ክፍል አንድ
የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 16ኛ መደበኛ ስብሰባውን ሰኔ 30ቀን 2014 አካሂዷል። በእለቱም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በምክር ቤቱ ተገኝተው ከአባላቱ ለተነሱላቸው ወቅታዊ ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ ሰጥተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡትን ማብራሪያና ምላሽ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ለንባብ አቅርበነዋል።
የተከበሩ አፈጉባኤ እንዲሁም የምክር ቤት አባላት ለምታነሷቸው ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት እድል ስለሰጣችሁኝ እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ።በመጀመሪያ በግፍ ሕይወታቸውን ላጡ ፤ ለተገደሉ ንጹሀን ዜጎች የሚሰማኝን ጥልቅ ሃዘን ለመግለጽ እወዳለሁ። እነዚህ ዜጎች ባልሰሩት ወንጀል በማይመለከታቸው ጉዳይ በአገራቸው በቀያቸው ሕይወታቸውን ለማሸነፍ እና ለማሻሻል ደፋ ቀና ሲሉ ባልተገባ መንገድ ሕይወታቸውን የሚቀጥፉ ገዳዮች አጥፊ ስብስቦች ያደረሱባቸው ጥቃት በእጅጉ የሚያሳዝን ከመሆኑም ባሻገር ሕይወታቸውን ለመታደግ ባለመቻላችን እንደ አገር ፣ እንደ መንግሥት እንደ ሕዝብ ጥልቅ ሃዘን ይሰማናል።
ኢትዮጵያ ቀደም ሲል በብዙዎቻችሁ እንደተ ገለጸው በአገሯ የሚገኘውን ችግር ሽብር ፣ ግጭት ብቻ ሳይሆን ሌሎች ወንድም የአፍሪካ አገራት የሚያጋጥሟቸውን ችግር ለመፍትት ጥረት ያደረገች እና የምታደርግ አገር ናት። ይህ ሆኖ ሲያበቃ አሁን ባለው አጠቃላይ ጂኦ ፖለቲካል ሁኔታ ኢትዮጵያ ውስጥ ለእናንተ ምን አልባት በየወሩ በየሳምንቱ ለእኛ ግን በየሰዓቱ በየደቂቃው መርዶ እና መርዶ የሚያስከትሉ ዜናዎች እንሰማለን።በዚህ ምክንያት የጸጥታ ተቋማት እና መንግሥት ይህን ነገር ለማስቀረት ከፍተኛ እርብርብ እያደረገ መሆኑን የምታውቁት ቢሆንም እስከመቼ? እስከመቼ ? እስከመቼ ? ላላችሁት የንጹሃንን ደም በከንቱ የሚያፈሱ የትኛውም ስብስብ ሸኔም ይሁን ሌላ አሸባሪ ኃይል፤ በጀመርነው መንገድ ጉዟችንን አጠናክረን የምንቀጥል ከሆነ ይጠፋሉ። አላማ የላቸውም፤ ግብ የላቸውም ፤ እሳቤአቸው ጥፋት ስለሆነ የእኛን ጉዞ ማደናቀፍ አይችሉም ።መፈተን ይችላሉ ።ፈትነዋል።ግን ማሸነፍ አይችሉም ።
እንዴት እንደዚህ ዓይነት ድርጊት ማስቀረት እንደምንችል በዝርዝር ወደኋላ ስለምገልጽ እስከመቼ የሚለውን በጥቅሉ የጥፋት እና የክፋት ኃይሎች ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያውያንን መግደል ፣ማጎሳቆል ፣መግፋት ፣ ማሸበር ይችሉ እንደሆን እንጂ ከዋነኛው አላማችን ሊያስቀሩን አይችሉም ፤ አይችሉም።
ይህም ሆኖ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረገው ግድያ አንዳንዶች እንደሚገልጹት በቸልታ ፣ መንግሥት ሥራውንም ስለማይሠራ፣ ኃላፊነቱን ስለማይወጣ ተደርጎ መወሰድ የለበትም። መንግሥት 24 ሰዓት የዜጎቹን ሕይወት ለመታደግ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋል። በዚህም በጣም በርካታ ሕይወት መታደግ ችሏል። ያመለጡ በዚህም የጠፉብን ዜጎች እንዳሉ እንደተጠበቀ ሆኖ ማለት ነው።
ይህን አንደኛ በሚፈጠረው ችግር ሁሉ ሕይወታቸውን የሚገብሩ የጸጥታ አካላት እንዳሉ መገንዘብ ተገቢ ነው። በቅርቡ የተከበረው ምክር ቤት የጸጥታው ተቋማት ኃላፊዎች መጥተው በዝርዝር እንደገለጹላችሁ በየቀኑ ፖሊስ ይሞ ታል ፤ በየቀኑ ወታደር ይሞታል። ደራሼ ላይ ብቻ በነበረው ግጭት ፖሊስ እና የወረዳው አመራሮች ከ80 ያላነሰ ሰው ሞተዋል። በጋምቤላ ሞተዋል፤ በደምቢዶሎ ሞተዋል፤ በጊምቢ ሞተዋል፤ በአሙሮ አካባቢ ጠላት ሊዋጉ እየሄዱ በገፍ ባልተገባ መንገድ ፖሊሶች ተገድለዋል።ወታደሮች የክልል ልዩ ኃይሎች ሕይወታቸውን ገብረው ዜጎቻቸውን ለመታደግ ጥረት ያደርጋሉ።
የተከበረው ምክር ቤት ማወቅ የሚገባው በየቀኑ እየሞተ ሕይወት የሚታደገው ፖሊስ የተለየ ጥቅም ያለው አይደለም።እጅግ ዝቅተኛ ክፍያ የሚከፈለው፤ ከሚከፈለው ክፍያ በተጨማሪ የሚሰማራበት አካባቢ ምቹ ባለመሆኑ፤አሁን ለምሳሌ ወለጋ 30 ፤ 40 ኪሎሜትር ጭቃ ውስጥ በእግር የሚጓዝ ፤ መሠረተ ልማት በበቂ ስሌለለ። ችግር አጋጥሟል በሚባልበት አካባቢ በእግር እየተጓዘ የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ ጥረት ይደርጋል።ይህ ሳይከፈለው አገሩን ወዶ እና አክብሮ ሕይወቱን የሚከፍለውን የጸጥታ ተቋም የተከበረው ምክር ቤት ክብር ሊሰጠው ይገባል።
እናንተ የጠፋውን ብቻ ስለምታዩ ምን አልባት ምን ያህል እንዳዳኑ ሙሉ መረጃ ላይኖራችሁ ይችላል።የእናንተ ልጆች ወጣቶች፣ ፖሊሶች አገራቸውን ስለሚወዱ ሕዝባቸውን ለመታደግ ከፍተኛ መሰዋዕትነት እየከፈሉ ነው።ይህ ነገር ተጠናክሮ እስከቀጠለ ድረስ የጥፋት ኃይሎች የኢትዮጵያን ጉዞ ሊያደናቅፉ አይችሉም።
ሽብርን በሚመለከት ሽብር አሁን ባለው ሁኔታ የጠቅላላው ዓለም ፈተና ነው። በኢንቫይሮሜንት ፈተና አለ፤ በኢንፍሌሽን እና ንግድ ትስስር ፈተና አለ፤ በግጭት ፈተና አለ።በግጭት ውስጥ ግን ሽብር የዓለም ሁሉ ፈተና ነው።ለኢትዮጵያ ተለይቶ የተሰጠ ፤ ኢትዮጵያ ላይ ብቻ ተለይቶ የሚከናወን አድርገን ማሰብ የለብንም።በዓለም አቀፍ መድረኮች እንደ ትልቅ አጀንዳ እያነሳን የምንወያይባቸው ጉዳዮች፤ ሽብር መልኩ ብዙ ለመከላከል አዳጋች በመሆኑ እንዴት ተባብረን የዜጎቻችንን ሕይወት ልንታደግ እንችላለን አጀንዳ ቀዳሚ ውይይት የሚደረግበት ነው ።ለምሳሌ በዓለም ላይ ጠንካራ ወታደራዊ እና የደህንነት ተቋም ያላት አሜሪካ ነች ።
በዓለም ላይ አሜሪካን የሚያክል ጠንካራ ሎው ኢንፎርስምንት ኤጀንሲስ የሚባል ትልቅ ሀብት የሚያንቀሳቅስ ፤ ትልቅ ቴክኖሎጂ የሚያንቀሳቅስ ሀገር የለም። አሜሪካ በኒዮርክ ያጋጠመውን የአሸባሪዎች ጥቃት ትተን በ2020 ዓ.ም አሜሪካ ውስጥ ቁጥር ከፍ ይላል በጣም ቀንሼ ነው የምናገረው ከ20 ሺ ሰው በላይ በሽብር ሞቷል። አሜሪካ ውስጥ ! የሞተው ህጻን ተማሪ በየቦታው መሳሪያ ይዘው በሚሄዱ አምስት ፤ አስር ሰው በሚገድሉ ሰዎች ከ20 ሺህ እጅግ ከፍ ያለ ሰው ሞቷል።
ባለፉት 6 ወራት ብቻ ከጃንዋሪ እስከ ጁን ሎሳንጀለስ በሚባለው ከተማ 172 ሰው ሞቷል። ሎሳንጀለስ ካውንቲ በሚባለው ብቻ ፤ ሎሳንጀለስ ስቴቱ አይደለም። ሎሳንጀለስ እና በአቅራቢያው ያሉ ከተሞች ብቻ 224 ሰው ሞቷል። ፍላደልፊያ ላይ በአለፉት 6 ወራት 257 ሰው ሞቷል። ዋሽንግተን ዋናው ከተማ 104 ሰው ሞቷል። በአካባቢው ያሉ ከተሞችን ሳይጨምር ማለት ነው። ኒዮርክ 197 ሰው ሞቷል።ችካጎ 300 ሰው ሞቷል። በጥቅሉ በአሜሪካ ባለፉት 6 ወራት በሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች በአሸባሪዎች ፤መሳሪያ ይዘው በሚገድሉ ሰዎች ሞተዋል።
አሜሪካ እና የአደጉ አገራት በመሳሪያ አንድ ሰዎች መኖር የለባቸውም ብሎ የሚያምን ግለሰብ ወይም ቡድን ሄዶ ከሚፈጀው ፍጅት ባልተናነሰ በዚህ ምድር ላይ መኖሬ ትርጉም አልባ ነው ብለው ራሳቸውን የሚገድሉ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ነው። ይህ የዓለም ችግር ነው። ራሱን የሚያጠፋ ሰው በርካታ መሆን፣ መሳሪያ ያላቸው ሰዎች ሄደው ተማሪዎችን ፣ ሴቶ ችን ፣ አቅመ ደካሞችን ፣ የአሜሪካ ችግር፣ የአውሮፓ ችግር የብዙ አገራት ችግር ነው ፤ የኢትዮጵያም እንደ ዚሁ።
ስፔሻል ነገር ኢትዮጵያ ላይ ብቻ ያለ፣ የኢትዮጵያ የጸጥታ ተቋማት ሊከላከሉት ያልቻሉት አይነት እንድምታ መያዝ የለበትም።በቅርቡም ብሪክስ በጠራው ስብሰባ ላይ አንዱ ንግግራችን አሸባሪነት በሁሉም የዓለም ቀጠና ፈተና እየሆነ ስለሆነ እንዴት በጋራ ተባብረን ልንገታው እንችላለን? የሚል ምክክር ነው የነበረው።ከምንመካከረው ውስጥ ምን ያህሉን በትብብር እንሰራለን የሚለውን ጥያቄ ውስጥ እንደገባ ሆኖ ማለት ነው ።
አሸባሪዎችን ከዘር ጋር ብቻ ማያያዝም ችግር አለበት። ነገርየውን በቁንጽል እንድናይ ነው የሚያደርገን ። ለምሳሌ አልሻባብ መቶ ፐርሰንት ባይባልም አብዛኛው የአልሻበብ አመራር እና አባል ሶማሌዎች ናቸው። በእምነት ሙስሊም ናቸው ።በዘር ሶማሊዎች ናቸው። በቋንቋ አብዛኛዎቹ ሶማሊኛ ይናገራሉ።ነገር ግን በሶማሊ ውስጥ በኬንያ አልፎ አልፎም ኢትዮጵያ በሚያደርጉት ሙከራ እስካሁን አልሻባብ ከገደለው አብዛኛው ሰው ሶማሊዎች ናቸው ።
አልሻባብን ለማጥፋት የአሜሪካ መንግሣት የኬንያ መንግሥት ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ፣ የሶማሌ መንግሥት የሌሎች አገራት መንግሥታትም በትብብር ለአለፉት 10 አመታት እየሰራን ነው። የብዙ አገራት ወታደር ሶማሌ ውስጥ አሉ። ነገር ግን ሞትን ዜሮ ማድረግ አልቻልንም። ከጅቡቲ እየተነሳ አሜሪካ በአየር ድጋፋ እያደረገ ቢሆንም ፤ በምድር ላይ በርካታ የአፍሪካ አገራት ወታደሮች ቢኖሩም አልሻባብን ይህ ሁሉ አገር ተባብሮ ሊያስቆመው አልቻለም።ሽብርን በደንብ መገንዘብ ያስፈልጋል።
በምዕራብ አፍሪካ በተለይም ናይጀሪያ ቦኮሃራም የሚያስከትለውን ችግር ታውቃላችሁ። ናይጀሪያ በሕዝብ ቁጥርም በሀብትም ከኢትዮጵያ የምታንስ እና እንደዚያ አይነት አሸባሪን መከላከል የማትችል አገር ሆና ሳይሆን የሽብር ባህሪው ፤ የሚከተለው የጥፋት ስልት ልክ ቲፒኤልኤፍ ጋር በመጀመሪያ በነበረው ውጊያ ግንባር ለግንባር እንዳደረግነው አይነት አድርጋችሁ አትውሰዱት ።መጨረሻ መቀሌን ከተቆጣጠርን በኋላ ጠላት በሕዝቡ ውስጥ ተሰግስጎ እና ተደብቆ የነበረበት ያሳለፍነው ስምንት ወራት አይነት ባህሪ ማለት ነው ።
ቦኮሃራም ናይጀሪያን እና ምዕራብ አፍሪካን ይፈትናል ፤ አልሻባብ ምሠራቅ አፍሪካን ይፈትናል ፤ ሌሎቹ አሸባሪዎች እንዲሁ በተለያየ ቀጠናዎች ይፈትናሉ።ለምሳሌ የመን ላይ ሁቲ የተባለው ሽብር ቡድን በኢኮኖሚም በወታደርም ሻል ያለ አቅም ያላቸው አገራት የመን ግብተው በርካታ ሥራዎችን ሊሠሩ ሞክረው ሁቲን አላጠፉትም።
በቅርቡ ሁላችሁም እንደምታውቁት ሁቲ ወደ አቡ ዳቢ ኤርፖርት ሮኬቶችን ሚሳኤሎችን እየላከ ጥቃት ፈጽሞ ነበር።ሁቲ በማንኛውም መመዘኛ ከዩናይትድ አርብ ኤምሬት መከላከያ እና የደህንነት ተቋማት ጋር ሊነጻጸር አይችልም ። ከየመን አቡዳቢ ደርሶ ማጥቃት የቻለው በራሱ ብቻ ቆሞ አይደለም።
በድምሩ ሸኔ እና ሌሎች የሽብር ቡድኖች የራሳቸው እግር የላቸውም። እግር የሚገጥምላቸው ሰው ሲያገኙ ሮጠው ያጠፋሉ።የራሳቸው ማሰቢያ ጭንቅላት የላቸውም። ታስቦ የጥፋት ሥራ ሲሰጣቸው ጥፋት ያካሂዳሉ። ለምሳሌ በቅርቡ የተፈጸመውን በደል ብንወስድ በእኔ መመዘኛ እና በእኔ እሳቤ ከወሎ በ1977 ዓ.ም ወደ ወለጋ የሄዱ ሰዎች የ5 ዓመት ፣ 6 ዓመት ልጅ ሄዶ ቢሆን ዛሬ 40 አጋማሽ ጎልማሳ ሰው ነው ።ወሎ ይወለድ እንጂ ፤ አራት አምስት አመት ይቆይ ፤ይህ ሰው ከ30 ዓመት በላይ የኖረው፣ ያደገው ፣ የተማረው፣ ያገባው ፣ የወለደው፣ ያረሰው ፣ ያመረተው አሁን ባለበት አካባቢ ነው ።
ሰው ደግሞ እንደምታውቁት ሰው ነኝ አገሬ የሚለው የሚጠራውም ተራራ ፣ የሚጠራውም ወንዝ የዋኘበትን የተጓዘበትን አስቦ ነው። እነዚህ ግለሰቦች በአምስት፤ በስድስት አመታቸው ከውልደት ቦታቸው የሄዱት ሰዎች በአካባቢያቸው ብዙ የሚተርኩለት፤ የሚናገርሉት ነገር የላቸውም። ያደጉበት የኖሩበት አገራቸው አሁን ያሉበት ነው።
እነዚህን ሰዎች በግፍ መግደል ምንም ዓይነት የፖለቲካ ዓላማን ሊያሳካ አይችልም።የፈለገ የሽብር ቡድን ተገቢም ባይሆን በዚያ መንገድ ማሰብ ከወታደሩና ከፖሊሱ ጋር መጋፈጥ፣ መጋደል ተገቢም ባይሆን ይሻላል።ንፁሃን ዜጎችን በዛ መንገድ ማጥፋት የሽብር ባህሪ ፤ ኢትዮጵያን ለመበተን ለማፍረስ የሚፈልጉ ኃይሎች መሻትን በገሃድ የሚያሳይ ነገር ነው። እኛ ጋር ያለው ችግር ምንድን ነው? መንግሥት የሕዝቡን ሰላም ማስከበር ቀዳሚ ተግባሩ ነው ብላችኋል።እውነት ነው። ሕዝብም የመረጠውን መንግሥት የማድመጥ እና የማገዝ ቀዳሚ ተግባሩ ነው።
መንግሥት ፖሊሲ ሲቀርፅ፤ መረጃ ሲሰጥ ሃሳብ ሲሰጥ፤ ሁሉም የሚያደምጥና የሚከተል ከሆነ ብዙውን ነገር ልናስቀር እንችላለን።አሁን አድማጭ የለም።ሁሉ አቅጣጫ ጠቋሚ ብቻ ነው።ባለው ውስን መረጃ ላይ ባለው ውስን ዕውቀት ላይ ቆሞ፤ በዚህ መንገድ መሆን አለበት የሚል ብቻ ነው የበዛው። ይህ ወደፊትም የበለጠ ኪሳራ እንድናስተናግድ ያደርገናል። አንደኛ ሽብርን መገንዘብ ያስፈልጋል።ሁለተኛ ከፋም ለማም መንግሥት ከእናንተ በተሻለ፤ ከዜጎች በተሻለ የሽብርን እንቅስቃሴ መረጃ እንደሚያገኝም ማሰብ ጠቃሚ ነው።
በቅርቡ እንዳያችሁት የመከላከያ እና ደህንነት ተቋማት ባለፉት አስራ አምስት እና ሃያ ዓመታት ከነበሩበት በእጅጉ የተሻለ ቁመና ይዘዋል።አይታችኋል ከትናንትና በእጅጉ የተሻለ ቦታ ላይ ናቸው። ሕዝቡ አላየም እናንተ ግን አይታችኋል። ቅድሚያ ሰጥተን ሎኢንፎርስመንት ኤጀንሲን እንደተቋም ማጠናከር ያስፈለገው፤ ለምንድን ነው? ያላችሁን እንደሆነ የሽብር ኃይሎች በተቀናጀ መንገድ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ያላቸውን ፍላጎት እና መሻት ስለምናውቅ ነው። አሁን በቅርቡ ዛሬ አሶሳ ላይ ፕላን አላቸው።በዚህ ሳምንት ውስጥ አዲስ አበባ ውስጥ ከስድስት ጊዜ በላይ ፕላን ከሽፏል።
በርካታ ሰዎች ሰልጥነው ይገባሉ።ሙስሊም አገር ሰላም ነው ብሎ አረፋ ሊሰግድ ሲወጣ ሙስሊም ነኝ ብሎ ጀለቢያ ለብሶ ቦምብ ይዞ ሊገባ የሚዘጋጅ ኃይል ብዙ ነው። የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል ምንም ያክል ለማጠናከር ሙከራ ያደረግን ቢሆንም እንደምታውቁት 100 ሚሊዮን ወታደር የለንም። ዜጎቻችን መቶ ሚሊዮን ናቸው። ለእያንዳንዱ ዜጋ አንዳንድ ወታደር ማስቀመጥ አንችልም።እዚህ ጋር ስንጠብቅ በሌላ በኩል እዚህ ጋር ያልፋል።እየመጣ ያለው ቀይ ወይም ሌላ የተለየ መልክ ያለው አይደለም።በየቦታው የሚሽሎከለከው እኛን የሚመስል የእኛን ቋንቋ የሚናገር ሰው ነው። የመንግሥት ቀዳሚ ተግባር ነው ትክክል ነው። የሕዝብም ቀዳሚ ተግባር ነው። ተሰናስሎ አገርን መታደግ ያስፈልጋል።
ከሳሽ ጠያቂ ብቻ ሳይሆን ኃላፊነት የሚወስዱ ዜጎችም ያስፈልጋሉ።ቅድም ባነሳሁት በምዕራቡ ዓለም ሲኒየር ዜጎች፤ ሥራቸውን አገባደው በጡረታ ላይ ያሉ ዜጎች አካባቢያቸው ላይ ተቀምጠው ዋና ሥራቸው አዳዲስ ነገር ሲያዩ ለመንግሥት ያመለክታሉ። ሳይከፈላቸው ይጠብቃሉ።አሮጊቶች ሽማግሌዎች በአካባቢያቸው ሲንቀሳቀሱ አዲስ ምልክት ካዩ ለመንግሥት ሪፖርት ያደርጋሉ።አልቃይዳ ትዩዩ ህንፃዎችን ኒዮርክ ላይ ሲያፈነዳ ሚስቱ ልጁ ወንድሙ የሞተበት የአሜሪካ ዜጋ ከመንግሥታችን ጋር ሆነን አሸባሪዎችን እንፋረዳቸዋለን ይላል።ቅድም ያነሳሁት በየትምህርት ቤቱ ህፃናት ይገደላሉ።መቼም ልጁ ሲሞት የማይሸበር ሰው የለም ነገር ግን እየተሸበረም ቢሆን ከመንግሥቴ ጋር ሆኜ ይህንን ሕገወጥ ገዳይ እፋረዳለሁ ይላሉ።እኛ ጋር ደግሞ ሰው በሞተ ቁጥር ይሔ መንግሥት ይባላል።ይሔ ትክክል አይደለም፤
መንግሥት አሸባሪ አይደለም።አሸባሪን የሚፋለም ኃይል ነው። በየቀኑ ከአሸባሪ ጋር ሲፋለም የሕይወት መስዋትነት የሚከፍል ኃይል ነው።የሕዝብ ሥራ አሸባሪውን ከለየ በኋላ ከመንግሥት ጎን ቆሞ ጥፋት እንዲቀነስ ማድረግ ነው።ለዚህ ደግሞ ያለው ችግር ምንድን ነው? ከተባለ የኢትዮጵያን ፈተና የምናይበት ፈርጅ መለያየቱ ነው።
የኢትዮጵያ ፈተና የተሰባበረ ብዙ ፐርስፔክቲቭ ያለበት ቢሆንም የተከበረው ምክር ቤት በሁለት ማዕቀፍ ቢያየው መልካም ነው።አንደኛው ኢትዮጵያ ለዓለም ያላት አስተዋፅኦ፤ እኛ ኢትዮጵያውያን እንደምናስበው አለመሆኑ ችግር ፈጥሮብናል።ለምሳሌ ቀደም ብዬ የአሜሪካን አካባቢ ያነሳሁት ችግር አሜሪካን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ይህንን ነገር በደንብ ያውቃሉ። በየቀኑ በየከተማዎቻቸው የሚፈፀመውን ድርጊት ያውቃሉ።ሁለት ችግር አለባቸው። በአንድ በኩል በአሜሪካን እና በአውሮፓ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ስለኢትዮጵያ የዕለት ኑሮ ሲሰሙ ኢትዮጵያ ውስጥ ምንም እንቅስቃሴ ያለ አይመስላቸውም። ምንም ዓይነት ሥራ እየተሠራ ያለ አይመስላቸውም።
በየቀኑ ወንድሞቻቸው እና እህቶቻቸው እያለቁ እንደሆነ የሚያስቡ ጦርነትና መርዶ ብቻ ይሰማሉ። በጣም የሚጨነቁ ቤተሰቦች አሉ።ራቅ ብሎ መስማት እና እንደናንተ ቀረብ ብሎ ማየት ጉዳዩ ለየቅል ነው። ከዚህ አንፃር በውጪ አገር ላሉ እና ራቅ ያሉ አገር ያሉ ዜጎች ማድረግ ያለባቸው አቅም በፈቀደ መጠን እየመጡ ማየት ነው።የሚባለው እና ያለውን ማየት ያስፈልጋል።በአብዛኛው የሚባለው ክፉ ክፉ ስለሆነ ያ የበለጠ እንዳያራርቅ በተጨባጭ መሬት ላይ ያለውን ነገር ማየት እና የራስን ፍርድ መስጠት ያስፈልጋል።
ሁለተኛ ጥፋት ሲካሔድ ካሉበት አገር አንፃር ልምድ እየወሰዱ፤ በእነርሱም ከባቢ መሰል ችግር እንዳለ፤ ግን ያንን ችግር ለመከላከል መንግሥት እና ሕዝብ እንዴት እንደሚሠሩ ማስተማር ይጠበቅባቸዋል።ያ ሲሆን በጣም ጠቃሚ ግብአት ይገኝባቸዋል።ቀደም ብዬ እንዳነሳሁት ኢትዮጵያ ለዓለም ያላት አስተዋፅኦ እና ኢትዮጵያ ለማደግ ያላት ዓቅም ዕድልም ፈተናም አለው።
ለዓለም ያላትን አስተዋፅኦ በአራት ከፍለን እንመልከተው።አንደኛው ታሪካዊ ነው።እኛ ኢትዮጵያውያን በሚያጣላን ታሪክ ላይ ብዙ ጊዜ የምናጠፋ ቢሆንም በዓለም ታሪክ እንየው ሲባል ግን ኢትዮጵያ የሥልጣኔ መነሻ ናት የሚለው ከሞላ ጎደል የሚያግባባ ነው።ወይም የሥልጣኔ መነሻ ከሆኑ ጥቂት አገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ናት የሚለው የሚያግባባን ነው። ይሔ ለእኛ የረከሰብን ነው እንጂ፤ አሁን ያደጉ ብዙዎቹ አገራት እንደዚህ ነው ብለው የሚናገሩት ታሪክ የላቸውም። የስልጣኔ መነሻ ብቻ አይደለም፤ ኢትዮጵያ የሰው ልጅ መገኛም ናት።ስለሰው ልጅ መነሻ ስናካሂድ ኢትዮጵያን ማየት መዳሰስ የግድ ነው።ስለስልጣኔ መነሻ ስናስብ ኢትዮጵያን ማየት ግድ ነው ብሎ በታሪክ ውስጥ ከፍ ያለ ቦታ እንድንይዝ ያደርገናል።
ከዚህ ባሻገር ከ50 ሺ በላይ ጥንታዊ መፅሐፍት በተለያዩ የዓለም ቤተመዛግብት እና ቤተመፃሕፍት ይቀመጣሉ።ከመቶ ሺህ በላይ የኢትዮጵያ ቅርሶች በዓለም ላይ ይኖራሉ።ቅርሶች አሉ፤ ጥንታዊ ፅሑፎች አሉ።በዚህ ምክንያት ሰው ታሪክ እና ትናንትናን ሲመለከት፤ የኢትዮጵያ ቅርስ በእርሱ ቤተመፅሐፍት ስለሚገኝ፤ የኢትዮጵያ መፅሐፍት በእርሱ ላይብረሪ ስለሚገኝ የኢትዮጵያን ነገር ቸል ብሎ ማየት ይቸገራል። ወደዚህ ደግሞ ከመጣ ተጨባጭ ነገር አለ። ላሊበላን ያያል።ዓለምን ቢዞሩ ላሊበላን ማየት አይቻልም።ሶፍዑመርን ያያል፤ ዓለምን ቢዞሩ ሶፍዑመርን ማየት አይቻልም። ትልቅ የስልጣኔ አሻራ ነው።አክሱምን ያያል።
እነዚህ በየቦታው ያሉ ተጨባጭ ነገሮች ኢትዮጵያ በተፃፈ ብቻ ወይም በቅርፅ ብቻ ሳይሆን አገሯ ላይ ሲገኙ የሚጨበጥ የሚዳሰስ ነገር እንዳለ ያሳያል። ይህን ለማወቅ የተከበረው ምክር ቤት ለአንዳንድ ሥራ ስትንቀሳቀሱ ወደ ሌሎች አገሮች ስትሔዱ ያደጉ የተሻለ አስፓልት የተሻለ ፎቅ ያላቸው አገራት ብትሔዱ በዛ ልክ እድሜ ጠገብ የሆኑ ነገሮችን ማግኘት አትችሉም። ይህ ታሪክ ለእኛ ረከሰብን እንጂ ለዓለም አልረከሰም።
ስለፅሑፍም አንስቶ ዓለም ቢነጋገር በዓለም ላይ 18 አገራት ብቻ ናቸው የራሳቸው ፊደል ያላቸው። ከእነርሱ ውስጥ አንዷ ኢትዮጵያ ናት የሚለው ጉዳይ ወይም በአፍሪካ ብቸኛዋ ኢትዮጵያ ናት የሚለው ጉዳይ ከታሪክ አንፃር ቀላል ቦታ የሚሰጠው አይደለም።ይህንን ታሪክ እንዲጠፋ እንዲንኳሰስ የሚፈልጉ ኃይሎች ቀላል አይደሉም። ምክንያቱም ሀብት ከታሪክ ጋር ይያያዛል።ለምሳሌ በእኛ አገር ሰዎች ድንገት ሀብታም ሲሆኑ አሁን አሁን እየቀረ ነው እንጂ ሰዎች ድንገት ሀብት ሲይዙ የቤተሰባቸው ዘር እየተነሳ ይንቋሸሻል፤ ታውቃላችሁ። ይሔ ማታ ማታ የሚጋልብ ነው።ይሔ ሀብት እያመጣ ያለው በዚህ መልክ ነው ሲባል ታውቃላችሁ። ያለው ሀብት ይራከሳል።
ሀብት በየዘመናቱ እያደገ የሔደባቸው ሀብታሞች እና በሆነ ጊዜ ድንገት ሀብታም የሆኑ ሰዎች እኩል አይደሉም። በእኛ አካባቢ በድንገት ሀብታም የሆኑ ሰዎች ድሃዎች እንኳን አንጋባም ፤ ልጃችንን አንድርም ይላሉ፤ ይጠየፋሉ።እንደትክክለኛ የሀብት ምንጭ አይወስዱም።ታሪካቸውን አንቋሸው አንጋባም ይላሉ።ይህ በግለሰብ ደረጃ ነው።ይሔ በአገር ደረጃም ቢሆን ሀብት ብቻውን መጥቶ ታሪክ አልቦ ሲሆን ያስቸግራል።ትናንት የሌለ ነገር ሲሆን ያስቸግራል። ይሔን ከታሪካዊ ጉዳይ ጋር ያለው የኢትዮጵያ ጉዳይ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የተከበረው ምክር ቤት በደንብ ሊያጤነው ይገባል፡፡
በ17ኛው ክፍለ ዘመን ጀምስ ብሩስ የተባለው ሰው ኢትዮጵያን መጥቶ ካሰሰ በኋላ አስራ አምስት ግመል ሙሉ ጭኖ የሔደው ጭኮ አይደለም።የገብስ ቆሎ አይደለም፤ ውሃ አይደለም፤ ታሪክ እና ቅርስ ነው፤ መፅሐፍት ነው ጭኖ የሔደው።አፍሪካ ውስጥ ለምናደርገው ነገር ይህች ታሪክ ጠገብ አገር መዳከም አለባት ብሎ የሚያስበው ኃይል ቀላል አይደለም። ዕድልም ነው፤ ፈተናም ነው። ከዚህም ባሻገር ታሪክን አስታከን ብዙ ነገር ልናነሳ እንችላለን።
ሁለተኛው ተፈጥሯዊ ሀብት ነው። አትርሱ አልተገዛንም፤ አውጥተን ባንጠቀምበትም ስላልተገዛን እንደተገዙ አገራት አልተበዘበዝንም።የተፈጥሮ ሀብት ሲባል አንደኛው የአየር ንብረት ፤ አሁን እዚህ ኢትዮጵያ የምታዩት አዲስ አበባ የምታዩት አየር እኛ ጎረቤት አገራት ብትዞሩት አታገኙትም፤ የለም። ይሄንን የአየር ንብረት ለፍተኝ ያመጣነው ባይሆንም በተፈጥሮ ያገኘነው ፀጋ ነው። ንፁህ ውሃ ዝናብን ጨምሮ እኛ የምናገኘው ንፁህ ውሃ ሩቅ አይደለም። በቅርብ ጎረቤት አገራት እንኳን አያገኙትም።
በዓለም ላይ ሰፋፊ ወንዝ ጅረት የሚጠጣ ንፁህ ውሃ ያላቸው አገራት ጥቂት ናቸው።ከእነርሱ ውስጥ ኢትዮጵያ አንዷ ናት። ለም መሬት ሰፊ ሊታረስ የሚችል ለም መሬት አላት። በጣም በርካታ የዱር አራዊት አሏት።እነዚህ ሁሉ እኛ እንብዛም ግምት የማንሰጣቸው በዓለም ላይ ግን ብዙ ትርጉም ያላቸው ናቸው። ዕፅዋትን እንኳን ብንወስድ በዓለም ላይ ከ60 ሺ የማይበልጥ ዝርያ አለ ይባላል።ከዚህ ውስጥ ከስድስት ሺህ እስከ ሰባት ሺህ ዝርያ ከኢትዮጵያ የተወሰደ ወይም ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝ ብቻ ነው።በዕፅዋት ዝርያ እንኳ ከዓለም ያለንን ድርሻ ተመልከቱ፤ ይህ የተፈጥሮ ሀብት ካለው የሕዝብ ቁጥር ጋር ተያይዞ እያደጉ ከሔዱ ምን ሊፈጥሩ ይችላሉ? የሚል ስጋት የሚያሰጋቸው ቡድኖች ቀላል አይደሉም።
ሦስተኛው ፖለቲካ እና ዲፕሎማሲ ነው። ቀደም ሲል የተከበሩ የምክር ቤት አባል እንዳነሱት እኛ ያልተገዛን ነፃ አገር ነን። ነፃ ያልተገዛን አገር ነን ማለት ተራ ንግግር አይደለም። በብዙዎች አጥንት ደም የተገኘ ድል ነው። ብዙዎች ማሳካት አልቻሉም። በዓለም ጫፍ እስከ ጫፍ በኤዢያም፣ በአሜሪካም በአፍሪካም ቢኬድ፤ አሁን አደጉ የሚባሉ አገሮች ሳይቀሩ በሙሉ የተገዙ ናቸው። ያልተገዛን መሆናችንን ደጋግመን የምናወሳው ብቻ ሳይሆን በፖለቲካ እና በዲፕሎማሲው ትልቅ ቦታ የሚያሰጠን ነው።
እኛ ያልተገዛን መሆናችን ብቻ አይደለም።አገራት እንዳይገዙ ያደረግነው አስተዋፅኦ ቀላል አይደለም። አሁን ነፃ የወጡ የአፍሪካ አገራት ብዙዎቹ እኛ አገር የሰለጠኑ ናቸው። በተደጋጋሚ የደቡብ አፍሪካው የአፓርታይድ ትግል እና የአፓርታይድ መሪ ሚስተር ማንዴላ ኢትዮጵያ ውስጥ እዚሁ ኮልፌ መሰልጠናቸውን ሰምተናል።ግን ይሄ በፖለቲካ ነው። ከፖለቲካ ውጪ አቶ ይድነቃቸው ተሰማ የኳስ ፌዴሬሽንን ሲመሩ እነዚሀ እንደአፓርታይድ ያሉ የአፍሪካ ሕዝቦችን የሚጨቁኑ አገራት በዓለም የእግር ኳስ መድረክ ላይ እንዳይገኙ እና እንዳይሳተፉ የነበራቸው አስተዋፅኦ እጅግ ከፍተኛ ነው።
መንግሥታት ብቻ ሳይሆኑ ግለሰቦች እን ኳን በዓለም መድረክ ዕድል ሲያገኙ ለሌሎች ወንድሞቻቸው ነፃ መሆን በእጅጉ ተጋድሎ አድርገዋል።ታንዛኒያ የምትባል ምሥራቅ አፍሪካ ውስጥ አንድ አገር አለች።ታንዛኒያ ከኮሎኒያሊዝም ነፃ ስትወጣ፤ ጎረቤት ሞዛምቢክ በፖርቹጋል ተይዛ ነበር። ይህንን የማወራችሁ የዛሬ 60 እና 70 ዓመት የነበረ ታሪክ ነው። ታንዛኒያ ነፃ ከወጣች በኋላ፤ ታንዛኒያ የአየር ክልሏን መጠበቅ አትችልም። ሞዛምቢክ ያለው የፖርቹጋል የአየር ኃይል (ኤር ፎርስ) በታንዛኒያ የአየር ክልል እየሔደ በምድር ባይገባም በአየር ላይ ሲመጣ ይሰጋሉ፤ ይሸበራሉ።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል አንድ ቡድን (አንድ ስኳድ) ልኮ በኢትዮጵያን አብራሪዎች ለወራት የታንዛኒያን አየር ክልል ጠብቀዋል።ይህንን ያደርጉ ሰዎች አንዳንዶች አሁንም በሕይወት አሉ።የታንዛኒያ ነፃነት ሲወራ የአየር ክልሏን የጠበቀ አገር እንዳለ ሳይወሳ ሊያልፍ አይችልም። ታሪክ ስለሆነ።ፖለቲካ ውስጥ ዲፕሎማሲ ውስጥ በአፍሪካ ጉዳይ ስንነጋገር እኛ ነፃ ሳትወጡ ብዙ የረዳናችሁ ናችሁ ብለን በስልጠና በዚህ ብለን የምንጠቅሳቸው ብዙ ታሪኮች አሉ።ያኔ ታንዛኒያ ኢትዮጵያውያን ሲሔዱ ሰዎቹ ጥቁር አብራሪ አይተው ስለማያውቁ ኢትዮጵያውያን በየቀኑ ለአየር ፍተሻ በሚነሱበት ሰዓት በርከት ያለ ሕዝብ ወጥቶ ያያቸው ነበር። ጥቁር አየር የሚያበር አለ ብለው ለማየት ማለት ነው።እናም በአፍሪካ ውስጥ የነበረን ሚና ቀላል አልነበረም።
ከዛም ሲሻገር ቀደም ሲል እንደገለፅነው በአፍሪካ ሊጎፍኔሽን መስራች ብቸኛዋ አገር ኢትዮጵያ ናት።አፍሪካ ዩኒየንን ከመሰረቱ ሦስት አገራት መካከል ኢትዮጵያ አንደኛዋ አገር ናት። ከአፍሪካ ውጪ ኮሪያ በነበረው የእርስ በእርስ ጦርነት የኢትዮጵያ ጦር ኮሪያን ለመታደግ መስዋትነት ከፍሎ ታሪክ የሰራ መከላከያ ነው ያላት።በኮንጎም በነበረው ብዙ የአፍሪካ አገራት በማይታሰቡበት ጊዜ፤ ኢትዮጵያ የኮንጎን ሰላም ለማስጠበቅ ትልቅ ተጋድሎ አድርጋለች።ይሔ ታሪክ ነው።በዲፕሎማሲው በፖለቲካው የሚወሳ ነገር ነው።እንደነዚህ ዓይነት ነገር በርካታ ልናነሳ የሚገባቸውን ነገሮች ብዙዎች አያነሱትም።
ከፖለቲካ ውጪ በማህበራዊ ደግሞ ስንወስድ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ኢትዮጵያውያን እምብዛም ዋጋ ያልሰጠነው ከፍተኛ ማህበራዊ ግንኙነት (ሶሻል ካፒታል) አለ። ሰው ሞቶ፤ ሰው ለመቅበር ሰልፍ የሚያጨናንቅ አገር ብትፈልጉ ኢትዮጵያ ነው።አንድ አዛውንት ሞቶ፤ አዛውንቱን በክብር ለመቅበር፤ ታክሲ የሚችል ታክሲ፤ መኪና የሚችል በመኪና ያልቻለ በእግሩ ከክፍለ አገር ወደ ክፍለአገር ሔዶ ለቀብር የሚሰለፍበት አገር ኢትዮጵያ ነው።ይሔ ለእናንተ ቀልድ ተደርጎ መታየት የለበትም።አሁን ያደጉት አገር ጋር ብትሔዱ አባት እና እናት ሲታመሙ ጊዜ የለኝም ነርስ ያስታማቸው፤ ከተባለ በኋላ ሲቀበሩ፤ አሁን ያለው ዝንባሌ ለመቅበርም ጊዜ የለንም መንግሥት ይቅበራቸው የሚል ትውልድ ያለበት ነው።እናትን፣ አባትን ማስታመም አለመቻል ብቻ ሳይሆን መቅበር የማይችሉ፤ ነገር ግን ብር ያላቸው ፎቅ ያላቸው አገራት በዝተዋል።ይሔ እኛ አገር ስላለ እንዳናራክሰው፤ እነዛ አገራት በጀት በጅተው ሚኒስትሪ አቋቁመው ፕሮፖጋንዳ ሰርተው፤ እባካችሁን ወደ ቀደመው እንመለስ ማህበራዊ ግንኙነት እናምጣ ወሳኝ ነው ቢሉም አይሳካላቸውም፤ ተበላሽተዋል።
ግለኝነት ጥግ ስለደረሰ ሰው ከራሱ አልፎ እናቱን እና አባቱን የሚሸከምበት ማንነት ጠፍቷል። ይሔ ግን እኛ ጋር አለ። ይህ ሲባል ተራ ነገር አይደለም። ልክ በሞት ላይ እንደምንረባረበው በነፃነት ጉዳይ ላይም እንረባረባለን ማለት ነው።ከዚህ ቀደም ስም አልጠቅስም፤ ከፍተኛ ተጋድሎ አድርገው አገራቸውን የጠበቁ አገራት፤ ሁሉም ዜጎቻቸው ወታደር የነበሩባቸው አገራት፤ አሁን ወታደር ሁኑ ሲባሉ፤ አይ ወታደር ለምን ከአፍሪካ አትቀጥሩም እያሉ ነው። አገራቸውን ለመጠበቅ ማለት ነው፡፡
እኛጋ ያሉ ሀብቶች የሁሉ ነገር መመዘኛ ከውጪ የምንሰማው ስለሆነ እኛ አገር ያለው አይታየንም። ብር እና ፎቅ የሆነ ቦታ አለ፤ የዕድገት፣ የብልፅና መገለጫ ደግሞ እርሱ ብቻ ነው ተብሎ ይወሰዳል።ነገር ግን እርሱ ብቻ አይደለም። ለምሳሌ ዕቁብ ምንም አይነት ህግ ሳይኖር በአንድ ሰፈር የሚኖሩ ሰዎች ተማምነው በእቁብ በየሳምንቱ አንተ ውሰድ አንተ ውሰድ እየተባባሉ ለወራት የሚቆይ ነገር ያደርጋሉ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ። ይሔ ቀላል ነገር አይደለም። ዕድር አንድ ሰው ሲሞትበት ከማስቀበር ጀምሮ ምግብ ሳይሰራ ኩሽና ሳይገባ ጎረቤት እየሔደ ያስተናገደ አገር ኢትዮጵያ ነው።
ይሔንን ሌላ አገር ይኖራል ብላችሁ እንዳትገምቱ። ሌላ አገር ደሕና ሰው ከሞተ እና ቀብር ከተኬደ ነጭ አበባ ተይዞ ተሂዶ ተጥሎ ወደ ቤት ይኬዳል እንጂ መንጋት የለም።ከቀበረ በኋላ ሰውየው ከፍሪጅ አውጥቶ አሙቆ መብላት አለበት። ይሔ አይርከስብን ብዙዎች ጋር የሌለ ነገር ነው። የቤተሰብ ሥርዓት፣ ታላቅ ማክበር ብዙዎች የኛዎቹ እንደዚህ አይደሉም እያሉ ይናገራሉ። አሁን የታሪክ፣ የተፈጥሮ፣ የፖለቲካ እና የዲፕሎማሲ ማህበራዊ ሀብቶቻችን እነዚህ ቢሆኑም ሰዎች ለእኛ መንገር የሚፈልጉት ድርቅ አለ፤ ድህነት አለ፤ ሽብር አለ፤ ኢትዮጵያውያን ስትባሉ የሚታወቅላችሁ ድርቅ ነው።እኛ አይደለም ሊነገር የሚችል ታሪክ አለን ብለን ስለምንመዝ።
ሁለተኛ ኢትዮጵያ ለማደግ እና ለመለወጥ ያላት አቅም የሰው ሀብት ቅድም ተገልጿል። ከዛም በላይ ቁጥር፣ ወጣት መስራት የሚችል የሰው ኃይል ያለባት አገር ናት። ብዙዎቹ ደግሞ በአዛውንት የተሞላ አገር ነው ያላቸው። እንደኛ ተስፋ የላቸውም።ብዙዎቹ ያደጉ አገራት አሁን የደረሱበት የደረሱት በአባቶቻቸው ነው። ልጆቻቸው እንደአባቶታቸው የማይተጉ በመሆናቸው ማስቀጠል ፈተና ነው። የሰው ሀብት፣ ገፀምድር ላይ ያለ ሀብት፣ ከርሰምድር ላይ ያለ ሀብት ኢትዮጵያ ከተጋች እና ከሰራች ለመለወጥ የምትችል አገር መሆኗን ያሳያል። ይሔ ሁለት ነገር ዕድልም ፈተናም ስለሆነ ጠላት በብዙ መንገድ የማጥቂያ አቅጣጫ ወስዶ ያዳክመናል። በብዙ መንገድ፤ በቀጥታ እየታየ ብቻ አይደለም (በፊዚ ካል) ብቻ ሳይሆን በብዙ መንገድ፤ ኢትዮጵያ ላይ አሁን እየተካሔደ ያለው ጦርነት ፤ ግራጫ ጦርነት ነው።
በብዙ መንገድ ኢትዮጵያ ላይ አሁን እንየተካሄደ ያለው ጦርነት የግራጫ ጦርነት ነው። ነጭ መዝገብ ላይ ወይም ጥቁር መዝገብ ላይ የተቀመጠ ሳይሆን የግራጫ ጦርነት ባህሪ ነው ያለው ።ነጭ እና ጥቁርን ለጊዜው አላነሳውም ።የግራጫ ጦርነቱ ላይ ብቻ ላተኩር ፡-
የግራጫ ጦርነት ሲባል አንደኛው የመረጃ ጦርነት ነው። ለምሳሌ በወለጋ አንድ ቀበሌ ውስጥ ነገ ሞት የሚካሔድ ከሆነ በብዙ ዓለም ያሉ የመረጃ ተዋናዮች ያውቁታል። ጫፍ ጫፍ ይላሉ፤ ልክ እንደሞተ የዓለም ሚዲያዎች ይዘግባሉ። እኛ ገና መረጃውን ሰምተን ወታደር በምናሯሩጥበት ጊዜ ከእኛ በላይ አጀንዳውን ማስፋት የሚችል ኃይል አለ። የመረጃ ጦርነቱ አካል ስለሆነ። ይህ መረጃ ጦርነት በስንዴ ላይ ወይም በግሪን ሌጋሲ ላይ ኢትዮጵያ አስደማሚ ሥራ ብትሰራ ሥራም አላጣ አይገኝም እዚያ ። ይህንን የግራጫ ጦርነት አንድ አካል የሆነ የመረጃ ጦርነት ኢትዮጵያ አሁን ባላት አቅም ሙሉ በሙሉ መከላከል ትቸግራለች።የተቀናጀ ስለሆነ። ትሞክራለች በብዙ ግን ቀላል አይደለም።
ሁለተኛው ዲፕሎማሲ ነው። ዳታውን ላለማጋነን ፈርቼ እንጂ በአደጉ አገራት በየደቂቃው ነው ግድያ ያለው። በየቀኑ ሰው ይሞትባቸዋል አገራት ፤ በምንም መመዘኛ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፈው አመት ተደምሮ ቅድም ካነሳኋቸው አገራት አንጻር በጣም ጥቂት ነው ፤ ወደ ቁጥር ከመጣን። እዚያ ግን ሎካል ሚዲያው ከሚያወራው ውጭ የአገርኛ ሚዲያ አጀንዳ ስለማይሆን ፤ እኛም ጋር ስለማይደርስ ፤ በየቀኑ እየሞተባቸው ያሉ አገራት ሳይቀር ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ጉዳይ አስጨንቆአቸው የዓለም ሚዲያ አጀንዳ ያደርጉታል። በከተማቸው ሰው እየሞተ፤ ልጆቻቸው እየሞቱ፤ ያን መከላከል ሳይችሉ የእኛን ጉዳይ ግን የዓለም አጀንዳ ማድረግ ይፈልጋሉ። ብዙ ነው መንገዱ፤ ሦስተኛው የሳይበር ጦርነት ነው። ቁጥሩ እየጨመረ ነው ያለው ።
አራተኛው የተልኮ ውጊያ ነው። እግር አልባ ተላላኪዎች፤ ባንዳዎች ያሉበት አገር ሲሆን ጨው እያቀመስክ ትልካቸዋለህ። እነዚህ እግር አልባ ባንዳዎች ሳይቸገሩ የራሳቸውን ዜጋ የራሳቸውን ቤተሰቦች ለመግደል ይፍጨረጨራሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ያለውን በጋራ የመኖር እና ኢትዮጵያን የማጽናት ፍላጎት ለማፍረስ የተመረጡ አካባቢዎች አሉ። አንደኛው ኦሮሞ እና አማራን በተቻለው አጋጣሚ ማፋጀት ነው። ሁለተኛው አማራን እርስ በርስ ማፋጀት ነው። ሦስተኛው ኦሮሞን እርስ በርስ ማፋጀት ነው። አራተኛው አፋር እና ሶማሌን ማፋጀት ነው። አምስተኛው ሲዳማ እና ወላይታን ማፋጀት ነው። ስድስተኛው ቤኒሻንጉልን ከኦሮሞም ከአማራም ማፋጀት ነው።ከዚያም ሲያለፍ ሙስሊም እርስ በርሱ ክርስቲያን እርስ በርሱ እንዲፋጅ ማድረግ ነው።
ስለዚህ እናንተ( የሕዝብ ተወካዮችን) የሲዳማ እና የወላይታውን ሳትሰሙ መንግሥት ገብቶ ካረገበ በኋላ የጸጥታ ተቋሙ አረገብኩ ብሎ የአፍታ እረፍት ሳያገኝ ኢሳ እና አፋር ሊባል ይችላል። እዚያም መሮጥ አለበት።ኢሳ እና አፋር ስትሮጥ ደግሞ ቤኒሻንጉል እና አማራ ወይም ቤኒሻንጉል እና ኦሮሞ ሊባል ይችላል። እነዚህ ቀጠናዎች ቅድም ባነሳኋቸው በመረጃ ጦርነት፣ በዲፕሎማሲ በሚላላኩ ጀሌዎች እና ባንዳዎች ከፍተኛ ዘመቻ ተደርጓል። እስካሁን በዚህ ሂደት ኢትዮጵያን ማፍረስ አልተቻለም። በብዙ አገራት ያለው ልምምድ እነዚህ ካልተሳኩ ሰበብ ፈጥረህ ጦር ማዝመት ነው። የዚህ የመጨረሻ ግብ አይደለም። በሚዲያ ካፈረስክ በሚዲያ ማፍረስ። ያ ካልሆነ በዲፕሎማሲ ጫና ማፍረስ ያም ካልሆነ በተልኮ ውጊያ ማፍረስ ያ የማይሳካ ከሆነ ደግሞ ምክንያት ፈጥረህ ገብተህ ማፍረስ ነው።
ለተከበርከው ምክር ቤት ላረጋግጥ የምፈልገው ማንም አገር፤ ማንም አገር ከኢትዮጵያ ጋር ተዋግቶ ኢትዮጵያን ማሸነፍም ማፍረስም አይች ልም። መግደል ይችላል፤ ማጋደል ችሏል፤ በኢኮኖሚ ጫና ማዳከም ችሏል።ይህንን እድሜ ልካችንን አድርገውታል። ምንም በኢኮኖሚ ጫና ቢያዳክሙን፤ ምንም ዕርስ በርስ ሞኝ ተላላኪ እየላኩ ቢያጋድሉን ኢትዮጵያን ማፍረስም ሆነ ማሸነፍ አይችሉም። አባቶቻችን አላደረጉትም፤ እኛም አናደርገውም። ልጆቻችንም ይህን ይከተላሉ። ይህን በተግባር የምናየው ጉዳይ ይሆናል።
ይህ ሲባል ግን እጃቸውን ጠቅለው አርፈው ይተኛሉ ማለት አይደለም። በሩ ብዙ ነው ዛሬ በሰሜን ነገ በምሥራቅ ከዚያ በደቡብ በየቀኑ የሚያንኳኩበት፤ የሚያዳክሙበት እና ከሥራ የሚያስፈቱበት ነገር ይፈጥራሉ። ለምሳሌ ኢትየጵያውያን አንዳንዶች ኢትዮጵያ በብዙ መንገድ ስትደበደብ ፤ በብዙ መንገድ ስትወቀጥ የት እንደነበሩ የማናውቃቸው ሁሉ ግድያ ሲኖር ይሸቅጡበታል፤ ይነግዱበታል። የግድያ ነጋዴዎች አሉ። በሞት ሸቅጠው ማትረፍ የሚፈልጉ ሰዎች አሉ። እነኝህ ሰዎች ወረራ ሲካሄ ድብን ይህ ሁሉ ጫና ሲካሄድብን ልክ አሁን በሞት መሸቀጥ እንደሚያስቡ ቢሸቅጡ ኖሮ ባልከፋ ነበር። ይህ በጣም ሰፊ ነው።ባንዳው እዚያ የሚዋጋው ሸኔ ብቻ አይደለም። አዲስ አበባ ያለም ባንዳ አለ። በየመጂሊሱ የሚሸቅል ማለት ነው። እንደዚህ ዓይነት ሸቃጭ ስብሰብ በሚኖርበት ሰዓት የሚያጠቁን ኃይሎች የተሻለ ጉልበት ያገኛሉ።
ለዚህ ዙሪያ መለስ ፈተና እና የግራጫ ጦርነት ቀድመን ስለተገነዘብን ኢትዮጵያ ውስጥ ማድረግ የሚገባን ነገር ሎው ኢንፎርስሜንት ኤጄንሲ ማጠናከር ነው። መከላከያን፣ ፖሊስን፣ ደህንነትን ማጠናከር ነው። ስናጠናከር በተቻለ መጠን አራት ነገሮች የእነኝህ ተቋማት መርህ እንዲሆኑ አድርገን መፍጠር አለብን።
አንደኛው ዘር ነው።ዘር የሌለው ግለሰብ የለም። የእራሱ ሆነ ዘር አለው። ነገር ግን መከላከያ ውስጥ ሲገባ ተቋሙን የዘር መጠቀሚያ ማድረግ የለበትም። አንተ ኦሮሞ አይደለህም፤ አማራ አይደለህም፤ ጉራጌ አይደለህም ባንለውም ዘር የግሉ ቢሆንም መከላከያ ሲገባ ግን ቃል የገባበትን ፤ የማለበትን በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠውን ከማስፈጸም አልፎ በዘር ጉዳይ የሚሳተፍ እንዳይሆን አድርገን እንስራ።
ሁለተኛው እምነት ነው። ኢትዮጵያውያን በግራም ቢሆን በቀኝ እምነት አላቸው። አብዛኛው ወይ ክርስቲያን ነው ወይ ሙስሊም ነው፤ በግሉ።ያን የእምነት አቋም ይዞ መከላከያ ውስጥ ፤ ደህንነት ውስጥ መግባት የለበትም፤ በግሉ አትመን አንለውም። የተቋሙ እምነት ግን ማድረግ የለበትም።
ሦስተኛው ፖለቲካዊ አመለካከት ነው።ሰው የእራሱ የሆነ የፖለቲካ አመለካከት አለው። ሁሉም ሰው።ያ አመለካከቱን እነዚህ ተቋማት ውስጥ ማስገባት የለበትም። በግሉ አምኖ ምርጫ ሲመጣ ሊመርጥ ይችላል። የፖለቲካ አመለካከቱን መጠቀሚያ ማድረግ የለበትም።
አራተኛ፤ አቅም በፈቀደ መልኩ በጥቅም ተገዝቶ፤ በጥቅም ተታሎ የአገርን አንድነት አደጋ ውስጥ የሚያስገባ መሆን የለበትም በሚል ሰፋፊ ጽሑፎች ስልጠናዎች ተዘጋጅተው መከላከያ ደህንነት ተቋማት ሲሠሩ ቆይተዋል። ይህን እናንተ ባይናችሁ አይታችኋል።
ዛሬ ያለንን መከላከያ ትናንት ካለን መከላከያ ጋር ለማወዳደር የሚያስችል ክራይቴሪያ የለም።በእጅጉ የተሻለ ነው። ከፍተኛ የሆነ የተቋም ግንባታ ሥራ እየተሠራ ነው። በሁሉም የደህንነት ተቋማት እንዳያችሁት፤ ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ነገ የሚረከቡ ልጆችን ታሳቢ አድርገን እየገነባን ነው።
በዚህ ሂደት መከላከያ ቢያንስ ዘጠና አምስት ፐርሰንት ተሳክቶለታል። ወደ መቶ ፐርሰንት ማደግ አለበት ።ፖሊስ በብዙ አድጓል፤ ደህንነት በብዙ አድጓል።ፖሊስ ዛሬ 30 እና 40 ኪሎሜትር በእግር ተጉዞ ዜጎችን ከጥቃት ለመከላከል የሚጥር ኃይል ፈጥሯል።ቅድም ብያለሁ ደራሼ ላይ ብቻ 80 የሚጠጉ ፖሊስ እና የካድሬ አባላት ሞተዋል።የተለየ ጥቅም የላቸውም።ይህን እያጠናከሩ መሄድ ያስፈልጋል። የተከበረው ምክር ቤት መገንዘብ የሚገባው ነገር ኢንሲደንት እናንተ ጋር ሲደርስና እናንተ ጋር ሳይደርስ እዚው ሲቀጭ ያለው የቁጥር ልዩነት በጣም ሰፊ ነው፡፡
ለምሳሌ ጥምቀት ባለፈው ዓመት በኢትዮጵያ ደረጃ 22ሺ ቦታ ታቦት ወጥቶ ጥምቀት ተከብሮ ገብቷል።ችግር የገጠመን ወይብላ ማርያም ነው።አንድ ቦታ።ስለ21ሺ900 በላይ ቦታዎች የሚያወሳ ሰው አታገኙም።እነሱ 21ሺ ቦታዎች ተጠብቀው ነው ወጣቶች ወጥተው በምታውቁት ሥርዓት በዓላቸውን ሲያከብሩ ተጠብቀው ነው።ፖሊስ 21ሺውን መጠበቅ መቻሉ ጥሩ ነው። አንድ የጎደለችውን መሙላት አለበት፤ እኛም አግዘን፣ ሕዝብም አግዞ ማደግ አለበት።ግን አንድ ሲበላሽ አልሠራም ካልን በልፋት ላይ ውሃ መቸለስ ይሆናል።
የባለፈው የረመዳን ኢድ በኦሮሚያ ብቻ ከስምንት ሺ800 በላይ ቦታ ላይ የጀመዓ ሰላት ተሰግዷል።ሰዎች በጋራ ወጥተው ኢድ አክብረዋል።አፋር፣ ሱማሌ ሰፊ ቦታ ነው እንደምታውቁት።በአማራ ክልል በምሥራቅ አማራ አብዛኛው ቦታ እንደዚያ ነው።በብዙ ሺ የሚቆጠር ቦታ የጀመዓ ሰላት ተሰግዶ ቢወጣም አብዮት አደባባይ ላይ አንድ ችግር ገጥሟል። ደሴ የሰገደው፣ ጅማ ሰግዶ የገባውም፣ ሰመራ ሰግዶ የገባውም ስለአዲስ አበባው ጭስ ነው የሚያወራው እንጂ የእርሱ ሰላም ተጠብቆ እንደገባ አይናገርም።
በየቀኑ ትንኮሳ አለ፤ በግራ፣ በቀኝ።የሰራዊት አባላት በየቀኑ ይህን ለማስታገስ ይሮጣሉ።ዛሬ በዚህ ቀበሌ መጣ፣ ነገ በዚያ ቀበሌ ሄደ፣ ሁሌም ሩጫ ነው፤ በየቀኑ።አልፎ አልፎ ደግሞ አጥፊዎች ጥቂት ሆነው፣ ተመሳስለው፣ ንፁሃንን ስለሚገድሉ ከፖሊስ ጋር ስላልሆነ የሚያደርጉት እንደምታውቁት አሳዛኝ ነገር ያጋጥማል።አሳዛኝ ነገር ሲያጋጥም ከተከበረው ምክር ቤት የሚጠበቀው፣ ከኢትዮጵያ ሕዝብ የሚጠበቀው መጀመሪያ ጠላትን መለየት ነው።ወገን መሰብሰብ ነው፤መከፋፈል አይደለም፤መሰብሰብ ነው፤ ሰብሰብ ብለን ጠላታችንን መከላከል፣ ማጥፋት የምንችልበትን አቅጣጫ መከተል ነው። የዓለም ልምድ ይሄ ነው።
ኮሽ ባለቁጥር እርስ በእርስ መጠራጠርና መከፋፈል ከፈጠርን ለነዚያ ኃይሎች ምቹ ነገር እንፈጥራለን። ይህን የተከበረው ምክር ቤት በውል እንዲገነዘበው እፈልጋለሁ።አዲስ አበባ ላይ አሁንም ሰፋፊ ፍላጎቶች አሉ፤ በየቀኑ በርካታ ሥራዎች ሠርተን ሕይወት ለመታደግ እየሞከርን ነው። ቦምብ እየያዝን ነው፤ ፈንጂ እየያዝን ነው። መሳሪያ እየያዝን ነው።ከተለያየ አገር የመጣ የሰለጠነ ወታደር እየያዝን ነው።ትናንትናም ይዘናል፤ ከትናንት ወዲያም ይዘናል። ወለጋ ባጋጠመ በሦስት ቀን ውስጥ ለገጣፎ ብቻ አዲስ አበባ የሚገቡ 55 ሰው ይዘናል።
አሸባሪ እዚህ ገብቶ ፓርላማው ላይ የማይተኩሰው እዚህ አካባቢ ቀድሞ የሚጠበቅ ጥበቃ ስላለ ነው።በሁሉም ቀበሌ ላይ ጥበቃ ማስቀመጥ ብንችል፣ በሁሉም ዜጎች በር ላይ ጥበቃ ማስቀመጥ ብንችል ችግሩ ሊቀንስ ይችላል።ያን ማድረግ ደግሞ ኢትዮጵያ አትችልም። አሜሪካም አትችልም፤ኢትዮጵያም አትችልም። ለ100 ሚሊዮን ሕዝብ 100ሺ ወታደር ተይዞ እንዴት እንከን አጋጠመ አይባልም።
እናንተ ምን አስባችኋል እንደ መንግሥት፣ እንዴት ልትከላከሉት ነው እየሠራችሁት ያላችሁት፣ ስትራቴጂያችሁ ምንድን ነው የሚል ጥያቄ ተነስቷል። እኛ ግልጽ የሆነ ስትራቴጂ አስቀምጠን እየሠራን ነው። በእንግሊዝኛው ‹‹ፎር ፒ››፣ በአማርኛው ‹‹አራቱ መ›› በሚል ስልት ነው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ነገር ለመከላከልና ኢትዮጵያን ለማፅናት እየሠራን ያለነው። የመጀመሪያው ፒ፣ ፕሪቬንት ማድረግ ነው፣ መከላከል። ችግሮች ሲያጋጥሙ፣ እንዳያጋጥሙ ቀድሞ አውቆ መከላከል።
ከዚህ አንፃር ቀደም ብዬ እንዳነሳሁት ተቋማት በማጠናከር፣ ሕዝብ በማንቃት ብዙ ሕይወት መታደግ ችለናል።ሙሉ ግን አይደለም፤ ባዳንነው ልክ መኩራራት ሳይሆን በጎደለው ልክ ተግተን መሥራት ይጠበቅብናል፣ እንደ መንግሥት፣ እንደሕዝብ። ተቋማትን ይበልጥ ማጠናከር አለብን።ሕዝብ መንቃት አለበት። ወሬ ሲሰማ ከማን ሰማሁ ማለት አለበት።ኦፖርቹኒስትና ጊዜ ጠብቀው የሚያፋጁ ኃይሎችን መለየት አለበት።ዝም ብሎ መከተል የለበትም።ይህንን ካደረገ ከመከላከል አንፃር ያለው ውጤት ያድጋል።
ሁለተኛው ፒ ፐርሲው ነው፤ መከታተል።ዛሬ ወለጋ ላይ ችግር ሲፈጠር ወለጋ አበቃ ካልን ጉድ ነው።ጋምቤላ ይቀጥላል፤ ጎንደር ይቀጥላል።ስሙን ነው የሚቀያይረው።ኮንቲኒየስሊ መከታተል ያስፈል ጋል። ለዚያ የክትትል አቅማችንን ለማሳደግ ሰፊ ሥራ እንደተሠራ ስላያችሁ መግለጽ አልፈልግም። አሁንም ጥረት ያስፈልጋል።አንዳንዴ መረጃውን አግኝተን መድረስ የሚያቅተን ጊዜ አለ።አንዳንዴ መረጃ አግኝተን ደርሰን በቦታው ላይ ምንም የማናገኝባቸው ጊዜዎች አሉ። ይሄን እያጣጣሙ እያደጉ መሄድ ይፈልጋል።
ሦስተኛው ፒ ፕሮቴክት ነው፣ መጠበቅ። የምን ጠብቀው የጠላት ዋና ዋና ታርጌት የሆኑ ፕሮጀክቶች፣ ተቋማት፣ አካባቢዎች በተለየ እንጠ ብቃለን። የቀረውን ደግሞ ሕዝቡ በየአካባቢው እያደራጀን የሚጠብቅበትን መንገድና ድጋፍ ሲያስፈልግ የሚጠይቅበትን መንገድ ይበልጥ እያጠናከርን እንሄዳለን፡፡
አራተኛው ፕሪፔር ነው፣ መዘጋጀት።አሁንም መዘጋጀት፣ በየቀኑ መዘጋጀት። ሰው ሞተ ሲባል አንድ ሳምንት ተጯጩኸን ከዚያ ደግሞ ረስተን የምንገባ ሳይሆን ተጨማሪ ሰው እንዳይሞት በየጊዜው ዝግጅት ማድረግ፣ ለሚቀጥለው ፈተና ራስን እንደአገር እንደ ተቋም ማዘጋጀት ያስፈልጋል።
ይህን ስትራቴጂ ካውንተር ለማድረግ፣ ይህን ስትራቴጂ ተገዳድሮ ውጤት ለማምጣት በጠላቶቻችን በኩል የሚሠሩ ሥራዎች አሉ። አንደኛ በመዋቅር ውስጥ ሰው ይገዛሉ። ይህ ሰው አብሮ ያቅዳል፣ አብሮ ይነጋገራል፣ ያበላሻል። ቅድም መዋቅር አይጠራም ወይ የተባለው ባለፈው ሪፖርት አቅርቤያለሁ። ባለፉት ሁለት ወራት ከአምስት ሺ ያላነሱ ሰዎችን አጥርተን ግማሹ ከደረጃ ዝቅ ብሏል፤ግማሹ ታስሯል፤የተለያየ እርምጃ ተወስዷል። አሁንም ይወሰዳል፡፡
ይህ የሚወሰደው በአሉባልታ አይደለም። አሉባልታ ሸኔዎች እዚህ ይገድሉና በሌላ ሸኔዎች ደግሞ የሚከላከሉ ሰዎች ሊያስጠቁ ይፈልጋሉ።እሱ ከእናንተ በላይ መረጃ ስላለን ማን ምን እንደሚሠራ በፕሮፖጋንዳ የሚወሰድ እርምጃ የለም፤ በመረጃ ብቻ ነው እርምጃ የሚወሰደው። ማን ማንን ፋይት ያደርጋል፣ ማን ምን እያደረገ ነው ቢያንስ የተሻለ ግንዛቤና መረጃ እኛ ጋ አለ፡፡
አሁን እዚህ ጋ ካጠቁ በኋላ ትንሽ ጠንከር የሚሉባቸውን ግለሰብና ቡድኖች ደግሞ በሰፊው በአባሎቻቸው ያስጮሃሉ።ከዚህም ለማዳከም፤ በግድያም ብቻ ሳይሆን በውስጥም ለማዳከም።እሱ ድራማ እኛ ጋ አይሠራም።እኛ ያደግንበት ስለሆነ በእንደዚህ ዓይነት ነገር እኛን ማታለል ብዙም የሚቻል ስለማይመስል፤መዋቅር ውስጥ ግን ችግር አለ፡፡
ሁለተኛ የተቀናጀ የሚዲያ ዘመቻ ነው።እናንተም አንስታችኋል፤የግራጫ ጦርነት አንዱ ስልት ሚዲያ ነው። በአንድ ጊዜ ነው ዓለም የሚንጫጫው።ከአገር ውስጥም በጣም ብዙ ሰዎች አሉ እንደዚሁ መንግሥት ቢይዘንም ምንም አያደርገንም ያሻንን አድርገን ብራችንን እንውሰድ የሚሉ ሰዎች አሉ።በተቻለ መጠን ሕግ ለማስከበር ሙከራዎች እየተደረጉ ነው፤ ይጠናከራሉ።
ሦስተኛው ባንዳዎች ናቸው።ዛሬ ሳይሆን በጣሊያን ወረራ ጊዜ ባንዳዎች ነበሩ። ኢትዮጵያ በዘመኗ ባንዳዎች ጠፍተዋት አያውቁም። በዘመኗ ልጆቿ ሳይወጓት ቀርተው አያውቁም። በዘመኗ ጠላት የልጆቿን መከፋፈል ሳይጠቀም በር አንኳኩቶ አያውቅም። ሁሌም ታሪካችን ይሄ ነው።አሁንም ባንዳዎች አሉ። ግማሹ አዲስ አበባ ተቀምጦ በሚዲያ የሚገዛ ባንዳ፣ ግማሹ ክላሽ ተሸክሞ ጫካ የገባ ባንዳ፣ ብዙ ባንዳ አለ። በየኤንጂውና ኢንተርናሽናል ተቋማት እየተሽከረከረ የሚውል ባንዳ ብዙ ነው።ናሽናል ኢንተረስት ላይ ሳይሆን የራሱ ጉዳይ ላይ የሚያተኩር። ይህንም አቅም በፈቀደ መጠን ፋይት እናደርጋለን።
ለምሳሌ ድርቅ እንውሰድ፣ በቅርቡ በሱማሌ በአፋር አካባቢና በደቡብ አካባቢ ያጋጠመን ድርቅ ባለፉት 40 ዓመታት ከገጠመን ድርቅ የከፋ ነው።40 ዓመቱን ደግሞ እንተወው። 2009 አ.ም በሱማሌ ክልል የገጠመን ድርቅ እና የዘንድሮው ድርቅ መሳ ለመሳ አይታዩም።የተራራቁ ናቸው፤ በሸፈነው ዞን፣ ባጠቃው የቤት እንስሳ እና በጥቃቱ ኢንቴንሲቲ የአሁኑ በእጅጉ ይበልጣል።ከሱማሌ ክልል የመጣችሁ ታውቁታላችሁ፤ ታሪኩን።
2009 በሱማሌ ድርቅ ላይ ኢንተርናሽናል ተቋማት ከፍተኛ ድጋፍ አድርገውልናል፤ ከፍተኛ።በ2014 ያኔ ከደገፉን ሩብ አልደገፉንም። ይሄስ ሰው ግድያ ነው፤ ድርቅ ለምን ፖለቲካ ይሆናል ታዲያ።2014 አ.ም ሳንደገፍ የሱማሌ ክልል መንግሥት፣ የሱማሌ ሕዝብ፣ የሁሉም ክልል ሕዝቦችና መንግሥት፣ ፌዴራል መንግሥት ተረባርቦ ባደረጉት ርብርብ ግን አንድ ሰው በድርቅ አልሞተብንም። 2009 በአንድ ወረዳ ብቻ ከ100 በላይ ሰው ሞቷል። ሰው ሳይሞትብን ከብቶች ሞተውብን መከላከል የቻልነው እንደ አገር ፌዴራልም ክልልም በነበረው ርብርብና መደጋፍ እንጂ ከውጭ የነበረው ድጋፍ በእጅጉ ከዚያ የተለየ ነው።
በኢኮኖሚ ቅድም ተገልጿል፤ መልሼ አልገል ፀውም። ዋናው ፖይንት በየቀኑ እየተወጋን፣ በየቀኑ እየተፈተን፣ በየቀኑ መስዋዕትነት እየከፈልን፣ በየቀኑ እጅግ ለማመን የሚከብዱ ነገሮች ውስጥ እያለፍን ነው። የሚገርማችሁ በየቀኑ እየጠነከርን ነው፤ በየቀኑ እየተማርን ነው።
ለጠላቶቻችን መንገር የምንፈልገው አንደኛ የኢትዮጵያ መንግሥት ረዚሊየንት መሆኑንና አገር ማሻገርን በጽኑ የሚያምን ብቻ ሳይሆን አስፈላጊ ከሆነ መስዋዕትነት የሚከፍል ስለሆነ ዝም ብሎ በሆያ ሆዬና ግርግር በጫት ላይ በምርቃና ወሬ የሚፈርስ አለመሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። አንደኛው ነገር ማለት ነው፤ አስፈላጊ ከሆነ መስዋዕትነት። ከዓላማችን፣ ከመበልጸግ ጉዟችን ንቅንቅ የሚያደርገን ነገር የለም። አልተፈተንም አላልኳችሁም፤ግን አንሸነፍም። ይሄ ግራ የሚገባቸው በጣም ሰፊ የሚታለሉ ሰዎች አሉ። ይሄ ነገር እያለቀ ይሆን ብለው ቶሎ ብለው መስመራቸውን ወደዚያ ወደዚህ የሚያደርጉ ሰዎች አሉ፤ የእያንዳንዱ ሰው የራሱ ብቃትና የጥንካሬ አቅም ስለሚለያይ።
ዋናው ጉዳይ ፈተናዎች ይበልጥ እያጠነከሩን፣ በፈተና ውስጥ ወደፊት እየተጓዝን ነው ያለነው፤ ቁስልም ቢኖረው።ሰዎች እየቀበርን ቢሆንም፣ የህፃናት፣ የንፁሃን ደም ጩኸት እንቅልፍ የሚነሳ ቢሆንም።በቅርቡ የሞቱትን ሰዎች ዘር ምናምን ተዉና የእናንተ ልጆች ቢሆኑ ብላችሁ አስቡ።የእናንተ እዚህ ያላችሁ ሰዎች፤ ህፃናት ትምህርት ቤት ሄደው ቢገደሉ ማን ነው ተኝቶ የሚያድር።ይሄ ውስጥም ቢሆን መከራው እናሸንፋለን፡፡
(ይቀጥላል)
አዲስ ዘመን ሐምሌ 2 ቀን 2014 ዓ.ም