
አበባ፦ “ኢትዮጵያን ለነገው ትውልድ ስናስረክብ ምቹ የመኖሪያ አካባቢን ጭምር መሆን እንዳለበት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ አሳሰቡ። ሚኒስትሩ በቦሌ ክፍለ ከተማ የ10 አቅመ ደካሞች ቤቶች እድሳት መር ሀ ግብርም አስጀምረዋል።
የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች የ4ኛ ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን በፒኮክ መናፈሻ ከ1000 በላይ ችግኞች በመትከል አስጀምረዋል፡፡ ከሶስት ዓመት በፊት ስለአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ ሲወራ ጊዜያዊ ይመስል ያሉት ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ ዛሬ ላይ ከህጻናት እስከ አዛውንቱ ስለ ችግኝ መትከል እና በባለቤትነት የመንከባከብ ግንዛቤ ተፈጥሯል ብለዋል። በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያውያን አዛውንቶች እና የሃይማኖት አባቶች በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ እየተሳተፉ መሆናቸውንም አመላክተዋል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴርም የዚህ አካል መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ውሃ ሕይወት እንደሚሰጥ ሁሉ ለራሱም ሕይወት ይፈልጋል፤ ውሃ ሕይወት እንዲኖረው ከፈለግን ለሰው ብቻ ሳይሆን ለውሃም ምቹ አካባቢ መፍጠር ይገባል ብለዋል፡፡
አካባቢን ማልማት ችግኞችን መትከል፣ ተፋሰሶችን መጠበቅ፣ ምንጮች እንዲጎለብቱ ማድረግ የውሃ ሀብት ለማልማት አስፈላጊ እንደሆኑም ጠቁመዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የ10 አቅመደካሞችን ቤት የማደስ እና በቀን አንድ ጊዜ መብላት ለማይችሉ 20 አቅመ ደካማ እማወራዎች የማዕድ ማጋራት ሥራም አከናውኗል፡፡
የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ አራት ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ትዕግስት ለገሰ በበኩላቸው እንደገለጹት የአቅመ ደካማ ቤቶችን በማደስ ስራ ከሌሎች ባለሀብቶች እና በጎ ስራ ከሚሰሩ የሃይማኖት ተቋማት ጋር በመሆን በወረዳው 50 ቤቶችን ለማደስ ታቅዶ 30 ቤቶችን የማደስ ስራ ተጀምሯል ብለዋል። ከእቅድ በላይ ለመስራት ፍላጎት እንዳለም ጠቁመዋል።
“ምግቤ ከበሬ” በሚለው መርሀ ግብርም የኑሮ ውድነት ጫናውን ለመቋቋም እና የገቢ ምንጭ ለመጨመር የሚያስችል እና አነስተኛ ኑሮ ላይ የሚገኙ የወረዳው ነዋሪዎችን የማገዝ ስራ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
በወረዳው በአራተኛው ዙር ከ20 ሺህ በላይ ለመትከል የታቀደው ተግባራዊ ሆኗል ያሉት ከ500 በላይ አቅመ ደካማ እና በዝቅተኛ ኑሮ ደረጃ የሚገኙ እናቶች ፣ ወላጅ አልባ ሕጻናት፣ ኤች አይቪ ቫይረስ በደማቸው ለሚገኝ ህጻናት እና ለአካል ጉዳተኞች ማዕድ የማጋራት ስራ በተከታታይ የሚደረግ መሆኑንም አመላክተዋል።
በኃይሉ አበራ
አዲስ ዘመን ሰኔ 27/2014