
አዲስአበባ፡- ኢንዱስትሪዎች የሚለቁትን በካይ ጋዝ ለመከላከል ችግኞችን በብዛትና በዓይነት መትከል ግድ እንደሚል የኢንduስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል እንደተናገሩት በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚካሄደውን የችግኝ ተከላ መርሃግብር ባለፈው ቅዳሜ ባስጀመሩበት ወቅት እንደተናገሩት፤ ኢንዱስትሪዎች አካባቢን በመበከል ረገድ በቀዳሚነት የሚሰለፉ በመሆናው በሚገነቡባቸው አካባቢዎች በታቻለ መጠን የሚያመነጯቸውን የካርቦንዳይ ኦክሳይድ በካይ ጋዞች ለመቀነስ ችግኞችን መትከል ይገባል፡፡
በኢንዱስትሪ ፓርኮች የችግኝ ተከላ ስራን በመጀመራችን ብዙ ትርጉም አለው ያሉት አቶ መላኩ፤ ይህም ከኢንዱስትሪዎች ልማት ጋር አብረን አረንጓዴ ኢኮኖሚን እንድንገነባ ያስችለናል ብለዋል፡፡
በተለያዩ ጊዜያት የተሰሩ ስራዎችም ጥሩ ውጤት ላይ ያሉ መሆናቸውን በመጠቆም የበለጠ አጠናክሮ መሄድ መቻል አለብን ሲሉ አቶ መላኩ ተናግረዋል፡፡
ኢንዱስትሪዎች አካባቢያቸው ለሰራተኞቻቸው ሳቢና ማራኪ፣ ለስራ ምቹ እንዲሆኑና የሚያመነጩትን በካይ ጋዝ ወደራሳቸው ሊመጡ የሚችሉ ዛፎችን እየተከሉ እንዲሄዱ ማድረግ ባህል እንዲሆን የማስተማር ሥራ መስራት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
አገራችንና ዓለማችን ትልቁ ችግር እየሆነ ያለው የተፈጥሮ ሀብት መራቆት ነው ያሉት ሚኒስትሩ፣ ያንን ተከትሎ የሚመጣው የአየር ንብረት መዛባት፣ ድህነት፣ የፖለቲካ ቀውሰ፣ አብዛኞቹ ነገሮች ከድህነትና አየር ንብረት መዛባት ጋር ተያይዘው የመጡ ናቸው ብለዋል፡፡
እንደ አገር የጀመርናቸው የልማት ስራዎች ሊሳኩ የሚችሉት የዜጎችና አገልግሎት ዘርፉ ላይ ያሉት ሰራተኞች ቀናነትና ትብብር ሲኖር ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ አገርን ለመለወጥ፣ ለማልማት፣ ለማሳደግ፣ ሳንታክት ከሰራን አሁን ካለንበት የኑሮ ውድነት፣ የፀጥታ ችግር፣ የውስጥና የአጎራባች አገራት ትንኮሳና ችግሮችን መቀለበስ እንችላለን ብለዋል፡፡
በአገራችን እየተስተዋሉ ያሉት ግጭቶች ምንጭ የኢኮኖሚው አለማደግ ነው፡፡ ሀገርን ለማሻሻል ኢንዱስትሪዎቻችን መሻሻል አለባቸው፣ ይህ ደግሞ የሁሉም ኃላፊነት ነው፣ ለአገራችን ሁሉንም ዋጋ ከፍለን ኃላፊነታችንን መወጣት አለብን ሲሉ አቶ መላኩ በአጽኖት ተናግረዋል፡፡
በ2013ዓ.ም በመስሪያ ቤቱና ተጠሪ ተቋማት አመራሮችና ሰራተኞች በአረንጓዴ አሻራ ከተተከለው ችግኝ ውስጥ 82 በመቶ በላይ የሚሆነው መጽደቁን ገልጸው፣ የትላንቱንና መሰል የአረንጓዴ አሻራ የማሳረፍ መርሀ-ግበር በሌሎችም የኢንዱትሪ ፓርኮች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል፡፡
ሙሳ ሙሐመድ
አዲስ ዘመን ሰኔ 27/2014