ያሸዋል ሲሉ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ስለ ሀገሪቱ ወቅታዊ ሠላም እና ደህንነት አስመልክቶ፤ ‹‹በብዙ መንገድ ኢትዮጵያ ላይ አሁን እየተካሄደ ያለው ጦርነት የግራጫ ጦርነት ነው። ነጭ መዝገብ ላይ ወይም ጥቁር መዝገብ ላይ የተቀመጠ ሳይሆን የግራጫ ጦርነት ባህሪ ነው ያለው›› ሲሉ ለህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት አባላት ሐሳባቸውን ገልጸዋል።
በማብራሪያቸውም ወቅት፤ የግራጫ ጦርነት ሲባልም አንደኛው የመረጃ ጦርነት መሆኑን አብራርተዋል። ይህንንም በምሳሌ አስደግፈው ሲናገሩ፤ በወለጋ አንድ ቀበሌ ውስጥ ነገ ሞት የሚካሔድ ከሆነ በብዙ ዓለም ያሉ የመረጃ ተዋናዮች ያውቁታል። ልክ ሞት እንደተከሰተም የዓለም ሚዲያዎች ይዘግባሉ። እኛ ገና መረጃውን ሰምተን ወታደርን በምናሯሯጥበት ጊዜ የመረጃ ጦርነቱ አካል ስለሆነ ከእኛ በላይ አጀንዳውን ማስፋት የሚችል ኃይል አለ ብለዋል።
ሁለተኛው ሰላምን የማወክ ስራው ዲፕሎማሲ ተኮር ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ዳታውን ላለማጋነን ፈርቼ እንጂ በአደጉ ሀገራት ግድያ ያለው በየደቂቃው ነው ብለዋል። ሀገራት በየቀኑ ሰው ይሞትባቸዋል፤ በምንም መመዘኛ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፈው ዓመት ተደምሮ ወደ ቁጥር ከመጣን በጣም ጥቂት ነው። እዚያ ግን የሀገሬው ሚዲያ ከሚያወራው ውጭ አጀንዳ ስለማይሆን፤ እኛም ዘንድ ስለማይደርስ፤ በየቀኑ ሰው እየሞተባቸው ያሉ ሀገራት ሳይቀር ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ጉዳይ አስጨንቋቸው የዓለም ሚዲያ አጀንዳ እንደሚያደርጉት ነው የተናገሩት ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በከተማቸው ሰው እየሞተ፤ ልጆቻቸው እየሞቱ፤ ያን መከላከል ሳይችሉ የእኛን ጉዳይ ግን የዓለም አጀንዳ ማድረግ ይፈልጋሉ›› ሲሉ ለህዝብ እንደራሴዎች ማብራራታቸው ይታወሳል። ከዚህ በተጨማሪም የሳይበር ጦርነት እና የተልዕኮ ውጊያም የአፍራሽ አካላት ሚና መሆኑን ዶክተር ዐቢይ አብራርተዋል።
ታዲያ ይህን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር ከምሁራን እይታ አኳያ እንዴት ይታያል ሲል የዝግጅት ክፍላችን ለምሁራኑ ላቀረበላቸው ጥያቄዎች ንግግሩን በተመለከተ ሙያዊ ማብራሪያ ከሰጡት መካከል አንዱ የህግ ባለሙያው አቶ በፍርዴ ጥላሁን ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በህዝብ እንደራሴዎች ለቀረበላቸው ጥያቄዎች የሰጡት ምላሽ ከሞላ ጎደል መልካም የሚባል ነው፤ ነገር ግን ብዙ መስተካከል የሚገባቸው ነገሮችም አሉ። ከዚህም ውስጥ በተለይም በአደጉት ሀገራት የሆነውን የወንጀል ድርጊት ከኢትዮጵያ ጋር ለማነፃፀር የተሄደበት መንገድ አግባብ አለመሆኑ ተጠቃሽ ነው።
ለዚህም ማብራሪያ ሲሰጡ እንደተናገሩት፤ በአደጉት ሀገራት በብዛት የሚሰማውና እየተከናወነ ያለው የጅምላ ጭፍጨፋ ሳይሆን እየተፈጸመ ያለው በህገ ወጥ መንገድ በታጠቁት የጦር መሳሪያ አጠቃቀም የመነጨ ጋጠ-ወጥነት ነው። አሊያም በአደንዘዥ ዕፅ በከፍተኛ ሁኔታ በመጠቀምና በመጦዝ ወይንም በአዕምሮ መታወክና ግልፍተኝነት የሚፈፀም ወንጀል ነው።
ይህም ቢሆን በህግ አግባብ መስመር ለማስያዝ አቅም መገንባታቸውን የገለጹት የህግ ባለሙያው አቶ በፍርዴ፣ በፍርድ አደባባይም እንደሚያቆሙት አስረድተዋል። ይሁንና በኢትዮጵያ ውስጥ እየተከሰተ ያለው ደግሞ በተወሰነ አካባቢ ላይ ያነጣጠረ ተደጋጋሚ ግድያና ማፈናቀል እንደሆነ ጠቅሰው፤ ይህን አስመልክቶ የህዝብ እንደራሴዎች ላነሱት ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡት ምላሽ አጥጋቢ እንዳልሆነ ነው የተናገሩት።
እርሳቸው እንደሚሉት፤ በተለያየ ቦታ በጅምላ የሚሞቱት ሰዎች በመሆናቸው ብቻ በሰብዓዊነት ሁሉም በጋራ ድርጊቱን ሊያወግዘው እና ሊቆጣጠረው ይገባል። ይሁንና አማራ ሲሞት አማራ ብቻ የሚቆረቆር እና የሚጠይቅ፤ ሌላው ብሄር ሲሞት ደግሞ የብሄሩ ተወላጅ ብቻ ሊያወግዘው ወይንም ሊቆረቆር አይገባም። ይልቁንም ይህ በሰው ልጆች ላይ የተፈፀመ ወንጀል መሆኑን በማመን በአንድነት ማውገዝ ይገባል።
የዜጎች ሞት የፖለቲካ ነጥብ ለማስቆጠር የሚነሳ ሳይሆን ለሁሉም አካል የጋራ ህመም ስለመሆኑና ሰብዓዊነት ላይ የተፈጸመ በመሆኑ በጋራ በመቆም መኮነን ይገባል። እውነታውን በግልጽ ይፋ በማድረግ የህዝብን ድጋፍ መያዝና የህዝብን በሠላማዊ ሁኔታ የመኖር መብት ማስጠበቅ የመንግስት ኃላፊነት መሆኑን መገንዘብ ይገባል ብለዋል። የህግ ባለሙያው ከዚህም በዘለለ ስለሁኔታው ማብራራት ብቻ ሳይሆን ይቅርታ መጠየቅንም ያካትታል ባይ ናቸው።
የሀገሪቱ ህገ-መንግስት የሁሉም ገዢ በመሆኑና በሁሉም ቦታ ገቢራዊነቱ መረጋገጥ ስላለበት የህዝብ እንደራሴዎችም ይህን በማረጋገጥ ረገድ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል። ከአንዱ ጫፍ ያለው አዋጅ ሆነ መመሪያ የሁሉም እና የጋራ ስለመሆኑም ሊጤን እንደሚገባ ባለሙያው ያስገነዝባሉ። ይህ ካልሆነ ግን ችግር ፈጣሪዎች ቦታ እና ሁኔታዎችን እየቀያየሩ መቀጠላቸው አይቀሬ ነው የሚል እምነትና ሙሁራዊ ምልከታ እንዳላቸው አመልክተዋል።
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር እና ጥረት በተጨማሪም የማህበራዊ ሚዲያ እና ማህበረሰብ አንቂዎች የሚሄዱበት መንገድ ሀገሪቱን ከችግር ለማላቀቅ የራሱ የሆነ ሚና አለው። በተለይም ደግሞ ሀገሪቱን በአሁኑ ወቅት ለመታደግ መጥፎ ዜናዎችን ሆን ብሎ ከማሰራጨት በመቆጠብ አቀራራቢ ሐሳቦች ላይ ማተኮርም አንዱ መፍትሄ መሆኑን ባለሙያው ያብራራሉ። እነዚህ ሚዲያውን የሚዘውሩ አካላት ገንዘብ የመስራት ፍላጎታቸውንም መጥፎ ነገሮችን ከማውራት ይልቅ በመልካም ነገሮች ላይ በመንተራስ ገንዘብ ማግኘት እንዳለባቸውም ማጤን እንዳለባቸው ያመለክታሉ። ነገር ግን ችግሮችን በማድበስበስ እና በመሸፋፈን ማለፍ በቀጣይ ችግሮችን የበለጠ ሊያወሳስብ ስለሚችል የጥንቃቄ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚገባም ነው የሕግ ባለሙያው አቶ በፍርዴ የሚያሳስቡት።
በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የዲፕሎማሲና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር አቶ እንዳለ ንጉሴ በበኩላቸው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለዲፕሎማሲ ጦርነት ያነሱት ጉዳይ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ትልቁ የጦርነት መሳሪያ ስለመሆኑ ይናገራሉ። በርካታ ሀገራት በቀጥታም ይሁን በእጅ አዙር ምኞታቸውንና ፍላጎታቸውን ለማሳካት ይህን ስልት እንደሚጠቀሙ ይገልጻሉ።
እንደ አቶ እንዳለ ገለፃ፤ የዲፕሎማሲ ጦርነት ምዕራባውያኑ የተካኑበት ሲሆን፣ ፍላጎታቸውን በአቋራጭ ለማግኘት እና ያለሙትን ደግሞ በሌላው ላይ ለመጫን ይጠቀሙበታል። በዚህም ዓለም አቀፍ ተቋማት ጭምር ተናበው የሚሰሩበት ነው። በዚህ የግራጫ ጦርነት በርካቶችን መጉዳታቸው ይነገራል። እነዚህ ሀገራት ይህን ስውር ሴራ ሲሠሩ ደግሞ ብቻቸውን ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሰሚነት ያላቸውን የመገናኛ ብዙሃን አውታሮችንም ጭምር በመያዝ ነው።
ዓለምአቀፍ ተቋማት በግራጫ ጦርነት እና የመገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም ዓለም ምስቅልቋል አውጥተዋል ይላሉ። ለአብነትም ሶሪያ፣ ሊቢያ፣ ኢራቅ እና በርካታ ሀገራትም የፈረሱት እና እየፈረሱ ያሉትም በዚህ የተናበበ አካሄድ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ሰሞኑን የሱዳን ትንኮሳን አስመልክቶ የምዕራባውያን ሚዲያዎች ሲሰጡት የነበረው ሽፋን የግራጫ ጦርነቱ አንድ አካል መሆኑን ይናገራሉ። ከዚህም በተጨማሪ የአውሮፓ ህብረት ህዳሴ ግድብን አስመልክቶ የግብፅ ጥቅም መነካት የለበትም በማለት ያወጣው መግለጫ ሚዛናዊነት የጎደለው ከመሆኑም በተጨማሪ ግራጫ ጦርነት አንዱ መልክ ነው ሲሉ ተናግረዋል። ይህንንም ለማድረግ የተፈለገው ዓላማቸውንና ፍላጎታቸውን ለማሳካትና ኢትዮጵያን ጫና ውስጥ ለማስገባት በማሰብ እንደሆነ አስረድተዋል።
ኢትዮጵያን ጫና ውስጥ በዲፕሎማሲ እና ግራጫ ጦርነት በተባለው ስልት ለመጠቀም ብዙ ጥረት መደረጉን አክለውም ተናግረዋል። ህብረቱ ለዚህም ይረዳው ዘንድ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በተፈጠረው ጦርነት በርካቶች ለሕወሓት በመወገን መንግስትን ሲወቅስና ሲተች ነበር። ይሁንና ይህን ለማድረግ የዳዱት እውነታውን ስለሚያውቁት ሳይሆን ለዘመናት ሀገሪቱን ብሄራዊ ጥቅም ለግለሰቦች ብሎ አሳልፎ የሰጠውን ሕወሓትን ለመታደግ እና ወደ መንበሩ ለመመለስ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ለ40 ዓመታት በኢትዮጵያ ላይ ተሰርቶ የነበረው ሴራ በመክሸፉ ለዚህ መነሳሳት እንደ ምክንያት ይሆናቸዋል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ዓለም ሁሉ ትኩረቱ ዩክሬን ላይ ሆኖ ሳለ የኢትዮጵያን ጉዳይ ግን በዋናነት መያዙም በቀላሉ መታየት የለበትም የሚሉት አቶ እንዳለ፣ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳይ ሌላኛው የትኩረት መስክ በመሆኑ ነው ይላሉ። በተለይም ደግሞ በቀጣናው የኢትዮጵያ ሚና የላቀ በመሆኑ ትኩረታቸውን አሁንም ድረስ እንዳሳረፉበት ተናግረዋል። ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵውያን ከዚህ ጫና ለመላቀቅ ግን አንዳች ነገር ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ሲሉ ምክራቸውን ለግሰዋል።
በተለይም አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ኢትዮጵያን ለመጉዳትና ጫና ለማሳደር በሚሯሯጡበት ወቅት በሀገር ውስጥ ተባባሪ ሆኖ መገኘት የለባቸውም ይላሉ። ህብረተሰቡም ቢሆን በተለያዩ አካላት የሚሰጡ መረጃዎች በሙሉ ትክክል ናቸው ብሎ ከመቀበል ይልቅ ጉዳዮችን በጥልቀት መመርመር እና ሀገራዊ ጥቅምን ማስቀደም ይጠበቅባቸዋል። በተለይም ደግሞ ኢትዮጵያ ወደ ከፍታ ለመጓዝ በምታደርገው ሂደት ተፃራሪ የሆኑ አካላትን መጠቀሚያ ከመሆንም መጠንቀቅ ይገባል። መንግስትም ወቅታዊ መረጃዎችን በወቅቱ ለዜጎች በመስጠት ሀገሪቱን ከጫና ማላቀቅና ህዝቡን ከጎኑ ማሰለፍ አለበት ባይ ናቸው።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ሐምሌ 12/2014