ወደ ጥበብ ገበታ ቀርቦ መቋደስ የማይፈልግ ፤በጥበብ ትሩፋት ዘልቆ ነፍሱን ማደስ የማይሻ የሰው ልጅ መኖሩ ያጠራጥራል። ጥበብ በአንድ ወይም በሌላ መልክ በሰዎች ሁለንተናዊ ህይወት ውስጥ ይገለጣል። ሰዎች እራሳቸውን የሚገልጡበት፣ባህልና ማንነታቸውን የሚያስውቡበት ስብዕናቸውን የሚያንፁበትና አኗኗራቸው የሚያንፀባርቁበት ልዩ መድረክም ነው። ታዲያ ጥበብ ጥበበኛን ሁሉ በእኩል አትጣራም። ወደ መግቢያ በርዋ ለሚቀርብ ሁሉ በእኩል ምላሽ አትሰጥም።
ጥበብ በራስዋ ሚስጥር ናትና በራስዋ መንገድ ሰዎችን በተለያየ መንገድ ወደራሷ ትጣራለች። ጥበብ ለጥሪዋ ምላሽ የሚሰጡ ዕድለኞችን ትመርጣለች። አንዳንዱን በሯዋን በሰፊው ከፍታ ከማዕድዋ ይቋደስ ዘንድ ገራገር ትሆንለታለች። ቤተኛዋ ይሆን ዘንድ ፈቅዳ ያላትን ሁሉ እንካ ብላ ከበረከትዋ ይቋደስ ዘንድ ትፈቅድለታለች።በዛሬ የዘመን ጥበብ ገፃችን እራሱን ከጥበብ ጋር ካስታረቀ ወጣት የብዕር ሰው ስራዎችና ተሞክሮው ለማየት ወደናል መልካም ንባብ።
ለጥበብ ጥሪ የተሰጠ ምላሽ
ጥበብ ወጣቱ ደራሲ ዘላለም ከሚወደው የቀለም ትምህርቱን አሸፍታ የአንተ መክሊት እኔ ጋር የተቃረበ ነው ብላ ግብዣ አቀረበችለትና ተቀላቀላት። በትምህርት ቤት ህይወቱ በጥሩ ውጤት ከሚታወቁ ተማሪዎች አንዱ ነበር። ወደኋላ ላይ ግን ውስጡ አንድ ጥያቄ መፈጠር ጀመረ። እኔ የተፈጠርኩት እዚህ ምድር ላይ ለምን አላማ ነው?ማሳካት የምፈልገው ምንድነው? ውስጤ ወዴትኛው አቅጣጫ ነው መሄድ የሚፈልገው? የሚል። ታዲያ በትምህርት ቤት ቆይታው ያዘወትረው የነበረው የምንባብ ፍቅርና በትምህርት ቤት ኪነ ጥበብ ክበብ ይሳተፍበት ወደነበረው ጥበባዊ ጉዳይ ላይ የእሱ ስሜት ስስ መሆኑን ተረዳ። ከትምህርቱ ጎን ለጎን አዘውትሮ ኪነጥበባዊ መድረኮች ላይ መገኘትና እራሱም መሳተፍ ጀመረ።
በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የኢንጅነሪንግ ተማሪ ሆኖ በተመደበ ሰዓት ግን ከራሱ ጋር መከረ። እናም አንድ የራሱ የሆነ ፍልስፍና ነበረውና እርሱን መኖር ፈለገ። “የሰው ልጅ በምድር ላይ የሚገኘው አንድ ጊዜ ነውና ድንቅ ሰውነቱን በሚወደው ሙያ ላይ ማሳረፍ አለበት” የሚል መርህ ለእርሱ ተገለጠ። የሚወደው ኪነጥበባዊ ጉዳይ ላይ መሳተፍ የጥበብ ሰው መሆንን ነበርና በዋናነት እሱን በትርፍ ሰዓቴን ደግሞ የቀለም ትምህርቱን መማር አለብኝ ብሎ ወሰነ። ያ ውሳኔው ዛሬ ላይ የሚደሰትበትና ፍሬ ያፈራለት የሚፈልገው ላይ መኖር ያስቻለው ወደሚወደውም ያስጠጋው ሆነለት፤ደራሲ ወጣት ዘላለም።
በ2007 የጀመረው እርሱ ጋር ያለው ጥልቅ የጥበብ ፍቅርና ልዩ ተሰጥኦ በትምህርትና ልምድ አዳብሮ መፅሀፍትን በመፃፍ የጀመረው ጉዞው ዛሬ ላይ 15 መፅሀፍ ፅፎ ለህትመት አብቅቷል። እርሱ በብዕሩ ፍቅርን ሰብኳል፣ በፅሁፎቹ አንድነትን ነግሯል፣በጥበብ አዋዝቶ ማህበራዊ ህፀፆች ይታረሙ ዘንድ ጠቁሟል። ብዙዎች በራሱ የአፃፃፍ ስልቱ የሚደነቁበት ደራሲ ዘላለም የሳጥን ወርቅ ማህበራዊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች እያነሳ የግል ፍልስፍናውንና ልዩ ምልከታውን በማይነጥፈው ብዕሩ አንፀባርቋል።
የደራሲው ስራዎች
ሰኔ 18 ቅዳሜ 4 ኪሎ በሚገኘው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የመሰብሰቢ አዳራሽ የደራሲ ዘላለም የሳጥን ወርቅ 15ኛ መፅሀፍ የሆነው “የነፍስ ዜማ” የተሰኘ መፅሀፍ ታዋቂ የኪነ-ጥበብ ሰዎች በተገኙበት ተመርቋል። በምሽት ትምህርቱን ቀን ላይ ደግሞ ጥበባዊ መሻቱን ለማሳካት ሲባትን የነበረው ዘላለም ከሌሎች ጋር በመሆን ሶስት የተለያዩ የግጥምና አጫጭር ልቦለድ ስራዎቹን አሳትሞ ወደ ድርሰት ሙያ ተቀላቀለ።
የራሱ ወጥ ስራ ሰርቶ ሌተቀን ጥረት ማድረጉን ቀጠለ በመጨረሻም ከአንድ በቅርቡ ካለው ለፅሁፍ ዝግጅት እዲሆነው የተበረከተለት ኮምፒዩተር መግዣ ገንዘብ ቀድሞ ያዘጋጀው መፅሀፉን ሊያሳትምበት ወሰነና “እፀ ሳቤቅ” የተሰኘ የራሱን ስራ ለህትመት አበቃ። በዚህም ብዙዎች በጎ አስተያየትን ሰጡት ያሳተመው ህትመት ቁጥሩ የበዛም ባይሆን በሁለት ወር ውስጥ ተጠናቆ ባየ ጊዜ ለራሱ ብርታት አገኘ። የሚወደውና የሚፈልገው ስራ መፃፍ በኪነጥበቡ ዓለም የራሱን አበርክቶ አንካችሁ ማለት ነበርና መንገዱን ተያያዘው በትጋት መፃፍ ቀጠለ።
ደራሲው ባለፉት 7 ዓመታት ውስጥ ከፃፋቸውና አንባቢ ጋር ካደረሳቸው መፅሀፎች ውስጥ እፀ ሳቤቅ፣ እፀጳጦስ አሁን፣እፀሲና፣ሊቶስጥራ፣ብኤልዘቡል፣ሽርፍራፊ ልቦች፣ፍካትና ንጋት፣የህይወት ዋጋ፣ፊትና ኋላ፣ አዳፋ ነብሶች፣እንደ ፍቅር፣እውነት፣ ሰውነት፣አሁንና የመጨረሻ መፅሀፉ የነፍስ ዜማ የተሰኙት ተጠቃሾች ናቸው።
በተለይም የማህበረሰባችን ልዩ ልዩ መልኮች በግጥም በወግ በአጭርና በረጅም ልቦለዶቹ እያፈራረቀ በመፅሀፎቹ ለአንባቢያን የሚያበቃው ወጣቱ ደራሲ ዘላለም፤ በራሱ የአፃፃፍ ስልት በተለየ የአተራረክ ዘይቤ በሚያቀርባቸው የመፅሀፍ ጽሁፎቹ ይታወቃል።
በመፅሀፎቹ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን እያነሳ በልዩ የአተራረክ ስልት በውብ ቃላት ከሽኖ የሚያቀርበው ደራሲ ዘላለም ስለ ፍቅር፣ስለ አገር፣ስለ እናትና አባት፣ስለቤተሰብ፣ እና ማህበረሰብ፣ስለ ባህልና እምነት እውነት እያራረቀ በተለያዩ ታኮች አሳይቶናል።
ስለደራሲው ምን ተባለ
ደራሲ ዘላለም የሳጥን ወርቅ “የነፍስ ዜማ” የተሰኘው መፅሀፉ ባለፈው ሳምት ባስመረቀበት ወቅት በአገራች በስነፅሁፍ ተፅዕኖ መፍጠር የቻሉ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ተገኝተው ነበር። በዚሁ ደማቅ የምረቃ ስነ ስረዓት ላይ የደራሲው ቀደምት ስራዎችና ስነ ፅሁፋዊ ይዘታቸው በተመለከተ ሀሳብ ሰጥተው ነበር።
የመርሀ ግብሩ የክብር እንግዳ የነበረው መምህር ደራሲና ፀሀፊ ተውኔት አያልነህ ሙላቱ የደራሲው ስራዎች በተመለከተ በመድረኩ ላይ አስተያየት ሰጥቶ ነበር። ወጣቶች ከንባብ ርቀው ጊዜያቸውን አልባሌ ቦታ ላይ በማሳለፍ አሉታዊ ተፅዕኖ እየፈጠሩ ባሉበት በዚህ ሰዓት የደራሲ ዘላለም አይነት ትጉህና በብዕሩ ሰዎችን ለማስተማርና ማህበረሰቡን ለማቅናት እንዲሁም በአስተሳሰብ ለመለወጥ የሚጥር ወጣት መገኘቱ ተስፋ ያለመልማል በማለት ስለ ወጣቱ ደራሲ ዘላለም ያለውን አስተያየት ሰቷል።
በደራሲው የአፃፃፍ ስልት እጅጉን የሚደነቅ መሆኑን የገለጸው ፀሀፊ ተውኔት አያልነህ ሙላቱ “ደራሲ ዘላለም በድርሰቱ ውስጥ የሚጠቀምባቸው ቃላት ውበትና የአገላለፅ ብስለት ጥበባዊ በመሆኑ ይማርካል፤በተለይ አካባቢና ተፈጥሮን በተለየ መልክ የሚያሳይበት ስዕላዊ ቃላቱ ይለዩብኛል።” በማለት የደራሲው ስራዎች የተመለከቱበት አስተያየታቸውን አጋርቷል። በተለይም መፃፍ ቀርቶ ማንበብ ብዙም ልምድ የሌለው ማህበረሰብ ውስጥ ተገኝቶ በዓመት ሁለት ደረጃቸውን የጠበቁና ስነ ፅሁፋዊ ፋይዳው ከፍ ያለ መጽሀፍ ፅፎ ለአንባቢ ማድረስ እጅጉን ከባድ መሆኑን የገለፀው ፀሀፊ ተውኔት አያልነህ ሙላቱ ደራሲ ዘላለም በ7 ዓመታት ውስጥ 15 መፅሀፍን ለንባብ ማድረሱ ለብዙዎች ትምህርት እንደሚሰጥና ጊዜን መጠቀም ዋጋ እንዳለው አመላካች መሆኑን ጠቅሷል።
መጽሀፍ ምርቃት ስነ ስረዓት ላይ ደራሲው ከዚያ በፊት የፃፋቸው መጽሀፍት በተመለከተ አስተያየት ከሰጡ ባለሙያዎች አንዷ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ስራ አስኪያጅ የሆነችው ደራሲት የዝና ወርቁ የደራሲው ቀደምት ስራዎችና አዲሱ መፅሀፍ በተመለከተ እንዲህ ብላለች። ደራሲ ዘላለም ከእድሜው በላይ ከፍ ያለ ስራዎችን መስራት ያስቻለው ታላላቅ ከሆኑ ሰዎች ዝቅ ብሎ ምክር መቀበሉና በጥሩ ስነምግባር ከሰዎች ጋር ተግባብቶ ሙያው ካላቸው ሰዎች መቅሰም በመቻሉ እንደሆነ አስረድታለች።
በፅሁፎቹ ውስጥ የሚያነሳቸው ርዕሰ ጉዳዮች እደምትደነቅና ጉዳዮቹን የሚገልፅበት መንገድ ልዩ መሆኑን የምትናገረው ደራሲት የዝና፤ በእርሱ እድሜ ያሉ ወጣቶች እጅጉን ሊማሩበት እንደሚገባ ገልፃለች።በገፀባህሪያቱ ውስጥ የሚስላቸው ሴቶች ለሌሎች አርአያ የሚሆኑና ደራሲውም ለሴት ልጅ ያለው አመለካከት እጅጉን የተቃና መሆኑን አመላካች ነው ያለችው ደራሲት የዝና የማህበረሰባችንን ባህልና ጥሩ ገፅታን በመገንባትም ደራሲው በብዕሩ የራሱን የላቀ ሚና በመወጣት ላይ የሚገኝ መሆኑን አስረድታለች።
የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮችን በራሱ ዓይን ተመልክቶ ወደሌሎች በማጋባት ተፅዕኖ መፍጠርም የቻለ ትጉህ ደራሲ መሆኑንም ነው የገለፀችው። ወጣቱ ደራሲ በተባ ብዕሩ እና በራሱ ፍልስፍና ዓለምን ባየው ልክ ሊያመላክተን እድትሆን በሚፈልጋት ጥሩ መልክ ስሎና የራሱን ልዩ አለም ፈጥሮ የማቅረብ ልዩ ክህሎት እንዳለው መስክራለች።
በመድረኩ ላይ ተገኝተው በደራሲው ስራዎች ላይ ዳሰሳዊ ፅሁፍ ያቀረበው ደራሲ ጌታቸው በለጠ (ዳግላስ ጴጥሮስ) በበኩሉ፤ ደራሲውን በስራዎቹ እንደሚያውቀውና ፅሁፎቹ እጅጉን እንደሚማርኩት የአፃፃፍ ስልቱና የሚያነሳቸው ሀሳቦቹ እንደሚገዝፉበት ገልጿል። ደራሲው ከመፅሀፎቹ በተጨማሪ ጋዜጦች ላይ በሚያጋራቸው የተለያዩ ፅሁፎቹ አገራዊ እይታዎቹ የሚያስደንቁ መሆናቸውን የጠቆመው ደራሲ ጌታቸው በወጣትነት እድሜው እንዲህ የስነ ፅሁፍ ክህሎትና የነጠረ ሀሳብ ማቅረብ መቻሉ የሚገረምበት መሆኑን ገልጿል።
ደራሲው በድርሰት ስራዎቹ ውስጥ በሚስላቸው ገፀ ባህሪያት እና ታሪኮች ቤተሰባዊ ማህበረሰባዊና አገራዊ ጉዳዮች በተለያየ መልክ በማሳየትና በማስተማር የሚታወቅ መሆኑን ገልፆ የራሱ የሆነ የአገላለፅ መንገድ መከተሉም በስነፅሁፉ ረገድ የተሻለ ክህሎት ያለው ለመሆኑ ምስክር መሆኑ ከመፅሀፎቹ እየወሰደ የጠቃቀሳቸው ማስረጃዎችን በማቅረብ አመላክቷል።
ጥበብ በተለይም መጽሀፍት ማህበረሰብን በማነፅ ትውልድን በመቅረፅ ያላቸው ሚና ከፍተኛ ነው። በተለየ ምልከታ በተከሸነ መልኩ ጉዳዮች አዋዝቶ በማሳየትና በማስተማር ረገድ ጠቢባን ይህንን አደራ ተረክበው በየዘርፋቸው ማህበረሰባቸውን ያስተምራሉ ያነቃሉ። ደራሲ ዘላለም የሳጥን ወርቅ በመጽሀፎቹ በተለያየ መልኩ ትውልዱን በማስተማርና በማነፅ በትጋት በመስራ ላይ እንደሚገኝም ፅሁፎቹን በመድረክ ላይ አቅርበው አስተያየት በሰጡ የስነ ጽሁፍ ሀያስያን ተገልጿል ።
እኛም በወጣትነት በዘርፉ ስኬታማ ከሆነውና ለብዙ ወጣቶች በትጋቱ አርአያ ይሆን ዘንድ በማሰብ ስራዎቹን የዳሰስንበት ፅሁፍ ለደራሲው ቀጣይ ስኬት በመመኘት ቋጨን። ቸር ያሰማን።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ሰኔ 23/2014