የዓለም ስልጣኔን በእጅጉ ካፈጠኑና ካረቀቁ ክስተቶች መካከል የሳይንስና ቴክኖሎጂ ግኝቶች ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ። በተለይም በባለተሰጥኦ ወጣቶች ሲደገፍ የማይተካ ሚናን ሲጫወትም ይታያል። እንደውም አሁን አሁን ዓለም እየተዋበች የመጣችውም በዚህ ክስተታዊ ድርጊት እንደሆነም ይታወሳል። ከግብርናውም ሆነ ከሌሎች መሰል ዘርፎች በተለየ ሁኔታ ሳይንስ አገራትን እየቀየራቸውም ነው። ሚናውን አጉልቶ ለሰዎች ተጠቃሚነት የማይተካውን ድርሻ እየተወጣ ነው።
የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና መሰል የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራ ሥራዎች የሰው ልጆችን የእለት ከእለት እንቅስቃሴ በሙሉ መምራት ችለዋልም። ኢትዮጵያም ዓለም ከደረሰበት የእድገት ማማ ላይ ለመድረስ ዘመኑን የዋጀ ተግባር እየከወነች ትገኛለች። አንዱ ደግሞ ይህ ዓለምን ኃያል ያደረጋት ተግባር ሲሆን፤ የሰው ኃይል በአግባቡ መጠቀም ያስቻላትም ነው። በተለይም ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ወጣቶችን ከአንድ ጎራ አሰልፋ እንዲሰሩ ለማስቻል የያዘችው እቅድና ተግባር ደግሞ የፈለገችው ደረጃ ላይ ለማድረስ ምንም የሚያግደው ነገር እንደሌለው ብዙዎች ይስማማሉ።
እራሷን ለማዘመን በዚህ ፈጣን የባቡር ሃዲድ ውስጥ ለማስገባትም ዳዴ የምትልበትን የተስጦኦና ተውህቦ ልማት ኢንስቲትዩትን በቅርቡ ገንብታ አጠናቃለች። በ20 15 ደግሞ ወደ ሥራ የምታስገባው እንደሆነም ተሰምቷል። እያንዳንዱን ዘርፍ በዘመናዊው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ውጤቶች ለመምራትም ይህ ኢንስቲትዩት የጎላ ሚና እንደሚኖረውም ተነግሮለታል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በዋናነት ሁኔታውን የሚከታተለው ሲሆን፤ ያለበትን ሁኔታና የቀጣይ ሥራውን በተመለከተ ጉብኝት በተደረገበት ወቅት ሚኒስትሩ ዶክተር በለጠ ሞላ ለተሳታፊዎቹ የተለያዩ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል። እርሳቸው እንዳሉትም፤ ኢትዮጵያ አቅም ያላቸው፣ ሀሳብ ያላቸው፣ ተስፋ ያላቸው ብዙ ወጣቶች ያላት አገር ነች። ይሁንና ምርጦቿን የሚመጥን ተቋምና አሰራር ባለመኖሩ ወጣቶች መስራት ያለባቸውን ሳይከውኑ መክነዋል፣ ደክመዋል፤ ባክነዋልም። አሁንም እየወደቁ እየተነሱና እየጀመሩ ሳይጨርሱ የሚቀሩ ጥቂቶች አይደሉም። ስለሆነም ተፈልገው ሊታገዙ ይገባቸዋል።
ልዩ ተሰጥኦና ተውህቦዎች ስንል እንደከበረ ማዕድን ፈልገን አውጥተንና አበልጽገን ልንጠቀምበት የሚገባ የሰው ልጅ እምቅ አቅም ማለታችን ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ባለ ልዩ ተሰጥኦዎችና ባለተውህብዎች ደግሞ ካልወጡ ልንጠቀምባቸው አንችልም። እናም እነርሱን ለመጥቀምም ሆነ ለመጠቀም በተቻለ መጠን አቅም ፈጠራና ችሎታ የሚገለጥበትን፤ ምናባቸው የማይገደብበትን ምቹ ሁኔታ ሲፈጠር ነው። ለዚህ ደግሞ ምርጦችን ወደ አንድ ማዕከል ማሰባሰብ የውዴታ ግዴታ እንደሚሆንም አንስተዋል።
በሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም ኢኖቬዥን የላቀ ደረጃ የደረሱ አገራት ስኬት ምስጢር የላቀ ሀሳብና ዝንባሌ ያላቸውን ዜጎች ማስተናገድ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ አስቀምጠው መጠቀም መቻላቸው ነው። እናም ኢትዮጵያም ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ ባለ ተሰጥኦ ወጣቶችን በአንድ ኢንስቲትዩት ውስጥ የመሰብሰቧ ሥራ ይህንን እውን ለማድረግ ነው። ምክንያቱም ይህ ኢንስቲትዩት ወጣቶቹ ተሰጥኦዋቸውን እንዲገልጡ የሚያደርግ ማጎንቆያና ማሳደጊያ ነው ይላሉ።
ይህ ተቋም ለኢትዮጵያ የመጪው ዘመን ባለምናቦች፣ ባለ ራዕዮችና የፈጠራ አቅሞች በቂ ባይሆንም እንደመነሻ ሆኖ ግን ያገለግላል። ለክልሎችም ባላቸው አቅምና ሀሳብ እንዲሰሩ ማስተማሪያ ነው። በተጨማሪም ሀሳብ ይዘው ፣ የሚገለጥ ህልም ኖሯቸው፣ የፈጠራና ዝንባሌ ባለቤት ሆነው በአካባቢ ሁኔታ፤ በማህበረሰብ እይታና በኢኮኖሚ ገደብ እየተሰናከሉ ያሉትንም የሚያወጣና ኢትዮጵያ እንድታሳድጋቸው የሚያደርግ እንዲሁም ህልማቸው ላይ የሚያደርሳቸው እንደሆነም ያስረዳሉ።
ባለ ልዩ ተሰጥኦና ተውህብኦ ኢንስቲትዩትም የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ማዕከል ኢትዮጵያ የባለ ተሰጥኦ ልጆች አገር እንደሆነች ለአለም የምንገልጥበትም ነው። የቅንጦት ሳይሆን የውዴታ ግዴታ ጉዳይ ተደርጎ የተወሰደውም ለዚህ እንደሆነ የሚያነሱት ሚኒስትሩ፤ አገርን ወደፊት ለማሻገር ዓለምን የሚቀይሩ ግለሰቦችን ማሳደግ ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ እንደ አገር አንድ እርምጃ መጓዛችንንም ያብራራሉ።
ይህ ግንባታ የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት ቀድሞ ሊታሰብ የሚገባው ድርጊት ነበር። ሆኖም እስካሁን አልሆነም። አሁንም አረፈደምና በ2015 ዓ.ም ባለተሰጥኦዎችን የማሳደግ፣ የማስተማርና የመደገፍ ኃላፊነት የተሰጠው ባለ ልዩ ተሰጥኦና ተውህብኦ ኢንስቲትዩት ሥራ ይጀምራል። ይህ ሆነ ማለት ደግሞ ትምህርታችውን በአግባቡ የሚከታተሉና ለፍላጎታቸው መሳካት የሚጣጣሩ በርካታ ዜጎች ይፈጠራሉ። አገራዊ እድገትን በዘመኑ ልክ እያራመዱ የሚሄዱ ትውልዶችም ይበራከታሉ። በዚህ ውስጥ ደግሞ ባለተሰጥኦዎች የፈጠራ ሥራዎቻቸው እንዳይባክኑም ያስችላቸዋል። በዚያ ሆነው እንዲመራመሩም እድል ይሰጣቸዋል። በተጨማሪም ሥራቸው መሬት እንዲወርድና ለአገር ጥቅም እንዲውልም ያደርገዋል ይላሉም።
እንደ ዶክተር በለጠ ገለጻ፤ያለፈው ትውልድ ረብ በሌለው የፖለቲካ ትርክት በርካታ ጊዜያትን አባክኗል። ይህ ትውልድ ግን ከዚያ የተለየ መሆን ያስፈልገዋል። ኢትዮጵያ የምትለወጠው በፖለቲካ ሳይሆን በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሥራ መሆኑን መረዳት አለበት። ለዚህ ደግሞ የዘርፉ ተዋንያን ብዙ መሥራት ይጠበቅባቸዋል። የጉብኝቱም ዓላማ ይህንን አጽኖት ለመስጠትና መሰል ተቋማት በየክልሎች እንዲገነቡ፣ የፈጠራ ሀሳብ ያላቸውን ተለይተው እንዲያቀርቡ ለማድረግ የተዘጋጀ ነው። በተመሳሳይ አመራሮች ዝግጁነቱን አይተው እንደየክልላቸው ባህሪ ሀሳቡን በመውሰድ ትውልዱን ለዚህ ዓላማ የማነሳሳት ሥራ እንዲሰሩ ለማስቻል ነው።
ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር ናት ያሉት ዶክተር በለጠ፤ ሁሉንም ባለተሰጥኦ በዚህ ብቸኛ ተቋም ማስተናገድ አይቻልም። ስለዚህም በቀጣይ ተመሳሳይ 30 ወይም 40 ተቋማትን በመላ ኢትዮጵያ ማቋቋም ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ቁርጠኛ መሆን ተገቢ ነው። እስከዚያው ግን ይህ ልዩና ፈር ቀዳጅ ሆኖ ያገለግላል ማለታቸውንም የተቋሙ ድረገጽ አመላክቷል።
ኢንስቲትዩቱን መጠናቀቁና ያለበትን ሁኔታ እንዲሁም የተማሪዎቹ ማረፊያ ምን እንደሚመስል የየክልል ቢሮ ኃላፊዎች መጥተው መጎብኘታቸውን ያነሱት ሚኒስትሩ፤ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና የክልል የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ቢሮ ኃላፊዎች ትልቁን ኃላፊነት የሚወስዱ ቢሆንም የትምህርት ዘርፉ ላይ የሚሰሩ አካላትም ትልቅ ድርሻ አላቸው። ስለሆነም ሁሉም ተረባርበው የተያዘውን እቅድ ከግብ ማድረስ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል። የፈጠራ ሀሳብና ሥራ ኖሯቸው ወዴት መሄድና ማንን ማገኘት እንዳለባቸው የማያውቁትን የመለየት የማሳወቅ እንዲሁም የማበረታታት ሥራም የዘርፉ አመራር ተቀዳሚ ተግባር መሆኑን አስገንዝበዋል።
ማዕከሉን በቦታው ተገኝተው እንዳዩትና ፋይዳው ቀላል እንደማይሆን የጠቆሙት ደግሞ የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ መገርቱ መሀመድ ናቸው። እርሳቸው እንዳሉት፤ ይህ ኢንስቲትዩት የመማር ማስተማሩን ሥራ በእጅጉ የሚያሳልጥ ከመሆኑም ባሻገር ተማሪዎች ፍላጎታቸውን አውቀው የተሻለውን እንዲያዩ ያስችላቸዋል። ለአገራቸው የሚያበረክቱትን ነገር እንዲያውቁም እድል ይሰጣቸዋል። በተጨማሪም የማያውቁትን ግን የሚፈልጉትን ልምድ ከሌሎች ተማሪዎች እንዲቀስሙም ያደርጋቸዋል።
አሁን ያለውን ዓለም ለመወዳደርና የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ልዩ ተሰጦ ያላቸው ወጣቶች ከምንም በላይ አስፈላጊ ናቸው። ይሁንና እነርሱን ለይቶ የማብቃት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ግን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። በመሆኑም የዚህ ኢኒስቲትዩት ሥራ መጀመር ይህንን ችግር በብዙ መልኩ ይፈታል የሚል ግምት እንዳላቸው የሚያስረዱት ምክትል ቢሮ ኃላፊዋ፤ ተበታትነው ከሚሰሩት ሥራ በህብረት የሚከውኑት ተግባር በብዙ መልኩ የተሻሉ ያደርጋቸዋልና ይህ እድል መምጣቱ ይበል ያስብላልም ብለዋል።
ሥራውን ወደማህበረሰቡ ለማውረድና ወደተግባር ለመቀየር በአንድ መሰባሰቡ እንደሚበጅ የሚያነሱት ወይዘሩ መገርቱ፤ ተግባሩ ከወጪም ጭምር የሚታደግ ነው። በተጨማሪም የክልል ትምህርት ቤቶች በእስከዛሬ ጉዞዋቸው ያደረጓቸውን ልዩ እገዛም የሚያጎላ ነው። ምክንያም ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ተማሪዎች በመለየት የተለያየ ማበረታቻ አድርጓል፤ ልዩ ተሰጥኦዋቸውን እንዲያወጡም በክበባት አደራጅቶ እንዲሳተፉና ከሌሎች ክልሎች ጋር እንዲወዳደሩ እድል ሰጥቷቸዋል። ይህ ደግሞ የራሳቸውን የገቢ ምንጭ ጭምር እንዲፈጥሩ አስችሏቸዋል።
በየትምህር ቤቱ እስከዛሬ ሲደረግላቸው የቆየው ተግባር ከሽልማት ያለፈ አይደለም የሚሉት ቢሮ ኃላፊዋ፤ የፈጠራ ሥራቸው ለራሳቸው እንዲሁም ለአገራቸው ጥቅም እንዲውል ከተፈለገ እንዲህ አይነት እድሎች መስፋት ይኖርባቸዋል። ይህ ማዕከል ብቻም ችግሩን ሙሉ ለሙሉ የሚፈታ ነው ሊባል ኤችልምም። ሆኖም አንድ እርምጃ ያስኬዳልና ተግባሩን ማድነቅ ከሁሉም ይጠበቃል። በተለይም በትምህርቱ ዘርፍ ላይ ካሉ ሰራተኞች አንጻር ድጋፍ ጭምር ሊታከልበት የሚገባ እንደሆነ ያብራራሉ።
እንደነዚህ አይነት ተግባራትና ኢንስቲትዩቶች በአገር ላይ መስፋታቸው አገርን ከማስጠራትም በላይ ናቸው። ምክንያቱም የፈጠራ ባለሙያዎቹ የተማሩትን ትምህርት ተመርኩዘው አዳዲስ አገር በቀል ውጤቶችን በሁሉም መስክ እንዲያቀርቡ ያደርጋቸዋል። በራስ አቅም ምርቶች ተመረቱ ማለት ደግሞ ከእስቲኪኒ ጀምሮ ከውጪ አገር የምታስገባው አገራችን የራሷን ምርት በራሷ መጠቀም እንድትችል ያደርጋታል። በራስ አቅም መሥራትን ያስተምራል፤ ያስጀምራልም፤ ሰርቶም በአገር ውስጥ ምርት መጠቀምን ያለማምዳል ብለዋልም።
በዶላር እጥረት የምትሰቃየውን ኢትዮጵያን እፎይታን በሁለት መልኩ ያቀዳጃታል። የመጀመሪያው ወጪን መቀነሷ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ገባያውን በማስፋት ለውጪ ጭምር የመላክ አጋጣሚን ያመቻቻልና በአቅራቢነቷ ዶላርን መሰብሰቧ ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ የአገር ምርት በቀላሉ ስለሚገኝ ድሃው ማህበረሰብ በተመጣኝ ዋጋ እንዲስተናገድ እድል ይሰጠዋልም። በተመሳሳይ የተማረው ኃይል በራሱ የሥራ እድል እንዲፈጥርና ሥራ አጣሁ ብሎ እንዳይቀመጥ ያደርገዋልም ይላሉ።
ይህ እድል ለተማሪው ብቻ ሳይሆን ለመምህሩና ለማህበረሰቡ ታላቅ አበርክቶ ያለው እንደሆነ የሚያነሱት ወይዘሮ መገርቱ፤ ለዚህም ማሳያው በየትምህርት ቤቱ በሚደረግላቸው እገዛ ብቻ ሻማን የመሳሰሉ የፈጠራ ሥራዎችን እየከወኑ ገቢ የሚያገኙ ፤ የራሳቸውን ደብተር በራሳቸው የሚገዙ ተማሪዎች መኖራቸው ነው። ይህ ልምድ እያደገና ተሰጥኦዋቸው ተደግፎ በአንድ ማዕከል ተሰብስቦ ሲሰራበት ደግሞ አገር ለያዘችው የእድገት ጉዞ ሁነኛ መፍትሄ እንደሚሰጥ እሙን ነውም ብለዋል።
የወይዘሮ መገርቱን ሀሳብ የሚደግፉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የትምህርት ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አበበ ቸርነት በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የኢንስቲትዩቱ መገንባት ለትምህርት ዘርፉ እድገት ብቻ ሳይሆን ለተማሪዎችም ጭምር መልካም እድሎችን ይዞ የመጣ ነው። ተማሪዎች በብቃትና በጥራት እንዲማሩ የሚያግዛቸውን አማራጭ የሚያገኙበት ነው። በተለይ ፍላጎታቸውን ለይተው እንዲሰሩ በብዙ መንገድ ያግዛቸዋል። በትምህርት ቤት ውስጥ አልሟላ ያሏቸውን ነገሮች በቀላሉ አግኝተው ውጤታማ እንዲሆኑም ይረዳቸዋል። ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ተማሪዎች የተሻለ ማንነት እንዲኖራቸው የሚገነባም ነው። ተሰጦአቸውንም ለተሻለ ሥራ ለማዋል ትልቅ አስተዋጽኦም ያበረክታል።
ዘመናዊ ቴክኖሎጂ እየተደራጀ ያለውና በከፍተኛ ጥንቃቄ የተገነባው ይህ ተቋም እስከ 1000 ባለተሰጥኦዎችን ተቀብሎ የማስተናገድ አቅም እንዳለው የጠቆመው የተቋሙ መረጃ፤ ተቋሙ 60 በመቶውን የተግባር ተኮር ትምህርትና ልምምድ 40 በመቶውን ደግሞ በጽንሰ ሐሳብ ትምህርት የሚሰጥበት ነውም ተብሏል። በ31 የመማሪያ ክፍሎች ሁለት ባለ ከፍተኛ ደረጃ መማሪያ አዳራሾች፤ የሴቶችና የወንዶች መኖሪያ ክፍሎች፤ ዘመናዊ ቤተ-መጻህፍት፣ የሮቦቲክስ እና ኤሌክትሮኒክስ ቤተሙከራዎች፣ የእንጨትና የብረታብረት ወርክሾፖች እና ሌሎች አስፈላጊ አስተዳደራዊ ክፍሎች የተሟሉለት መሆኑም ተነግሯል።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 11/2014