በ2017 ዓ.ም የሴት ልጅ ግርዛትና የልጅነት ጋብቻን ሙሉ ለሙሉ ለማስቀረት እየተሰራ መሆኑን የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ገለፀ፡፡
የሚኒስቴሩ ሚኒስትር ወ/ሮ ያለም ፀጋዬ የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ የሴት ልጅ ግርዛትና የልጅነት ጋብቻን ለማስቀረት እየተሰሩ ያሉ ጉዳዮችን አስመልክቶ ባዘጋጀው መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር በኢትዮጵያ በሴቶች ላይ ስር ሰዶ የቆየው የተዛባ ማህበራዊ አመለካከትና ድርጊት ሳቢያ በተለያዩ የዕድሜ ክልል ውስጥ በሚገኙ ሴቶች ፆታንና ዕድሜን መሰረት አድርጎ ለሚፈፀም የሀይል ጥቃቶች ተጋላጭነት ከፍተኛ ነው፡፡
በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ የሀይል ጥቃቶች መካከል አስገድዶ መድፈር፣ፆቃታዊ ትንኮሳ፣ጠለፋ፣በቤት ውስጥ የሚፈፀም ድብደባና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል ያለዕድሜ ጋብቻና የሴት ልጅ ግርዛት ዋነኞቹ ናቸው፡፡
እነዚህ በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ የሀይል ጥቃቶችና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በሴቶችና በህፃናት ህይወት ላይ የጤና፣አካላዊ፣ ስነ ልቦናዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖዎችን ከማስከተላቸው በላይ በድህነት ቅነሳ ፣በምጣኔ ሀብታዊ ዕድገትና በማህበራዊ መስተጋብራቸው ላይ ከፍተኛ ጫናን ያሳድራል፡፡
መንግስት ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት የስርዐተ ፆታ እኩልነትን በማረጋገጥ በሴቶች ላይ የሚደርሱ የሀይል ጥቃቶችን ለማስቀረት የሚረዱ የህግ መዕቀፎችን በማውጣትና የአለም አቀፍ ስምምነቶችን በመፈረም ተግባራዊ እያደረገች ትገኛለች ፡፡
ከእነዚህም መካከል መንግስት በ2011 ዓ.ም የሴት ልጅ ግርዛትና የልጅነት ጋብቻን ሙሉ በሙሉ ለማስቀረት በአለም አቀፍ መድረኮች ላይ ቃል የገባ ሲሆን ተፈፃሚነቱ በህብረተሰቡ፣በሀይማኖት ተቋማትና በእምነት አባቶች እንዲሁም በሀገር ሽማግሌዎች ዘንድ እንዳለ በመተማመን እንደሆነ በመግለፅ የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ያዘጋጀው መድረክም ይህን ለማሳካት ትልቅ አስተዋፅኦም እንዳለው ሚኒስትሯ አያዘው ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ጠሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሀፊ መጋቢ ዘሪሁን ደጉ በበኩላቸው ሀገራችን በሰኔ ወር 2017 ዓ.ም ባስተናገደችው የታዳጊ ሴቶች አገራዊ ጉባኤ ላይ የሴት ልጅ ግርዛትና የልጅነት ጋብቻን በ2017 በሀገር ደረጃ ሙሉ በሙሉ ለማስቀረት በአፍሪካና በአለም አቀፍ ደረጃ የሚደረጉ ጥቃቶችን ለማገዝ ለተግባራዊነቱ በትኩረት እንደምትሰራ ቃል ገብታለች፡፡ጉባኤአችንም ችግሩን ለማስቀረትና ሀገራዊ እቅዱም እንዲሳካ እንደባ ለድርሽ አካላት የበኩሉን ሀላፊነት ለመወጣት ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር የተለያዩ ስራዎችን በመስራት ላይ ትገኛለች፡፡
ስለዚህም የሀይማኖት መሪዎች በምዕመኑ ዘንድ ባላቸው ልዩ ስፍራና ተደማጭነት በህብረተሰባችን ውስጥ በሴቶችን በህፃናት ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን ለማስቀረት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ መወጣት ይኖርባቸዋል ሲሉ መጋቢ ዘሪሁን አሳስበዋል፡፡
በወይንሸት ካሳ
ፎቶ፡- በፀሀይ ንጉሴ