አዲስ አበባ፤ ‹‹ምሳሌ የከባድ መኪናዎች አሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ አካዳሚ›› የተግባር፣ የንድፈ ሀሳብና በምስለ ተሸከርካሪ የታገዘ ስልጠና በማቀናጀት የሙያ ክህሎትና መልካም ስነ ምግባር ያላቸውን አሽከርካሪዎች ለማሰልጠን በሚያስችል መንገድ የተገነባ በቂ ዕውቀት፣ ክህሎትና ስነምግባር ያላቸው አሸርካሪዎችን ለማፍራት የሚያስችል መሆኑን የትራሰፖርት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ፤ በሰላም የህጻናት መንደር ስር የሚገኘው የሰላም ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ በተግባር፣ በንድፈ ሀሳብና በምስለ ተሸከርካሪ የታገዘ ስልጠና በአንድ ቦታ ላይ በማቀናጀት ለማሰልጠን የተገነባውን ‹‹ምሳሌ የከባድ መኪናዎች አሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ አካዳሚ›› ትናንት ሲመረቅ እንደገለጹት፤ ማዕከሉ የሙያ ክህሎትና መልካም ስነ ምግባር ያላቸውን አሽከርካሪዎች ማፍራት የሚያስችል ስርዓተ ትምህርት ቀርጾ ከፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኤጀንሲ ጋር በጋራ አይቶ አዘጋጅቷል፡፡
የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ የአሽከርካሪ ተቋማትን የስልጠና አሰጣጥና የጥራት ደረጃ ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን የጠቆሙት ወይዘሮ ዳግማዊት፤ በኃላፊነት መንፈስ የዜጎችን ደህንነት የሚያረጋግጡ፣ የትራፊክ አደጋ እንዳይከሰት የሚያደርጉ፣ በቂ ዕውቀት፣ ክህሎትና ስነምግባር ያላቸው ሰልጣኞች የሚፈልቁበት አሰራር መዘርጋት እንደሚያስፈልግና ማሰልጠኛው ማሳያ እንደሚሆንም ጠቁመዋል፡፡
የትራፊክ አደጋ በኢትዩጵያ በከፍተኛ ሁኔታ የዜጎችን ደህንነት ስጋት ላይ መጣሉን ያስታወሱት ወይዘሮ ዳግማዊት፤ በጥናት እንደተረጋገጠው የትራፊክ አደጋ ከአሽከርካሪዎች ብቃትና ክህሎት፣ ከተሸከርካሪ ደህንነትና መንገዶች ደህንነታቸው የተጠበቀና በቂ ምልክቶች የሌላቸው ከመሆናቸው ጋር ተይይዞ እንደሚከሰት አብራርተዋል፡፡ ብቃትና ክህሎት ያላቸውን ባለሙያዎች ለማፍራት፣ ከአገር ውስጥ አልፈው ሌሎች አገሮች የሚሰሩ አሽከርካሪዎችን ለማፍራት ማሰልጠኛው ወሳኝነት እንዳለውም ጠቁመዋል፡፡
ወደፊት የግል ዘርፉ ማሰልጠኛዎችም ብቃታቸውን እንዲያሳድጉ እንደ ጥሩ ማሳያ መሆኑን አስታውሰው፤ መንግስት የግል ዘርፉን ለመደገፍም በቅርቡ ይጸድቃል ተብሎ በሚጠበቀውና ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበው የትራንስፖርት ፖሊሲ የግሉ ዘርፍ አጋርነት የሚጠናከርበት ሁኔታ የተለየ ትኩረት እንደተሰጠውም ተናግረዋል፡፡
የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ምትኩ አስማረ፤ በአገር አቀፍ በተለያየ ደረጃ የሚያሰለጥኑ 535 የተለያዩ ማሰልጠኛዎች እንዳሉ ጠቁመው፤ ምሳሌ ማሰልጠኛ አካዳሚ በአገር አቀፍ ደረጃ ከሚደርሱ አደጋዎች 75 በመቶዎች ውስጥ የሚፈጠረውን ከአሰልጣኞች ብቃት ጋር የሚያያዘውን ችግር ለማስተካከል ከፍተኛ ድርሻ ይኖረዋል ብለዋል፡፡
አካዳሚው የሚቀበላቸው ሰልጣኞች ችግረኛ ወጣቶች መሆናቸው፣ በመንግስትና በግል የጋራ ስምምነት የተደረገበት መሆኑ፣ የማሰልጠኛ መሳሪያዎቹ በምስለ ተሸከርካሪ መታገዙ ከሌሎች ማሰልጠኛዎች እንደሚለየው ተናግረው፤ በዓመት 480 የሚደርሱ የአሰልጣኞች አሰልጣኝ ለማፍራት የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የኢንደስትሪ ልማት ድርጅት (UNIDO) በኢትዩጵያ ዳይሬክተሯ አውሎሪያ ካላብሮ በበኩላቸው፤ አካዳሚው አለም የደረሰበትን ቴክኖሎጂ የሚጠቀም እንደመሆኑ በከባድ ተሸከርካሪዎችና የትራንስፖርት ዘርፍ ላይ ለሚሰማሩ አሽከርካሪዎች ክህሎት እንዲላበሱ ይረዳቸዋል ብለዋል፡፡ በቂ ዕውቀት እንደሚያስጨብጥና ሰፊ የሥራ ዕድል እንደሚከፍትም ጠቁመዋል፡፡
ፕሮጀክቱ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የተሳተፉበት ሲሆን፤ የተባበሩት መንግስታት የኢንደስትሪ ልማት ድርጅት (UNIDO)፣ ስዊዲሽ አለም አቀፍ ልማትና ትብብር ድርጅት (Sida)፣ ቮልቮ ግሩፕ (Volvo group)ና ሰላም የህጻናት መንደር ተሳትፈውበታል፡፡
ዘላለም ግዛው