‹‹ተሿሚዎች የባከነውን ገንዘብ ማስመለስ ካልቻሉ በሕጉ መሠረት እቀጣለሁ›› – የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት
አዲስ አበባ፡- በስምንት ዓመታት ውስጥ የባከነው ገንዘብ 3ነጥብ2 ቢሊዮን ብር መሆኑ ተገለጸ። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የባከነውን ገንዘብ ማስመለስ ባልቻሉ ተሿሚዎች ላይ በሕጉ መሠረት እቀጣለሁ ብሏል።
ለመንግሥት ተመላሽ መሆን ያለበትን የኦዲት ግኝት በተመለከተ ከመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክክር በተደረገበት ወቅት ዋና ኦዲተሩ ገመቹ ዱቢሶ እንዳሉት፣ ገንዘቡ ተመላሽ እንዲሆን ለማድረግ ዋና ኦዲተር ከጠቅላይ ዐቃቤ ሕግና ከፓርላማው ጋር በትብብር እየሰራ ነው።
ዋና ኦዲተሩ እንዳሉት ከ2002 እስከ 2009 ዓ.ም ባለው ጊዜ ለመንግሥት ተመላሽ መሆን የነበረበት የገንዘብ ጉድለት 2ነጥብ1 ቢሊዮን ብር ሲሆን እስካሁን ተመላሽ የሆነው 50 ሚሊዮን ብር አይሞላም።
የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዶክተር ጌድዮን ጢሞቲዎስ በበኩላቸው፣ አስተዳደራዊ እርምጃዎች ከመወሰዳቸው በፊት ኃላፊዎች የመንግሥትን ገንዘብ ተመላሽ እንዲያደርጉ መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ተጠያቂነትን ለማስፈን እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፣ በዚህም 190 ተቋማት የኦዲት ግኝት እንዳለባቸው ጠቅሰዋል። ከእነዚህ ውስጥ 35 ተቋማት ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ተለይተዋል ብለዋል።
ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ጉድለት የታየባቸው 35 ተቋማት መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር ጌድዮን፣ 15ቱ የፌዴራል መስሪያ ቤቶች ሲሆኑ 20ዎቹ ደግሞ ዩኒቨርሲቲዎች መሆናቸውን አስታውቀዋል። ጉዳዩን ወደ ሕግ ለማቅረብ የሚያስችል ሥራም ተሰርቷል ብለዋል።
በዋና ኦዲተር እና የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ
ሕግ በያዛቸው የኦዲት ግኝቶች ያለው ጉድለት 3ነጥብ2 ቢሊዮን ብር መሆኑ ተጠቁሟል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አቶ ታደሰ ጫፎ በበኩላቸው፣ ይህንን የሕዝብ ሀብት ለማስመለስ ኃላፊዎቹ በትኩረት ካልሰሩ ጉዳዩ በሕግ ተጠያቂ እንደሚያስደርግ ገልጸዋል።
ምክር ቤቱ በአፈ-ጉባዔው የሚመሩ የተለያዩ የቁጥጥር ኮሚቴዎችን አደራጅቶ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ተመላሽ ገንዘቡን በኃላፊዎች ጥረት ለማስመለስ መመካከር እና ተናቦ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል። ይህ ካልተሳካ ግን ምክር ቤቱ የሥራ ኃላፊዎቹን ፖለቲካውም ሆነ ሕጋዊ ተጠያቂነት እንዲኖራቸው እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።
በኦዲት ግኝት መሠረት የተመላሽ ገንዘቡ ጉድለት ዋና መነሻ ሕግና መመሪያን ያልተከተለ አሠራር የተሟላ ሰነድ ሳይቀርብ በወጪ የተመዘገበ የጥሬ ገንዘብ ጉድለት፣ አለግባብ በብልጫ የተከፈሉ ክፍያዎች፣ በቅድሚያ ክፍያ እና ከገቢ ግብር ጋር የተያያዙ መሆናቸው በመድረኩ ላይ ተገልጿል።
አዲስ ዘመን መጋቢት18/2011
በጋዜጣው ሪፖርተር