የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃ በሀገር ሕልውና እና በሕዝቡ ደህንነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው። በሚሰራጩ ሐሰተኛ ዘገባዎች ሰዎች በማንነታቸው እንዲሁም በሚከተሉት እምነታቸው ጥቃት እየደረሰባቸው ይገኛል። በመሆኑም የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ ተፈጻሚ መሆን አለበት የሚሉ አስተያየቶች በርክተዋል። በሌላ በኩል የሕጉ ተፈጻሚነት የመናገር መብትን እንዳይገድብ ያሰጋል የሚል አስተያየት የሚያነሱም አልጠፉም ።
የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር አዋጅ ቁጥር 1185/2012 ወጥቷል። አዋጁ የወጣው ሆን ተብሎ የሚሰራጩ የጥላቻና ሐሰተኛ ንግግሮችን በሕግ መከላከልና መቆጣጠር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ነው። በአዋጁ ላይ እንደተመላከተው የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት ለማኅበራዊ ስምረት፣ ለፖለቲካ መረጋጋት፤ ለሀገራዊ አንድነት፣ ለሰብዓዊ ክብር እና ለእኩልነት ጠንቅ መሆኑን በመገንዘብ ነው። እንዲሁም መሠረታዊ መብቶች ላይ የሚጣሉ ገደቦች በሕግ የተደነገጉ፣ በዲሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ ውስጥ ተቀባይነት ያለውን ዓላማ ለማሳካት አስፈላጊ የሆነ ተመጣጣኝና በጠባቡ የተበጁ መሆን እንዳለባቸው በመገንዘብ ነው ይላል።
የፋክት ቼክ መሪ የመረጃ አጣሪ ወይዘሪት ረሆቦት አያሌው በሰጡት አስተያየት፤ ሰዎች በነጻነት ያለገደብ ሃሳባቸውን እንዲገልጹ ይፈለጋል። ይሁን እንጂ ሰዎች በመረጃና ማስረጃ በልምድ ላይ ተመርኩዘው ሳይሆን በስሜትና ስሜት ቀስቃሽ በሆኑ ንግግሮች ሀሳባቸውን ይገልጻሉ። የኅብረተሰቡን የአኗኗር ባህል የሚሸረሽሩ የጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃዎች በተለያየ መንገድ ይተላለፋል። ይሄ በተለይ በአሁኑ ወቅት ትልቅ ፈተና ሆኗል። ሐሰተኛ መረጃዎች በተለይ በስፋት የሚሰራጩት በዩቲዩውብ፣ በቲውተር፣ በቴሌግራም እና በኢንስታግራም ነው። በሌሎች እንደ ቲክ ቶክ ባሉት የመገናኛ ዘዴዎች ይተላለፋል። በመሆኑም ኅብረተሰቡ ይህን መረዳት አለበት። የሚያገኛቸውን መረጃዎችም ለራሱም ሆነ ለሌሎች ከማሰራጨቱ በፊት እውነታውን ማወቅ አለበት። ያገኛቸውን መረጃዎች ሁሉ ከማሰራጨት መቆጠብ ይኖርበታል። በሁሉም የመገናኛ ብዙኃን እና የበይነ መረብ የሚተላለፉ መረጃዎች እውነተኛ ናቸው ብሎ ከመውሰድ መቆጠብ ያስፈልጋል።
አሁን ያለንበት የቴክኖሎጂ ዘመን ነው። ቴክኖሎጂው በስፋትና በብዛት ኅብረተሰቡ ጋር ይደርሳል። ለምሳሌ በሀገራችን የቴክኖሎጂ ተጠቃሚው ቁጥር 25 በመቶ ደርሷል። ይሄ ቁጥር ካለፈው ዓመት ጋር ሲተያይ ዘንድሮ የአምስት በመቶ ብልጫ አሳይቷል። ይሄ ማለት እስማርት ስልኮችን በመጠቀም ኅብረተሰቡ በቀላሉ እጁ ላይ መረጃዎችን ያገኛል ማለት ነው። የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ደግሞ በሕዝቡ ተቀባይነት አላቸው ። በመሆኑም የተገኘው መረጃ ሁሉ ትክክል መሆን አለመሆኑን ማጣራት እንደሚያስፈልግ የመረጃ ማጣራት ባለሙያዋ ይናገራሉ።
ሌላው አስተያየታቸውን የሰጡት የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዚዳንትና የአሀዱ ሬዲዮ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ ናቸው። እርሳቸው እንዳሉት የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃ ከሚሰራጭባቸው መንገዶች አንዱ አሁን ከብሔርና ከሃይማኖት ጋር በተያያዘ ወገንተኝነትን ይዘው በተቋቋሙ መገናኛ ብዙኃን ነው። እነዚህ መገናኛ ብዙኃን የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ይዘው የተፈጠሩ ናቸው። ቀደም ሲል የነበሩት ደግሞ ወደ አንድ የመንግሥት ጎን ያደሉ ናቸው።
አሁን ላለንበት ሁኔታ ሌላው ችግር ቀደም ሲል የተፃፉ ታሪኮች፣ ፊልሞች እና መሰል ነገሮች ናቸው። በባህላችን በብዙ መጽሐፍት የተጻፉትን ፣ሙዚቃዎች የግጭት መነሻ አድርገዋል። ብዙ የኢትዮጵያ ታሪክ እና ባህል የተጻፈውም በውጪ ጸሐፍት ነው። ስለዚህ ባህሎቻችንና ታሪኮቻችን መታየት አለባቸው ሲሉ ጋዜጠኛ ጥበቡ ይጠቅሳሉ። ባለፉት 25 ዓመታት ጋዜጠኞች ታስረው የነበረው በፃፉት ውሸት ሳይሆን በሠሩት እውነት ነበር ሲሉ ይሞግታሉ። አሁን ደግሞ በመደበኛ ሚዲያዎችም ቢሆን ባለስልጣናት የሚናገራቸው ከፍተኛ የጥላቻ መርዝ ያለባቸው ንግግሮች የሚተላለፉበት ሁኔታ አለ። ይሄም ቢሆን ትኩረት ሊሰጠው ይገባል የሚል እምነት አላቸው።
በፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የሕግ ጥናትና ማርቀቅ ዳይሬክተር ጀነራል አቶ በላይሁን ይርጋ እንዳሉት፤ ለሰው ልጆች ከተሰጡት መብቶች መካከል የመጀመሪያው ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ነው። ይሄ ያለገደብ የሚፈጸም መብት ነው። ሆኖም ግን በልዩ ልዩ ሁኔታ ያለ ገደብ ሀሳብን መግለጽ ሊያደርሰው ከሚገባ ጉዳት አንጻር ተመጣጣኝ በሆነ መልኩ ሊገደብ ይችላል። ክብረ ነክ፣ ባለስልጣናት ላይ ጥርጣሬ እንዲኖር የሚያደርግ፣ ጥላቻን የሚያሰፋ፣ አንዱን ሃይማኖት በሌላው ላይ የሚያነሳሳ ፣ አንዱን ብሔር ከሌላው ጋር የሚያጋጭ እንዳይሆን በመጠኑ በሕግ ገደብ ሊጣልበት ይገባል።
ለምሳሌ በጀርመን ሀገር ሂትለር በአይሁዶች ላይ ከነበረው ጥላቻ በመነሳት በርካቶች እንዲገደሉ ተደርጓል። ሰዎቹ እንዲሞቱ ከመደረጉም በላይ በሰውነታቸው ውስጥ ያለው ስብ ተወስዶ ሳሙና እንዲሠራበት ሆኗል። ይሄ እጅግ ከሰብዓዊነት የወጣና ጭካኔ የተሞላው ዘግናኝ ድርጊት ነው።
እንዲሁም በሩዋንዳ በቱትሲ እና ሁቱ ጎሳዎች መካከል የተፈጠረው የእርስ በእርስ የዘር ማጥፋት ዘመቻ በበርካታ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል። ይሄ በታሪክ ተመዝግቦ ያለ ነው። በሀገራችንም በተለያየ ከማንነትና ከሃይማኖት ጋር ተያይዞ የተፈጸሙ ክስተቶች አሉ። ይሄ ከሐሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግር ጋር ተያይዞ የተፈጠረ ክስተት ነው፤ ሀገራችንም ችግሩን በዚህ መልኩ ካልተቀበለችውና የሕግ ተጠያቂነት ካልሰፈነ ችግሩ የከፋ ደረጃ ላይ ይደርሳል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ እየተለማመደችው ባለው አዲስ የዴሞክራሲ ሥርዓት ጽንፈኝነትና አሸባሪነት ጎልቶ እየታየ መምጣቱን አንስተዋል። በዚህ የዴሞክራሲ ሥርዓት ውስጥ የሚስተዋለው ውጥረት «አዲሱ ተለምዶ» መሆኑን ያሳያል ብለዋል።
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ ኢትዮጵያ ከመረጃ ቴክኖሎጂ በኋላ ድህረ እውነትና አዲስ የዴሞክራሲ ልምምድ እያደረገች ትገኛለች። በዚህም ሁኔታ እንደ ፖለቲከኛ፣ አክቲቪስትና ማኅበራዊ ሚዲያ ያሉ የተከፋፈሉ ኃይሎች ተፈጥረዋል። ይህ ለአገሪቷ አዲሱ ተለምዶ ሲሆን፣ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችና ውጥረቶችም በአዲሱ የዴሞክራሲ ሥርዓት የተፈጠሩ ናቸው። ዴሞክራሲያዊ ባልሆነ ሁኔታ ውስጥ እነዚህ እውነታዎች የሉም፤ በዚህ የልበ ሰፊነት የዴሞክራሲ ልምምድ ውስጥ ሐሰተኛ መረጃዎች መስፋፋት ችለዋል።
በኢትዮጵያ የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃዎች ስርጭት ለፖለቲካ አለመረጋጋት፣ ለአገራዊ አንድነትና ለሰብዓዊ ክብር ጠንቅ በመሆናቸው፤ የሐሰት መረጃንና ጥላቻ ንግግር የሚያሰራጩትን መቆጣጠር አስፈላጊም እና ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን አስምረውበታል።
በሀገራችን የቴክኖሎጂ መስፋፋት አለ። የቴክኖሎጂ እድገቱ ትክክለኛ መረጃ ከማግኘት ይልቅ ስሜት ኮርኳሪና ሐሰተኛ መረጃዎች እንዲበዙ በር ከፍቷል። ይህንን በመታገልና የመረጃዎችን እውነትነት በመመርመር ጠንካራ አገር መፍጠር ይገባል ሲል ነው የተከራከሩት።
አሁን ያለንበትን ምህዳር መረዳት ያስፈልጋል፤ ሐሰተኛ መረጃ ዓለምአቀፋዊ ነው። አንዳንዴ በዲጂታል ቴክኖሎጂው ከውጪ የሚመጡ መረጃዎች አሉ። ዓለምአቀፉን ማኅበረሰብ ለማሳሳት የሚፈበረኩ መረጃዎችም እንደሚኖሩ መረዳት ይቻላል። ሁሉንም ደግሞ መቆጣጠርና መከላከል አዳጋች መሆኑ ይናገራሉ።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ እድሪስ በበኩላቸው፣ የአገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት እንዲጎለብት የሀሳብ ነፃነት ከፍተኛ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሐሰተኛ መረጃና ጥላቻ ንግግር እየተስተዋለ እንደሚገኝና ለእዚህ ደግሞ የሕግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ ምክክር እየተደረገበት መሆኑን ነው ያስታወቁት።
በኢትዮጵያ እየተስተዋለ ያለው የሐሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግር ስርጭት እየሰፋና በሕዝብ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው። ይህም የመረጃ አካላት ትክክለኛውን መረጃ በወቅቱ ባለማድረስ እንደሚፈጠርና በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ እንቅፋት እየሆነ መምጣቱን አንስተዋል።
ሐሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግር የአገር ግንባታን ሊፈትን ስለሚችል ችግሩን ለመግታት የሚያስችሉ የሕግ ማዕቀፎችን ለኅብረተሰቡ ማስገንዘብ እንዲሁም ተጠያቂነትን ማስፈን ላይ በትኩረት መሥራት ያስፈልጋል ሲሉ የመፍትሔ ሀሳብ ያሉትን አቶ መሐመድ ጠቁመዋል።
ዶክተር ለገሰ ደግሞ፤ ሐሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግርን ለመታገል የመፍትሔ ሀሳብ በማለት የጠቀሱት በቅድሚያ የኅብረተሰቡን ንቃተ ሕሊና ማሳደግ ላይ መሥራት ነው ። ኅብረተሰቡ በሐሰተኛ ወሬዎች እንዳይወሰድ፣ እውነት እና ሐሰት የሆኑ ነገሮችን መለየት እንዲችል ግንዛቤውን ማሳደግ ዋነኛ ጉዳይ መሆን አለበት ብለዋል።
በመረጃ ተቀባይና በመረጃ አጋሪው ዘንድ ያለውን ክፍተት እንዴት እንሙላው በሚለው ዙሪያ ወይዘሪት ረሆቦት የመፍትሔ ሀሳብ ያሉትን አጋርተውናል። አንደኛ ተማሪዎች በትምህርት ቤት ደረጃ ሐሰተኛውን መረጃ ከእውነታው እንዴት መለየት እንደሚችሉ እውቀቱ እንዲኖራቸው ማድረግ፤ ዋና ዋና የሚባሉ መደበኛ መገናኛ ብዙኃን ደግሞ ትክክለኛውን መረጃ በፍጥነት መስጠት እንዲሁም የመረጃ ማጣራት ተቋሞችን በማስፋፋት መረጃዎችን በፍጥነት አጣርቶ እውነታውን ለሕዝቡ ማሳወቅ ይገባል። አሁን ባለው ሁኔታ በሀገር ቤት ሁለት ሀገር በቀል የመረጃ ማጣራት ሥራ የሚሠሩ ተቋማት ብቻ ናቸው ያሉት። በመሆኑን ሁሉንም ሐሰተኛ መረጃዎች አጣርቶ እውነታውን ማሳወቅ አይቻልም ብለዋል።
ሁሉም አስተያየት ሰጪዎች የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃ ሕዝብንና ሀገርን እየጎዳ መሆኑን፤ በሚሰራጩ ሐሰተኛ መረጃዎች ምክንያት በሀገራችን እጅግ አስከፊና አሳዛኝ ጭካኔ የተሞላባቸው ጥቃቶች ሃይማኖትንና ማንነትን መሠረት አድርገው መፈጸሙን ተስማምተውበታል። በመሆኑም ይሄ ጥፋት አሁን ካለው በላይ ተስፋፍቶ እንዳይቀጥል ሕዝቡ ሐሰተኛ መረጃዎችንና የጥላቻ ንግግሮችን መለየት እንዲችል ከስር ጀምሮ ማስተማር፣ ንቃተ ሕሊናውን ማሳደግ እንዲሁም ሕዝብን ከሕዝብ፤ ሃይማኖት ከሃይማኖት ለማጋጨት በሚሠሩት ላይ ደግሞ በሕጉ መሠረት እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል።
ባለሙያዎቹ የሰጡት ሀሳብ በፍጥነት የማይከናወን ከሆነ ግን አሁን ከሚታየውና ከሚሰማውም በላይ የሀገርን አንድነት እና የሕዝቦች ማኅበራዊ መስተጋብር ፈተና ውስጥ የሚከት ይሆናል። ሀገርም ለብተና ይዳርጋል።
አልማዝ አያሌው
አዲስ ዘመን ሰኔ 28 /2014