ኢትዮጵያ አንድ ክፍለ ዘመን በላይ ታሪካዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ካላቸው የአውሮፓ አገራት መካከል ፈረንሳይ በግንባር ቀደም ትጠቀሳለች። አገራቱ በተለይም ካለፉት 125 ዓመታት ጀምሮ በፖለቲካና በኢኮኖሚ ብሎም በህዝብ ለህዝብ ትስስር ጠንካራ የሚባል ግንኙነት ያላቸው ወዳጅ አገራት ናቸው። በዚህ ግንኙነትም በዋናነት ኢኮኖሚያዊ ትብብር በመፍጠር የጋራ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎችን አከናውነዋል። ለአብነት ያህልም በዳግማዊ ምኒልክ ዘመነ መንግስት የተሰራው የመጀመሪያው የባቡር መስመር ዝርጋት በከፍተኛ ደረጃ የሚጠቀስ ነው። የፈረንሳይ የኪነ-ህንፃ ባለሙያዎች በኢትዮጵያ ከተሞች እድገት ያሳረፉት አሻራም ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ነው።
የለውጡ መንግስት መምጣቱን ተከትሎ ደግሞ የሁለቱ አገራት ሁለንተናዊ ግንኙነት ይበልጥ እየተጠናከረ የመጣ ሲሆን በተለይም ፈረንሳይ በወታደራዊ መስክ ያላትን ልምድና የቴክኖሎጂ ተሞክሮ ለኢትዮጵያ ማካፈል የምትችልበትን እድል የሚፈጥር ስምምነት ፈፅመውም ነበር። በዚህም የስምምነት ማዕቀፍ በዋናነት የኢትዮጵያን ባህር ኃይል ዳግም ለማደራጀት በሚደረገው ጥረት ፈረንሳይ ቃል መግባቷን እናስታውሳለን። በዚህና ለአንድ ዓመት ያህል እየተከበረ ባለው 125ኛ ዓመት ዲፕሎማሲ ግንኙነት ዙሪያ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሆነው እየሰሩ ካሉት አምባሳደር ሬሚ ማሪሾ ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል።
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያና ፈረንሳይ የዲፕሎማሲ ግንኙነት 125ኛ ዓመት እየተከበረ እንደሆነ ይታወቃል። እስቲ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ የተገኙ ዋና ዋና ስኬቶች ምን እንደሆኑ ያብራሩልንና ውይይታችንን እንጀምር ?
አምባሳደር ሬሚ፡- በቅድሚያ በአፍሪካ የፖለቲካ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ ተመድቤ በመስራቴ ያለኝን ታላቅ ደስታ ለመግለፅ እወዳለሁ። ፈረንሳይና ኢትዮጵያ ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር ሲነፃፀር ረጅም እድሜ ያስቆጠረ እና ጠንካራ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ነው ያላት። ኢምባሲያችን በእድሜው ረጅሙ ሲሆን የፈረንሳይ ባህል ማዕከል ተቋቁሞ የሁለቱን አገራት ወዳጅነት የበለጠ እንዲጠናከር ለበርካታ ዓመታት ሲሰራ ቆይቷል። በጣም አስፈላጊው ነገር ደግሞ አገራቱ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሲፈጥሩ ገለልተኛ እና ሉዓላዊ ሆነው መቀጠሉ ነው።
ከዚህ በመነሳት ከኢትዮጵያ ጋር ያለንን የዲፕሎማሲ ግንኙነት የተለየና የህዝብ ለህዝብ ትስስሩም ጠንካራ ነው ማለት ይቻላል። ይህንን በዓል ማክበራችንም የሁለቱንም አገራት የዲፕሎማሲ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እና ለመገንባት ብሎም በጋራ ለምንሰራቸው የልማት ፕሮጀክቶች የጀርባ አጥንት ሆኖ ያገለግላል ብለን እናምናለን። ለዚህም ነው የዚህን ዓመት እያንዳንዱን ወር በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ሰይመን ስናከብር የቆየነው። ለአብነት ያህልም በትምህርትና ቋንቋ ዘርፎች በጋራ በምንሰራባቸው ሊሴ ገብረማርያምና በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም በአገር ፍቅር ቲያትር ቤት የሙዚቃ ኮንሰርት በማዘጋጀት አክብረናል። በቅርቡም በአርቴክቸሩ ዘርፍ የፈረንሳይ ባለሙያዎች በአዲስ አበባ ኪነ-ህንፃ ላይ እንዲሁም ከተማዋን በማዘመን ረገድ ያላቸውን አበርክቶ የሚዳስስ ዘጋቢ ፊልም ታይቷል።
በተጨማሪም በሥነ-ቅርስ ጥበቃ ሥራዎችም አገራችን ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገች እንደሆነ ይታወቃል። ከእነዚህም መካከል በላሊበላ ውቅር አብያተ-ክርስቲያናት እድሳትና በእንጦጦ ፓርክ ግንባታ ላይ ፈረንሳይ ከኢትዮጵያ ጎን በመሆን የልማት አጋርነቷን በማረጋገጥ ላይ ትገኛለች። በቀጣይ ወራትም የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያጎለብቱ መርሃ ግብሮች በዓሉ የሚከበር ነው የሚሆነው። በመስከረም ወር የላሊበላ ስሪ-ዲ ኤግዚዚሽን በእንጦጦ ፓርክ ይከፈታል። ስለዚህ ይህንን የጋራ ስኬት ወደፊት ለጋራ ፕሮጀክት ለመገንባት የሁለትዮሽ ግንኙነቱን አንድ ገጽታ በሚያሳይ መልኩ በየወሩ እያከበርን እንቀጥላለን።
አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ በዓይነቱ ልዩ የሆነ የፈረንሳይ የብቅል ፋብሪካ በአዲስ አበባ መቋቋሙ ይታወሳል። በእናንተ እይታ ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ምን ያህል ተስማሚ ናት?
አምባሳደር ሬሚ፡- ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ምቹ የሆነ የተፈጥሮ ሃብት ያላት አገር ነች። በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ መዋዕለንዋያቸውን ለማፍሰስ የሚመጡ የፈረንሳይ ኩባንያዎች ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ ጨምሯል። ለዚህም ቀደም ብለን ያነሳነው የብቅል አምራች ፋብሪካ ኢንቨስትመንት ጥሩ ማሳያ ነው። ይህንን ፕሮጀክት የሚተገብረው የፈረንሳይ ኩባንያ ከኢትዮጵያ የልማት ስትራቴጂ ጋር መጣጣም መቻል አለበት። የዚህ ብቅል ፋብሪካ ፕሮጀክት በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ከውጭ የሚያስገባውን ለመተካት ያስችላል ተብሎ ትልቅ ቦታ የተሰጠው ነው።
በተመሳሳይ እህት ኩባንያ የሆነው ቦልት ማልት ከተሰኘውና ደብረብርሀን ላይ የተቋቋመው ፋብሪካም አገሪቱ ለብቅል የምታወጣውን የውጭ ምንዛሬ ይቀንሳል ተብሎ ይታመናል። በዚህ ረገድ የመንግስት ስትራቴጂ ግልፅ ነው። ስለዚህ ቢራ ፋብሪካዎች ከውጭ ከማስመጣት ይልቅ በአገር ውስጥ የሚመረተውን ብቅል እንዲገዙ የግብር ማበረታቻም አለ። ስለዚህ ይህ ለኢንቨስትመንት በጣም ተስማሚ ነው ማለት ይቻላል።.
ይሁንና ሊፈቱ የሚገቡ ብዙ ችግሮች አሉ፤ እነዚህ ኩባንያዎች በዋናነት በውጭ ምንዛሬ እጥረትና በተንዛዛ አሰራር ምክንያት በከፍተኛ ደረጃ እየተፈተኑ ነው ያሉት። እንደሚታወቀው ኩባንያዎቹ መለዋወጫ እቃዎችንና ወሳኝ ግብዓቶቹን ለፋብሪካው ከውጭ ማስመጣት አለባቸው። ሆኖም የውጭ ምንዛሬ እጥረት በመኖሩ ስራቸውን በአግባቡ ለመከወን ተቸግረዋል። በእርግጥ ይሄ ችግር የፈረንሳይ ኩባንያዎች ላይ ብቻ ያጋጠመ ሳይሆን እንደአገር የሚታይ ነው። በግሌ እንዲሰመርበት የምፈልገው ነገር ግን ይህ ኢንቨስትመንት ለዚህች አገር እድገት ወሳኝ ሚና ያለው በመሆኑ እነዚህን ችግሮች መፍታት ወሳኝ መሆኑን ነው።
በነገራችን ላይ በቅርቡ ቱሉ ሞዬ ጂኦ-ተርማል 150 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት የሚያስችል ፕሮጀክት ለማቋቋም ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ውል የተፈራረምን ሲሆን ለፕሮጀክቱ ተፈጻሚነት ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር በቅርበት እየሰራን ነው። በመሆኑም 100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ የሚደረግበት ይሄው ኢንቨስትመንት ኢትዮጵያ ከታዳሽ ኃይል የምታገኘውን የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን በእጅጉ ይጨምራል ተብሎ የሚታመንበት ነው። በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ባላት እምቅ ሀብት የፈረንሳይ ኩባንያዎች ተሳትፏቸውን እንዲያጎለብቱ በቀጣይነት እንሰራለን።
አዲስ ዘመን፡- እርሶ እንዳነሱት ምንም እንኳን ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ ችግር ቢኖርባትም የብቅል ፋብሪካው በኢትዮጵያ መገንባት ሌሎች የፈረንሳይ ባለሃብቶችን ለመሳብ አያስችልም ብለው ያምናሉ?
አምባሳደር ሬሚ፡- ትክክለኛ ጥያቄ ነው ያነሳሽው፤ ደግሞ ይህንን ብዙዎቻችንን የምንስማማበት ጉዳይ ነው። ለዚህም ነው ባለሀብቶች እድሉን ፈልገው ሲመጡ ኤምባሲያችን ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር የማገናኘት ሥራ የሚሰራው። ምክንያቱም አቅም ያለው አንድ ኩባንያ ወደ አገር ውስጥ መምጣቱ ለሌሎች በር ከፋች ነው የሚሆነው። እዚህ ጉዳይ አሳማኙም ነገር የሚሆነው ቀድሞ የገባውን ስራ የጀመረው ኩባንያ ተሞክሮ ነው ሌሎችን ለመሳብ የሚያስችለው። ይህ የቀደመው ድርጅት ያሳለፈው ውጣ ውረድና የደረሰበት ስኬት ለሌሎች አርዓያ ለመሆን እድል የሚሰጠው ነው የሚሆነው። አንቺም እንዳልሽው የፈረንሳዩ ብቅል አምራች ኩባንያ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ለሌሎች አለምአቀፍ የፈረንሳይ ኩባንያዎች ትኩረትን የሚስብ ነው የሚሆነው።
አዲስ ዘመን፡- በተያዘው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ለአቅም ግንባታ እና ለቅርስ ጥበቃ 19 ሚሊዮን ዩሮ የሚሆን ስምምነት መፈረሙ ይታወሳል። ይህ ስምምነት መቼ ነው ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው?
አምባሳደር ሬሚ፡- አጠቃላይ ወጪው ለሁለት የተለያዩ ፕሮጀክቶች የሚውል ነው። አንደኛው ለኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ሃይል ማሰልጠኛ ማዕከል ግንባታ የሚውል ነው። ቀሪው ደግሞ የብሔራዊ ቤተመንግስትን ወደ ሙዚየምነት ለመቀየር ለታቀደው ፕሮጀክት የተመደበው ነው። በመሰረቱ እኛ በኢትዮጵያ ሁለት ወሳኝ የቅርስ ጥበቃ ስራ የምናከናውንበት ፕሮጀክቶች አሉን። የመጀመሪያው ላሊበላ ውቅር አብያተ-ክርስቲያናት ጥበቃና እድሳት ስራ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ አስቀድሜ ያነሳሁት የብሔራዊ ቤተመንግስቱ ወደ ሙዚየም የመለወጥ ስራ ነው።
በነገራችን ላይ ይህ የሙዚየም ግንባታ ስራ ትልቅና 14ሺ ካሬ ቦታ የሚሸፍን ነው። የሲቪል ስራው ተጀምሯል፤ የአቅም ግንባታው ስራው ደግሞ የሚቀጥል ነው የሚሆነው። ሙዚየሙን የሚያስተዳድሩ ባለሙያዎችን የማሰልጠኑ ስራ በፈረንሳይ ታዋቂ የሆነው ቨርሳይ ሙዚየም አስተባባሪነት የሚመራ ሲሆን የዚህ ሙዚየም ከፍተኛ ባለሙያዎች ለኢትየጵያውያን ባለሙያዎች የቴክኖሎጂ ሽግግርና ድጋፍ የሚደረጉ ነው የሚሆነው። ይህም የሚደረገው የኢትዮጵያ ታሪክና ቱፊት በጠበቀ መልኩ ነው። የሙዚየም መገንባት ለኢትዮጵውያውያን የታሪክ አሻራ የሚያንፀባርቅ ከመሆኑም ባሻገር ቱሪስትን የሚስብ ነው የሚሆነው። እንዲህ አይነቱ መስህብ በተለይ ቱሪስቶች በከተማዋ ለረጅም ቀናት እንዲቆዩ ያደርጋል ተብሎ ይታመናል። ምክንያቱም የሁለቱም ፕሮጀክቶቻችን ዋነኛ አላማ ቅርሶችን ማሥጠበቅ ብቻ ሳይሆን የቱሪስቱን ቁጥር መጨመርና የስራ እድል መፍጠር ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ ጋር ተያይዞ በየዘርፉ የምታደርጉትን ድጋፍ እንዴት ነው የምትገ መግሙት ?
አምባሳደር ሬሚ፡- በኢትዮጵያ ለምንደግፋቸው እያንዳንዱ ፕሮጀክት ክትትል የሚያደርግ ቋሚ ኮሚቴ አዋቅረናል። ይህንን የክትትል ሥራ የምናከናውነው ግን ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመተባበር ነው። በዚህ ኮሜቴ አማካኝነት በየጊዜው የፕሮጀክቶቹን አተገባበር ሪፖርት ይቀርብና እንገመግማለን። ፕሮጀክቶቹ እስከሚጠናቀቁ ድረስ በዚህ መልኩ የመጡ ለውጦች የሚፈተሹና ችግሮች እንዲታረሙ የሚደረግበት አሰራር አለን።
አዲስ ዘመን፡- የለውጡ መንግስት መምጣቱን ተከትሎ ኢትዮጵያና ፈረንሳይ በጋራ ለመስራት ከተስማሟቸው ሥምምነቶች አንዱ ወታደራዊ ድጋፍ ነበር። ሆኖም በዚህ ማዕቀፍ ያሉ ስምምነቶች በታሰበው ልክ እየተተገበሩ አይደለም። ለመሆኑ ምክንያቱ ምንድን ነው?
አምባሳደር ሬሚ፡– በነገራችን ላይ ስምምነቱ አሁንም እንዳለ ነው፤ ይህም ሰምምነት እንዳልሽው ወታደራዊ ትብብር ላይ የተመሰረተ ሲሆን ለጊዜው እንዲዘገይ ተደርጓል። ግን በተቻለ ፍጥነት እንዲቀጥል ይደረጋል። ይህም የሚሆነው ግን በተለይ በሰሜን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ግጭት ሲቆምና በተሻለ መልኩ ለውጥ ማምጣት ሲችል ነው። ስለዚህ ይህ የወታደራዊ ስምምነት ተግባራዊ እንዳይሆን የተደረገው በቀጥታ ከሰሜኑ ጦርነት ጋር ተያይዞ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተፈፅሟል ተብሎ በመታመኑ ነው። ይህንንም የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽኑ የተገለፀ ሲሆን በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ መንግስት ጠንካራ የሆነ ቁርጠኝነት አሳይቷል። በተለይ ተፈፅመዋል በተባሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በመርመርና ሪፖርቶችን በማጣራት ረገድ ያሳየው ተነሳሽነት የሚደነቅ ነው። እኛም ከፍትህ ሚኒስቴር ጋር ተቀራርበን የምንሰራ በመሆኑ የመጡ ለውጦችን ለማየት ችለናል። ይህ ግን ወደ ፖለቲካዊ ውይይት ማደግ አለበት ብለን እናምናለን። እነዚህ ሁኔታዎች እንደተስተካከሉ ግን በተቻለ ፍጥነትና ሁኔታ በስምምነቱ መሰረት ድጋፎቹ የሚቀጥሉ ነው የሚሆኑት። በተለይም የኢትዮጵያ ባህር ኃይል እንዲጠናከር አገራችን በጋራ የምትሰራ ነው የሚሆነው።
አዲስ ዘመን፡- እርሶም እንዳሉት የኢትዮጵያ መንግስት በአገሪቱ ብሔራዊ መግባባት እንዲመጣ የምክክር ኮሚሽን እስከማዋቀር ድረስ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው የሚገኘው። እርሶ ይህንን የመንግስትን ጥረት እንዴት ይመለከቱታል?
አምባሳደርሬሚ፡- ለእኔ ይህ ትልቅና የሚበረታታ ዜና ነው። የእኔ መንግስትም ይህንን የኢትዮጵያ መንግስት እያደረገ ያለውን ጥረት በይፋ አድንቋል። ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ብዙ መግለጫ ባናወጣም በቀጥታ ግን ከኢትዮጵያ መንግስት የሚመለከታቸው አመራሮች ጋር ውይይት አድርገናል። በወቅቱ በዚህ ጦርነት ኢትዮጵያ የምታተርፈው አንዳች ነገር እንደሌለ አቋማችንን አስታውቀናል። ምክንያቱም ይህ ጦርነት ዋነኛ ተጎጂ የሚያደርጋቸው ንፁሃንን በመሆኑ ነው። ሠላም ለማስፈን ደግሞ ብቸኛው አማራጭ በፖለቲካዊ መረጋጋት መፈጠሩ ነው።
በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ መንግስት ሠላም እንዲሰፍን ሲል የተናጠል ተኩስ አቁም ከማድረግ ጀምሮ እስረኞችን በመፍታት የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የውይይት መድረክ ለመፍጠር የተጀመረው በጣም የሚበረታታ ነው። ሠላምን በአገር ላይ መልሶ ለማምጣት ብቸኛውና አስተማማኝ መንገድ ፖለቲካዊ ምክክር ነው። እኛ ከራሳችን ተሞክሮ በመነሳት በሌሎች አካባቢዎች ያሉ ቀውሶች ልምድ፣ ፖለቲካዊ መፍትሄ ብቻ ዘላቂ ሰላም ሊያመጣ ይችላል ብለን እናምናለን።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ለህዝቦቿ ልማትን ማምጣት ብቻ ሳይሆን ጎረቤቶቿን ተጠቃሚ ማድረግ እንዳለባት እየጠቆመች ያለች ሲሆን ከዚህም ባሻገር ታላቁ ህዳሴ ግድብ አንዱ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን የተሳሳተ መረጃ በኢትዮጵያ ላይ ፈተና የሆነባት ይመስላል። ይህ እንዴት ነው የተስተናገደው ብለው ያስባሉ?
አምባሳደር ሬሚ፡– በመጀመሪያ ደረጃ ለማንኛውም አገር እድገት የኤሌክትሪክ ሃይል የማምረት አቅም ማሳደግ ቁልፍ ነው ብዬ አስባለሁ። በዚህ ረገድ አሁንም ቢሆን የመብራት አገልግሎት የማያገኝ እጅግ በጣም ብዙ ኢትዮጵያዊ አለ። ከዚህ ባሻገርም በመንግስት የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ሁሉ ልክ እንደ ኢንደስትሪ ፓርኩ ተጨማሪ የኤሌክትሪክ ኃይል ያስፈልጋቸዋል። ስለሆነም የኤሌክትሪክ ኃይል የማምረት አቅምን በተለይም በታዳሽ ሀይል አቅም ማሳደግ በጣም አስፈላጊ መሆኑም አገራችን ታምናለች። ለዚህም ነው በአሁኑ ወቅት ፈረንሳይ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የጂኦተርማል ኤሌክትሪክ ምርትን ለማሳደግ ከኢትዮጵያ መንግስት ጎን ሆኖ እየሰራች ያለችው። በዚህ አጋጣሚ ተጨማሪ የኤሌክትሪክ የማምረት አቅምን ማሳደግን በተመለከተ አገራችን ምንም ጥያቄ የሌላት መሆኑን መግለፅ እወዳለሁ።
በመሆኑም የአባይ ውሃም ሆነ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሁሉም የተፋሰሱ አገራት ትስስር እንጂ የክርክር ጉዳይ መሆን የለበትም። በዚህ ረገድ በአውሮፓም ሆነ በአፍሪካ ድንበር ተሻጋሪ የሆኑ ወንዞችን በጋራ በሰላም መጠቀምና ማስተዳደር ላይ አገራት ጥሩ ተሞክሮ አላቸው። ለአብነት ያህልም በአውሮፓ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ኔዘርላንድስ እና ቤልጂየም መጥቀስ ይቻላል። በምዕራብ አፍሪካ የሚገኘው የሴንጋል ወንዝም ላይም ማሊ፣ ሴኔጋል እና ሞሪታኒያ የወንዙን ተፋሰስ በጋራ ለማስተዳደርና ለመጠቀም ተስማምተው እየሰሩ ነው የሚገኙት። በመሆኑም በአባይ ወንዝ ላይም በተመሳሳይ ኢትዮጵያ፤ ሱዳንና ግብፅ በጋራ ለመጠቀምና ለማስተዳደር መስማማት አለባቸው የሚል እምነት አለኝ። በዋናነትም በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት የሚደረገው ውይይት መቀጠልና የጋራ መግባባት መፍጠር አስፈላጊ እንደሆነ እናምናለን።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ እየተገበረች ያለችው የአገር በቀል ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ምን ያህል አዋጭ ነው ብለው ያምናሉ?
አምባሳደር ሬሚ፡- አገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት እየተገበረች ያለችውን የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያም ሆነ ኢኮኖሚ ፕሮጀክቶችን ትደግፋለች። በተለይም በፈረንሳይ መንግስት የልማት ኤጀንሲ ባለሙያዎች አማካኝነት የኢኮኖሚ ማሻሻያ በመደገፍ የልማት አጋርነቷን እያረጋገጠች ነው ያለችው። እንዲሁም የመንግስት ኩባንያዎችን አስተዳደር ለማሻሻል እና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ መርሃ ግብር በአገሪቱ እንዲተገበር አገራችን ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገች ነው። በዋናነትም በገንዘብ እና ባለሙያዎች በማሰባሰብ ኢትዮጵያ ያሰበችው የልማት ግብ ከስኬት እንዲደርስ በጋራ እየሰራን ነው የምንገኘው።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ የቱሪስት አቅሟን በተሻለ ሁኔታ ማሳደግ አስፈላጊ ነው ብለን እናምናለን። በዚህረገድ በፈረንሳይ ውስጥ የቱሪዝም ሃብቷን በአግባቡ መጠቀም በመቻሏ ዘርፉ ለኢኮኖሚዋ ዋነኛ የጀርባ አጥንት ከመሆኑም ባሻገር አገሪቱ በዓለም የመጀመሪያዋ የቱሪስቶች መዳረሻ መሆን ችላለች። ይህ ብቻ ሳይሆን በዘርፉ ለበርካታ ፈረንሳውያን የስራ እድል መፍጠር ተችሏል። በአንፃሩ ግን ኢትዮጵያ ምንም እንኳን እምቅ የቱሪዝም ሃብት ቢኖራትም ከዘርፉ የሚገባውን ያህል ተጠቃሚ እየሆነች አይደለም። በመሆኑም ዘርፉን ለማሳደግና ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት አለበት። በተለይም ቱሪስቱ በአዲስ አበባ ረዘም ላለ ጊዜ እንዲቆዩ ተጨማሪ ምክንያት የሚፈጥር ማንኛውም ፕሮጀክት ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል። የአገራችን መንግስትም በሙዚየሙና በላሊበላ ላይ የሚያደርገው ድጋፍም ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሰላም፣ ልማትና ሁለንተናዊ ክብር መረጋገጥ ያበረከተችውን አስተዋፅኦ እንዴት ያዩታል?
አምባሳደር ሬሚ፡- በመግቢያዬ ላይ እንደገለፅኩት አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን መቀመጫ ሆና እያገለገለች ነው። አዲስ አበባም የአህጉሪቱ መዲና ሆና የተመረጠችው ኢትዮጵያ ለአህጉሪቱ ሰላምና አንድነት ባበረከተችው አስተዋፅኦ መሆኑን ሁላችንም እናውቃለን። ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያ ወታደሮች በሰላም ማስከበር እንቅስቃሴ ውስጥ በመሳተፍ ለአካባቢው ሰላምና ደህንነት ያበረከቱትን አስተዋፅዖ የምንገነዘበው ነው። ስለዚህ ይህ በጣም አስፈላጊ ነው ብለን እናምናለን። የፓን-አፍሪካን እንቅስቃሴ እና የፓን አፍሪካን ውህደት መገንባትን በተመለከተ ዋናው ነገር በተጨባጭ ፕሮጀክት ላይ መስራት ነው። ይህንን ያልኩት ከራሳችን የአውሮፓ ህብረት ልምድ በመነሳት ነው። እንደሚታወቀው እኛ ባለፈው ክፍለ ዘመን በነበሩት ጦርነቶች የተከሰቱት እና አገራዊ ጥቅማችንን በማቀናጀት ከብሄራዊ ጥቅም አልፈን የጋራ ጥቅምን ለመገንባት ወስነናል። በኢኮኖሚ ውህደት ያደረግነውም በዚሁ ምክንያት ነው። አሁን ደግሞ የአውሮፓ ህብረት ለአህጉሩ እጅግ ረጅሙን የሰላምና የብልጽግና ጊዜ የሰጠበት ወቅት ነው። ስለዚህ ከአፍሪካ ውህደት ጋር በተያያዘም በተለይም በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ማጠናከር ወሳኝ ጉዳይ እንደሆነ እናምናለን። ኢኮኖሚያዊ ውህደቱን እውን ለማድረግ በተጨባጭ ለመስራት ነፃ የንግድ ቀጠናው አስፈላጊነት ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም።
እንደሚታወቀው ደግሞ የማዳበሪያ ዋጋም ሆነ የእህል ዋጋ እየጨመረ ያለው በዩክሬንና በሩስያ ጦርነት ምክንያት ነው። በዚህ ረገድ አፍሪካ የተቀናጀ አህጉራዊ ገበያን ብትጨምር አብዛኛው ችግር ሊቀረፍ ይችላል ብዬ አምናለሁ። ምክንያቱም ነፃ የንግድ ቀጠናው ከተፈጠረ ከሌሎች የአፍሪካ አገራት እህልና ማዳበሪያ ለማስገባት ቀላል ይሆናል። ስለዚህ የአፍሪካ ውህደት የመጨረሻ ግብ ልንደግፈው የምንችለው ይህንን በአውሮፓ ስላጋጠመን እና በዕለት ተዕለት ህይወታችን ለሁሉም ዜጎች የሚሰጠውን ጥቅም ስላሳለፍን ነው።
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ የለውጡ መንግስት መምጣቱን ተከትሎ የመናገር ና የመፃፍ ነፃነት በተጨባጭ ተግባራዊ እንዲሆን ተሰርቷል። በዚህ ረገድ በተለይም የመገናኛ ብዙሃን አቅም እንዲጎለብት የተሰራውን እንዴት ይመለከቱታል?
አምባሳደር ሬሚ፡– ልክ ነው፤ ይህ ጉዳይ አስቀድሜ ይህ ያልጠቀስኩት ኢትዮጵያና ፈረንሳይ በጋራ የሚሰሩበት አንዱ ገጽታ ነው፤ ለ125ኛ ዓመት የምስረታ በዓልም ትኩረት ከተሰጡ ጉዳዮች መካከል ዋነኛው ይሄ ነው። በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የታተመው ጋዜጣ በፈረንሳይኛ ቋንቋ መታተሙ ይታወሳል። አሁንም ድረስ ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ጋር ኤምባሲያችን ጠንካራ ግንኙነት ነው ያለው። ከዚህም ባሻገር በየጊዜው ለኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ስልጠና እና ድጋፍ እንሰጣለን።
ወደጥያቄሽ ስመጣ እንዳልሽው በተለይ ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የመናገርና የመፃፍ ነፃነት እንዲከበር በመንግስት በኩል የተሰሩ መልካም ስራዎች አሉ። ሆኖም አገሪቱ ከሁለት ዓመታት በላይ ከዘለቀው ግጭት ጋር ተያይዞ ለመገናኛ ብዙሃኑ ባለሙያዎች አስቸጋሪ ነገር ሊኖር እንደሚችል ግልፅ ነው። በተለይም ገለልተኛ ሆኖ መዘገብ ላይ የራሱ የሆነ ተፅዕኖ ሊኖር እንደሚችል ግልፅ ነው። በመሰረቱ በቅርቡ በኢትዮጵያ ስላለው የፕሬስ ሁኔታና ስለቀጣይ አቅጣጫዎች ለመወያየት ከሁሉም የሚዲያ ሥራ አስኪያጅ ጋር ኮንፈረንስ አድርገን ነበር። ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሌሎች አገሮች ጦርነት እንደሚገጥማቸው ጋዜጠኞች ግንባሩ ላይ ለመድረስ ሁኔታውን ሙሉ በሙሉ ለመዘገብ አስቸጋሪ መሆኑን እናውቃለን። እንዲሁም በሁለቱ ወገኖች ፕሮፓጋንዳ ምክንያት ባለሙያዎቹ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ እንደሚሆኑ እንገነዘባለን።
በመሆኑም የራሱን የሥነ-ምግባር ደንብ ለመፍጠር ከኢትዮጵያ ሚዲያ ምክር ቤት ጋር በጋራ እየሰራን ነው። ይህ ደግሞ የጋዜጠኝነት ሙያ መንግሥት እንዲሠራው ከመጠየቅ ይልቅ የራሱን ሥነ-ምግባር፣ የጋዜጠኞችን የሥራ አካባቢ ማስተዳደር እንዲችል ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን እምነት ተይዟል። በአጠቃላይ ግን በተለይ ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ አገሪቱ ያጋጠማት የፖለቲካ እና ወታደራዊ ቀውስ ጋዜጠኞች በነጻነት ለመስራት ምቹ ሁኔታ አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻ ማንሳት የሚፈልጉት ሃሳብ ካለ እድሉን ልስጥዎት?
አምባሳደር ሬሚ፡- ጥያቄሽ ሁሉንም ሃሳብ የሚሸፍን ይመስለኛል። ይሁንና ሰሞኑን ኤምባሲያችን የፈረንሳይን ብሔራዊ የነፃነት ቀን እያከበረ ነው ያለው። የጭካኔ ቀን የሆነውን ብሔራዊ ቀን እያከበርን ነው። ስለዚህ ቀኑ የፕሬዚደንታችን ልደት አይደለም፣ የነጻነት ቀን አይደለም፣ የሕገ መንግሥት ቀን አይደለም፣ አብዮት እያከበርን ነው። እንደሚታወቀው ይህ ‹‹ባስቲል ቀን ››በመባል በየዓመቱ የምናከብረው በዓል የፈረንሳይ ህዝብ ከጭቆና ቀንበር ለመላቀቅ ብርቱ ተጋድሎ ያደረጉበትና የሕይወት መስዋዕትነት የከፈሉበት በመሆኑ በመላው ህዝባችን ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ነው። በመሆኑም ለመላው ህዝባችን ለዚህ የድል ቀን እንኳን አደረሳችሁ ማለት እፈልጋለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ውድ ጊዜዎትን ሰውተው ከእኛ ጋር ቆይታ ስላደረጉ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ሥም ከልብ አመሰግናለሁ።
አምባሳደር ሬሚ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ሐምሌ 9/2014