
በሳን አንቶኒዮ ቴክሳስ ግዛት ወጣ ብሎ በሚገኝ ስፍራ አንድ የጭነት መኪና ውስጥ ስደተኞች እንደሆኑ የታመኑ ቢያንስ 46 ሰዎች ሞተው ተገኙ። በሕይወት የተረፉ አራት ህጻናትን ጨምሮ 16 ሰዎች ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውን አንድ የእሳት አደጋ ባለሥልጣን ተናግረዋል።
በሕይወት የተረፉ ሰዎች ሰውነታቸው በሙቀት ግሎ እንደነበርና በከፍተኛ ሁኔታም መዛል ታይቶባቸዋል ተብሏል። ከአሜሪካ እና ሜክሲኮ ድንበር 250 ኪሎሜትር ላይ የምትገኘው የሳን አንቶኒዮ ከተማ ለህገወጥ ሰዎች አዘዋዋሪዎች ዋና መተላለፊያ ናት።
ወደ አሜሪካ መሻገር የቻሉ ሰነድ የሌላቸው ስደተኞችን ለማጓጓዝ ሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች የጭነት መኪኖችን ይጠቀማሉ። “የሞቱት ሰዎች ቤተሰብ አላቸው። የተሻለ ሕይወት ለማግኘትም ይሆናል ወደዚህ የመጡት። አሰቃቂ የሰብአዊ ሁኔታ ነው” በማለት የሳን አንቶኒዮ ከንቲባ ሮን ኒረንበርግ ተናግረዋል።
የሳን አንቶኒዮ የእሳት አደጋ መከላከያ አዛዥ ቻርለስ ሁድ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት የአደጋ ጊዜ ምላሽ ሰጪዎች መጀመሪያ ወደ ስፍራው የደረሱት በአገሬው ሰዓት አቆጣጠር 12 ሰዓት ከምሽቱ ነው። “የጭነት መኪናውን በር ከፍተን ስናይ እንዲህ የተደራረቡ አስከሬን እናያለን ብለን መቼም አልጠበቅንም። ማናችንም ብንሆን ያንን አስበን ወደ ሥራ አንመጣም” ብለዋል ።
አሽከርካሪ የሌለው የጭነት መኪና ምንም አይነት የአየር ማቀዝቀዣ እንዲሁም ለመጠጥም የሚሆን እንዳልነበረው አክለዋል። የሜክሲኮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርሴሎ ኢብራርድ ወደ ሆስፒታል ከተወሰዱት መካከል ሁለት ጓቲማላውያን ይገኙበታል ብለዋል። የሌሎቹ ተጎጂዎች ዜግነት እስካሁን አልተገለጸም። ከዚህ ጋር በተያያዘ ሶስት ሰዎች በእስር ላይ ሲሆኑ ምርመራውም ለፌዴራሉ ፖሊሶች መተላለፉን ቢቢሲ ዘግቧል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 22/2014