እውነቱን ለመናገር ዕለቱን ‹‹ደስ የሚል ቀን ›› ብሎ መጀመር ቀናችንን እጅግ አስደሳች ያደርገዋል። ቀደምቶቹ ወላጆቻችንም ብሩህ ቀን እንዲሆንላቸው በማሰብ ይመስለኛል‹‹ በቀኝ አውለኝ›› ሲሉ በጸሎት የሚማጸኑት። ሰው የአፉን ፍሬ ይበላል ይባል የለ። መቼም ግንባርን አሹሎ፣ አንገት አጎንብሶ፣ ፊትን ከስክሶ ደባሪ ቀን ብሎ ከመጀመር፤ ከአንገት ቀና ብሎ፤ ፊትን ፈገግ አድርጎ መልካም መልካሙን ተመኝቶ ውሎን እንደመጀመር የሚያስደስት ነገር የለም። ‹‹ደስ የሚል ቀን ነው›› ብሎ ደስ በሚል መነሳሳት ስራን መጀመር ቀኑን መልካም ሊያደርገው እንደሚችል እርግጠኛ መሆን ባይቻልም፤ በተወሰነ መልኩ ቀኑ መልካም ሆኖ ሊውል እንደሚችል መገመት አያዳግትም።
ድሮ ድሮ ሌሊቱን ሙሉ የማህበራዊ ድረ ገፅ ተመልካች ከመሆናችን በፊት ለማለት ነው ‹‹ቀኑ ደስ ይላል›› ብሎ መጀመር ከባድ አልነበረም። አሁን አሁንማ ሌሊቱን ሙሉ ሲተገትገን የሚያድረው እና አይናችን እስኪፈዝ የምናነበው እውነተኛውም የፈጠራውም ዜና የሌሊት እንቅልፍ ማጣቱ ተጨምሮበት ‹‹ቀኑ ደስ ይላል›› ብሎ ለመጀመር እንዲያቅተን ካደረገ እነሆ በጣት የሚቆጠሩ ዓመታትን አሳለፍን።
ዕድሜ ለቴክኖሎጂ፤ ይኸው አሁን የደረስንበት ቦታ ላይ ለመገኘት አብቅቶናል። መረጃን በቅርበትና በፍጥነት ለማግኘት። ግን ግን እኮ ሁልጊዜ የሚሰራጩ መረጃዎች እውነተኛ ይሆኑ ብሎ መጠርጠር ይገባል። ያልጠረጠረ ተመነጠረ እንዳንሆን ማለቴ ነው። አይናችንን ያፈጠጥንባቸው መረጃዎች ገደል እንዳይከቱን ከስሜት ወጣ ብለን በስሌት መመርመሩ አይከፋም ብዬ ነው።
የእኛዎቹ መገናኛ ብዙሃን ሥራቸውን ሲሰሩ፤ የተለያዩ በይነ መረብ የዜና መዓት ሲያዠጎደጉዱ እኛም መረጃና ማስረጃ ሳንል ያንኑ እያየን እንቅልፍ እያጣን ስንወናበድ ዛሬ ላይ ደርሰናል። እኛም ተቀብለን እውነት ሀሰቱን እየደባለቅን፤ በጭንቀት ማዕበል እየተናጥን ይሄው አለን። አንዳንዱ የጨነቀው የሰው አገር አገሩ ይሆንለት እየመሰለው ‹‹ነገ ምን እንደሚፈጠር አይታወቅም፤ እንደው ቢቻል ወደ ውጭ አገር የሚልክ ሰው ከተገኘ ተጠራርገን ብንጠፋ ይሻለን ይሆን›› ይላል።
ስንቱ ከአገር መውጣት ይችላል? ቢባል እርሱ የሚሸጠው ቤት እና መኪና ወይም ሱቅ ስላለው ያንን ሽጦ ከአገር ስለመውጣት እንጂ ስለሌላ ወገኑ፣ ስለቅርብ ዘመዶቹ ወንድም እህቶቹ የሚያስብበት አዕምሮ የለውም። ነገሩ ምን ያድርግ የዜናው ጋጋታ አዕምሮውን ወጥሮት በምን መንገድ እንዴት ማምለጥ እንደሚችል እንኳ ለማገናዘብ ቸግሮታል። በዚህ ሳቢያ አንዳንዱ ብቻ ሳይሆን የብዙሃኑ ሰው ደስታ ጥያቄ ውስጥ ወድቋል።
ነገሩ እኛ ደስታ እንጣ እንጂ ‹‹የበሬ ወለደ ዜና ምንጮቻችን›› ደስታ ያጡ አይመስለኝም። ማለቴ በሰው ሀዘን፣ እንባ እና መከራ ኪሳቸው ስለሚያብጥ፤ ግን እኮ እሱም ቢሆን የውስጥ ደስታን ሳይሆን ጭንቀትን እንደሚያስከትል መገመት አይከብድም። አንዳንዱ የመረጃ ምንጭ ‹‹ሰው ተገደለ›› የሚል ዜና በማግኘቱ ደስታው ወደር ያጣል። ለእሱ የሰው ሞት የቁጥር ጨዋታ ነው። ሰው በሰውነቱ ሳይሆን ከሞቱ ለማትረፍ ዘር ተጠቅሶ ጄኖሳይድ ነው አይደለም በሚለው ላይ ይከራከራል።
ከጥፋት አለቃው የተሰጠውን መመሪያ ለመፈጸም ኪሱንም ዳጎስ ለማድረግ በሂሳብ ትምህርቱ ላይ አልገባ ያለው የማባዛት ስሌት እዚህ ላይ ማባዛትን ሲለማመድ ይታያል። ጫፍ ይዞ ‹‹አለቅን›› ሲል ያለቀልቃል። በአፉ ‹‹አለቅን›› ቢልም የውስጥ ልቡ ግን በደስታ የሚፍነከነክ ይመስላል። ይሄኛው ለሞቱት ዜጎች የሚያዝን ህሊና የሌለው ከመሆኑ በተጨማሪ አለቅን የሚል ወሬ በመንዛት የሚያገኘውን የራሱን ጥቅም ያስባል። በሌላ በኩል አንዳንዱ ሰዎቹ ስለሞቱ የእርሱ ርዝራዥ የሥልጣን ዘመን የተራዘመችለት ይመስለዋል። ጥግ የደረሰ ስግብግብነት፤ ከሌላው ጥፋት ያለመማር የዋህነት ልበለው ? እንደ እኔ አላማ ቢስ ስግብግብነት ብለውስ ?
እንዲህ አይነት ባህል መዳበር ከጀመረ አመታት እየተቆጠሩ ነው። ማጥላላት፤ የሆነ ያልሆነውን ማውራት፣ ማስወራት እና ማስፋት ልማድ ሆኗል። እዚህ ላይ ደግሞ የሆነ ቡድን ሲያልቅ የዛ ብሔር ተቆርቋሪ መስሎ ስለዛ ብሔር እያወሩ ዜናቸውን እየሰሩ ማራገብ የሚወዱ ጥፋቱ ሲቀጥል እነርሱንም ጠራርጎ እንደሚወስድ የዘነጉ ይመስላሉ። የሰው ልጅን ለማዳን ሳይሆን እያቀጣጠሉ አንዱ በሌላው ላይ እንዲነሳ መግፋት በሚመስል መልኩ የስሜት ፈረስ እያዘጋጁ ጋልብ እያሉ የሚገፋፉ፤ በአፍ እያዘኑ በልባቸው በሰዎች ማለቅ የሚደንሱ ቀላል አይደሉም። እነኚህ በሕዝብ እልቂት ስማቸውን የሚገነቡ፤ ራሳቸውን የሚያነግሱ እና ስልጣናቸው መሬት እየያዘ እንደሚቀጥል ተስፋ የሚያደርጉ፤ እንኳን ስልጣን ለሆዳቸው ቁራሽ የሚያጡበት ጊዜ ሊመጣ እንደሚችል ነጋሪ አያሻም። ጠንቋይ መሆንን አይጠይቅም። ምክንያቱም የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃልና ነው። ከአያያዛቸው መውደቂያቸው ይታያል።
በማያውቀው ታሪክ ላይ ተመስርቶ እግረ መንገዱን ያለችውን ስልጣን አስታኮ መራራ ጭቆና ለማድረስ የሚዳዳ የሰው መናኛ በሚሰራው ሴራ ከመኩራት ይልቅ መፍራት ይኖርበታል። ከትናንቱ ትርክት የዛሬው ከከፋ ምኑን ከትናንቱ ተማርነው፤ ምኑን ከሌላው አጥፊ ተሻልነው? የሌሎችን አገራት የእርስ በእርስ ግጭት ያደረሰውን ጉዳት አላየንም እንዴ፤ አልሰማንም እንዴ? ይሄ እዚህ አይሆንም ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው። አንዱ ሌላውን ጎድቶ ደልቶት ይኖራል ብሎ ማሰብ የህጻን ጨዋታ እንደማለም ነው።
አንዳንድ ሰዎች እምነታቸው የቀበሌም ሆነች የወረዳ፤ የከተማም ሆነች የክልል ስልጣናቸው ለማራዘም ሰዎች መንገድ፣ ጤና ጣቢያ፣ ሆስፒታል አጠቃላይ መሰረተ ልማት አልተሟላልንም ብለው ጥያቄ እንዳያቀርቡ፤ አንዳንዴም ኑሮ ተወደደብን እያሉ እንዳይነጫነጩ የመኖር ህልውናቸውን በመፈታተን ከጥያቄ ነፃ ሆኖ ስልጣንን ማራዘም ይቀላል ይላሉ። እውነት ነው፤ በጀቱን ለራስ ማድረግ እየተቻለ ማን መሰረተ ልማት በመገንባት ጊዜውን እና ጉልበቱን ያባክናል። ባይሆን በበጀቱ እየተንደላቀቁ እያናጩ መኖር ይቀላል። ታዲያ እንደነዚህ ሰዎች ገለፃ ከሆነ ሰው በማፋጀት ጥቅምን ለማግበስበስ እና ለማስጠበቅ መሞከር ከስግብግብነት ውጭ ምን ሊሰኝ ይችላል?
በእርግጥ የእነ እገሌ ወገንም ሆነው በሰዎች እልቂትና መፈናቀል የግል ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ የሚጣጣሩ አሉ። ታዲያ እነኚህም ሰውነትን እና ስብዕናን በሚያወርድ ስግብግብነት ውስጥ እየዳከሩ አይደለም ማለት ይቻላል? ይህንን ለመጠየቅ ያነሳሳኝ መራራ ጭቆና ሳይደርስ መራራ ጭቆና ደረሰ ብሎ የሀሰት ወይም የተጋነነ ተረክ በመተረክ የሥልጣን ዕድሜውን ለማራዘም የሚፈልጉ ብዙዎች ናቸው። ብሔርን መሸሸጊያ ሃይማኖትን መከለያ አድርገው በሰው ቁስል ጨው የሚነሰንሱ በመኖራቸው ነው።
ይሄኛው በዘራችንና በብሔራችን ላይ መራራ ጭቆና እየደረሰ ነው ብሎ በመጮህ እና በማጯጯህ ስልጣን የማግኛ አገርን፣ ክልልን ወይም ወረዳንም ቢሆን በማስተዳደር ስለሚያገኘው ጥቅማ ጥቅም ይጨነቃል። ወይም ደግሞ የብሔር ፍጅት በኢትዮጵያ እየታየ ነው በሚል ዜና የዩቲዩብ ገቢውን ያዳጉሳል። በሌላ በኩል ደግሞ የስልጣን ጊዜውን ያራዝማል። እንግዲህ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ የሚባለው ይሄኔ ነው። ከዚህ ውጭማ ይሔ ብሔር …ይሄ ብሔር እያለ የሚጮህ በሙሉ ስለብሔር ገብቶት ይሆን? ከተባለ መቼም ገቢውን ማግኘት ምናልባት ትንሽ ሳያደክም አይቀርም። ብዙሃኑ የእገሌ ብሔር ተጠቀመ፣ ተጎዳ እና ተጨፈጨፈ የሚለው ስግብግብ ሆኖ የራሱን ጥቅም አስቦ እንጂ ብሔር የሚለው ቃል ትርጉሙ ገብቶት አይመስለኝም።
እንግዲህ የዘርፉ ተመራማሪዎች እንደውም ተመራማሪዎች አይደሉም ፈላስፋዎች አንድን ቡድን አንድ ብሔር ነው ለማለት የሚቻለው አንድ አይነት ቋንቋ የሚናገር፣ በአንድ አገር ውስጥ የሚኖር፣ የተሳሰረ የኢኮኖሚ አኗኗር ያለው፣ በባህሉ ተመሳሳይ ስነልቦና የተመሰረተና ታሪክ ያቆራኘው የፀና ማህበረሰብ ሲሆን ነው ብለዋል። እንኳን የተሳሰረ ኢኮኖሚ ሊገለፅ የሚችል ትንሽ የሚነገርለት ኢኮኖሚ ሳይኖር፣ ያን ያህል የቋንቋ ልዩነት ሳይኖር አንዳንዴም ከቋንቋ አልፎ ባህል ሳይቀር ተሳስሮ፤ በስነልቦና ተቆራኝቶ ዘመናትን ያሳለፈ ሰው የተለየ ብሔር ነው በሚል ሰበብ የሌለ ታሪክ ጠቅሶ ሰው መጥላት፤ ከመጥላት አልፎ መግደል፤ ከመግደል አልፎ መጨፍጨፍ ብሔራዊ ስሜትን በተሳሳተ መንገድ በመተግበር እና በማስተግበር የብሔርን እና የአገርን ደህንነት ከማስጠበቅ ይልቅ የራስ ስሜትን ብቻ በማዳመጥ ቅጥ ባጣ ስግብግብነት የዘር ማጥፋት ዘመቻን ማበረታታት በእውነቱ እንደ ኢትዮጵያውያን ባሉ አስተዋይ ሕዝቦች ዘንድ ለትዝብት ይዳርጋል።
በሌላ በኩል አንድን ብሔር ብቻ የመጠበቅ ዘመቻ በሚመስል መልኩ በደቡብ እርስ በእርሱ ሕዝብ እየተጫረሰ ሰዎች እየሞቱ፤ በሰሜኑም በምስራቁም በምዕራቡም በወሰን እና ሌላም ሌላም በሚባሉ የተለያዩ ሰበቦች ሰዎች እየተጨፋጨፉ ሰው ለምን ሞተ ብሎ ከመጠየቅ ይልቅ፤ ተቆርቁሮ ከማልቀስ እና ከማስለቀስ ይልቅ በየሚዲያው ለምን የሰው ልጅ ይሞታል? ብሎ ጥያቄ ማንሳት ሲገባ ዘር እየመረጡ መጮህ ከሰብዓዊነት ያፈነገጠ ተቆርቋሪነት ነው፤ ይሄ እንደ እኛ ላለ በደምና ስጋ ለተጋመደ ሰው አያዋጣም።
ይህንን ማለት ካልተቻለ ለሁሉም የየክልል ወይም የየዞን አመራሮች የስልጣን ማራዘሚያ እራት መሆን ያጋጥማል። ብሔር እንደልዩ ተፈጥሮ እያዩ መመፃደቅ እና ማመፃደቅ በኋላ ማባሪያ ለሌለው እልቂት ይዳርጋል። እውነተኛ ለወገን መቆርቆር ከሆነ ብሔር ለይቶ ብቻ ሳይሆን ሰው ለምን ይገደላል ብሎ መጠየቅ ይገባል። ከዛ ውጭ ለሞተው አስክሬን ብሔር እየጠቀሱ ሃይማኖት እየሰጡ ስሜትን መቀስቀስ ለማንም አይበጅም። ቅጥ ባጣ ስግብግብነት በመታወር የሰው ልጅ ሞትን እየተለማመደ ድርጊቱም እንደትክክለኛ ተግባር መውሰድ ከቀጠለ አደጋው የከፋ ይሆናል። የሩዋንዳዎች አጀማመራቸው እንዲሁ ነበር።
እንደ ጎርጎሮሲያዊያኑ በ1994 ያለቅጥ ስግብግብነት ነግሶባት በነበረችው ሩዋንዳ ከ800 ሺህ እስከ 1 ሚሊየን 200 ሺህ ሩዋንዳውያን እንደሞቱ ይገመታል። በመቶ ቀናት ብቻ የሩዋንዳ ፕሬዚዳንት ጁቬኔል በአውሮፕላን ሲጓዙ በተሰነዘረባቸው ጥቃት መሞታቸውን ተከትሎ የቱትሲ ጎሳዎችን የማጥፋት ዘመቻ ታወጀ። በዘር ማጥፋት ዘመቻው ቱትሲዎች ብቻ ሳይሆኑ ለዘብተኛ ሁቱዎችም ከሞት አላመለጡም ነበር። ይህንን ዓለም የሚያውቀው ትልቅ መጥፎ የሩዋንዳውያን ታሪክ ነው። ታሪኩ የሁቱዎች ወይም የቱትሲዎች ብቻ አይደለም። የመላው ሩዋንዳውያን ታሪክ ነው።
ለእዚህ ተግባር ተባባሪ ሆነው ያለቅጥ መስገብገባቸው ከሰውነት ክብራቸው ወርደው የብዙ ሩዋንዳውያን ደም እንዲፈስ ካደረጉት መካከል በመከላከያ ሚኒስትር ውስጥ ቁልፍ ሚና የነበራቸው ኮሎኔል ቦጎሶራ ያን አንዱ ነበሩ። እርሳቸውን የመሳሰሉ ሌሎች የጊዜው ስግብግቦች የራሳቸውን የሥልጣን ጥማት ለማርካት ሲሉ በቀሰቀሱት እና ባቀጣጠሉት እሳት ብዙ ሩዋንዳዎች ተማግደዋል። ሕይወታቸው የጠፋው እንደሰው ሳይሆን ከዱር አውሬ ባነሰ ለማሰብ እና ለመገመት በሚያስቸግር ዘግናኝ መልኩ ነበር። ‹‹የአበራሽን ጠባሳ ያየ በእሳት አይጫወትም›› እንደሚባለው ሁሉ ሩዋንዳ ላይ ትልቅ ጠባሳ ጥሎ ያለፈው የዘር ፍጅት አሁን ከሚታየው በባሰ እና በከፋ መልኩ ኢትዮጵያ ውስጥም እንዳይፈጠር ከወዲሁ መጠንቀቅ ይገባል።
ከኖረው ትርክት ወጥተን፤ ከተላላኪዎቻችን አምልጠን፣ ቆም ብለንና አስተውለን ለአንድነታችን ብንሰራ የታሪክ አሻራችንን እንተክላለን። ብሔር፣ ሃይማኖትም ሆነ ስልጣን ከአገር በላይ ነውና። ከሩዋንዳ ተሞክሮ እንደታየው ስልጣን ለመያዝ እና የሥልጣን ዕድሜን ለማራዘም የቋመጠው በዘር ጭፍጨፋው ውስጥ ቁልፍ ሚና የነበረው ኮሎኔል ቦጎሶራ ቅጥ ያጣ ስግብግብነቱ መጨረሻ ላይ እንዳሰበው ዓላማው ግብ አልመታም። ይልቁኑ ለዓመታት ዕድሜውን በእስር ቤት ሆኖ እንዲፈጅ ተፈረደበት። አሁን በሩዋንዳ ሕዝብን ያስጨረሱ እና የጨረሱ ሞት ባይፈረድባቸውም እንኳን ለዘላለም የህሊና እስረኛ ሆነዋል። አጥር በሌለው እስር ቤት ውስጥ ያሉ የዘር ጭፍጨፋ ፈፃሚዎች ህሊናቸው በመታሰሩ በአካል እጃቸው በካቴና ባይታሰር እንኳ፤ ትልቅ ግንብ በተገነባ እስር ቤት ባይቀመጡ እንኳ ለመጥፋት አይዳዱም። ያ የፈፀሙት እጅግ አሰቃቂ ድርጊት አሁኑ እጅ እና እግራቸውን አስሯቸዋል።
ሆ ብሎ መጓዝ፤ በስልጣን ፈላጊዎች ተታሎ ጥግ ይዞ ብሔር ላይ እየተንጠላጠሉ ወቀሳ ከመሰንዘር እና ለይቶ ግርግር እየፈጠሩ ከማልቀስ ይልቅ አንዱ የሌላውን መብት አክብሮ ይንቀሳቀስ። ስግብግብ ስልጣን ፈላጊዎች፤ ከሰውነት በታች ያሉ ምክንያት አልባዎች እንዲያፍሩ ሕዝብ መንቃት አለበት። ማንም የማንም መጠቀሚያ መሳሪያ እንዳይሆን መንቃት የግድ ነው። የሰዎች አስተሳሰብ መከበር አለበት።
የብሔሮች መብት መከበር አለበት። ይሔ ሲሆን እገሌና እገሊት ስልጣን እናጣለን ብለው ከሚሰጉ ሁለቱም በሥራቸው ላይ ብቻ ቢተጉ ያለባቸውንም የአቅም ችግር በመማርም ሆነ በማንበብ ለመፍታት ቢሞክሩ ይበጃል። ጭፍን ስግብግብነት ‹‹አያ በሬ ሆይ ሳሩን አየህና ገደሉን ሳታይ እንደተባለው›› የኢትዮጵያ ሕዝብ ምንም እንኳን አስተዋይ ሆኖ ብዙ ነገሮችን አይቶ እንዳላየ ቢያልፍም፤ የተናጠ ወተት ቅቤ ይወጣዋል ብሎ ቢታገስም ከሕዝብ የተሸሸገ ምንም ነገር ስለማይኖር በኋላ ስልጣን ላይ ያለውም ሆነ ስልጣንን ቋምጦ ሕዝብ እንዲጨፈጨፍ ዳር ሆኖ የሚገፋውን በቃህ ብሎ የሚገፈትርበት አሯሩጦ ገደል የሚጨምርበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 7/2014