አስናቀ ለረጅም ሰዓት እያነበበ ከተቀመጠበት ቦታ ላይ የመነጠቀው የስልኩ ጥሪ ነበር።የሚያነበውን መጽሐፍ ገታ አድርጎ ወደ ስልኩ ሲያስተውል የጓደኛው የናሆም ስምና ቁጥር ስልኩ ስክሪን ላይ እየቦረቀ አገኘው። ስድስት ሰዓት አለፍ ሲል ሁሌ ይደውልለታል። ምሳ ተለያይተው በልተው አያውቁም። ከምሳ በኋላ ግን የሁለት ዓለም ሰዎች ናቸው። መሽቶ ማታ አንድ ቤት፣ አንድ አልጋ ላይ ራሳቸውን እስኪያገኙት ድረስ የተለያዩ ሰዎች ናቸው። በየፊናቸው የሚያስቡ፣ በየፊናቸው የሚጋልቡ የሕይወት ባልደራስ። ሕይወት ለአስናቀ ተጠንቅቆ መርገጥ፣ ተጠንቅቆ ማሰብ፣ ተጠንቅቆ መኖር ነው።
ለናሆም ደግሞ ፈንጠዝያ..። ሕይወት ለአስናቀ የሸማኔ መወርወሪያ ናት። በየት መጥታ በየት እንደምትሄድ የማትታወቅ የአንድ ጊዜ ስጦታ። እያንዳንዱ ቀን፣ እያንዳንዱ ድርጊት ከጠመጠምነው የሕይወት ድውር ላይ የምንቀንሰው ነው ይላል። ለዚህም ሕይወት ፈንጠዝያ ብቻ አይደለችም ሲል ያምናል። ለናሆም ይሄ እብደት ነው..ሕይወት ለእሱ በየቀኑ መኖር አይደለም።በየቀኑ መደሰት ነው።በየቀኑ መስከር፣ በየቀኑ መጦዝ ነው።በቃ በየቀኑ ራሱን ከሚያስደስተው ከማንኛውም ቦታ ማግኘት።
ናሆም መጣ..። ፊቱ ላይ የተለኮሰ የደስታ ማሾ ይንቦገቦጋል። የሸሚዙ አዝራር ደረጃ ስቶ አለባበሱን አመሳቅሎታል። ‹ዛሬ በጣም ነው ደስ ያለኝ› ሲል ጓደኛውን በተቀመጠበት አቀፈው። የድምጹ ቃና የእውነትም ደስ እንዳለው ያሳብቅ ነበር።
‹ምን ተገኘ? አስናቀ ግዴለሽ መስሎ ጠየቀ።
‹ብዙ ነገር..! እስኪ ገምት› ሲለው እድሉን ሰጠው።
‹ብድርህን ከፈልክ?
‹አይደለም..› ናሆም መለሰ።
‹አበል ተጻፈልህ?
ናሆም ራሱን ነቀነቀ።
‹መጠጥ አቆምክ?
‹የማይሆነውን ምን ነካህ..
‹ታዲያ ምንድነው? አስናቀ ጠየቀ።
‹ከሊሊ ጋር ታረቅን..
‹ታዲያ ምን ይገርማል ትጣሉ የለ። በዚህ ሳምንት እንኳን ሰባት ጊዜ ነግረኸኛል። ሲል አስናቀ መለሰለት። ‹ዓለም ላይ እንደ እናንተ ተጣልቶ የታረቀ ጥንድ አላውቅም። ድሀ ሀገር ላይ መሆንክ ነው እንጂ አውሮፓና እስያ ብትሆን ጊነስ ቡክ ላይ ትመዘገብ ነበር።
‹እኛም ሀገር እኮ ጊነስ ቡክ ተጀምሯል..
‹የእኛ ሀገር ጊነስ ቡክ የተፋቱ አይመዘግብም። ሀገራችን ነውር የምታውቅ ናት። በቀን አስር ጊዜ ለሚፋታ ለእንዳንተ አይነቱ ወንበዴ ቦታ የላትም። ጠንካራ ወንድ በሆነ ባልሆነው ከፍቅረኛው ጋር የሚጣላ ሳይሆን በትዕግስት ጎጆ የሚቀልስ ነው›። አለው።
‹ባክህ አትነዝንዘኝ..ዛሬ በጣም ደስ ስላለኝ መጠጣት እፈልጋለሁ..
‹ያልጠጣህበት ቀን አለ እንዴ? ሁሌ እንደጠጣህ እኮ ነው›።
‹የዛሬው ግን የተለየ ነው..
‹ቆይ ግን አንተ ሕይወትን ጠጥቶ ከመስከር ውጪ ማሰብ ያልቻልከው ለምንድነው? ስትደሰት ጠጥተህ፣ ስትከፋ ጠጥተህ እንዴት ትችለዋለህ? የሰው ልጅ ደስ ሲለው መጸለይ ነው ያለበት። ደስታህን ግሮሰሪ ቤት ሳይሆን አዕምሮህ ውስጥ ነው መፈለግ ያለብህ። ለነገሩ ምንም ብልህ አትሰማኝም…
‹ለምን እንደማንግባባ ታውቃለህ? በምወደው ስለመጣህብኝ እኮ ነው። የሰው ልጅ በሚወደው ከመጣህበት አታሸንፈውም። ምንም ያክል ፈርጣማና ክንደ ብርቱ ብትሆን እንኳን እስከ መጨረሻዋ የሕይወቱ ፍጻሜ ድረስ ይታገልሀል እንጂ አይተውህም። አንተም የማፈቅረውን እንድጠላ እየመከርከኝ ነው…ይሄ ደግሞ የማይሆን ነው›።
‹ከመጠጣት ጋር..ጠጥቶ ከመስከር ጋር ሰው እንዴት ፍቅር ይይዘዋል? ግሮሰሪ ውስጥ ካሉ ሰካራሞች ጋር፣ ገላቸውን እየሸጡ ከሚኖሩ እንስቶች ጋር ሰው እንዴት በፍቅር ይወድቃል? ብታውቅ ኖሮ እየባከንክ ነው። በዓለም ላይ ተዓምር እንድትሠራበት በተሰጠህ ጊዜህ እየቀለድክ ነው። የሰው ልጅ መሞት የሚጀምረው ከዚህ ነው። ሞት ማለት ከሕይወት ማፈግፈግ፣ ከእውነታ መራቅ፣ ከተፈጥሮ መሸሽ ነው። ስትጠጣ ትሰክራለህ፣ ስትሰክር አእምሮ ይጎድልሀል፣ አዕምሮ ሲጎድልህ ደግሞ ለጥፋት ትሰናዳለህ። በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ የምታጎድለው እንጂ የምትሞላው የሕይወት ክፍል አይኖርህም› አለው።
‹ሕይወት ለኔ አሁን ናት። አንተ እንደምትለው ከዛሬ ወደ ነገ የምሄደው አይደለም። ስለዚህ የሚያስደስተኝን ሁሉ ከማድረግ ወደ ኋላ አልልም።ይልቅ ባትደክም ነው የሚሻልህ› ሲል መለሰለት።
‹ሕይወት አንተ እንደምትለው ፈንጠዝያ ብቻ አይደለችም። ፈንጠዝያ ነች ብንል እንኳን አሁን አንተ እየሆንከው እንዳለው አይደለም። ዓላማህ ደስታ ከሆነ ጠርሙስ ሳትጨብጥ፣ ግሮሰሪ ወንበር ላይ ሳትቀመጥ መደሰት ትችላለህ። ማየት ከቻልክ የሕይወትን እውነትነት ሊያስረዱህ የሚችሉ ብዙ መልካም ኩነቶች በዙሪያህ አሉ። ችግሩ ሕይወትን ጠልቆና አርቆ የሚያይ አዕምሮና ልብ አለማዳበርህ ነው። ዓላማህ ደስታ ከሆነ ከቤተሰብህ ጋር በመሆን፣ ከምትወዳቸው ጋር ጊዜ በማሳለፍ፣ በማፍቀርና ይቅር በማለት ደስታን ማግኘት ትችላለህ›
‹አሁን እየራበኝ ነው ምሳ መብላት እንችላለን?
‹የምልህን የማሰማ ከሆነ አይደለም ዛሬ መቼም ከአንተ ጋር ምሳ መብላት አልፈልግም። በገዛ እጅህ ስትሞት እያየሁ ዝም አልልህም።
‹እንግዲያውስ ከተፈጠርን ብለን በታሪክ የምናስታውሰው የብቻ ምሳ ተለያይተን እንብላ› ሲል ተናግሮ ትቶት ሄደ።
ለመጀመሪያ ጊዜ ተለያይተው ሊበሉ ነው።አይናገሩት እንጂ ሁለቱም ልብ ውስጥ የባይተዋርነት ስሜት ተፈጥሮ ነበር። ለብቻ መብላት ምን እንደሚመስል አያውቁትም። ለዘመናት አንድ ወንበር ላይ ተቀምጠው፣ አንድ አይነት ምግብ በልተዋል።ዛሬ ገና ባልተግባቡበት የሕይወት እውነት ተቃርነው በየፊናቸው ነጎዱ። ናሆም ምሳውን ለብቻው አዞ ሲበላ አዕምሮው እየወቀሰው ነበር። ያለመደብህ..ወንድምህን ትተህ ምነው እያለው።
የጠቀለለውን ጉርሻ ጉሮሮው መቀበል ተስኖት ወደ ገበታው መለሰው። ለአፍታ ስድስት ሰዓት አለፍ ሲል እየተሳሳቁ ምሳ የሚበሉባቸውን እነዛን ወርቃማ የአብሮነት ጊዜያቶች አስታወሳቸው። እንከን አልባዎች ነበሩ። እንከን አልባ የሆኑት ደግሞ በጓደኛው እንከን አልባነት እንደሆነ ሲያውቅ የጥፋተኝነት ስሜት ተሰማው።አልቆየም..ያስቀረበውም ምግብ ትቶ ወደ ጓደኛው ዘንድ ሄደ።
አስናቀ ግን በስፍራው አልነበረም። ናሆም ምሳውን ለብቻው መብላት ተስኖት ጦሙን ዋለ። ማታ ደርሶ ራሱን ከጓደኛው ጎን እስኪያገኘው ድረስ ጊዜው ዝንተ ዓለም ሆነበት። እንደዛሬ ማታ፣ እንደዛሬ የጀምበር መጥለቅ አጓጉቶት አያውቅም። ጓደኛውን ይቅርታ መጠየቅ ፈልጓል። ይሄን ሁሉ ጊዜ እንኳን ከሊሊ ጋር ሲጣሉ የነበረው በእሱ ጠጥቶ መስከር ነው። መጠጣቱ ወዳጆቹን ካሳጣው ሕይወት ለእሱ ምን ትርጉም ይኖራታል? ከዚህ ጥያቄ በኋላ ነበር ሕይወት ማለት አስናቀ እንደሚለው ተጠንቅቆ መርገጥ፣ ተጠንቅቆ ማሰብ፣ ተጠንቅቆ መኖር እንደሆነች የገባው።
ማታ ሲሆን ራሱን ከጓደኛው ጎን አላገኘውም። ብቻውን ተኝቶ ብቻውን ነቃ። በሕይወቱ ላይ ሁሌም በመጥፎ የሚያስታውሳቸውን ሁለት አስጸያፊ ታሪኮችን ጻፈ። ብቻውን ለምሳ መቀመጡንና ብቻውን ተኝቶ መንቃቱን።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵያ)
አዲስ ዘመን ሰኔ 17/2014