ለከተሞች ከሚያስፈልጉ መሰረተ ልማቶች መካከል የመንገድ መሰረተ ልማት አንዱ ነው፡፡ የመንገድ መሰረተ ልማቶች ለተሽከርካሪዎችና ለእግረኞች እንቅስቃሴ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ እንደ አዲስ አበባ ላሉት በርካታ ተሽከርካሪዎች ለሚርመሰመሱባቸው ከተሞች ደግሞ የትራፊክ ፍሰትን ለማሳለጥና ሁለንተናዊ እድገትን እውን ለማድረግ ጉልህ ሚና ይኖራቸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም የመንገድ መሰረተ ልማት ሽፋንን ከፍ ለማድረግ እንዲሁም ለማዘመን እየሰራ ይገኛል፡፡ ይህን ተከትሎም የከተማዋ የመንገድ መሰረተ ልማት ሽፋን እያደገ መጥቷል፡፡ እስካሁን የተገነቡ የመንገድ ፕሮጀክቶች ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየታየ ካለው የከተማዋ መስፋፋት እና እየጨመረ ካለው የከተማዋ የህዝብ ቁጥር እንዲሁም የተሽከርካሪ ብዛት ጋር የሚጣጣሙ አይደሉም፡፡
ይህን ችግር ለመፍታትም የከተማውን ትራፊክ ፍሰት ለማሳለጥ እና የመንገድ ሽፋኑን ከፍ ለማድረግ የሚሰሩ ስራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል፡፡ ከተማ አስተዳደሩ የመንገድ ግንባታን ዋናው የርብርብ ማዕከል በማድረግ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ከከተማዋ መሰረተ ልማት ጋር የተጣጣመ የመንገድ መሰረተ ልማት ለመዘርጋት ከአገራዊ ለውጡ በኋላ የበርካታ የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ በመከናወን ላይ ናቸው፡፡ ከለውጡ በኋላ መገንባት ከጀመሩት የመንገድ ፕሮጀክቶች ውስጥ አንዳንዶቹ መጓተት የሚታይባቸው ቢሆንም፣ በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ የተጠናቀቁ ለቀጣይ የመንገድ ፕሮጀክቶች ተሞክሮ የተቀሰመባቸው ግንባታዎችም አሉ፡፡
መልካም አፈጻጸም ከታየባቸው የመንገድ ፕሮጀክቶች መካከል ከፑሽኪን አደባባይ – ጎፋ ማዞሪያ – ጎተራ ማሳለጫ የመንገድ ፕሮጀክት አንዱ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ ከለውጡ በኋላ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከተገነቡት የመንገድ ፕሮጀክቶች ውስጥ በትልቅነቱ ይጠቀሳል፡፡ በፕሮጀክቶች ጥራትም ሆነ ፍጥነት አዲስ ልምድ እየዳበረ መምጣቱን ያመላከተ ሆኗል፡፡
የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቱ በ2012 በጀት ዓመት መስከረም ወር ላይ ከተጀመሩ ፕሮጀክቶች አንዱ ሲሆን፣ በአጠቃላይ 3 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር ርዝመትና ከ30 እስከ 45 ሜትር የጎን ስፋት ያለው ነው፡፡
የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ምክትል ኃላፊ አቶ ኢያሱ ሰለሞን በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፤ ይህ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ነው ግንባታው እየተከናወነ ያለው፡፡ የመንገድ ግንባታው በቻይና ፈርስት ሀይ ዌይ ኢንጂነሪንግ በተባለ ተቋራጭ ድርጅት እየተከናወነ ሲሆን፤ የማማከር ስራውን ደግሞ ቤስት አማካሪ ድርጅት እያከናወነ ይገኛል፡፡
ቀደም ሲል ከፍተኛ የትራፊክ ጫና የነበረበትን የሳር ቤት – ጎተራ እና የጨርቆስ – ጎፋ ማዞሪያ መስመር ከፍተኛ መጠን ያለው የትራፊክ ፍሰት ለማሳለጥ ከፍተኛ ሚና አለው፡፡ በተለይ ከጎተራ ማሳለጫ ወደ አሌክሳንደር ፑሽኪን አደባባይ እና ከዚያ ጋር ከሚጋጠሙ ሌሎች መንገዶች ጋር የመንገድ ኔት ወርኩን ማስፋፋት ያስቻለ ትልቅ ፋይዳ ያለው የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ነው ብለዋል፡፡
እንደ አቶ ኢያሱ ማብራሪያ፤ በተለይ ጎፋ ማዞሪያ ተብሎ የሚጠራው እና በተለምዶ ቄራ ተብሎ የሚጠራው አካባቢ በሶስት ደረጃዎች የተከፈለ የትራፊክ ማሳለጫ ግንባታ ተከናውኖለታል፡፡ አንደኛው የውስጥ ለውስጥ የመኪኖች መተላለፊያ ዋሻ ነው፡፡ ይህ ዘመናዊ ዋሻ በከተማዋ የመንገድ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያ የሆነ በሁለቱም አቅጣጫዎች 320 ሜትር ርዝመት ያላቸው የውስጥ ለውስጥ መተላለፊያ ዋሻ ግንባታዎች ተከናውነውለታል፡፡
ይህ ረጅም ዋሻ የአካባቢውን የትራፊክ ፍሰት በማሳለጥ ረገድ ፋይዳው ላቅ ያለ ነው፡፡ ምክንያቱም ተሽከርካሪዎች ውስጥ ለውስጥ እንዲሁም በላይ ማለፍ ይችላሉ፡፡ ይህ አይነት መንገድ በአዲስ አበባ በሌሎች አካባቢዎች እንዲሁም በመላ አገሪቱ ከተሞች አካባቢ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታየ ያለውን የትራፊክ መጨናነቅ ለመቅረፍ ጥቅም ላይ መዋል አለበት፡፡ መሰል ፕሮጀክቶች የአገራችንን ከተሞች ገጽታ ለመቀየር ከፍ ያለ ፋይዳም ይኖራቸዋል፡፡
እንደዚሁም ደግሞ ከዋሻው በላይ በኩል የሚመጡ ተሽከርካሪዎች ምንም ነገር ሳያውካቸው እንዲያልፉ የሚያስችሉ መንገዶች ተገንብተዋል፡፡ ከጎፋ ወደ ለገሃር አቅጣጫ እንዲሁም በተቃራኒው ከጎፋ ማዞሪያ ወደ ለገሀር አቅጣጫ ለሚሄዱ ተሸከርካሪዎች ደግሞ አደባባይ ውስጥ መግባት ሳያስፈልጋቸው የሚያሻግር የማሳለጫ ድልድይን ጨምሮ በቀጣይ ከአካባቢው የመንገድ መረብ ጋር የተሳሰረ የፈጣን የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት እንደሚሰጥበት የሚጠበቀው መንገድ (Bus Rapid Transit) አካቶ የተገነባ መሆኑን ነው ያብራሩት፡፡
እስከ ሳር ቤት የተሻለ መንገድ እንዲሁም እስከ ጎተራ ድረስ ቀደም ብሎም የተሻለ መንገድ መገንባቱን አስታውሰው፣ ቄራ አካባቢ በጣም መጨናነቅ ይታይበት እንደነበር ተናግረዋል፤ ይህንን መጨናነቅ ለመቅረፍ መንገዱን መገንባት ማስፈለጉን አቶ ኢያሱ ይገልጻሉ፤ ፑሽኪን አደባባይ – ጎፋ ማዞሪያ – ጎተራ ማሳለጫ ሲገናኝ እና ቀጥሎ ሜክሲኮ ድረስ ያለውን በማገናኘት ከተማዋን የማስዋብ ስራ የተሳካ እንዲሆን ስለሚያስችል ነው፡፡
የፑሽኪን አደባባይ፣ ጎፋ ማዞሪያ እና ጎተራ ማሳለጫ የመንገድ ፕሮጀክት ብቻውን ቆሞ የመንገድ ፕሮጀክት አይደለም፡፡ ጎተራ ሲሚንቶ ፋብሪካ የነበረበት አካባቢ የሚሰሩ ብዙ ፕሮጀክቶች አሉ፡፡ ከነዚህ ፕሮጀክቶች አንዱ ይገነባል ተብሎ የሚታሰበው ‹‹አዲስ ቱሞሮው›› የተሰኘው ዘመናዊ ከተማ ነው፡፡ ያንን ከተማ፣ ቦሌን፣ ቄራን እና ሳር ቤትን የሚያስተሳስር ፕሮጀክት እንደመሆኑ ፋይዳው ላቅ ያለ ነው፡፡
አቶ ኢያሱ ይህ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት አሁን በመጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡ ከሁለት ሳምንት በፊት ባለስልጣኑ ይፋ እንዳደረገው መረጃም ግንባታው 98 በመቶ ገደማ ተጠናቋል፡፡ የመንገድ ፕሮጀክቱ አሁን ላይ ካልተጠናቀቁ ጥቂት የእግረኛ መንገድ እና ከአንዳንድ የእርማት ስራዎች በስተቀር ሌሎች የግንባታ ስራው ዋና ዋና ተግባራት ተጠናቀው በሁሉም አቅጣጫ ለትራፊክ ክፍት ሆኗል፡፡
የመንገድ ፕሮጀክት ከሌሎች ፕሮጀክቶች አንጻር ሲነጻጸር በፍጥነት የተገነባ ፕሮጀክት ነው ያሉት አቶ ኢያሱ፤ ከፕሮጀክቱ ጋር የተጀመሩ አንዳንድ ፕሮጀክቶች ግንባታ በሚፈለገው ፍጥነት አለመሄዱን ጠቅሰዋል፡፡ ለዚህም እንደ ማሳያ ያነሱት ከአውቶቢስ ተራ በመሳለሚያ ወደ 18 ቁጥር ማዞሪያ የመንገድ ፕሮጀክትን ነው፡፡ ሁለቱም የመንገድ ፕሮጀክቶች በተመሳሳይ ጊዜ የግንባታ ስራቸው የተጀመረ ቢሆንም፣ ከአውቶቢስ ተራ በመሳለሚያ ወደ 18 ቁጥር ማዞሪያ የሚወስድ መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት መጓተት ታይቶበታል ብለዋል፡፡
የፑሽኪን – ጎፋ ማዞሪያ – ጎተራ ማሳለጫ ፕሮጀክት ሲታይ ሰፊ ስትራክቸራል ስራዎች የሚያስፈልጉት ፕሮጀክት ሆኖ እያለ በፍጥነት ወደ መጠናቀቂያ ምዕራፍ ደርሷል። የአውቶቢስ ተራ- መሳለሚያ- 18 ማዞሪያ ፕሮጀክት ግን ከወሰን ማስከበር ጋር የነበሩ ችግሮች እና በጣም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ በሚኖርበት ቦታ ላይ እየተሰራ ያለ የማስፋፊያ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ መጓተት ታይቶበታል። የወሰን ማስከበር ችግር የአውቶቢስ ተራ- መሳለሚያ – 18 ማዞሪያ ፕሮጀክት ብቻ ችግር ሳይሆን ለሌሎች ፕሮጀክቶችም መጓተት ምክንያት ሆኖ ቆይቷል፡፡
የፑሽኪን- ጎፋ ማዞሪያ- ጎተራ ማሳለጫ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክትም ከወሰን ማስከበር ችግሮች የጸዳ አልነበረም ይላሉ አቶ እያሱ፡፡ ያጋጠሙትን የወሰን ማስከበር ችግሮች በመፍታት ረገድ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ሰፊ ርብርብ ማድረጋቸውን ጠቅሰው፣ ይህም ለግንባታ ስራው በፍጥነት መጠናቀቅ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል ብለዋል፡፡
እንደ አቶ ኢያሱ ማብራሪያ፤ በከተማዋ የሚገነቡ የመንገድ ፕሮጀክቶች በሚፈለገው ፍጥነት እንዳይጠናቀቁ እንቅፋት ከሚሆኑ መካከል የግንባታ ተቋራጮች ልምድ እና አቅም ማነስ አንዱ ነው፡፡ የፑሽኪን አደባባይ፣ ጎፋ ማዞሪያ ጎተራ ማሳለጫ ፕሮጀክት ግንባታ እያከናወነ የሚገኘው ተቋራጭ በተለያዩ የመንገድ ግንባታ ስራዎች ውስጥ ሰፊ ልምድ ያለው የግንባታ ተቋራጭ መሆኑ ፕሮጀክቱ በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ የበኩሉን አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡
ያለ ህዝብ ሁለንተናዊ ተሳትፎ የትኛውንም ፕሮጀክት በፍጥነት በስኬት ማጠናቀቅ የሚታሰብ አይደለም ያሉት አቶ ኢያሱ፤ የፑሽኪን አደባባይ – ጎፋ ማዞሪያ – ጎተራ ማሳለጫ ፕሮጀክት በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዲከናወን ከሁሉም በላይ የግንባታው ባለቤትና ዋነኛው ተጠቃሚ የሆነው የግንባታ ስራው በሚከናወንበት አካባቢ ያለው የከተማው ነዋሪ ለግንባታ ስራው መቀላጠፍ የበኩሉን ድርሻ በማበርከት ለስራው መሳካት ትልቅ ድርሻ ማበርከቱንም ጠቅሰዋል፡፡
በከፍተኛ ወጪ ተገንብቶ ወደ መጠናቀቅ ደረጃ እየተቃረበ የሚገኘው ይህ የመንገድ ፕሮጀክት ከተገነባለት ዓላማ ውጭ ለተሽከርካሪ ማቆሚያ ሥፍራነት እየዋለ መሆኑን ጠቁመው፣ ይህም በትራፊክ ፍሰቱ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እያሳደረ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ በሁሉም የመንገድ አካላት ላይ እንዳይከናወኑ የተከለከሉ እንደ መኪና እጥበትና ጥገና የመሳሰሉ ህገወጥ ተግባራት በመንገድ ወሰኑ ውስጥ እየተፈፀሙ መሆናቸውን አመልክተው፣ ይህም በሂደት መንገዱን ለብልሽት እንደሚያጋልጠው አስገንዝበዋል፡፡
ከፍተኛ መዋለ-ንዋይ ፈሶበት የተገነባው ይህ ዘመናዊ መንገድ ለታለመለት ዓላማ ብቻ ይውል ዘንድ በመንገዱ ላይ ያልተፈቀዱ ተግባራትን የሚያከናውኑ ወገኖች ከህገ ወጥ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከወዲሁ በጥብቅ እንደሚያሳስብ ነው አቶ ኢያሱ የተናገሩት፡፡
የመንገድ ግንባታው ሂደት በመንግስት የቅርብ ክትትል ሲደረግበት የቆየ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አንዲሁም የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ መጎብኘታቸው ይታወሳል፡፡
ከንቲባዋ ባለፈው ሳምንትም ግንባታውን ተዘዋውረው ጎብኝተው በአካባቢው ችግኝም ተክለዋል።
መንገዱ በተያዘለት ጊዜ እና ወጪ የግንባታ እየተጠናቀቀ መሆኑን ገልጸዋል። ፕሮጀክቱ በተያዘለት ወቅት ምንም አይነት የገንዘብና የጊዜ ጭማሪ ሳይጠይቅ በነበረው ጥብቅ የስራ ክትትል በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል።
መንገዱ የከተማዋን የወደፊት ዕድገት ታሳቢ ባደረገ መልኩ የተገነባ ነው ያሉት ከንቲባዋ፣ የአካባቢው ነዋሪዎች የመንገድ ልማት ፕሮጀክት በመንከባከብና ለምግብነትም ሆነ ለጥላ የሚሆኑ ችግኞችን በመትከል ፕሮጀክቶቹን በቅንጅት እንዲያስውቡ ጠይቀዋል።
በቅርቡ የሚመረቀው የመንገድ ፕሮጀክት በአካባቢው ሲስተዋል የነበረውን የትራፊክ መጨናነቅ ከመቅረፍ ባሻገር ፈጣን አውቶብስን ጨምሮ የእግረኛና የብስክሌት መንገዶችን ደረጃውን ጠብቆ የተገነባለት መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ የመንገዶች ኢንጅነር ሞገስ በመርሀ ግብሩ ላይ ተናግረዋል። በአገራችን ደረጃ የመጀመሪያ የመንገድ ግንባታ መሆኑንም ገልፀዋል።
የፑሽኪን አደባባይ – ጎፋ ማዞሪያ – ጎተራ ማሳለጫ ፕሮጀክት በብዙ መልኩ በአዲስ አበባ እና በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች እየተገነቡ ላሉት እና ወደፊት ለሚገነቡት ፕሮጀክቶች ተምሳሌት ሊሆን የሚችል ነው፡፡ የከተማዋን የትራፊክ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በሚያስችል መልኩ ዋሻ ያለው የመንገድ ፕሮጀክት መሆኑ አንዱ እንደ ተምሳሌትነት እንዲጠቀስ ያደርገዋል፡፡ ከዚያ ባሻገር ወሰን ማስከበር ችግሮችን በአጭር ጊዜ በመፍታት ረገድ የታየው መልካም ተሞክሮ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሚገነቡ የመንገድ ፕሮጀክቶች እንዲሁም በመላ አገሪቱ ለሚገነቡ የመንገድ ፕሮጀክቶች እንደተሞክሮ መወሰድ ያለበት ነው፡፡
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 9/2014