ፋሽን ከወቅት ጋር ያለው ቁርኝት እጅጉን የጠበቀ ነው። ዋነኛ የፋሽን ባህሪያት ከሆኑት ጉዳዮች ውስጥ ወቅታዊነት አንዱ ነውና ዘመን፣ ቦታና ሁኔታ የሚሉት ጉዳዮች ይገለጡበታል። አንድ ፋሽን በየትኛው ዘመን በነበሩ ሰዎች ይዘወተራል፣ አልባሳት ከሆነ በየትኛው ወቅት ይለበሳል ወይም መዋቢያ ይሆን ነበር። የትኛው ቦታና በምን ሁኔታስ ይዘወተር ነበር? የሚሉት ጥያቄዎች ፋሽን ከወቅት ጋር ያለውን ጥብቅ ትስስር በግልጽ የሚያመላክቱ ናቸው።
ለዚህም ነው አንድን ፎቶ ግራፍ ወይም ተንቀሳቃሽ ምስል ስንቃኝ፤ ከአለባበሱ ተነስተን በየትኛው ዘመን ላይ እደነበር ለመገመት የምንችለው። በዚያን ወቅት ብዙ ሰዎች የሚያዘወትሩትና አምረው ተውበው ይታዩበት የነበረውን ፋሽን ተመርኩዘን ከዘመኑ ጋር እናስተሳስረዋለን። አለባበስ ብቻም ሳይሆን የጸጉር ቁርጥና አሰራር፣ የሜካፕ አጠቃቀምና አጋጌጥም፤ ዘመን በፋሽን ውስጥ በተለየ መልክ እንደሚታይ፣ ፋሽንም በዘመን ውስጥ የሚያልፍና የሚቀያየር ለመሆኑ ማሳያ ናቸው።
አንድ ፋሽን በፋሽንነቱ ተለምዶ በብዙዎች ይዘወተር ዘንድ መነሻ የሚሆኑ በርካታ ምክንያት ይኖሩታል። መቼና የት ተፈጠረ? እንዴትስ ተስፋፋ? የሚሉት ጥያቄዎች ደግሞ ለዚህ ምላሽ ይሆናሉ። አሁን አሁን ብዙዎቻችን አውቀን አልያም ሳናውቀው የፋሽን ዘርፉ ተካፋይና በፋሽን አልባሳት የምንዋብ ሆነናል። ወቅቱን ጠብቀን ሽክ ማለት፣ የአየር ጠባዩንም ለይተን በመልበስ ማጌጥና መዘነጥ እያዘወተርን ነው። የክረምት ወቅትን ደረብረብ አድርገን ብርዱን የተከላከልንበትንና ወፍራም ገበር ያለውን ሙቀት የሚጠብቅ ልብስ፤ የጸደይ ወቅት ብቅ ሲል መቀየር የግድ ይለናል።
በጋ ላይ ደግሞ ሙቀትን የሚቋቋም ሳሳ ያለ፣ ከቅለቱ ባሻገር ስንለብሰውም የሚያዘንጠንን ልብስ ከመደርደሪያችን መምረጥ፤ ከሌለንም ወደ መሸጫ ሱቆች ጎራ ማለታችን አይቀርም። ወቅት ለፋሽን መለያ ባህሪው ነውና በእርግጥም ወቅቱን መምሰል ራሳችንን ከሁኔታዎች ጋር ከማዋደዱም ባለፈ ዘናጭና ከጊዜው ጋር የምንራመድ ያደርገናል።
ወቅት ከፋሽን ጋር ያለው ጠንካራ ቁርኝት በሌሎች ጉዳዮች እንደሚወሰንም የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ። ባህል፣ እምነት፣ የአኗኗር ሁኔታ፣… ከተጽዕኖ አሳዳሪ ምክንያቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው። ምን በምን አይነት ቦታዎች ላይ ይለበሳል የሚለውን ጨምሮ፤ የዘወትር፣ የበዓል አሊያም ሁነቶችንም መሰረት ያደርጋል። ቀን፣ ማታ፣ ጸደይ፣ በጋ፣ ክረምት የመሳሰሉትም እንደ አየር ንብረቱና ወቅቱ አለባበሳችንን ሊወስኑ ይችላሉ። ፋሽንም እነዚህን መሰረት አድርጎ፤ የማህበረሰቡን ባህል፣ እምነትና ልማድ መሰረት ባደረገ መልኩ ይተገበራል።
የፋሽን ዲዛይነርዋ ስምረት ኃይሌ ለሁለት ዓመት በፋሽን ዲዛይን ሙያ ስትሰራ ቆይታለች። ባለሙያዋ ከአየር ንብረት ጋር የሚሄድ ሲለብሱት እና ሲያጌጡበት ከሰውነት ቅርጽና የአለባበስ ምርጫ ጋር የሚሄድ ፋሽን መከተል የሰዎች ተለምዷዊ ተግባር እየሆነ መምጣቱን ትናገራለች። ማህበረሰባችን ለፋሽን ያለው ምልከታ እያደገ መሆኑን የምታስረዳው ዲዛይነር ስምረት አቅም በፈቀደ መልኩ ወቅቱን እና የአየር ንብረቱን ያገናዘበ አልባሳት በተለይም በከተሜው ዘንድ መለመዱን ታስረዳለች።
ከወቅቱ የአየር ንብረት ጋር ከመስማማቱም ባሻገር ፋሽን በብዙዎች ተመርጦ የሚለበስና የሚዘወተር ሲሆን፤ በወቅቱ ገኖ እንዲወጣ የሚደርገው ግን አልባሳቱን የሚለብሰው ማህበረሰብ ባህል ጋር የማይቃረን ከሆነ ብቻ ነው። ለምሳሌ ዲዛይነሮች የበጋ ወቅት ቀለል ያሉ አልባሳትን ሲያዘጋጁ ወቅቱን ብቻ ሳይሆን ባህሉንም መሰረት ያደረገ ቢሆን ለፈጠራቸው ተቀባይነት አስተማማኝነቱ የቀረበ እንደሚሆን ዲዛይነር ስምረት ታነሳለች። ስለዚህ ባህልም እንደ ወቅት ሁሉ ፋሽን ላይ ትልቅ ሚና ይጫወታል ባይ ናት።
ፋሽን ወቅት መሰረታዊ ጉዳዩ ነው የምትለው ባለሙያዋ ይህንን ያገናዘበ፣ ተወዳጅ የሆነ ቀለምን የተላበሰ፣ በጥሩ ዲዛይነር ባማረ መልኩ ተሰናድቶ ለህረተሰቡ ሲቀርብ የማይወደድበት ምክንያት ፈጽሞ እንደማይኖርና የዲዛይነሮች ትኩረትም ምን መሆን እንዳለበት ታስረዳች። በመሆኑም ከላይ ያሉትን ቅድመ ሁኔታዎች አሟልቶ ከለባሹ ማህበረሰብ ባህል ጋር ከተሳካ ወይም ከገጠመ ልብሱ በሌሎች እንዲወደድና በብዙዎች እንዲለበስ ምክንያት እንደሚሆንም ባለሙያዋ ጨምራ ታመላክታለች።
ልክ እንዳሁኑ ቅዝቃዜ ባለበት ወቅት ሰውነትን በሙሉ ሸፍኖ ብርድን የሚከላከልና የሰውነት ሙቀትን የሚጠብቁ በአብዛኛው ከጥጥ የተሰሩ ወፍራም ልብሶች በብዙዎች የመመረጡን ያህል፤ ወቅቱ በበጋ ሲለወጥ ደግሞ በአብዛኛው ቀለል ያሉ፣ ሙቀትን ሊቋቋሙ የሚችሉ፣ በቀለማቸው ፈካ ያሉና ከሰውነት አቋምና ቅርፅ ጋር የሚስተካከሉ አልባሳቶች በብዙዎች ይዘወተራል።
በእርግጥ እንደ ሰው ፍላጎትና የአለባበስ ምርጫ ቢለያይም ወቅቱን ባገናዘበ መልኩ ለመዋብ ሁሉም የበኩሉን ጥረት ያደርጋል። ከወቅቱ ጋር የሚሄዱ አልባሳት መልበስ አንድም በምርጫ ሲሆን ሌላኛው ጉዳይ ደግሞ ተፈጥሮ በራስዋ ታስገድዳለች። የሞቀው ሙቀቱን ሊከላከልለት የሚችል ልብስ የበረደውም ሰውነቱ በብርድ እንዳይጎዳና ስሜቱ እዳይረበሽ የሚያስችለውን ልብስ ለመልበስም ይገደዳል።
ማህበረሰባችን በተለያየ ጊዜ የራሱን አስተሳሰብና ባህላዊ ገጽታ የሚያንጸባርቁ አልባሳት ፋሽን አድርጎ ሲከተል ይታያል። ወጣቱ ዲዛይነር ሳምሶን በላይ ማህበረሰባችን ለወቅታዊ አለባበስ ያለው አጠቃላይ ምልከታ ምን ይምስላል ለሚለው ጥያቄ ምላሹ እንደሚከተለው ነው። አሁን ላይ ማህበረሰባችን በተለየ መልክ ፋሽን ተከታይ እየሆነ ነው የሚለው ሳምሶን እንደ ወቅቱ ዘንጦና አምሮ መታየት የሚያዘወትረው በርክቷል ይላል። የመግዛት አቅም ካልወሰነው በቀር፤ ወቅታዊና ከአየር ንብረቱ ጋር የሚሄድ እንዲሁም ለሰውነት ምቹ የሆነ ልብስ የመልበስ ፍላጎት እንዳለውም ምልከታውን ያጋራል።
እንደ ዲዛይነር ሳምሶን ገለጻ፤ ምንም እንኳን በዚህ ጊዜ ፋሽን እጅግ የተጋነነበትና ፈጣን መለዋወጥ የሚታይበት ቢሆንም እንደኛ ማህበረሰብ ወቅቱን በጠበቁ አልባሳት መዋብ እየተለመደ ነው። በዚህም ፋሽንና ወቅታዊ የአለባበስ ልምዶች አሁን ላይ እየተለመደ እንደሆነና ማህበረሰባችን የፋሽን ተከታይነቱን እንደሚያመላክትም ይገልጻል። ለዚህም ዘርፉ ያለውን ዕድገትና ለውጥ በማሳያነት ይጠቅሳል። ወጣቶች አሰርተው የሚለብሱዋቸው ልብሶች አልያም በራሳቸው ምርጫ ከልብስ መሸጫ መደብሮች ገዝተው የሚለብሱዋቸውና የሚጫሟቸው አዳዲስ ዲዛይን ልብሶች ለዚህ ማሳያ መሆኑንም ያስቀምጣል።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ሰኔ 27 /2014