እንደ ማዋዣ፤
የኢትዮጵያ ሕዝብ የምርጫ ካርዱን እንደ “ክብር መረማመጃ ቀይ ምንጣፍ በመደልደል” የአገሩን አደራ በጫንቃቸው ላይ አሸክሞ ለፓርላማ ወንበር ያበቃቸው “እንደራሴዎቹ” የሦስት ሩብ ወራት የተግባር ክራሞታቸውን አጠናቀው ከመንበራቸው ወደ “ጓዳቸው” ለመትመም ተሰነባብተዋል። ይህ የምክር ቤቱ የሰኔ 30 የስድስተኛ ዙር፣ የአንደኛ ዓመት የሥራ ዘመን የ16ኛ መደበኛ የማጠቃለያ ስብሰባ ግጥምጥሞሽ አንዳንድ ትዝታዎችን፣ ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ ጉዳዮችን እንድናስታውስ ግድ ብሎናል። ይህንን ማድረጋችን አንድም ለእውቀት አንድም ለማስታወስ አንድም ለማዋዣነት ይረዳ ስለመሰለን ነው። ውይይታችን ደረቅ በደረቅ እንዳይሆን በመስጋት ጭምር።
በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 58 “የምክር ቤቱ ስብሰባና የሥራ ዘመን” በሚለው ዋና ርዕስ፤ ንዑስ አንቀጽ 2 ሥር “የምክር ቤቱ የሥራ ጊዜ ከመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት ሰኞ እስከ ሰኔ ሠላሳ ነው፤…” ተብሎ ተደንግጓል። ይህ ዕለት ከሰኔ 30 የትምህርት ቤቶች መዘጋትና አይረሴ የሆኑ የተማሪነት ዘመን የመሰነባበቻ ትዝታዎችን እንድንቀሰቅስ ግድ ይለናል።
የፈተና ውጤታቸው የተሳካላቸው ተማሪዎች በሰኔ ሠላሳ ሲፈነጥዙ፤ በለስ ያልቀናቸው ደግሞ እዬዬ ማለታቸው የተለመደ ነው። ፍንጠዛውና እዬዬው በተማሪዎቹ ተግቶ ማጥናትና ያለማጥናት ስለሚወሰን ለጊዜው በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ለማለት ዐውዱ አይፈቅድልንም። ይህንን ገናና የሰኔ ወርና የመጨረሻውን ቀን የሚያስታውሱ በተማሪዎች የተገጠሙና የሚገጠሙ በርካታ አዝናኝ ግጥሞች ቢታወሱ ባልከፋ ነበር። ከርዕሰ ጉዳያችን እንዳያዘናጋን በመስጋት ብቻ እንዘለዋለን።
የፓርላማ ወንበረተኞቻችን የዓመቱ የየግል ቆይታቸው አላባና ገለባ በምን ወንጠፈት ተፈትሾ ማርክ እንደሚሰጣቸው ለጊዜው ዝርዝሩም ሆነ ምሥጢሩ ለወሳኝ ፖለቲከኞች ካልሆነ በስተቀር ለእኛ “ለመራጭ ዜጎች” እንድናውቅ የሚፈለግ ስለማይመስለን “መብታችን ነው” ብለን ለመሟገት አንደፍርም። በግላጭ ቢነገረን ኖሮማ “የምርጫ ካርዳችን ፍሬ ማፍራቱን ወይንም አለማፍራቱን” በሚገባ በገመገምን ነበር።
መቼም ደግ መመኘት በራሱ ደግ ስለሆነ ዲሞክራሲው ሰፋ ቢደረግልን ኖሮማ የመረጥናቸውን “እንደራሴዎቻችንን” ምን ሠራችሁ? ምን ውጤትስ አስመዘገባቸሁ? ምን ተግዳሮትስ ገጥሟችሁ ነበር? ብለን በአደባባይና በሚዲያ ፊት በግልጽነት በገመገምናቸው ነበር። ለምን ቢሉ “ለድምጻችን ክብር መስጠቱ ተገቢ ስለሆነ” መልሳችን ይሆናል። ችግሩ የመረጣችሁት “ፓርቲያችንን እንጂ ግለሰቦችን መች ሆኖ” ተብለን በድርጅታዊ አሰራር የሚሰጠውን ምላሽ “የለመድነው ስለሆነ” እጅግም ንትርኩን አናሟሙቅም።
እጅግ የሚያሳዝነው ግን ከመመረጣቸው አስቀድሞ ሜዳው ጠበብን፣ የሕዝብ ብሶትና እምባ እንቅልፍ ነሳን፤ የአካባቢያችንን ችግር በየቀኑ ማስተዋሉ መብል መጠጣችንን አመረረ ወዘተ. እያሉ ሲብከነከኑና ሲያማልሉን የነበሩ “የተከበሩት” የቅርብ ወዳጆቻችንና የሩቅ “ተደናቂዎች” የልባቸው ከሞላላቸው በኋላ ድምጻቸው ከመንበራቸው፤ ወዳጅነታቸው ከወትሮ ስፍራው ጠፍቶ የመሰወራቸው ምክንያት አልገባንም።
እስከ ምርጫው ድረስ እናደርገው እንደነበረ በቡና ላይም ሆነ በአጋጣሚ ስንገናኝ በእለት ተእለት ውሎ አምሽቷችን “አገር እንዴት ሰነበተች?” እየተባባልን ልንወያይ ቀርቶ የስልክ ግንኙነቱ ራሱ የተቋረጠው “የአፈ ጉባኤው መዶሻ” ጠረጴዛው ላይ ባረፈ የመጀመሪያው ቀን ነበር።
“የእናንተን የመራጮቼን ጥያቄ የተፈለገውን ዋጋ ከፍዬም ቢሆን አስፈጽማለሁ” ተብሎ የተገባልን ቃል ኪዳንም “ከተወካዮቻችን ዘንድ” እንደ ማለዳ ጤዛ በንኖ የተዘነጋ መስሎን በትዝብት አልፈነዋል። ዳሩ ከእነርሱ አእምሮ ይጠፋ ይሆናል እንጂ ከእኛ “ከምስኪን መራጮች” ልብ ግን ትዝብቱ ሊዘነጋ አይችልም። “ተራ ሰው” የመሆናቸው ቀን መድረሱ ስለማይቀር የምርጫ ዘመናቸውን አጠናቀው ሲቀላቀሉን “ትዝብቱ ለሚተርፋቸው ለእነርሱ ይብላኝላቸው” ከማለት ውጭ እኛ መራጮችማ ምን ማለት እንችላለን?
ሌላው የሰኔ ወር የመጨረሻ ቀናት በአብዛኞቹ የአገራችን አካባቢዎች ለገበሬው ልዩ ትርጉም ያላቸው መሆናቸው የሚታወቅ ነው። ገበሬው በሬውን ጠምዶ “ሆ!” እያለ በሙሉ ኃይሉ ወደ መኸር እርሻው የሚገባው በእነዚሁ የሰኔ መጨረሻ ቀናት ነው። “አንድ ሰኔ ያቆሰለውን ዘጠኝ ሰኔ አይፈውሰውም” የሚባለውም አርሶ አደሩን ለሥራ ለማበረታት ታስቦ ነው። “ሰኔ ሲመጣ ድግር ቆረጣ” እንደማይቻልም ሥነ ቃሉ ይመክራል።
የታታሪውን ገበሬ የክረምት ውሎ ማስታወሳችን አለብልሃት አይደለም። የአገራችን የእንደራሴዎች ምክር ቤት በሰኔ ሠላሳ እንዲዘጋ የተወሰነበትን ተለምዷዊ ዳራ ክክረምቱ ተፈጥሯዊ ባህርይ ጋር እያስተያየን አንዳንድ ሃሳቦችን እንሰንዝር። መንገድንና ድልድዮችን የመሳሰሉ መሠረት ልማቶች ባልተስፋፉባት የትናንቷ ኢትዮጵያ በሐምሌና በነሐሴ ወራት ወንዞች ስለሚሞሉ ከግብርና በስተቀር ብዙ ማሕበራዊ እንቅስቃሴዎች ይገደቡ ነበር። ስለዚህም ሁለቱ ወራት መሰባሰቢያ እንጂ እንደ ልብ ከቦታ ቦታ የሚጓጓዙባቸው አልነበሩም።
ሕገ መንግሥታችን ለዚህን መሰሉ “የትናንት እውነታ” እስረኛ ለመሆን ፈልጎ ይሆን ወይንም ሌላ ምክንያት ይኑረው ባይታወቅም፤ የሕዝብ እንደራሴዎቹ “ክረምቱ ጫን ሳይልና ወንዞች ሳይሞሉ ወደየመጡበት የምርጫ ክልል በጊዜ እንዲሰበሰቡ አዝኖላቸው” የሚሸኛቸው ጥንት ከተለመደው “ባህል” መላቀቅ ቢሳነው ይሆንን ብለን መጠየቃችን አልቀረም። ከሆነ መቼስ ምን እንላለን። “ልማድ ከጅማት እንደሚበረታ” የታወቀ ስለሆነ የዘመናዊ መጓጓዣዎች መኖር ተዘንግቶ ስለሚሆን “ለምን?” ብለን አንሞግትም።
ምክንያቱ በርግጥም “እንደራሴዎቻችንን ከወንዞች ሙላት ለመታደግ ታስቦ ከሆነ” ተመልሰው ሲሰባሰቡ የአገሪቱ ሁነኛ በጀት በመንገድና በድልድይ ግንባታዎች ላይ እንዲውል አጥብቀው ሊሟገቱ ይገባል። ቢሆንልንማ ኖሮ የሚሻለው “ተወካዮቹ” በተፋፋመው የበጋ ወራት አርፈው ትምህርት ቤቶች በሚዘጉበት ወራት ሥራቸውን ቢከውኑ ኖሮ ብዙ ጠቀሜታ ይኖረው ነበር ብለን እናምናለን። እንዴታውን እናብራራ።
የፓርላማው ዓመታዊ የእረፍት ዝግ በበጋ ወራት ቢሆንና ዋነኛው ሥራቸው የነገይቱ ኢትዮጵያ ተረካቢ ወጣቶች ከትምህርት ገበታቸው ላይ በሚያርፉባቸው የክረምት ወራት ቢሆን መልካም ነበር። ልጆቻችን በክረምት ወራት በእረፍት ላይ ስለሚሆኑ የምክር ቤቱን ውሎና አዳር ሃሳባቸውን ሰብስበው በሚገባ ለመከታተል እድል ያገኛሉ። ስለ መንግሥታዊ አሠራሮችም ለመወያየትና ለመተቸት በእጅጉ ይመች ነበር።
ገፋ ካደረግነውም በየእርከኑ ባሉት የየአካባቢዎቻቸው መሰል የተወካዮች ስብሰባ (ክልል፣ ዞን፣ ወረዳና ቀበሌ) በታዛቢነት እየተገኙ “በነጋቸው” ላይ የሚሰጡ ሃሳቦችንና ውሳኔዎችን ቢከታተሉ፤ ከታዘነላቸውም “ተወካዮቻችን” ብለው “የመረጧቸውን እንደራሴዎቻቸውን” የሚሞግቱባቸው እድሎች ቢመቻቹላቸው ብዙ ጠቀሜታ ሳይኖረው አይቀርም የሚል ግምት አለን። በሌሎች አገራት ይህን መሰል “ባህል” የተለመደ መሆኑን ልብ ይሏል።
በተለየ ሁኔታ ግን እንደ በቀደም እለቱ በሚሊዮን ቁጥሮች የሚታወቁት ተማሪዎቻችን የዓመቱ የእንደራሴዎች የማጠቃለያ ስብሰባ በሚደረግበት እለት በወሳኝ የመጨረሻ ፈተና ላይ ስለሚሆኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩንና የወንበረተኞችን ውይይት ልብ ተቀልብ ሆነው ስለመከታተላቸው እርግጠኛ ለመሆን ያዳግታል።
ሕገ መንግሥቱ ክረምቱን ለእንደራሴዎች እረፍት የወሰነው “የመረጣቸውን ሰፊውን አርሶ አደር አግኝተው እንዲያወያዩ ታስቦ ነው” የሚል ምክንያት የሚቀርብ ከሆነም “ከገበሬው የግብርና ስራ ውጥረት ጋር እቅዱ አብሮ ይጎዳኛል ወይ?” ብሎ ሊያስጠይቅ ይችላል። ምክንያቱ ይህ ከሆነም እንደራሴዎቹ ከእረፍት ሲመለሱ ሪፖርታቸው ላይ ጫን ብለው ስለየአካባቢያቸው አርሶ አደሮች ስኬትና ጉድለት በሚገባ እንደሚወያዩበት ተስፋ እናደርጋለን።
የሰኔ ሠላሳ የእንደራሴዎቻችን ውሎና ትዝብታችን፤
የበቀደሙን የፓርላማ ውሎ ብዙው ሕዝብ የተከታተለው በልዩ ንቃት ነበር ማለት ይቻላል። ምክንያቱ ደግሞ ግልጽ ነው። ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይቀርባሉ ተብለው የተገመቱ በርካታ አገራዊ ጉዳዮች በሕዝብ አንደበት ሲጉላሉ መክረማቸው ነው። “ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህና በዚያ ጉዳይ ላይ ምን መልስና አስተያየት ይሰጡ ይሆን?” የሚለው የሕዝቡ ጉጉት የማጠቃለያ ስብሰባው በጉጉት እንዲጠበቅ ምክንያት ሆኗል።
በትልቅ ጉጉት ሲጠበቁ የነበሩት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ያለወትሯቸው ፈገግታቸውን ደብዘዝ አድርገው መታየታቸው በአብዛኞቹ ዜጎች ላይ ግራ የመጋባት ስሜት ሽው ብሎባቸው እንደነበር ብዙዎች ሲናገሩ ተደምጠዋል። ለመሪ ከሚሰጠው የአክብሮትና የመወደድ መገለጫዎች አንዱ አካላዊ ገጽታ እንደሆነ የሰለጠንበትና ለማሰልጠን ዕድል ያገኘንበት የኮሚዩኒኬሽን ዘርፍ (Nonverbal communication) ፍንጩን ይሰጠናል። ለማንኛውም ውይይቱ እየተሟሟቀ ሲሄድ ስሜታቸውም ፈታ ማለቱን ወደነዋል።
ከአሁን ቀደም የፓርላማውን ውሎ በተመለከተ ትዝብታችንን የገለጽንባቸውን አንዳንድ ጉዳዮች መለስ ብሎ ማስታወሱ ተገቢ ይመስለናል። በመሠረቱ ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚቀርቡት ጥያቄዎች አጭርና ግልጽ መሆን ይገባቸዋል የሚል እምነት አለን። ምክንያቱም የፓርላማውን ሰዓት መሻማቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ወንበረተኛ ያልሆኑ በርካታ ታዛቢ የአገር ውስጥና የውጭ ዜጎች እንዳሉ ልብ ማለቱ ግድ ይላል። በሌላ አንጻርም አንድ ጥያቄ ለማቅረብ ዙሪያ ጥምጥም መዞሩ በፍጹም ተገቢ ነው የሚል እምነት የለንም።
አንድን ጥያቄ ለመጠየቅ ወደ ኋለኞቹ ዘመናት ተንደርድሮ ታሪክ መተረክ፣ ነገሮችን ለጥጦ ማብራራቱ ለጊዜው መድረኩ ስለማይፈቅድ ቁጥብነት እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ይታመናል። ለምሳሌ፡- “የኢትዮጵያና የሱዳን ወቅታዊ ግንኙነት በምን ደረጃ ላይ ይገኛል? እንዲህና እንዲህ የሚል መረጃ ስላለን ጉዳዩን ቢያብራሩልን?” ብሎ መጠየቅ እየተቻለ አንድ እንደራሴ ያንን ሁሉ ታሪካዊ ዳሰሳ ለማድረግ ለምን እንደፈለጉ አልገባንም። ከዚህ በተቃራኒው አንዳንድ ጠያቂዎች ቅልብጭ ያለ ጥያቄ መጠየቃቸው የሚያስመሰግናቸው ስለሆነ ሊበረታቱ ይገባል።
ይህ ጸሐፊ ከአሁን ቀደም እንደገለጸው ቢያንስ በዚህ የተከበረ ፓርላማ ውስጥ እድል አግኝተው ወንበር የያዙ እንደራሴዎች ሊከራከሩና ሊሟገቱ የሚገባቸው በፌዴራል ደረጃ በተሰሩና በሚሰሩ አገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ እንጂ ለመጡበት የወረዳ ወይንም የዞን አለያም የክልል ምክር ቤቶች የሚቀርቡ ጥያቄዎች መጠየቃቸው አግባብ ይሆንን ? ለምሳሌ፡- የልማት ፕሮጀክቱ የፌዴራሉ ድርሻ መሆኑን እንኳን ሳይገልጹልን “ያ መንገድ፣ ያኛው ድልድይ፣ ያኛው ምንትስ” እያሉ ፓርላማውና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሊመለከቷቸው ሥልጣን ባልተሰጣቸው ጉዳዮች ላይ ጊዜ ማባከኑ ለጊዜው ይህንን ጸሐፊና መሰል “መራጭ ዜጎችን” ግራ ማጋባቱ አልቀረም።
አንድ የፓርላማ ወንበረተኛ አንድን ጉዳይ ለክርክር ወይንም ለግልጽነት ጥያቄ ወይንም አስተያየት ሲያቀርብ በቂ ጥናትና አጥጋቢ መረጃ ሰብስቦ መሆን አለበት እንጂ ለመጠየቅ ብቻ የሚጠየቁ የሚመስሉ ጉዳዮች ላይ ጥንቃቄ ቢደረግና ተደጋግመው የሚሰነዘሩ ጥያቄዎችን በተመለከተም ለወደፊቱ ቢታሰብበት አይከፋም።
“ጥያቄዬን በንባብ አቀርባለሁ”፣ “ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ጥያቄያችንን ለመመለስ በመሃላችን ስለተገኙ እናመሰግናለን” የሚሉ መሰል ተደጋጋሚ (ያውም ጥያቄ ለማቅረብ እድል ባገኙት ተወካዮች ሁሉ) የንግግር መቅድም አቤቱታዎች ጉዳይ ደጋግሞ ቢመከርበት ይበጅ ይመስለናል።
ቢቻል እንደራሴዎቹ ጥያቄያቸውን በቃል አሳጥረው ቢያቀርቡ፤ ካልሆነም በየትኛውም የአገራችን ቋንቋ ሊሆን ይችላል በአግባቡ ቢያነቡልን መልእክቱ ለእኛ ለተመራጭ ዜጎች ያለምንም መንገራገጭ ሊደርሰን ይችላል። የጠቅላይ ሚኒስትሩን መገኘት በተመለከተም በእንደራሴዎቹና በራሳቸው ስም አፈጉባኤው የመግቢያ ንግግራቸው ውስጥ አንዴ ካመሰገኑ በቂ ይመስለናል።
በተረፈ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን “ይህንን ሕግ ያጸደቀው ይህ ፓርላማ አይደለም!” የሚለው አስተያየት ለብዙ ዜጎች ግርታ እንደፈጠረ መሸሸጉ አስፈላጊ አይመስለንም። በየትኛውም የፓርላማ ዘመን የጸደቀ ሕግ እስካልተሻረ ድረስ ማን፣ መቼና እንዴት አጸደቀው ተብሎ የሚጠየቀው ለእውቀትና ለምርምር እንጂ የገዢነቱ ክብርማ እንደተጠበቀ መቆየቱ የታወቀ ነው።
በመጨረሻም የመረጥናቸው እንደራሴዎች ተገዥነታቸው “ለሕገ መንግሥቱ፣ ለሕዝቡና ለሕሊናቸው” እንደሆነ በግልጽ ስለተደነገገ ለአገርና ለሕዝብ የሚጠቅሙ በረከቶች ከወንበረተኞቹ መንበር እንዲፈልቁ የሚያንጹ አስተያየቶችን መስጠቱ ተገቢ ስለሆነ ይህንን ብለናል፤ ወደፊትም መባል የሚገባውን ቅድሚያ እየሰጠን ብዕራችንን እናተጋለን። ሰላም ይሁን !
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ሐምሌ 6/2014