ኢትዮጵያ የውሃ ማማ በመባል ትታወቃለች። በቂ የዝናብ ውሃ አላት፤ ከራሷ አልፎ ጎረቤት አገሮችን ጭምር የሚያጠጡ ታላላቅ ወንዞች ባለቤት ናት፤ በርካታ ሀይቆችም አሏት። ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣው ለኃይል ማመንጫ የተገነቡ ግድቦች የያዙት ውሃም ሌላው የውሃ ሀብቷ ነው። ምንጮቿና የከርሰ ምድር ውሃ ሀብቷም እንዲሁ ይጠቀሳል።
እነዚህን የውሃ ሀብቶች ለልማት በማዋል በኩል ግን አንዳንድ የኃይል ማመንጫ ግድቦችን ተንተርሰው ከተሰሩ የመስኖ ልማት ስራዎች በስተቀር የሐገሪቱ የውሃ ሀብት በግብርናው መስክ እየተሰራበት አይደለም። የውሃ ሀብቷ ባለመልማቱ የተነሳ አገሪቱም በድርቅ ወቅት በእጅጉ የምትጎዳ፣ በመስኖ ልማት ስንዴ በስፋት ማምረት ስትችል የዳቦ ስንዴ ከውጭ ስታስገባ የኖረች አገር ናት።
እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ድርቅ ለሚያጠቃቸው አገራት አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ምርትና ምርታማነት መቀየር የመስኖ ልማት እጅግ አዋጭ ዘዴ ነው። የመስኖ ልማት ድርቅ በሚከሰትበት ወቅት የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ ከፍተኛ ፋይዳ አለው።
ይህን ሁሉ ታሳቢ በማድረግ የአገሪቱን የውሃ ሀብቶች ለማልማት ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል። በተለይ የውሃ ኃይል ማመንጫ ግድቦችን ለመስኖ አገልግሎት በማዋል የመስኖ ልማት ይካሄዳል። የመስኖ ልማቱ ግን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ላይ የተመሰረተ ሆኖ ነው የኖረው።
ይህን ሁኔታ ለመቀየር በሚያስችል መልኩ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የከፍተኛ፣ መካከለኛ እና አነስተኛ የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታዎች ተከናውነዋል። እየተከናወኑም ይገኛሉ። ግንባታቸው ግን በእጅጉ የተጓተተ መሆኑ ማነጋገሩን ቀጥሏል።
ግንባታቸው እየተካሄደ ከሚገኝ የመስኖ ፕሮጀክቶች መካከልም የላይኛው ጉደር የመስኖ ልማት ፕሮጀክት ይጠቀሳል። ይህ ፕሮጀክት ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ መገንባት ከጀመሩት ሰፋፊ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች አንዱ ነው። ፕሮጀክቱ በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ሸዋ ዞን በቶኬ ኩታዬ እና አምቦ ዙሪያ ወረዳዎች በዘጠኝ ቀበሌዎች በሁለት ክፍል ተከፍሎ እየተካሄደ ይገኛል።
የግድቡ ውሃ የመያዝ አቅም 56 ሚሊየን ሜትር ኩብ ሲሆን፤ ለፕሮጀክቱ ግንባታ ከሶስት ነጥብ ሶስት ቢሊየን ብር በላይ ተይዞለት ነው ወደ ግንባታው የተገባው፤ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ከአምስት ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በማልማት በቶኬ ኩታዬ እና አምቦ ዙሪያ ወረዳዎች የሚገኙ ከ10ሺህ በላይ ነዋሪዎችን የመስኖ ተጠቃሚ ያደርጋል። 40 ሜትር ከፍታ እና 300 ሜትር ገደማ ርዝመት አለው። በግድቡ ግንባታ በርካታ የአካባቢው ህብረተሰብ የስራ እድልም ተፈጥሮለታል። በጣም ዘመናዊ የሆነው የግፊት ስፕሪሊንክለር መስኖ ዘዴ የሚተገበርበት ፕሮጀክት ነው።
የግድብና የመስኖ ልማቱ ግንባታ በዋናነት የሚያካትታቸው የግድብ ግንባታ፣ 23 ኪሎ ሜትር ጂ.አር.ፕ. ቧንቧ፣ 150 ኪሎ ሜትር ዩ.ፕ.ቭ.ሲ.ቧንቧ፣ አራት ነጥብ ሰባት ኪሎ ሜትር ዋና ቦይ ቧንቧ፣ አራት ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር ዋና ቦይ የመጀመሪያ ቧንቧ፣ 13 ኪሎ ሜትር ዋና ቦይ ሁለተኛ ቧንቧ እንዲሁም 4926 ሄ/ር የመስኖ መሰረተ ልማት ግንባታዎች ናቸው።
የመስኖ ልማት ፕሮጀክቱ አርሶ አደሮችን በዓመት አንድ ጊዜ ሲያመርቱ ከኖሩበት የግብርና አሰራር በማላቀቅ በዓመት ሁለቴ እና ሶስት ጊዜ አትክልቶችን፣ ፍራፍሬዎችን እና ሰብሎችን እያመረቱ ራሳቸውም ተጠቃሚ እንዲሆኑ እና የአገሪቱን ምርትና ምርታማነት ከፍ እንዲያደርጉ ታስቦ እየተገነቡ ካሉ ፕሮጀክቶች አንዱ ነው። በተለይም አካባቢው ለአዲስ አበባ ቅርብ እንደመሆኑ አትክልት እና ፍራፍሬ በማምረት ለገበያ በማቅረብ አርሶ አደሩ ተጠቃሚ አንዲሆን ያስችላል።
ፕሮጀክቱ በሁለት ሎት ተከፍሎ የሚሰራ ነው፤ ሎት አንድ የግድብ ግንባታና ተያያዥ ስራዎች ግንባታ ነው፤ ይህም በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ይሰራል፤ ሎት ሁለትን ደግሞ የኦሮሚያ ውሃ ስራዎች ኮንስትክሽን ድርጅት የመስኖ አውታርና ተያያዥ ስራዎችን ይሰራል። የማማከሩን ስራ እንዲሰራ የተቀጠረው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ዲዛይንና ሱፐርቪዥን ስራዎች ኮርፖሬሽን ነው። የግድቡ ግንባታ በ2011 ዓ.ም ሰኔ ወር የተጀመረ ሲሆን፤ ግንባታውን በሶስት ዓመታት ውስጥ ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዞ ነበር ወደ ስራው የተገባው።
በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በቀድሞው የመስኖ ልማት ኮሚሽን፣ በአሁኑ የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር የላይኛው ጉደር ግድብ እና የመስኖ ልማት ፕሮጀክት ዝግጅት እና አፈጻጸም ረገድ የተከናወነውን የ2013 በጀት ዓመት የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ሰሞኑን በገመገመበት ወቅት እንዳስታወቀው፤ ኦዲቱ እስከ ተከናወነበት ድረስ በነበረው ጊዜ የላይኛው የጉደር መስኖ ልማት ፕሮጀክት የግንባታ ሥራው ከ45 በመቶ እስከ 50 በመቶ መድረስ ነበረበት። ይሁንና እስከ ጥር 2013 ዓ.ም. የነበረው አፈጻጸም 6 ነጥብ 2 በመቶ ብቻ መሆኑን ማስረዳቱን በኢፌዲሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፌስቡክ ገጽ ላይ የሰፈረው መረጃ አመላክቷል።
ፕሮጀክቱ በሚፈለገው መልኩ እየሄደ ላለመሆኑ እና ለመጓተቱ ዋነኛው መንስዔ የአዋጭነት ጥናቱ በአግባቡ አለመታየቱ መሆኑን የጠቆመው ቋሚ ኮሚቴው፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ መሠረታዊ ችግሩን ፈትሾ በትኩረት እንዲሠራም አሳስቧል። ኮሚሽኑ የመስኖ ውሃ የሚሄድበትን መስመር ዝርጋታ እንዲያከናውን ከኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ጋር ውል የተፈራረመው ሰኔ 2011 ዓ.ም እንደነበር ቋሚ ኮሚቴው መረጃ ጠቅሶ ገልጿል።
ለልማት ተነሺዎች ለንብረት ካሳ ክፍያ፣ ለመሬት ባለይዞታዎች ካሳ ክፍያ፣ በአጠቃላይ ለ16 ሺህ 231 ነዋሪዎች እንዲሁም ለዚህ ሥራ የተሰየመውን ኮሚቴ ውሎ አበል እና ስልጠና ጨምሮ ከተመደበው 571 ሚሊዮን 915 ሺህ ብር፤ እስከ አሁን ለ136 ሰዎች 278 ሚሊዮን 993 ሺህ ብር እንደተከፈላቸው፤ ቋሚ ኮሚቴው ግኝቱን መሠረት አድርጎ አስታውቋል። ይህም ከመነሻ ጥናቱ ጋር ሲነጻጸር፤ 99 በመቶ የሚጠጋው ክፍያ የሚገባቸው የልማት ተነሺዎች እንዳልተከፈላቸው፣ ኮሚቴው ከዋና ኦዲተር ያገኘውን የኦዲት ግኝት መረጃ ተንተርሶ ጠቅሷል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ክርስቲያን ታደለ፤ የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር በኦዲት ግኝት ማስተካከያው መርኃ-ግብር መሠረት እስከ ሐምሌ 5 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ የወሰዳቸውን የማስተካከያ ርምጃዎች የተመለከተ ሪፖርት ለኮሚቴያቸው እንዲያቀርብ ጠይቀዋል። ሪፖርቱ ለፌዴራል ዋና ኦዲተር እና ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን ለሚከታተለው ቋሚ ኮሚቴ በግልባጭ ሊደርሳቸው እንደሚገባም አመልክተዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከላይኛው ጉደር መስኖ ፕሮጀክት ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ብልሹ አሠራሮችን በመለየት፣ ክፍተቶችን በመሙላት፣ ጥፋተኛ በሆኑ ባለሙያዎች እና የሥራ ኃላፊዎች ላይ ርምጃዎችን ወስዶ በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ሊያሳውቀን ይገባል ብለዋል።
የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የሚያከናውናቸው የልማት ፕሮጀክቶች የአዋጭነት ጥናት የተሠራላቸው፣ የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ የሚደረግባቸው እና የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት እና ባለቤትነት የሚያረጋግጡ መሆናቸውን ግንዛቤ ወስዶ ሊንቀሳቀስ እንደሚገባ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ክርስቲያን አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከላይኛው ጉደር መስኖ ፕሮጀክት ጋር ተያያዥ በሆኑ የኦዲት ግኝቶች ማስተካከያ አፈጻጸም ረገድ፣ በየሦስት ወሩ ለቋሚ ኮሚቴው፣ ለዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት እና ለገንዘብ ሚኒስቴር ሪፖርት እንዲያቀርብ ያዘዙ ሲሆን፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የኦዲት ግኝቱን በ2015 በጀት ዓመት የዕቅድ ዝግጅት እንዲያካትትም አቅጣጫ ሰጥተዋል።
ቋሚ ኮሚቴው በላይኛው ጉደር የመስኖ ፕሮጀክት የክዋኔ ኦዲት ግኝት ላይ ላቀረባቸው ጥያቄዎች ሚኒስቴሩ በቂ ምላሽ ሰጥቷል ብሎ ስላልወሰደ፤ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ልዩ ኦዲት ሠርቶ ሪፖርት እንዲያቀርብ ሰብሳቢው አመላክተዋል። የኦዲት ግኝቱን መነሻ በማድረግ ተጠያቂነትን የሚያስከትሉ ጉዳዮች ካሉም ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት አቅጣጫዎች እንደሚቀመጡ አያይዘው አስገንዝበዋል።
የፌደራል ዋና ኦዲተር መሰረት ዳምጤ በበኩላቸው በመሬት ዝግጅት፣ አብሮ በመስራት፣ በዲዛይንና ካሳ ክፍያ መሰራት የነበረባቸው ባለመከናወናቸው ፕሮጀክቱ በተቀመጠለት ጊዜ እንዳይከናወን ሆኗል ብለዋል። ከካሳ ክፍያ ጋር የተያያዘ ችግር በመኖሩ ልዩ ኦዲት እንደሚደረግም አመላክተዋል።
የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የሥራ ኃላፊዎችም የሚፈለገውን ሥራ ለመሥራት ተቋሙ የአቅም ውስንነት እንዳለበት፣ መጠናከር እንደሚገባው እና ማነቆዎች መፈታት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ፤ መሥሪያ ቤታቸው አዲስ በመሆኑ ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አስታውቀዋል። ቋሚ ኮሚቴው የሰጠውን ግብረ-መልስ በግብዓትነት በመጠቀም፣ የፕሮጀክቱ ችግር እንዲፈታ የኦዲት ግኝቱን መሠረት በማድረግ በቀጣይ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
ግኝቶች አስተማሪዎች መሆናቸውን ሚኒስትሯ ጠቅሰው፣ የቀረቡ ግኝቶችንም ለቀጣይ ሥራዎች የጥንካሬ ምንጭ አድርገው መውሰዳቸውን ሚኒስትሯ ገልጸዋል። የካሳ ክፍያ ጉዳይ የአሠራር ክፍተቶች እንዳሉበት እና በቀጣይ መፈታት የሚችል መሆኑን ተናግረው፣ ከባለሙያዎች እና ከክልሎች ጋር በቅንጅት በመስራት አንደሚፈታም አስታውቀዋል። በላይኛው ጉደርና ሌሎች ፕሮጀክቶች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት በአሰራር የተደገፉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ማስረዳታቸውን የኢፌዲሪ ፓርላማ የፌስቡክ ገጽ ላይ የሰፈረው መረጃ አመላክቷል።
አገሪቱን ዋጋ እያስከፈላት ያለውን ድርቅ ለመቋቋም በዓመት የሚመጣውን ዝናብ ብቻ ጠብቆ ከሚመረተው ጎን ለጎን የመስኖ ልማትን ለማስፋፋት የመስኖ ልማቶችን ለማስፋፋት ተጀምረው በተለያዩ ምክንያቶች የተጓተቱን እንደ ጉደር መስኖ ልማት ፕሮጀክት ያሉ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል። ለእዚህ ደግሞ በመስኖ ፕሮጀክቶች ላይ ለሚያጋጥመው ችግር በጥናት ላይ ተመስርቶ መፍትሄ መስጠት ያስፈልጋል።
የነባር ፕሮጀክቶችን ችግሮችን ከመቅረፍ ጎን ለጎን አዳዲስ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶችን ግንባታ በጥናት ላይ ተመስርቶ ማስጀመር እና በተያዘላቸው ጊዜ አጠናቆ አርሶ አደሩ ተጠቃሚ እንዲሆን ማስቻል ዘመኑ የሚጠይቀው አርበኝነት ነው።
አርሶ አደሩ ከዝናብ ጠባቂነትና ጥገኛነት እንዲወጣ የመስኖ ልማት በመጠቀም ዓመቱን ሙሉ የተለያዩ ሰብሎችን፣ የጓሮ አትክልቶችን እየዘራና እየተጠቀመ የራሱንና የቤተሰቡን ህይወት እንዲለውጥ፣ አልፎም ተርፎም አገሪቱ በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት የያዘችውን እቅድ ለማሳካት በመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ በኩል የተጀመሩ ጥረቶች መጠናከር አለባቸው።
ፕሮጀክቶችን ለማፋጠን ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን የእውቀት እጥረት ለመስኖ ልማት አንዱ ተግዳሮት ሊሆን እንደሚችል በማወቅ ለችግሩ የሚመጥን መፍትሄ መስጠትም ወሳኝ ነው። አርሶ አደሩን በመስኖ ልማት ላይ ግንዛቤ በማስጨበጥ ረገድ ብዙ መስራት ይገባል። የግብርና ባለሙያዎቻችን ስለመስኖ ውኃ ጥቅምና ውጤታማነት ደጋግሞ በማስተማር ማሳወቅ ቢችል ምርትና ምርታማነት በወሳኝ መልኩ ማሳደግ ይቻላል። ከድርቅ ጋር ተያይዘው የሚከሰቱት ብዙዎቹ ችግሮቻችን መፍትሄ ሊያገኙ ይችላሉ። በኦዲት ሪፖርቱ ላይ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የስራ ኃላፊዎች ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጡን ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ሰኔ 25/2014