አንዳንዴ በሕይወት ዑደት ከፍ ማለት እንዳለ ሁሉ ቆይቶ ዝቅ የማለት እውነታ ሊያገጥም ይችላል። እንዲህ መሆኑ ለሌላው አንዳች ባይመስልም ለባለቤቱ ግን በእጅጉ የሚከብድ ዱብ ዕዳ ነው። ወዲህ መለስ እንበልና ከከባዱ የሕይወት ምዕራፍ አንደኛውን ገጽ እንግለጥ።
ለሦስት አሥርት ዓመታት የአእምሮ ህመምተኛን ሲንከባከቡ መቆየት ዱብ ዕዳውን ከማባስ አልፎ ኑሮን የገሀነም ያህል ያከብዳል ብንል እያጋነነን አይሆንም። ወቅቶች በቀውስ ውስጥ ሲገቡና ስርዓተ አልበኝነት ጉልበት በሌላቸውና የቀውሱ አካል ባልሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ላይ ሲሰለጠን ደግሞ ማንነት በጭንቀት መወጠሩ አይቀሬ ይሆናል። የዚህ አይነቱ ችግር ሰለባ ከሆኑም በተስፋ መቁረጥ የሚይዙ የሚጨብጡትን ቢያጡ ፍጹም አይፈረድም።
እንዲህ ዓይነቱ ዕጣ ፈንታ ግን በወይዘሮ ጀሚላ አሽረቃና ቤተሰባቸው ላይ ደርሷል።
ወይዘሮዋ የተወለዱት ገጠር ቢሆንም ኑሯቸውን መሳለሚያ አካባቢ በሚገኘው በእህል በረንዳ ወረዳ አራት ቀበሌ 26 ያደረጉት ገና በታዳጊነታቸው ነው። ኑሯቸውን በዚህ አካባቢ ለማድረግ ምክንያታቸው ደግሞ ትዳር መመስረታቸው ነበር። ገና ደረታቸው ላይ በወጉ ጡት ሳይኖር አንዲት ፍሬ ልጅ ሆነው ነው አቶ ሁሴን መሐመድን አግብተው ትዳር የመሰረቱት።
ባለቤታቸው አቶ ሁሴን የያኔዋን አንዲት ፍሬ ጀሚላ አሽረቃን ከማግባታቸው በፊት ጥሩ አባወራ ልሆንላት ያስችለኛል ያሉትን ሁሉ አሟልተው ነበር። ያኔ የቆሻሻ መከማቻ የነበረውንና አሁን ላይ በባለቤታቸው ላይ በመፍረሱ በአካባቢው በጎ አድራጊዎች እንደ አዲስ በብሎኬት እየተሰራ ያለውን ቤት አሳምረው ገንብተዋል። በውብና ማራኪ ዕቃዎችም ሲያሟሉት ቆይተዋል።
ትዳሬን ለማጠንከር አቅም ይሆነኛል ያሉትን ገቢ ማስገኛ ንግድም ከፍተው ነበር። ጎጇቸው ከቆመ በኋላ እንዳይናጋ በመስጋትም ንግድ ሥራቸው ሁለት ሦስት እንዲሆን አስችለዋል። አንዱ አሁን ባለቤታቸው እየኖሩበት ካለው መኖሪያ ቤት ጋር የተያያዘው ዳቦ ቤት ነበር። ዳቦ ቤቱ ገበያው የደራ ገቢውም ዳጎስ ያለ እንደሆነ የያኔዎቹ የባለቤታቸው የአቶ ሁሴን መሐመድ ጎረቤቶችና የአካባቢው ነዋሪዎች ዛሬ ድረስ ሲመሰክሩለት ይደመጣል።
በደረታቸው ጡት እንኳን ያልነበረው የያኔዋ ታዳጊ ልጃገረድ የዛሬዋ እናት ወይዘሮ ጀሚላ አቶ ሁሴን መሐመድን ማግባታቸው በእዚህ ሁሉ ሲሳዮች ተከበዋል። ዛሬ ከአርባ ዓመታት በኋላ ወደኋላ ተመልሰው ሁኔታውን ሲያስታውሱት ምቾቱ ያለ ሀሳብ በርካታ ልጆችን በላይ በላዩ እንዲወልዱ አድርጓቸው እንደነበር አይሸሽጉም።
ወይዘሮዋ አምስት ወንድና ሦስት ሴት ልጆቻቸውን ያለአንዳች ሀሳብ ነበር የወለዱት። ዕድሜ ለባለቤታቸው ይሁንና ሌላው ሳይጨመር በዳቦ ቤቱ ገቢ ብቻ ከነልጆቻቸው ድልቅቅ ያለ ሕይወት ይኖሩ እንደነበር አይዘነጉም። ጀሚላ የዛኔ እንደ አቅማቸው ለአካባቢው ሰዎችና ለሥራ አጥ ዘመዶቻቸው የሥራ ዕድል መፍጠር ችለዋል። ልጆቻቸውን በዕውቀት ለማነፅም ትምህርት ቤት አስገብተው አስተምረዋል። ልጆቹም የሚፈልጉት ሁሉ ተሟልቶ ደስተኛ ሆነው ነው አድገዋል። ባልና ሚስቱም ቢሆኑ በወቅቱ ችግር ምን እንደሆነ አያውቁትም ነበር።
ሕይወታቸው ግን እንዲህ ተደላድሎ አልዘለቀም። ባልና ሚስቱ ለቅርብ ዘመድ ለቅሶ አገር ቤት ቆይተው ሲመለሱ ያልታሰበ ድንገተኛ ችግር ገጠማቸው። ወቅቱ ወታደራዊው የደርግ መንግስት ስልጣን ላይ የነበረበት ነው። በጊዜው አንድ የቀበሌ አብዮት ጠባቂ በራሱ ይሁንታ ያሻውን የማድረግና ሀይል እንዲኖረው ስልጣን ተሰጥቶታል።
አብዮት ጠባቂው ይህን ስልጣኑን ተጠቅሞ በነዋሪው ላይ ግፍና በደል መፈጸሙ የተለመደ ነበር። መደብደብ፣ ማሰር ወጣቶችን በግዳጅ ውትደርና መላክና ሌሎችም የክፋት ተግባራት መገለጫዎቹ ናቸው። አንዳንዴ ደግሞ የቀበሌ ቤቶችን በጉልበት ሰብሮ በመግባት ያሻውን ለማድረግ ከልካይ አልነበረውም።
እነ ወይዘሮ ጀሚላን ከአገር ቤት መልስ ወደመኖሪያቸው ሲገቡ ቤታቸው በአንድ አብዮት ጠባቂ ተሰብሮ ያገኙታል። ሁኔታው ቢያስደነግጣቸው ፈራ ተባ እያሉ ለማጣራት ተጠጉ። ሰውዬው ከነሙሉ ንብረታቸው በቤታቸው መኖር ጀምሯል። ባልና ሚስቱ ማመን አቃታቸው። በጉልበተኛው ባለጊዜ ቤት ንብረታቸው ተነጥቆ ሜዳ መውደቃቸውን አወቁ፡
ከነልጆቻቸው መግቢያ ያጡት ጥንዶች ጎረቤት ዘንድ ተጠግተው ከረሙ። ቆይተውም በህግ ሞግተው አሸነፉት። ሰውዬው በዋዛ አልተዋቸውም ፤ ፍርዱን አስቀልብሶ ዳግም ከችሎት አቆማቸው። በመጨረሻ ከሰውዬው ሲሟገቱ የቆዩት ቤተሰቦች በፍትህ የፍርድ ሚዛኗን አገኙ። ቤታቸውን ከጉልበተኛው የአብዮት ጠባቂ አስመለሱ።
በወቅቱ በባልና ሚስቱ የደረሰው በደልና እንግልት ቀላል አልነበረም። ጥንዶቹ በውጣውረድ ጤና አጥተዋል። በብስጭት ተክዘዋል፣ በችግር ደጅ ጠንተዋል። በተለይ አባወራው ሁሴን ከችግሩ በኋላ በጭንቀት ያገጠማቸው ህመም ቀላል አልሆነም። በየደቂቃው ‹‹ራሴን ›› ማለት ያዝወትራሉ። ውሎ አድሮ የሁሴን ችግር የአእምሮ ህመም መሆኑ ታወቀ። ይሄኔ በድንገት የመላው ቤተሰብ ሕይወት ተናጋ ። የወጣችው ጀንበርም መልሳ ጠለቀች።
አቶ ሁሴን መሐመድን የማስታመሙ ሙሉ ሀላፊነት በወይዘሮዋ ጫንቃ ላይ ወደቀ። ለእሳቸው የአእምሮ ህመም ያለባቸውን አባወራ ማስታመም በእጅጉ ከባድ ነበር። አብሮ መሯሯጡ፣ ወዲያ ወዲህ ማለቱ ለእሳቸው ፈታኝ ሆነ። በየዕለቱ በድካም ቁም ስቅላቸውን አዩ። ሙሉ ጊዚያቸውን ባለቤታቸውን ለማስታመም አዋሉት። የግል ጉዳይና ማህበራዊ ሕይወት ይሏቸው ጉዳዮች ለሦስት አስርት ዓመታት ታሪክ እስኪመስሉ ራሳቸውን ሰጡ።
የችግሩ መስፋት ሌሎች ችግሮችን ማስከተሉ አልቀረም። በመኖሪያ ቤታቸው ግቢ የነበረውን ዳቦ ቤት ጨምሮ በየቦታው ያስፋፉት የንግድ ሥራ በልጆች እጅ መግባቱ ገበያውን አቀዛቀዘው። ውሎ አድሮም ሁሉም የገቢ ማስገኛ ንግድ ቤቶችና ሌሎች መተዳደሪያዎች ሥራ አቆሙ። በግቢያቸው የሚገኘው ዳቦ ቤትም ሙሉ ለሙሉ ስራ አቁሞ ተዘጋ።
‹‹እኔ ባለቤቴን ሳስታምም ልጆቼም ትምህርታቸውን አቆሙ። የዕለት ጉርስ እስከ ማጣት በመድረሳችንም በየፊናቸው እየተሯሯጡ ሊደግፉኝ ሞከሩ። እኔም ባለቤቴን ከማስታመም ጎን መኖሪያ ቤቴ ደጃፍ ላይ ሽንኩርትና ድንች እንዲሁም ዕጣንና ሌሎች ጭሳጭሶችን በመሸጥ ኑሯችንን መደጎም ጀመርኩ›› ይላሉ። እናት ጀሚላ።
ወይዘሮዋ በወቅቱ ችግር ያስጀመራቸው ሥራ ባለቤታቸውን ከማስታመም ጋር የሚስማማ አልነበረም። ሥራውን ባለቤታቸውን ከማስታመሙ ጋር ለማዛመድ ብዙ ታግለዋል። በከፈሉት መስዋዕትነት እጅግ ተጎሳቁለዋል። የልጆቻቸው አይዞሽ ባይነት ግን ብርታት ሆኖ ዛሬን በጽናት አቁሟቸዋል።
ወይዘሮዋ እንዳወጉን በተለይ ትልቋ ልጃቸው በደጃፋቸው ለሚሸጡት ጉልት የሚሆን ሽንኩርት እና ድንች በጀርባዋ እየተሸከመች በማምጣት ትልቅ እገዛ አድርጋቸዋለች። በየሰው ቤት ልብስ በማጠብና የተለያዩ ሥራዎችን በመሥራትም ኑሯቸውን እንዲደጉሙ ስታግዛቸው ቆይታለች። እሷ እስከ ስድስተኛ ክፍል እንኳን የደረሰችው ቀን በየሰው ቤት እየሰራችና ለእናቷ ድንችና ሽንኩርት በጀርባዋ እየተሸከመች ማታ በመማር ነው።
እያደር የወይዘሮ ጀሚላ ባለቤት እየተሻላቸው ነበር። ይሁን እንጂ የአዲስ አበባ ከተማ ምድር ቀውጢ በሆነችበት በምርጫ 1997 የወንዱ ልጃቸው እንደወጣ መቅረትን ሰምተው ክፉኛ መደንገጣቸው ሌላ ችግር መዘዘ። ድንጋጤው የአእምሮ በሽታቸውን ይበልጥ አባባሰው።
ወይዘሮ ጀሚላም ባለቤታቸውን ማስታመሙ ከልጃቸው ሀዘን ተደርቦ ጭንቀት ውስጥ ገቡ። ችግሮቹም እያደር አቅም አሳጣቸው። ዛሬም ይህ ውስጣዊ ድካምና ሀዘን አብሯቸው ዘልቋል ‹‹ልጄ እስከ አሁን እምጥ ይግባ ስምጥ አላውቅም። በረብሻው ጊዜ እንደወጣ ነው የቀረው›› የሚሉት ወይዘሮ ጀሚላ በዚሁ ሰበብ ባለቤታቸው የአእምሮ ህመማቸው ተባብሶ ለሞት መብቃታቸውን ያስታውሳሉ።
ጀሚላ የዛኔ ችግሩ ሲጠና በቤቱ የሚበላ እስከማጣት መድረሳቸውን በትዝታ ያወሳሉ። እንዳይሰሩ ወገባቸው በሽተኛ በመሆኑ በእጅጉ መቸገራቸውንም አይዘነጉትም። ሆኖም ‹‹ህልም ተፈርቶ ሳይተኛ አይታደርም›› እንዲሉት ተረት ‹‹በሽተኛ ነኝ›› ሲሉ ዝም አላሉም። ጉሊት መቸርቸርን ጨምሮ ያገኙትን ሲሰሩ ኖረዋል፤ በሥራና በትምህርት ገፍተው ራሳቸውን መቻልና እናታቸውን የመጦር ዕድል ያላገኙ ልጆቻቸውም የቻሉትን እየሰሩ ሕይወታቸውን አሰንብተዋል።
እናት ጀሚላ አለባበሳቸው ፀዓዳ ፤ ሰውነታቸው ድንቡሽ ቡሽ ነው። ይህን ላስተዋለ ምንም ችግር ያያቸው አይመስሉም። በተለይ በዘመነ ኮሮና በቤታቸው የሚላስ የሚቀመስ በመጥፋቱ በእጅጉ ሲቸገሩ ከርመዋል ። እንደ እሳቸው ላሉ ችግርተኞች ድጋፍ የሚያደርጉ ደጋግመው በአካባቢያቸው ቢመጡም ሊጎበኙዋቸው አልፈቀዱም። ውስጣቸውን ሳያዩ አለባበሳቸውን ብቻ አይተው ያለ አንዳች ድጋፍ በምዝገባ ብቻ አልፈዋቸዋል። ጀሚላ ይህንንም አይረሱትም።
ወይዘሮ ጀሚላ በ1997 ዓ.ም ከጠፋው የበኩር ልጃቸው በቀር ሁሉም ልጆቻቸው ከእሳቸው ጋር እየኖሩ ነው። ዛሬም ያልተለወጠው ሕይወታቸውና ከእጅ ወደ አፍ የሆነው ኑሯቸው ግን አሁንም እየፈተናቸው ይገኛል።
ያኔ አብዮት ጠባቂው ሰብሮ የገባው ቤት ጉዳይም በየወቅቱ እየተነሳ ሰላም ሲያሳጣቸው መኖሩንም ያስታውሳሉ። አብዮት ጠባቂው ቤቱን ሰብሮ ሲገባ ኪራይ ቀመስ አድርጎና የግል ቤት የሚል ፋይል ስላጠፋባቸው በዚሁ ጉዳይ እግራቸው እስኪቀጥን ቀበሌ ሲመላለሱ ኖረዋል።
ልጆቻቸው አባታቸውን በሽተኛ አድርጎ ለሞት ያበቃው ችግር የቤቱ ጉዳይ መሆኑን ያውቃሉ። ይህ መዘዝ ለእናታቸው ሰላም ማጣት ሰበብ ሆኖም እንዲጎዳቸው አይሹም። በዚህ ሳቢያም ስለሰላማቸው መኖር ቤቱ በቀበሌ ይዞታ እንዲቀጥል ፈቅደዋል። ያም ሆኖ በወቅቱ ሰውዬው በየወሩ ያስተመነው የ10 ብር ኪራይ ተጠራቅሞ ውዝፍ ባለ ዕዳ አድርጓቸው ቆይቷል።
‹በየጊዜው ጉዳዩ ሲነሳ ለመከራከር የገንዘብም ሆነ የዕውቀትና የጊዜ አቅም ስለሌለን የግላችንን ቤት ወድደንና ፈቅደን የቀበሌ አድርገነዋል› የሚል ማመልከቻ ማስገባታቸውንም አውግተውናል። ሆኖም ይሄው ቤት ከጊዜ ብዛት በማርጀቱ በየክረምቱ ሲያፈስ መቆየቱንም አልሸሸጉንም። እጃቸውንና መዘፍዘፊያ ደቅነው ቆመው የሚያድሩበት ጊዜም የበረከተ ነበር። በቅርቡ ደግሞ በእርጅና እና በዝናብ ምክንያት መፍረሱን ገልጸውልናል።
እኛ ወደ ወይዘሮዋ ቤት በሄድንበት ጊዜ በበጎ ፈቃደኛ ሰዎች ትብብር ቤቱ ፈርሶ በብሎኬት ሲሰራላቸው ነበር። እሳቸውም ደጃፉ ላይ ኑሯቸውን ለመደጎም እያገለበጡ ያኖሩትን የጉሊት ሥራ አቁመው ቤታቸውን ማሰራቱን ይዘዋል። ዛሬ አሮጌው ቤታቸው በአዲሰ መተካቱ አስደስቷቸዋል። ያልሞላው ኑሯቸው ግን ከነጎዶሎ እንደቀጠለ ተጉዟል።
ብርቱዋ ሴት እናት ጀሚላ መልካም ዓይኖች ቢጎበኙዋቸው ይሻሉ። ትናንትን አልፈው ዛሬ ላይ ሲቆሙ በአይቆጠሬ የመከራ መንገዶች እየተሻገሩ ነው። ነገ ግን ለእሳቸው ሁሌም ሌላ ቀን ነው። ማንም ከጎናቸው ቆሞ ጨለማውን ቢገፍ ብሩህ ተስፋ ከጎናቸው ይገኛል።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 9/2014