ዳመና ነው። ክረምቱ ከብዷል። የቆምንበት ሰፈር በወጉ መፈናፈኛ የለውም። ጥቂት ቤቶችን አልፈን ከአንድ ስፍራ ቆምን። ከጠባቧ መተላለፊያ የተቀመጡትን ወይዘሮ አየናቸው። በከሰል የጣዱትን ወጥ እያማሰሉ ቀና ብለው አስተዋሉን። ጠጋ ብለን ሰላምታ አቀረብን። ለምላሹ አልዘገዩም። በትህትና ተቀብለው አጸፋውን መለሱ። ፊታቸውን አይቶ ማንነታቸውን መገመት አይቸግርም። ትሁት ናቸው፣ ሽቁጥቁጥ።
ወይዘሮዋ ለስራው ደጁን ለምን እንደመረጡት መጠየቅ አላሻንም። ቤታቸው እጅግ ጠባብ ነው። መላወሻ የለውም። ቦታው ከክረምቱ ተዳምሮም ፈተና ሆኗቸዋል። የትኩስ ወጥ ሽታ በአፍንጫችን ውል እያለ ከጎናቸው አረፍ አልን። ወይዘሮ አሰገደች ይማም የልባቸውን ሊያወጉን ፈቀዱ። ጭውውት ጀመርን።
የልጅነት ህይወታቸው ከእውነተኛ ፍቅር ይቀዳል። ይህ እውነት ከማንነታቸው የታገለ፣ ዕምነት ሀይማኖታቸውን ጭምር የፈተነ ሀያል ነበር። በወቅቱ ማንም ስለሳቸው ምንም ቢል ጆሮ አልነበራቸውም። የዛኔ ከልብ ላፈቀሩትና ላፈቀራቸው አንድ ሰው ማንነታቸውን ሰጥተዋል።
ሀያል ፍቅር
የወሎዋ ጉብል የልባቸው ውድ የሆነው ወጣት ከዕምነት ሀይማኖታቸው አይዛመድም። እሳቸው ከእስልምና ፣ እሱ ደግሞ ከክርስትና ሀይማኖት ነው። ይህ ልዩነት ግን ከፍቅር በልጦ አልተገኘም። ጥንዶቹ ከምንም በላይ ውስጣቸውን አድምጠው፣ መዋደዳቸውን አክብረው ቁምነገርን አሰቡ። በአንድ ተጣመሩ፣ ጎጆ ቀለሱ።
አሰገደች ይማም ከልብ ከወደዱት፣ ውሰጣቸውን አሳልፈው ከሰጡት ወጣት ጋር በትዳር ተጣምረው ኑሮን ጀመሩ። ፍቅር በትዳር ታጅቦ ህይወት መድመቅ ያዘ።በአንድ ጣራ ስር ውለው ሲያድሩ የፍቅር ሀይል በእነሱ ተገለጠ ። ልቦቻቸው አንድ ሆኑ፣ነፍስያቸው ነፍስ ዘሩ።
የጥንዶቹ መተሳሰብ ሌሎችን እያስገረመ ነው። አሰገደች የትናንቱ እጮኛቸው ዛሬ የቤታቸው ራስ፣ የትዳራቸው አባወራ ሆኗል። በእሱ ውስጥ ነገን አሻግረው ያያሉ ። ስለመልካምነቱ፣ ስለደግነቱ ተናግረው፣ መስክረው አይጠግቡም። ሁሌም በአባወራቸው ደስ ይላቸዋል፤ በማንነቱ የጎደለ ዓለማቸው ይሞላል ፣ ሀዘን ትካዜያቸው ይጠፋል።
ድንገቴው አጋጣሚ
አሁን አሰገደች የትናንቱ ደሰታ ከእሳቸው የለም። ጠዋት ማታ ዓይናቸው በዕንባ እንደራሰ ሲያለቅሱ ይውላሉ። የሆነውን ሁሉ ማመን ባቃታቸው ጊዜ ያለፉበትን መንገድ እያሰቡ በግርምታ ይተክዛሉ። አሁን ነፍሳቸውን የሰጡት፣ ልባቸውን ያስጨበጡት አባወራቸው ከጎናቸው የለም። ሞት ድንገቴው ነጥቆ ወስዶባቸዋል።
አሰገደች ሀዘናቸው በእጅጉ ከፍቷል። ውስጣቸው ተጎድቷል። ሰማይ የተደፋባቸው፣ ምድር የዋጠቻቸው ያህል ከብዷቸዋል። የፍቅር ሀሁን ያስተማሯቸው ውድ ሰው ለእሳቸው ባል ብቻ አልነበሩም። እንደ እናት ፣እንደ አባት ፣ ልክ እንደ እህትና ወንድም ፣ ጎዶሏቸውን ሲሞሉ ቆይተዋል።
ለአሰገደች ከባላቸው ሞት በኋላ ህይወት ከባድና መሪር ሆነ ፤ቤት ሲገቡ፣ መንገድ ሲጀምሩ ከጎናቸው እንደሌሉ ያስባሉ። ድምጻቸው፣ ርምጃቸው፣ ይናፍቃቸዋል። ትዝታቸውን እንደዋዛ መተው፣ እንደቀላል መርሳት አልቻሉም።ብቸኝነት አንገት አስደፍቶ ሲያስተክዛቸው ይውላል።አባወራቸውን ከቀበሩ ወዲህ ደስታ ርቋቸዋል፣ ኑሮ ይሉት ወግ ከብዷቸዋል፡፤
ጊዜያትን በሀዘንና በብቸኝነት የገፉት ወይዘሮ ትናንትን በነበር እያስታወሱ ከትዝታ ጋር ዘልቀዋል። ከአባወራቸው ያሳለፉት ህይወት መልካምነትን ያሳያቸዋል። አይተው ያጡትን የትዳር ዓለም ሲያስታውሱ የባላቸውን ትዝታ አይዘነጉም። ዛሬ ከጎናቸው ባይሆኑም ደግነት በጎነታቸው ከልባቸው አይጠፋም።
አዲስ ህይወት
የጭንቅና የዕንባ ጊዜያት እየተቆጠሩ ነው።አሰገደች በትዝታ እየዋተቱ፣ ከብቸኝነት እየታገሉ፣ ጊዜያትን ዘልቀዋል። ደጉ ባላቸው ሁሌም ከዓይምሯቸው አይጠፉም። የውሰጣቸው ሻማ እንደሆኑ ይኖራሉ። አንድቀን ግን አሰገደች አርቀው አሰቡ። ሀሳባቸው ከመፍትሄ አደረሳቸው። ያሰቡትን ለማድረግ አልዘገዩም። አገር ቀዬውን ትተው ለመውጣትን ቆረጡ፤ እንዲህ ከሆነ እንደአባወራቸው የልጅነት ፍቅራቸውን አርቀው ይቀብራሉ። በትዝታ አይሰቃዩም፣ በነበር ታሪክ አይቆዝሙም።
ጉዞ – አዲስ አበባ
አሰገደች አንድ ማለዳ አዲስ አበባ ከሚያደርሳቸው አውቶቡስ ውስጥ ራሳቸውን አገኙት። ተወልደው ያደጉበትን የቦረና ምድር ለቀው ሲወጡ ሆድ ባሳቸው ።ቦረና ላይ የልጅነት ፍቅራቸውን አግኝተዋል።ቦረና ትዳር መስርተው ወግ ማዕረግ አይተዋል፡፤ አሁን ደግሞ አገሩን ከነትዝታው ትተውት እየወጡ ነው።
ካሰቡት ሲደርሱ የት እንደሚያርፉ አልወሰኑም። ዕድላቸው ግን ደጅ አላሳደራቸውም። እግራቸው ከተማውን ከመርገጡ ካገራቸው ሰዎች ተገናኙ። ሰዎቹ በእጅጉ መልካም ሆኑላቸው። አሰገደች እንግድነት ሳይሰማቸው ቤተኛ ሆነው ኑሮን ቀጠሉ።
አዲስ አበባ የመምጣታቸው ምክንያት አንጀራን ፍለጋ ነበር። በወቅቱ ግን ካሰቡት አልደረሱም፤ ከሰዎቹ ተዛምደው፣ እነሱን መስለው መኖር ጀመሩ። እንዳሰቡት ሳይሆን ቢቀር ዓመታት ያለ እሳቸው ሀሳብ ያለስራ አለፉ። አንዳንዴ አሰገደች በሀሳብ ይናውዛሉ:: ሁሌም በጥገኝነት ከሰው ቤት መኖሩ ያስጨንቃቸዋል። እንዲህ ባሰቡ ጊዜ ወጣ ብለው ስራ መፈለግ ያምራቸዋል። ይህ ደግሞ ከተማውን በወጉ ለማያውቅ የሰው አገር ሰው ከባድ ነበር።
አሰገደች አሁንም በቤተሰብ ላይ ተደርቦ መኖር ያሳስባቸው ይዟል። ነገሮች አስኪሳኩ ግን ምርጫ የላቸውም። እንዲያም ሆኖ የታዘዙትን በቅንነት ይሰራሉ። ለሰዎቹ ያላቸው ከበሬታና ፍቅር አርቆ አልወሰዳቸውም። እየተሳቀቁም ቢሆን አብረዋቸው ዘልቀዋል። የባዕድ ዘመድ የሆኑላቸውን ቤተሰቦች መቼም ማስቀየም አይሹም። በጥንካሬያቸው እንደተጉ ፣በቅንነታቸው እንደታዘዙ አብረው መኖር ወደዋል።
በአንድ ዕለት ግን የአሰገደችን ህይወት የሚቀይር አጋጣሚ ተፈጠረ። በየቀኑ ሁኔታቸውን ከሚያስተውል ጎልማሳ ዓይን ላይ ወደቁ። ዓይኑ ያረፈባቸው ሰው የአገራቸው ልጅ ነው። ስለማንነታቸው ጠንቅቆ ያውቃል። ቀስ እያለ አግባብቶ በወጉ ቀረባቸው። አልራቁትም። ውሎ አድሮ ለትዳር ተመኛቸው።አልተግደረደሩም።ቤተሰቡን ጋብቻ ጠየቀ። አልተከለከለም።
አዲስ ጎጆ
ዛሬ ትናንት አልሆነም። በአሰገደች ልብ ተዳፍኖ የኖረው የልጅነት ፍቅር በሌላ ሰው ተተክቷል። ከጥገኝነት የወጡት ወይዘሮ በራሳቸው ጎጆ መኖር ጀምረዋል፤ ኑሯቸው መልካም፣ ቤታቸው ሙሉ እየሆነ ነው።አሰገደች ያሳለፉት መከራ በተሻለ ዓለም መተካቱ ህይወታቸውን ለውጦታል።አሁን ሀሳባቸው ሰለቤትና ትዳራቸውስለአዲሱ አባወራቸው ነው።
አባወራቸው በቂ ስራ አለው። ከእሳቸው አንዳች ነገር አይጠብቅምዓመታትን በፍቅር እያለፉ ነው። አንድቀን ግን የሰሙት ጉዳይ ግን የነበረውን እንዳልነበረ አደረገው። አባወራው በድንገት ወደ አሜሪካ እብስ ማለቱን አወቁ። አሰገደች በድንጋጤ ክው እንዳሉ ቀሩ ። ያመኑት ባላቸው እንደዋዛ ትቷቸው ካገር መውጣቱ ልባቸውን ሰበረው።
ዓመታትን በተስፋ
አሰገደች ትዳሬ ካሉት ሰው የደረሰባቸውን በደል ማመን ተሳናቸው፤ ዞር ብለው ራሳቸውን ጠየቁ፣ ሰውየውን ከማመን በቀር ያጠፉት የለም።ዕድላቸውን እያማረሩ ሁኔታውን ሊያጣሩ ሞከሩ። ስለ ባልዬው ‹‹አየን ሰማን›› የሚል አላገኙም። ተስፋ አልቆረጡም። ያለመሰልቸት በታማኝነት ጠበቁ፣ ጠበቁ። ሰውዬውን የበላ ጅብ አልጮህ እንዳለ ዓመታት ተቆጠሩ።
ራሳቸውን ለማኖር የጀመሩት የእንጀራና ዳቦ ንግድ ከሚጠምቁት ጠላ ተዳምሮ ገበያቸውን አደራው ።በሚያገኙት ገቢ ኑሯቸውን እየደጎሙ መኖርን ቀጠሉ።ተኝተው በነቁ ቁጥር የአዲስ ቀን አዲስ ዜናን መናፈቅ ልምዳቸው ሆነ።
አሰገደች ባልዬውን በጠበቁባቸው ዓመታት ‹‹እናግባሽ›› ያሏቸውን ሁሉ መልሰዋል። የታመነው ልባቸው ሸብረክ ሳይልም በጽናት ኖረዋል።ውሎ አድሮ ግን ውሰጣቸው ለውጥን ፈለገ። ዳግመኛ ትዳር መያዝ ጎጆ ማቅናት አማራቸው። አንድ ቀን ለትዳር የጠየቃቸውን አንድ ሰው ሳይገፉ ተቀበሉት ። ከእሱ ጋር ሊኖሩ ልባቸው ፈቀደ። ከሀሳቡ ተስማሙ፣በቃሉ አደሩ። ያለፈውን ረስተው አዲስ ህይወት ጀመሩ።
ሶስተኛው ትዳር..
አሰገደች ዛሬም ለቤታቸው፣ለአባወራቸው መልካም ወይዘሮ ሆነዋል።አሁንም ትዳራቸውውን ያከብራሉ፣.ባላቸውን ይወዳሉ።ጥቂት ጊዜያትን የቆጠረው አዲሱ ህይወት ያለአንዳች ችግር እየተጓዘ ነው።ውሎ አድሮ የሚሰማቸው ህመም ግን ጤና እየሰጣቸው አይደለም።
ወይዘሮዋ ምክንያቱን ለማወቅ በየሆስፒታሉ ባዝነዋል።ሀኪሞችም ዕጢውን በቀዶ ጥገና አውጥተው ከማህጸን በላይ የቆየ እርግዝና እንደነበር ነግረዋቸዋል። በተለያየ የህመም ሰበብ ለቆዩት ሴት ይህ አይነቱ መርዶ ከባድ ነበር፡፡ ከህመም ጋር የዘለቁት ወይዘሮ ችግራቸው በወጉ አልተፈታም። ቆይቶ አስራአምስት ኪሎግራም የሚመዝን ዕጢ አስኪወጣላቸው በድካምና በከፋ ስቃይ ውስጥ አልፈዋል።
አሰገደች ሶስተኛው ባላቸው መልካም ሰው ነበሩ፤ የአቅማቸውን ሰርተው ሲገቡ የእጃቸውን አይነፍጓቸውም። በእሳቸው ሞትንና መከዳትን ረስተዋልና ኑሯቸውን በአክብሮት መርተውታል። ሰውዬው ከ1971 ዓ.ም ጀምሮ አብረዋቸው ነበሩ። ዛሬ የሚኖሩበትን የቀበሌ ቤት ያገኙትም በእሳቸው ሰበብ ነበር።
በትዳር ቆይታቸው ለልጅ ፍሬ አልታደሉም። እንዲህ በመሆኑ እያዘኑ ዳግመኛ ትዳራቸውን በሞት ተነጥቀዋል። አክባሪ ባላቸውን ያጡት ከዓመታት በፊት ቢሆንም ዛሬም ድረሰ ሀዘኑ ከልባቸው አልጠፋም። አሁን አሰገደች ብቸኛ ናቸው።ትዳርና ጎጆ ይሉትን ካጡ ቆይተዋል።
ዛሬ ከአንዲት የእህታቸው ልጅ ጋር ህይወትን በጠባቧ ቤት እየገፉ ነው። የእሷ መኖር የነገን ተስፋ ያሻግራቸዋል። ኑሯቸው አመቺ ሳይሆን እንደነገሩ ዓመታትን ዘልቀዋል። ያለፉበት ህመም እንዳሻቸው ጎንበስ ቀና አያደርጋቸውም፤ ዛሬ የትናንቱ ጥንካሬ ከእሳቸው የለም። ለኑሮ ባልተመቸው ጎጇቸው ችግርን ከነሰንኮፉ ተቀብለው ሲገፉ ኖረዋል።
አሰገደች ዛሬ
ከበራቸው ደጃፍ ተቀምጠው ያለፉበትን የህይወት መንገድ እያወጉን ነው። ዕንባ ከዓይናቸው አልተለየም፡፡በአሰገደች ልቦና ውስጥ ያለፈው ታሪክ ብቻ አይታይም። በእሳቸው አሁናዊ ገጽታ የቆሙበት፣ ያሉበት ህይወት ጭምር ቁልጭ ብሎ ይነበባል። መልካቸው ቢጎሳቆልም የትናንትናው ውበት መነሻውን አልሳተም። ወዘናቸው ቢሟጠጥም ጥንካሬቸው ዛሬም ድረስ ከእሳቸው ዘልቋል።
ቀድሞ ይሰሩ የነበሩ ሸካራ እጆች ዛሬ ተደጓሚ መሆናቸው ያሳዝናቸዋል። እንዲያም ሆኖ ፈጣሪያቸውን እያማረሩ አይወቅሱትም። ዛሬን በተስፋ አቁሟቸዋልና ስለነገውም እንደማይጥላቸው ያምናሉ።
ዕንባ አባሾቹ
በአዲስ ከተማ ክፍለከተማ ወረዳ አራት በተለምዶ ከሰል ተራ ተብሎ በሚጠራው የቀበሌ ቤት ከእጅ ወዳፍ በሆነ ኑሮ ያሉትን ወይዘሮ መልካም ዓይኖች እንደዋዛ አይተው አላለፏቸውም። በዚህ ቤት የሚኖሩ ነፍሶች ሰጪ እጆች ካሉ ብቻ ቀምሰው እንደሚያድሩ ጠንቅቀው ያውቃሉ።በአካባቢው ያሉ ቤቶች ለልማት ሥራ በፈረሱ ጊዜ ብዙ ችግሮች ተደራርበዋል።
ከዚህ ቀድም በአካባቢው ያሉ ነዋሪዎች በአንድ የጋራ መብራት ይጠቀሙ ነበር። አሁን የመብራት ግልጋሎት የላቸውም። ቤቶቹ በፈረሱ ጊዜ ቆርቆሮና ማገሩ ስለተወሰደ ቤቱ የክረምቱ ዝናብ እንዳሻው ይናኝበታልይህ አይነቱ እውነታ በስፍራው ለሚገኙ ነዋሪዎች ኑሮን አክብዷል። እንደቀድሞው ከቤት አብስለው መጉረስ አልቻሉም። ዝናብ እንደጎርፍ እየወረደባቸው ነው።በዚህም መቆሚያ መቀመጫ አጥተዋል።
በአካባቢው አሰገደችን መሰል ነዋሪዎችን የቃኙ ዓይኖች በዘንድሮው የቤት ማደስ መርሃግብር ተጠቃሚ ለማድረግ ጥረታቸውን ይዘዋል። ነዋሪዎቹ ከአካባቢያቸው አልራቁም። ነባሩ የጭቃ ቤታቸው በብሎኬት ተተክቶ ሊሰራላቸው ግንባታው ተጀምሯል። በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ አራት ባለሀብቶችን በማስተባበርም ተግባሩ እየተከወነ ይገኛል።
አሰገደች ኮሮና ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ወረዳው በብዙ መልኩ ሲደግፋቸው ቆይቷል። በቀጥታ ተረጅነትም 700 ብር እንደሚያገኙ አጫውተውናል። ከዚያ ባሻገር ዓለማየሁ አናግባ የሚባል አንድ ሰው በቋሚነት እያገዛቸው ይገኛል።እሳቸው ስለዓለማየሁ ተናግረው አይጨርሱም። ሁሌም ምስጋናቸው በእጅጉ የላቀ ነው።
ለማንም ሰው ቢሆን ቤት ብቻውን መቆሙ ብቻ ፋይዳ የለውም:: ቤት ትርጉም የሚኖረው በወጉ ገበናን ሸፍኖ ፣ነዋሪዎቹ በልተው፣ ጠጥተው ሲያድሩበት ጭምር ነው። ወይዘሮዋ አሰገደችም ቢሆኑ ስለቤትና ኑሮው ከዚህ የተለየ እሳቤ የላቸውም። ቤት ገበና ሸፋኝ፣ችግርን ከፋኝ፣ ክፉውን ከደጉ ከታች ስለመሆኑ ያምናሉ።
ዛሬም ቢሆን አሰገደች ይመር የልበ መልካሞች ሰፋፊ እጆች ቢዘረጉላቸው ይወዳሉ። አሁን እሳቸው እንደቀድሞው አይደሉም። በህመምና መከራ የተፈተነ አካላቸው ደክሟል። ቋሚ የሚባል የገቢ ምንጭ የላቸውም። ከጎናቸው አንድ ሁለት ብለው የሚጠሩት ደጋፊ ወዳጅ ዘመድን አያውቁም፡፤
ያም ሆኖ እንደአቅማቸው የሚሰሩበት መተዳደሪያ ቢኖር ይወዳሉ። እንዲህ ከሆነ ከቋሚ ተረጅነት መላቀቅ፣ ዘወትር የሰው እጅ ከመናፈቅ ይድናሉ። በእርግጥ እንደቀድሞው ሮጦ መስራት ወጥቶ መግባት ይፈትናቸው ይሆናል። አሁን የሚሰራው ቤት መንገድ ዳር መሆኑ ግን የጉልት ሸቀጦችን ከደጃፋቸው ዘርግተው እንዲሸጡ ዕድል ይሰጣቸዋል።
ይህ ራስን የመቻል ሀሳብ የወይዘሮ አሰገደች የብቻ ውጥን ነው። እሳቸውን ከዚህ በተሻለ መተዳደሪያ ለማቋቋም ግን የመልካም ሰዎች እጅና ልቦና መጣመር ውጤቱን በጎ ያደርጋል። አሰገደች ትናንትና ያለፉበት አስቸጋሪ የህይወት መንገድ በዕድሜያቸው ማምሻ ዋጋ እያስከፈላቸው መሆኑን ያውቃሉ።
ነገን በተሻለ ተራምዶ ህይወትን እንደወጉ ለመምራት ሸክምን የሚያቀሉ፣ ችግርን የሚጋሩ ልበ ቀና ወገኖች ሊኖሩ ይገባል። አሰገደችን የመሰሉ ኑሮና ችግር የፈተናቸውን እናቶች ለመጎብኘትም ረጅም ቀጠሮና የዓመታት ዕቅድ አያሻም። እግሮች ወደ እነሱ ደጃፍ ይደርሱ ዘንድ ሰው መሆን ብቻውን በቂ ነው።አዎ! ሰው መሆን ብቻ።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 2 ቀን 2014 ዓ.ም