በ1957 ዓም የታተሙትን የአዲስ ዘመን ጋዜጦች መለስ ብለን በመቃኘት ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት የነበሩ ዘገባዎችን ተመልክተን ለዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ አምዳችን በመቀጭንጨብ አቅርበናቸዋል። በወቅቱ አሁን ከጀመርነው ክረምት ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ ዛፎች ለመትከል ከሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የሚያሳዩ ዘገባዎችን ተመልክተናል። በባሌ በርካታ ችግኞች እንደሚተከሉ የሚነግረን ዝርዝር ዘገባ፣ የሚተከሉትን የችግኝ ዓይነቶች ብዛት ይገልፃል። እንዲሁም ተማሪዎች ክረምቱን በእንዝላልነት እንዳያሳልፉ በአዲስ አበባ በተወሰኑ ትምህርት ቤቶች መማር ለሚፈልጉ ማጠናከሪያ ትምህርት ለመስጠት መታሰቡንና ሌሎች ዘገባዎች መርጠን እንድታነቡት እነሆ ብለናል።
ለባሌ ዛፍ ተካዮች ፬፻፳ ሺህ ችግኞች
የባሌ ጠቅላይ ግዛት የእርሻ ሚኒስቴር ተጠሪ ፬፻፳ ሺህ የዛፍ ችግኞች ማዘጋጀቱን ኢ-ወ-ም ገልጧል፤ ችግኞቹ በቅርብ ጊዜ ለተካዮች ይታደላሉ።
ለመታደል የተዘጋጁት ችግኞች ፪፻፶ ሺህ የባህር ዛፍ ፩፻፶ ሺህ የውጭ አገር ግራር ፴ሺህ የውጭ አገር ጥድ ፴ሺህ ያገር ውስጥ ጥድ ፲ ሺህ ዝግባ ናቸው።
ከነዚህም በቀር የጓሮ አትክልት ችግኞች የተዘጋጁ በመሆናቸው እነዚህ ችግኞች ለገበሬዎች እንደሚታደሉ የጠቅላይ ግዛቱ የእርሻ ሚኒስቴር ሥራ አስኪያጅ አቶ ኃይለ ገብርኤል ሀብተማርያም ገልጠዋል።
(ሰኔ 20 ቀን 1957 ዓ.ም የወጣው አዲስ ዘመን)
ተማሪዎች እንዳይማግጡ የክረምት ትምህርት ቤት ይከፈታል
የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርስቲ በሚመጡት የክረምት ወራት ማለት ከሐምሌ ፭ ቀን እስከ ጳጉሜ ፫ ቀን ፶፯ ዓ/ም/ በአዲስ አበባ በሚገኙት ልዩ ልዩ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ለወጣቶች ለሌሎችም መማር ለሚፈልጉ ሁሉ ትምህርት ይሰጣል። የትምህርቱም ደረጃ ከአንደኛ ክፍል እስከ ስምንተኛ ክፍል ሲሆን ትምህርቱንም የሚሰጡት የዩኒቨርስቲ ትምህርት ያላቸው አስተማሪዎች መሆናቸው ታውቋል።
የፕሮግራሙ ዋና ዓላማ ወጣቶች በክረምት ወራት ጊዜያቸውን ሳያባክኑ በጠቃሚ ትምህርት ላይ እንዲያውሉት ማድረግ ነው። ተማሪዎቹ በልዩ ልዩ ምክንያት ሳይማሩ የቀረባቸውንም ትምህርት በክረምቱ ወራት ለመማር እንዲችሉ፤ደካማ የሆኑበትንም ትምህርት በጠለቀ መንገድ እንዲያሻሽሉ፤ በአሰልቺዎቹ የክረምት ወራት ያለምንም ሥራ ከቤት ውለው ዘመዶቻቸውን ከማስቸገርና ዘወትር በተጠሉና በማይፈለጉ ሥራዎች በመዋል መጥፎ ጠባይና ዓመልን ከመቅሰም እንዲታቀቡ ለማድረግ ዩኒቨርስቲው ያቀደው ፕሮግራም ዓይነተኛ መፍትሔ መሆኑ አይጠረጠርም።
ትምህርት ለጊዜው በአምሐ ደስታ፣ በዳግማዊ ምኒሊክ፣ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ተመላላሽ በአስፋው ወሰን፣ በሽመልስ ሀብቴ፣ በወይዘሮ ቀለመወርቅ፣ በልዑል መኰንንና በመድኃኒዓለም ትምህርት ቤቶች ውስጥ ይሰጣል። አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ሌሎች ትምህርት ቤቶች በተጨማሪ የሚከፈቱ መሆናቸው ይታመናል። ትምህርት ቤቶቹ የሚሰጡዋቸው የትምህርት ዓይነቶች አማርኛ፣ ሂሳብ፣ እንግሊዝኛ፣ ኅብረ ትምህርትና (ሶሺያል ስተዲስ) ሥነ ፍጥረት ናቸው።
የትምህርት ቤቶቹ ጠቅላላ አመራርና የትምህርት አሰጣጥ በዩኒቨርስቲውና በትምህርት ሚኒስቴር የቅርብ ተቆጣጣሪነት ሥር እንደሚሆን ታውቋል።
በነዚህ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ተመዝግበው ትምህርት ለመቀጠል የሚሹ ሁሉ በየወሩ ፬ (አራት ብር) መክፈል ይኖርባቸዋል። በዚህ ዓይነት የተገኘው ገቢ ትምህርት ቤቶቹን ለማካሄድ በቂ ሆኖ ካልተገኘ የሚቀረውን ዩኒቨርስቲውና የትምህርት ሚኒስቴር ለመክፈል ቃል መግባታቸውን የዩኒቨርስቲው የተማሪዎች ዲን ጽ/ቤት የወጣው መግለጫ አስገንዝቧል።
የትምህርት ሚኒስቴር ለመማሪያ የሚያገለግሉ መጻሕፍትን ለዩኒቨርስቲው ለመስጠት ተስማምቷል። ዩኒቨርስቲውም ትምህርቱን የሚያቀርበው ሚኒስቴሩ ባወጡት ካሪኩለም መሠረት እንደሚሆን ታውቋል።
(ሰኔ 19 ቀን 1957 የወጣው አዲስ ዘመን)
፭ የውጭ ሀገር በጎች በ፭ሺ ብር ተገዝተው መጡ
አምስት በጎች በአምስት ሺህ ብር ከፈረንሳይ ሀገር ተገዝተው ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል ፤በጎቹ የተገዙት በባሌ ግዛት ለተቋቋመው የበግ ርባታ ሥራ ነው። እነዚህ ከፈረንሳይ ሀገር የተገዙት አምስት በጎች በዓለም የታወቁት የበግ ዘሮች ውስጥ ምርጥ የሆኑት ናቸው።
እነዚህ በጎች በሀገራችን ካሉት በጎች ጋር ተደባልቀው ዘራቸው በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲባዛ ታስቦ የተገዙ ናቸው፤ለሱፍ ጠጉር ሥራ የሀገራችን በጎች ከውጭዎች ጋር በማዳቀል ጥሩ ጠጉራም በጎችን ለማግኘት በቅርብ ግዜ ምርጥ የሆኑ በጎች ከኬንያ ተገዝተው በባሌ ጠቅላይ ግዛት ለተቋቋመው የበግ ርባታ ሥራ እንደሚደርሱ ታውቋል።
የበጎቹ ርባታ ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ዋርት በባሌ ጠቅላይ ግዛት የተጀመረው የበግ ርባታ ሥራ በሚገባና ተስፋ ባለው ሁናቴ እንደሚካሄድ ገልጠዋል፤ለርባታው ሥራ አሥር ሺህ ያገር ውስጥ በጎች በተጨማሪ ለመግዛት ማስፈለጉንም ሚስተር ዋርት ተናግረዋል።
(ግንቦት 26 ቀን 1957 ዓ.ም የወጣው አዲስ ዘመን)
ሰውየው አንበሳውን በንክሻ አሸነፈ
ሉሲዮና ጃአኮም ቻንሳ የተባሉ ወንድማማቾች በአንጎላ ውስጥ በሚያድኑበት ወቅት አንድ አንበሳ ሉሲያን ይዞ እመሬት ላይ ጥሎት ነበር።
ሉሲያም በአንበሳው በተያዘ ጊዜ በእጁ ጠብመንጃ ባለመያዙ አንበሳውን ለመከላከል አልቻለም። ግን ወንድሙ ደርሶ አንበሳው ጀርባ ላይ በመሆን አንበሳውን ከወንድሙ ለማላቀቅ ሞከሮ ሳይሆንለትም ቀረ።
በመጨረሻም ጃኢኪዮ ቻንሳ ወንድሙን ለማዳን ያደረገው ትግል ስላልተሳካት የአንበሳውን አፍንጫ ነከሰው፤በዚህ ግዜ አንበሳው የያዘውን ሉሲዮንን ስለለቀቀው፤ሊሲዮ ተነስቶ አንበሳውን በወንድሙ ጠብመንጃ ሊገድለው ችሏል።
ሁለቱ ወንድማማቾች ሰውነታቸው ስለተጫጫረ በሆስፒታል ውስጥ በመታከም ላይ ናቸው፤ ቁስላቸውም የማያሰጋ መሆኑንን ሮይተርስ አስረድቷል። (ሰኔ 23 ቀን 1957 ዓ.ም የወጣው አዲስ ዘመን)
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ሰኔ 28 /2014