የግብርና ምርቶችን በብዛትና በጥራት በማምረት ለኢንዱስትሪ፣ ለኤክስፖርት፣ ከውጭ አገር የሚገባን ምርት በአገር ውስጥ ለመተካት እና የአገር ውስጥ የዜጎች የምግብ ፍላጎትን ለማሟላት እንዲቻል ሰፊ ርብርብ እየተደረገ መሆኑ ይታወቃል። የአገሪቱ የግብርና ምርቶች ደረጃቸውን የጠበቁና በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ መሆን እንዲችሉ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ይሁንና ምርቶቹን ለገበያ በማቅረብ ሂደት በርካታ ችግሮች ይስተዋላሉ። በተለይም እሴት የማይጨምሩ በግብይት ሰንሰለት ውስጥ የሚገኙ በርካታ ደላሎች የንግድ ስርዓቱን ገበያውን ሲረብሹት ይስተዋላል። በዚህ ጤናማ ባልሆነ የንግድ ሂደት አምራቹም ሆነ ሸማቹ ተጠቃሚ እየሆኑ አይደሉም።
ምርትና ምርታማነት የቱንም ያህል ቢያድግ የግብይት ስርዓቱ ዘመናዊነት በተላበሰና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ካልተመራ የአምራችና የሸማቹን ፍላጎት ማሟላት አይቻልም። አምራቹ የምርቱ ተጠቃሚ መሆን ካልቻለ ሌላ ምርት ለማምረት ይነሳሳል፤ ይህን ተከትሎ ተጠቃሚውም ይጎዳል።
ይህን ችግር መነሻ በማድረግም በቅርቡ በኢትዮጵያ ኅብራት ሥራ ኮሚሽን አነሳሽነት በአይነታቸው የተለዩ በኅብረት ሥራ ማህበራት አባላት የሚመረቱ የአርባ ምንጭ ሙዝ፣ የአዊ ድንች እና የጨንቻ አፕል ምርቶች አዳዲስ የብራንድ መለያዎች እንዲወጣላቸው ተደርጓል፤ ብራንዶቹን የማስተዋወቅ ተግባር ከሰሞኑ ተከናውኗል።
ምርቶቹ ዕውቅና በተሰጣቸው ወቅትም የኢትዮጵያ ህብረት ሥራ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወይዘሮ አያልሰው ወርቅነህ እንደገለጹት፤ የእነዚህ የግብርና ምርቶች ዋና ዋና ፈተናዎች ከሆኑት መካከል በአገር አቀፍ ገበያ በስፋት ተደራሽ መሆን አለመቻል፣ ደካማ የግብይት ትስስር፣ የገበያ መሰረተ ልማት እጦት እና በእሴት ሰንሰለት ውስጥ ጥቂት ነጋዴዎችና ደላሎች እንዳሻቸው የዋጋ ተመን በማውጣት ገበያውን እየተቆጣጠሩ ግብይቱን እያዛቡና እየገደቡ ያሉባቸው ሁኔታዎች ይጠቀሳሉ። በዚህ የተነሳም አምራቹም ሆነ ሸማቹ ተጠቃሚ መሆን እየቻሉ አይደለም።
ኮሚሽኑ የኢትዮጵያ ህብረት ሥራ ኮሚሽን ከግብርና ሚኒስቴር እና ከግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ምርቶቹ በሚገኙባቸው ክልሎች ያሉ ኅብረት ሥራ ማህበራትን በማጠናከር፣ ምርታማነትን ማሳደግና የምርቶቹን የግብይት ስርዓት ማዘመን እንዲቻል የተመረጡ የሙዝ፣ የአፕልና የድንች ምርቶችን ብራንድ በማድረግ ከተዛባ የገበያ ስርዓት የሚወጡበትን ሁኔታ ለመፍጠር እየሠራ ይገኛል።
‹‹የአርባ ምንጭ ሙዝ፣ የአዊ ድንችና የጨንቻ አፕል ምርቶች አዳዲስ የብራንድ እሴቶችና መለያዎች ምርቶቹ ሰፊ የገበያ መዳረሻዎች እንዲኖራቸው ያደርጋል›› ያሉት ዳይሬክተሯ፤ በተለይም የአርባ ምንጭ ሙዝ በተለየ ሁኔታ በሂደት በዓለም አቀፍ ገበያ ጭምር እንዲቀርብ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ሲሉ አስታውቀዋል። ይህም የአምራቹን ኑሮ በማሻሻል የጎላ አገራዊ ፋይዳ እንደሚኖረው አስረድተዋል።
የአማራ ክልል ህብረት ሥራ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ወልደትንሳኤ መኮንን እንዳሉት፤ በክልሉ 23ሺ259 የህብረት ሥራ ማህበራትና 72 ዩኒየኖች ይገኛሉ። እነዚህ የህብረት ሥራ ማህበራት የተለያዩ ምርቶችን በማምረት ለገበያ ያቀርባሉ።
በአስር ዓመት ስትራቴጂካዊ ዕቅድ አስር የግብርና ምርቶች ብራንድ ይደረጋሉ ተብሎ ዕቅድ ተይዟል ያሉት አቶ ወልደትንሳኤ፣ ከአስሩ መካከልም ሶስቱ ብራንድ መደረጋቸው በሶስት ምክንያቶች ወሳኝና እንደሆነም አንስተዋል። አንደኛው ገበያው ውስጥ በመለያው ለመድረስ፤ ሁለተኛው ምርቱ ተሻሽሎ በስፋት እንዲመረት ለማስቻል፤ ሶስተኛው ደግሞ ምርቱ በመሀል የገበያውን ስርዓት የሚያበላሹትን አልፎ በብራንዱ ወይም በመለያው መሰረት ወደ ገበያ እንዲገባ በማስቻልና ተጠቃሚውን ተደራሽ ማድረግ ይቻላል ሲሉ ያብራራሉ።
እነዚህ ምርቶች ወደ ገበያው የሚገቡትም በተደራጁ የኅብረት ሥራ ማህበራት ሲሆን፤ ለአብነትም የአዊ ብሔረሰብ አስተዳዳር ዞን የዘንገና አትክልትና ፍራፍሬ ኅብረት ሥራ ዩኒየን አዲስ አበባ ገበያ ድረስ ይዞ ይገባል። ብራንድ ሆኖ ወደ ገበያው ሲገባም በዋጋም ሆነ በመጠን ለማኅበረሰቡ ተደራሽ ለመሆን የተሻለ አማራጭ ይፈጥራል።
ገበያው ውስጥ ጥሩ ግብይት እንዳይኖር ከሚያደርጉ ችግሮች መካከል አንደኛው የምርት መጠን ማነስ ሲሆን፤ ሁለተኛው በአምራቹና በሸማቹ መካከል ያለው የግብይት ሥርዓት ነው። ሌላው ጥራታቸውን የጠበቁ ምርቶችን ከማቅረብ አንጻር የሚታዩ ችግሮችና በአምራቹና በሸማቹ መካከል ያለው የዋጋ ሁኔታ ስርዐት አልበኝነት ያለበት መሆኑ ነው።
አቶ ወልደትንሳኤ እንዳሉት፤ ይህን ብልሹ የገበያ ሂደት ለማስተካከልም ተደራጅቶ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል። አምራቾች ተደራጅተው ምርቱን ለኅብረት ሥራ ማህበራት ተደራጅተው ያስገባሉ። ኅብረት ሥራ ማህበራቱም ምርቱን ወደ ገበያ በማስገባት ለተጠቃሚው ተደራሽ ያደርጋሉ። በዚህ መሰረት ገበያውን ስርዓት ማስያዝ ይቻላል። አጠቃላይ የገበያ ሥርዓቱን ጤናማ ማድረግ እንዲቻልም ምርቶችን ብራንድ የማድረጉ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።
ከመቼውም ጊዜ በተለየ በአሁኑ ወቅት የኅብረት ሥራ ማህበራት ራሳቸውን እያደራጁ ጥሩ ድጋፍ እያረጉ መሆኑን ጠቅሰው፣ በፋይናንስ ረገድም መንግሥት እየደገፈ መሆኑን ነው ያመለከቱት። በተለያዩ አደረጃጀቶች ስልጠናዎችን በማዘጋጀት መንግሥት እየደገፈ ነው። ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግም የተሻሻለ ምርጥ ዘር እያቀረበ ይገኛል። ከዚህ አንጻር ኅብረት ሥራ ማህበራት እንዲጠናከሩ በራሳቸው ምርጥ ዘር እንዲያመርቱና ተደራጅተው ገበያ ውስጥ እንዲገቡ እየተደረገ ያለው ሥራ አበረታችና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ተግባር ነው ሲሉ ያብራራሉ።
‹‹መደራጀት አንድነት ነው›› በማለት በህብረት ሥራ ከተደራጁ ጊዜ ጀምሮ ሀሳባቸው መደመጥ እንደቻለና ምርትና ምርታማነት ላይም ውጤት ማስመዝገብ እንደቻሉ የገለጹት አርሶአደር ምክሩ ታረቀኝ በአማራ ክልል አዊ ዞን ዳንግላ ወረዳ የዘንገና መስኖ ቦርድ ሰብሳቢ ናቸው።
እንደ አርሶ አደር ምክሩ ገለጻ፤ አርሶ አደሮች በኅብረት ሥራ አማካኝነት የተለያዩ ዘሮችን ለአባሎቻቸው በቀላሉ ማግኘት ችለዋል። ምርቶቹንም ብራንድ ማድረግ ወይም መለየት መቻሉ በገበያ ይበልጥ ጠቃሚ መሆን ያስችላል። በገበያ ትስስር ምንም እሴት ከማይጨምሩ ደላላና ነጋዴዎች አርሶአደሩን ለመታደግ ይጠቅማል።
በአሁኑ ወቅት የአካባቢው የድንች ምርት ብራንድ መደረጉና መተዋወቁ ጤናማ የገበያ ስርዓት እንዲፈጠር ያደርጋል ሲሉም አርሶ አደሩ ተናግረው፣ ምርቱም ማህበራቱ በተደራጁበት አግባብ ለዩኒየኑ በቀጥታ ያደርሳል፤ ዩኒየኑም በቀጥታ ለሸማቹ ያቀርባል ብለዋል። በዚህም በቅድሚያ አባላቱ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ፣ ሸማቹም ያለደላላ ምርቱን ማግኘት በመቻሉ ተጠቃሚ ይሆናል ይላሉ።
አርሶ አደር ምክሩ አርሶ አደሩ ሰፊ የገበያ ትስስር የፈጠረ እንዳልሆነና በዚህም ምክንያት በስፋት ወደ ማምረቱ ስራ እንዳልገባም ይጠቅሳሉ። ትስስሩ ቢኖር ምርቱን አሁን ከሚያመርተው በእጥፍ ማምረት እንደሚቻልም ነው የሚጠቁሙት። በሙሉ አቅም ለማምረት የገበያ ትስስሩ አለመኖር እንደጎዳቸው ይገልጻሉ። ሌሎች ምርቶችም እንዲሁ የገበያ ትስስር የተፈጠረ ባለመሆኑ በስፋት ወደ ማምረቱ መግባት እንዳልተቻለም ጠቅሰው፣ በአሁኑ ወቅት እንዲህ አይነት የገበያ ትስስር በመፍጠር ምርቶቹን ብራንድ ማድረግ ወይም ማስተዋወቅ መቻሉ በራሱ ትልቅ አቅም ይፈጥራል ብለዋል።
የአዊ ድንች ብራንድ ሆኖ የገበያ ትስስር የተፈጠረለት በመሆኑ አሁን አርሶ አደሮች እያመረቱ ካለው በእጥፍ ማምረት ይችላሉ። ለዚህም የግብዓት አጠቃቀም፣ የማሳና የዘር አይነቶች ወሳኝ ናቸው። ስለዚህ እንደቦታና ግብዓት አጠቃቀም የሚገኘው ምርትም ይለያያል። ለአብነትም በአሁኑ ወቅት በአንድ ሄክታር ከ60 እስከ 80 ኩንታል ድንች የሚመረት ሲሆን፣ በቀጣይ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በሄክታር እስከ 120 ኩንታል ማምረት ይቻላል።
በአዊ ዞን አካባቢ የሚመረተው ድንች ለጤና እጅግ ተስማሚ፣ ጣፋጭ እንደሆነና ሶስት አይነት ዝርያ ያለው መሆኑን የጠቀሱት አርሶ አደር ምክሩ፣ እነሱም ቾልታ፣ አትርአበባና በለጠ ሲሆኑ፣ ሶስቱም የድንች አይነቶች ብራንድ ሆነው ተመዝግበዋል።
የድንች ዋጋ እንደ ገበያው ሁኔታ ከፍና ዝቅ ይላል። በአካባቢው ረከሰ ሲባል በኪሎ እስከ 10 ብር ሲወደድ ደግሞ እስከ 15 ብር ይሸጣል። በአካባቢው ድንችን ከምግብነት ባለፈ የድንች አረቄ ተሞክሮ ተወስዷል። ከስንዴ ዱቄት ጋር በመቀላቀልም እንጀራ መሆን እንደሚችል ተረጋግጧል። ከዚህ በተጨማሪም የአካባቢው ማህበረሰብ የራሱን ምርት በራሱ መጠቀም እንዲችል የድንች ችፕስ ፋብሪካ ለመትከል ዕቅድ ተይዟል።
የግብርና ሚኒስቴር የኢንቨስትመንትና ግብዓት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሶፊያ ካሳ የግብርና ምርቶች ወደ ገበያ የሚገቡት ደረጃ ወጥቶላቸው የሚታወቅ የምርት ብራንድ ይዘው እንዳልሆነ ጠቅሰው፣ ይህም የገበያ ተወዳዳሪነትን እየተፈታተነው እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታዋ ገለጻ፤ ይህን ችግር መነሻ በማድረግም የኢትዮጵያ ህብረት ሥራ ኮሚሽን ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የተለያዩ አይነቶች ድንች በሚመረትባቸው ክልሎች የሚገኙ የህብረት ሥራ ማህበራትን ማጠናከር፣ ምርታማነትን ማሳደግና የምርቶቹን የግብይት ስርዓት ማዘመን ትኩረት የሚሹ መስኮች መሆናቸውን በማመን ፕሮግራም ተቀርጾ ወደ ተግባር ተገብቷል።
ከእነዚህም መካከል የግብርና ምርቶች የራሳቸውን የጥራት መነሻ መሰረት ያደረገ መለያ ብራንድ በማውጣት ለገበያ ማቅረብ አንዱ ነው። በአሁኑ ወቅትም ሙዝ፣ አፕልና ድንች በብዛትና በጥራት በማምረት ያለውን ሰፊ የአገር ውስጥና የውጭ ገበያ እድል ለመጠቀምና የተዛባ የገበያ ስርዓቱን ለመለወጥ እየተሰራ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታዋ ጠቅሰው፣ ምርቶቹ በሚመረቱባቸው ክልሎች የራሳቸው ብራንድ እንዲኖራቸው ተደርገው ቀርበዋል። ይህም በግብይት ሥርዓቱ የሚስተዋሉ ችግሮችን በብዙ መልኩ መቅረፍ የሚያስችል እንደሆነም ሲሉ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ህብረት ሥራ ኮሚሽን ጠንካራ የብራንድ እሴቶችን መለያዎች በመፍጠር ታላቅ እውቅና እንዲጎናጸፉ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች እና በአማራ ክልሎች ከሚገኙ የህብረት ሥራ ማህበራት፣ የህብረት ሥራ ማስፋፊያ ኤጀንሲዎች፣ የግብርና ቢሮዎችና የዞን አስተዳደሮች ካሉ ባለድርሻ አካላት ጋር በከፍተኛ ትጋት እየሰራ እንደሆነም ጠቅሰው፣ የግብርና ሚኒስቴርም ሥራውን በቅርበት እየተከታተለ መሆኑን ነው ያስረዱት።
እሳቸው እንዳሉት፤ የኅብረት ሥራ ማህበራት ለምርት እሸጋ፣ ለመሰረተ ልማት፣ ጥራት ባለው አገልግሎት አሰጣጥ፣ ለምርት ማጓጓዣ፣ ለፕሮሞሽንና ለማስታወቂያና ለመሳሰሉት ሥራዎች ትኩረት በመስጠት ይሰራል። በአሁኑ ወቅትም ብራንድ የተደረጉት የአርባ ምንጭ ሙዝ፣ የአዊ ድንችና የጨንቻ አፕል አዳዲስ የብራንድ እሴቶችና መለያዎች ምርቶቹ ሰፊ የገበያ መዳረሻዎች እንዲኖራቸው በማድረግ የምርቶቹን ዋጋ ለማረጋጋትና የአርባ ምንጭ ሙዝ በተለየ በሂደት ዓለም አቀፍ ገበያ ጭምር እንዲያገኝ ያስችላል።
በመድረኩ ላይ እንደተጠቆመው፤ የአርባ ምንጭ በአገሪቱ በስፋት ዕውቅና ካላቸው የሙዝ ዝርያዎች ቀዳሚው ሲሆን፣ በኦርጋኒክነቱ በተለየ ጣዕምና ጥራቱ እንዲሁም ባለው ረጅም የቆይታ ጊዜ ይወደዳል። የጨንቻ አፕልም እንደዚሁ ባለው ልዩ ጣዕም፣ አነስተኛ የአሲድ መጠንና በውስጡ በያዘው የፈሳሽ ይዘቱ ጥቅጥቅ ያለ መሆኑና ሲበላ ለጥርስ ምቾት ያለው በመሆኑ የተለየ ያደርገዋል። የአዊ ድንች ደግሞ የተጠቀጠቀ፣ ጥሩ ቅርጽና ልስላሴ ያለው ሲሆን፣ በተለያየ የምግብ አይነት ተቀቅሎ፣ ተጋግሮና ተጠብሶ ሊበላ የሚችል ኃይል ሰጪና ሌሎች የምግብ ንጥረ ነገሮችን የያዘ ነው።
በሶስቱ የግብርና ምርቶች ማምረት ስራው ውስጥ በቀጣይ በርካታ የኅብረት ሥራ ማህበራት አባላት አባል ያልሆኑ በርካታ አርሶ አደሮችም ገብተው ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ ይገመታል። በተመሳሳይ በሌሎች የአገሪቱ ክልሎች የሚገኙ የህብረት ሥራ ማህበራትም ስራቴጂክ ተብለው በተለዩ የግብርና ምርቶች ላይ የብራንድ እሴቶችና መለያዎች የመፍጠር ሥራ የሚቀጥል ይሆናል። በዚህም መሰረት በሶማሌ፣ ቤኒሻንጉል ጉምዝ እና ኦሮሚያ ክልል በቅደም ተከተል የሚገኙት የፍየል፣ ማንጎና ቀይ ሽንኩርት ምርቶችን ብራንድ በማድረግ በሚደረገው እንቅስቃሴ የግብርና ሚኒስቴር እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ አንደሚቀጥል አረጋግጧል።
በሶስቱ የግብርና ምርቶች ማለትም በሙዝ 140 ሺ 355 አባላት ያሏቸው 30 መሰረታዊ የኅብረት ሥራ ማህበራት፤ በአፕል 242 ሺ 906 አባላትን ያቀፉ 12 መሰረታዊ ኅብረት ሥራ ማህበራት እንዲሁም በድንች 69ሺ 984 አባላትን ያቀፉ 29 የህብረት ሥራ ማህበራት ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ይጠበቃል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 6/2014