እኛ’ኮ ታዛቢዎች ነን፡፡ መታዘብን የባህል ያህል የተላመድን፤ የምንታዘበው ነገር የበዛ፤ ትዝብታችን በራሱ የሚያስተዛዝበን ታዛቢዎች ነን። እስኪ አስቡት ስልክ ደውለን “ታዘብኩህ” የሚል ድንቅ ልማድ ያለን እኛ’ኮ ጥሩ ታዛቢዎች ነን። ልክ ታዛቢ አድርጎ የሾመን ያለ ይመስል የራሳችን ትዝብት እራሱ የሚታዘቡትን ያህል ከፍ አድርገን በየአጋጣሚው የምንታዘብ ነን። ይሄኔ “ደሞ ማንን ታዝቦ ይሆን?…” ብላችሁ እየታዘባችሁኝ ይሆናል። እኔ ግን ታዘቡኝ እንጂ ትዝብቴን ከማካፈል ወደ ኋላ አልልም።
ዛሬ አለቆችን እንማ እንዴ?… እንሸርድድ? … ምን? ኧረ! አይባልም! መሸርደድ አያቃናው፤ መታማት አያንጸው! ባይሆን እስኪ ስለ አለቆች ባህሪይ እያወጋን ድርጊታቸውን እንታዘብ። በትዝብታችንም ስህተታቸውን እንዲያደበዝዙት እየመከርን መልካም ስራቸውን እናድምቅ።
በጎ አለቆች በጎ ስራና የስራ ቦታ መፍጠር እንደሚችሉ ሁሉ፤ በጎነት የራቃቸው አለቅነትን ብቻ የሚያስቡና በነገሮች ሁሉ የላቁ የሚመስላቸው ለቆች ደግሞ ስራና የስራ ቦታ ድባብን ያጠለሻሉ።
ለነገሩ በዚህች ምድር ላይ አለቃ ያልሆነ የለም። ሁሉም በየደረጃው የመሪነትን ሚና ይወጣል። እኔም፤ አንተም፤ አንቺም፤ እናንተም ለምንሰራው ስራና ለቤተሰቦቻችን፣ ለኑሯችንና ለህይወታችን አለቆች ነን። ለዚህ አለቅነታችንም ኃላፊነት በየደረጃውና በየመድረሻው ተሰፍሮ ተቀምጦልናል። ለአብነትም፤ ባለቤትህ በአንተ ላይ አንተም በእርስዋ ላይ አለቃ ናችሁ። አንተ ለልጆችህ ኃላፊና አለቃ ስትሆን በአንተ መጥፎ ተግባርና ተገቢ ያልሆነ ምግባር ደግሞ ቤተሰብህ ኃላፊ ነው። እናም ከመሪነት የራቀና የሚመራው የሌለው የሌለ ሰው ብቻ ነው።
ወደ ቀደመው ነገሬ ልመለስና ውድ ወዳጄ፤ በስራህ ስኬታማ ነህ?… የምትሰራውስ ስራ ያስደስትሀል?… የስራ ቦታህስ ይናፍቅሀል?… ከሆነ ዕድለኛ ነህ ብዙዎች እንደሚስማሙት ጥሩ አለቃ አለህ ማለት ነው። በተቃራኒው ደግሞ፤ ስራህን ስታስብ ካንገሸገሸህ መስሪያ ቦታህ ስትሄድ እየሰለቸህ ከሆነ አንተ ከውጤት የራቅክና በስራህም የማትደሰት ከሆነ ምክንያቱ አለቃህ ሊሆን ይችላል። በስራ የምትለግምና የተሰጠህን ኃላፊነት በትጋት የማትወጣ ከሆነና ውጤታማ ለመሆን የማትጥር አልምጥ ባህሪይ ካለህ ለውድቀትህ ተጠያቂው አንተው ነህና አንተው ተወጣው።
እኔ ምርጥ አለቃ ገጥሞኝ ያውቃል። ቀና የሆነ ስራን የሚያናፍቅ፣ እሁድ ላይ ቢሮ ካልገባሁ የሚያስብል፣ ስራ መፍጠር የሚችል፣ ስራን ከልብ መስራት የሚያስመኝና ሰርቶ የሚያሰራ አለቃ። ‹‹እንዲህ ብናደርግ መልካም ነው›› የሚል፤ ትዕዛዙ ሁሉ ልስስ ብሎ አድርገው አድርገው የሚያሰኝ። ሃሳቡ ሁሉ የተገራ ሆኖ ብዙ የሚያደምጡት አይነት። በቃ ‹‹አለቃ ብሎ ዝም!›› እንደሚባለው ዓይነት። ታዲያ እሱ አዞ እሱ እንስራ ብሎ የማይፈነቀል ድንጋይ፣ የማይሰራ ስራና የማይታይ ውጤት የለም።
አቤት! ደግሞ አለ አንዳንድ አለቃ … ገና ስራ ከተገባበት ቀን ጀምሮ በንግግሩ አለቅነቱን የሚያሳብቅ፣ ድርጊቱ ሁሉ አለቃ አለቃ የሚሸት፣ መምራትን ሳይሆን መላቁን በማሳየት የተጠመደ፣ ለሚያሰራው ስራ ጥራት ሳይሆን ለእርሱ የሚሰጠውን ክብርና ሙገሳ በታላቅ ጉጉት የሚጠባበቅ፣ ሰራተኞቹን ‹‹ምን ሰራችሁ›› ሳይሆን ‹‹ምን አላችሁኝ›› እያለ የሚያደነቁር፣ የስራውን አቅጣጫው አስቶ ሴራ የሚሸርብ፤ የሚያሰራውን ስራ እኳን በወጉ ያልተረዳና በአለቅነቱ መላቅን ብቻ የሚፈልግ ሲሆንም ታዝበናል።
አንዳንዴ ደግሞ አዲስ ስራ ስንቀይር የሚገጥመን ብዙ ጉድ አለና እስኪ እሱንም
እንታዘብ፤ መቼም ታዛቢ አድርጎን የለ!
አዲስነት ጣጣው ብዙ ነው። ብዙ ነገር ያሳያል፤ በርካታ ቁም ነገሮችን ያስተምራልም ያሳጣልም። ታዲያ አዲስ ቦታ ላይ አዲስ ሆነን ስራ ስንጀምር ከትንሽ እስከ ትልቁ (የስራ መደብ ማለቴ ነው) ሁሉም አዛዥና ፈላጭ ቆራጭ ይሆንብናል። አንተ ለነሱ ምንም የማታውቅ ነህና ያረጀህበትን ስራ እኛ ፈትፍተን እናጉርስህ ሲሉ ይታያሉ። አንዳንድ ጊዜ’ማ ገና ከጅምሩ ያንተ እዚያ ቦታ ላይ መምጣት በእርሱ እንጀራ ላይ እሬት የጨመርክበት ያህል የሚሰማውና ፊቱን ኮሶ የሚያደርግብህም አይጠፋም።
በተለይ’ማ ነባሩ ሰራተኛ ቀድሞ እዚያ ቦታ በመገኘቱ ብቻ በሁሉ ነገር የቀደመ ይመስለዋል። በዚህ ላይ ደግሞ አለቃውም ተጨምሮ በአለቅነቱ መላቁን ብቻ የሚዘምር አይነት አለቃ ከሆነ አንተ በቃ አልቆልሃል ማለት ነው።
ይሁን እንጂ ወዳጄ፤ ይህን አደገኛ አካሄድ አይተህ፣ አይተህ፣ ‹‹በቃ›› ብለህ ካላስቆምክ በስተቀር እስከሚያበቃልህ ድረስ ይቀጥላልና በብርቱ ልትፋለመው ይገባል።
እንግዲህ ውድ አለቃ፤“…መልካም መዓዛ ያለው ሽቶ ለራስህ ስታርከፈክፈው ለሌሎችም ይደርሳል” እንደሚባለው ያንተ ወይም ያንቺ እንዲሁም የናንተ መልካምነት ለሰራተኛው በሙሉ ይተርፋልና መምራታችሁ በጥበብ፣ በፍቅርና በአስተማሪነት ይሁን እንጂ ለመላቅ አይሁን እያልኩ፤ ጥቂት መሰረታዊ ጉዳዮችን ላስታውሳችሁ፡፡
መሪ ስትሆን ቀድመህ የሰዎችን ሃሳብ አድምጥ፤ ሰዎችን በእኩልና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ አስተናግድ፤ የሰውን መብትና ግዴታ አትጋፋ፤ በሃሳብ የምትረታና የተሻለ ሃሳብን አክብረህ የምትገዛ ዴሞክራት ሁን፤ በመጨረሻም ቆራጥና ፅኑ መሆንም የአንተ ልዩ ብቃት ሊሆን ይገባልና ዘወትር ተግብረው።
እንግዲህ ስራና አለቃ የማይነጣጠሉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች እንደመሆናቸው ለዛሬው አለቃን እንዲህ ታዘብነው እንጂ ትዝብትማ ሞልቷል፡፡ መቼ ድሮ ቀረ ብላችሁ ነው። ባለፍን ባገደምን ቁጥር አይደል እንዴ የምናየው የምንሰማው ሁሉ “ጉድ” እያስባለን፤ እያስገረመንና እያስደመመን ያለው … ታዲያ ‹‹ጉድ›› የሚያስብል ነገር በሞላበት ሀገር መታዘብን ማን ይከልክለን ትላላችሁ…ማንም! ማንም አይከለክለንምና በቀጣዩ ጊዜ ቀጣይ ተቀጣጣይ ትዝብቶችን ይዘን እስክንመለስ እናንተም መታዘባችሁን ቀጥሉ እያልን ተሰናበትን።
አዲስ ዘመን መጋቢት 18/2018
በተገኝ ብሩ ���������X3vE���