ዲያስፖራ ማለት ከአንድ መነሻ ሀገር ወይም አካባቢ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ተበታትኖ የሚኖር ሕዝብ ማለት ነው። ዛሬ ላይ በመላው ዓለም እስከ ሦስት ሚሊዮን የሚጠጉ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አባላት እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ። መንግሥት ወደ ሃገር ቤት ከሚላክ ገንዘብ ከሚያገኘው ገቢ /Remittance/ በተጨማሪ የዲያስፖራ አባላት በሀገራቸው ልማት ሲሳተፉ ሀገሪቱን ለማልማት ትልቅ አቅም ይፈጥራሉ። በተለይም በራስ አቅም በሚገነቡ እንደ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ያሉ ታላላቅ ፕሮጀክቶች ላይ የዲያስፖራው ድጋፍና ተሳትፎ ወሳኝ ነው።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለሀገራችን ብቻ ሳይሆን ለታችኛው የተፋሰሱ ሀገራትም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ግድብ ነው። ሆኖም በዓባይ ውሀ ላይ በግብጽ የመገናኛ ብዙኃንና በአንዳንድ አካላት ግድቡ ለተፋሰሱ ሃገራት ጉዳት እንደሆነ ተደርጎ ሲናፈሱ የነበሩ ሐሰተኛ ዘገባዎች የፈጠሩትን ብዥታ ማምከን ተገቢ ነው።ለዚህ ደግሞ ከመደበኛው የመንግሥት ዲፕሎማሲ ጥረት በተጨማሪ የዲስፖራው ድርሻ የጎላ ነው።
ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ በከፍተኛ መሪዎች ደረጃ ግንኙነቱ እየተጠናከረ መምጣቱ ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ውጭ ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ በሌሎች የተለያዩ የኢኮኖሚ፣ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ጉዳዮች በቅርበት ተባብሮ ለመሥራት መዘጋጀታቸው ትልቅ ግምት የሚሰጠው ተግባር ነው። ይህም የሚያሳየው ግድቡ ለቀጠናው ኢኮኖሚያዊ ትብብርና ውህደት ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ነው፡፡
ኢትዮጵያ ከመደበኛው የመንግሥታት ግንኙነት በተጨማሪ የሕዝባዊ ዲፕሎማሲ ቡድን ወደ ግብጽ፣ ሱዳን፣ ጅቡቲ እና ኡጋንዳ በመላክ የሀገራችን አቋም እና ፍላጎት ሁሉም የተፋሰሱ አገሮች በትብብር መሥራት እና የጋራ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ እንደሆነም አስረድታለች። በተጨማሪም የግብጽ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ወደ ሀገራችን በመምጣት ስለ ግድቡ ግንባታ ትክክለኛ መረጃ እንዲያገኝ ከመደረጉ በተጨማሪ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ የሀገራችን የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን አባላት ወደ ግብጽ እና ሱዳን በመሄድ በሀገራቱ ለሚገኙ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ስለ ግድቡ ትክክለኛውን መረጃ እና ኢትዮጵያውያን ለግብፅ እና ሱዳን ወንድም ሕዝቦች ያላቸውን መልካም ምኞት አስተላልፈው ተመልሰዋል።
ይህ የመደበኛና እና የሕዝብ ዲፕሎማሲ ሥራ በተፋሰሱም ሆነ በሌሎች ሀገራት በሚገኙ የኢትዮጵያውያን ዲያስፖራ አባላት ከታገዘ ስር የሚሰድ እና ዘላቂነት የሚኖረው ይሆናል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክቱ በ2003 ዓ.ም መጋቢት ወር ላይ ሲጀመር መንግሥት የዲያስፖራ ማኅበረሰቡን እንደ አንድ አጋዥ ኃይል አድርጎ በመውሰድ ከዲያስፖራው ማኅበረሰብ የሚጠበቀውን ድጋፍና አስተዋጽኦ በጉልህ ያስቀመጠ ነው። በግድቡ ግንባታ ላይ በፋይናንስና በዕውቀት የሚደረግ ድጋፍና እና ከግድቡ ጋር የተያያዘ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ተግባራትን እንዲያከናውኑ ዕቅድ ተይዞ ወደ ተግባር ተገብቷል።
የዲያስፖራው ማኅበረሰብ አባላት በሀገራቸው ተገኝተው ከሚያበረክቱት አስተዋጽኦ በተጓዳኝ ወደ ሚኖሩባቸው ሀገራት በሚመለሱበት ጊዜ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን አስመልክቶ ሊያከናውኗቸው የሚገቡ ዋናዋና ተግባራት አሉ እነዚህም፡- ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለሀገራችን ልማት ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ በመሆኑ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል በቦንድ ግዥም ሆነ በስጦታ የሚያደርገውን ድጋፍ አስከ ግድቡ ፍጻሜ አጠናክሮ እንዲቀጥል ማስገንዘብ አንዱ ነው።
እኛ ታላቁ የህዳሴ ግድብን የምንገነባው በራሳችን ሉዓላዊ መሬት ላይ ሆኖ ውሀው ተርባይን አንቀሳቅሶ ኤሌክትሪክ በማመንጨት ተመልሶ በተለመደው ፍሰቱ ወደ ግብጽና ሱዳን የሚፈስ መሆኑን፣ ሀገራችን በናይል ተፋሰስ በተለይም በታችኛው ተፋሰስ ሀገራት መካከል መተማመን ለመፍጠር ረጅም ርቀት እንደተጓዘችና እስካሁንም ያለውን የዲፕሎማሲያዊ ሂደት ማስረዳት ሌላው ኃላፊነት ነው።
ሀገራችን የናይል ውሀ ትልቋ አመንጪ ሆና እስካሁን ከውሀው ምንም አይነት ተጠቃሚ እንዳልሆነች፣የኢትዮጵያ አቋም ውሀውን ለብቻዬ ልጠቀም ሳይሆን ፍትሐዊና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ላይ ጉልህ ጉዳት ባለማድረስ ሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት ሊጠቀሙ ይገባል የሚል መሆኑን እና ታላቁ የህዳሴ ግድብ በተለይ ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት በርካታ ጠቀሜታዎች ያሉት መሆኑ ማስገንዘብ ይገባል፡፡
በተጨማሪም የግድቡን ግንባታ የማይፈልጉ ኃይሎችን እንቅስቃሴን በንቃት በመከታተል መመከት፣ የተለያዩ አፍራሽ ሚዲያዎች ስለግድቡ በሚነዙት የተዛባ መረጃ ባለመወናበድ ትክክለኛውን መረጃ ከሚመለከታቸው አካላት ብቻ መውሰድ፣ ይህን ግድብ ከዕቅድ ጀምሮ በማስተግበር በመገንባት ቁርጠኛ ፖለቲካዊ ውሳኔ ከወሰነው መንግሥት ጎን በመቆም ሁለንተናዊ ድጋፉን ማጠናከር እንዲሁም ለተለያዩ የውጭ ኅብረተሰብ ክፍሎች ስለ ግድቡ ትክክለኛውን መረጃ መስጠት መሠረታዊ ጉዳዮች ናቸው፡፡
ዲያስፖራው እነዚህን ከላይ የተዘረዘሩትን ተግባራት እንዲያከናውኑ መንግሥት በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የሚገኙ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ እና ታዋቂ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በማስተባበር በበርካታ ሀገራት የዲያስፖራ ህዳሴ ግድብ ምክር ቤት እና ኮሚቴ በማቋቋም በውጭ በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች እና ቆንስላዎች አማካኝነት በማስተባበር ላይ ይገኛል።በዚህም ዲያስፖራው በጋራም እና በተናጠል በመነሳሳት ለሀገሩ ታላቅ የልማት ፕሮጀክት ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
ያለፉት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ዓመታት በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገራት በሚኖሩ ዲያስፖራ አባላችን ዘንድ የሕዝባችን መጠነ ሰፊ ድጋፍ እና ክትትል በጉልህ የታየበት፤ ይህም ክትትል እና ድጋፍ ፕሮጀክቱ ወደፊት እንዲሄድ ተጨማሪ አቅም ከመሆን አልፎ፤ በፐብሊክ ዲፕሎማሲውም ረገድ መልካም ውጤት የተመዘገበበት ሆኖ መደበኛውንም ዲፕሎማሲ ረድቷል።
በተጨማሪም ዲያስፖራው ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በገንዘብ የሚያደርገው ድጋፍ ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ጊዜያቶች ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ ለማሰባሰቢያ ካበረከቷቸው ተሽከርካሪዎች በተጨማሪ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እስካሁን ድረስ ወደ 1.4 ቢሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል።
በተለይም በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለገና በዓል ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የቀረበላቸውን ጥሪ ተከትለው በርካታ ኢትዮጵያውያን የመጡ ሲሆን በተመሳሳይም መንግሥት ከዒድ እስከ ዒድ ወደ ሀገር ቤት! በሚል ባወጣው ፕሮግራም መሠረት በውጪው ዓለም የሚኖሩ በርካታ የእስልምና ዕምነት ተከታዮች ወደ ሀገር ቤት እየገቡ ነው። ከታኅሳስ እስከ ሚያዝያ /2014 ዓ/ም ከ53 ሚሊዮን ብር በላይ ለግድቡ በገንዘብ እና በሞራልም ድጋፍ አድርገዋል።በቀጣይም ከዲያስፖራው ሰፊ ድጋፍ ይሰበሰባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሀገራቸውን የወደፊት መፃኢ ዕድል በማሰብ ዛሬ ላይ ካለቻቸው አነስተኛ ገቢ ጭምር በመቀነስ ለግድቡ በገንዘብ፣ በቦንድ ግዢና በስጦታ ድጋፍ ከማድረግ በተጨማሪ በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ በተለይም በመካከለኛው ምስራቅ በቤት ሠራተኛነትና በተለያዩ ሥራዎች ተቀጥረው የሚሠሩ ሴት ዜጎቻችን ዘመናዊ አውቶሞቢሎችን በመግዛት ለድጋፍ ማሰባሰቢያነት እንዲውል በመላክ በቁሳቁስ ያደረጉት ድጋፍ ለሁሉም ዲያስፖራ አርአያነት ያለው ተግባር ነው፡፡
ዲያስፖራው በገንዘብ እና በዓይነት ከሚያደርገው የፋይናንስ ድጋፍ በተጨማሪም በዕውቀት ያደረገው የሚችለውን ድጋፍ እንደ አንድ ግብዓት በመሆን ቀድሞም በመንግሥት ዕቅድ ውስጥ የተያዘ ሲሆን በርካታ በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ምሑራን በቡድን እና በግል በግድቡ ግንባታ እና በፐብሊክ ዲፕሎማሲ መስክ የማማከር ሥራዎችን እያከናወኑ ይገኛሉ።
ለዚህም እንደ አብነት የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ድጋፍ ለዓባይ የተባለ የባለሙያዎች ቡድን በግድቡ ግንባታ ዙሪያ መንግሥትን እና ተደራዳሪዎቻችንን ከማማከርም አልፎ ትክክለኛ መረጃዎችን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በማሰራጨት በገንዘብ የማይተመን ሀገራዊ ግዴታቸውን በመወጣት ከመላው ሕዝባቸው ጎን መቆማቸውን አሳይተዋል።በሌላ በኩል የዲያስፖራው ዋነኛ ተግባር ተደርጎ በመንግሥት የተያዘው ዲያስፖራው በግድቡ ዙሪያ የሚያከናውነው የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ሥራ ነው።
ባለፉት ዓመታት ከ2400 በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ግድቡን በአካል በመገኘት የጎበኙ ሲሆን ወደሚኖሩበትም ሃገር በመሄድ የገፅታ ግንባታ እና የአምባሳደርነት ሚና እየተጫወቱ እንደሆነ በተለያዩ አጋጣሚዎች መመልከት ተችሏል።ለአብነት በቀድሞ የአሜሪካ መሪ ትራምፕ በኢትዮጵያ ላይ የተሰነዘረውን አግባብ ያልሆነ ንግግር በመቃወም በዓለም ዙሪያ ድምጻቸውን በማሰማት በተለይም የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ሊፍት ኢትዮጵያ ከተባለ ድርጅት ጋር በጋራ ባዘጋጁት ድምጻችን ለግድባችን በተሰኘ የአንድ ቀን የሦስት ደቂቃ ፕሮግራም በዓለም ዙሪያ በተለያየ እንቅስቃሴ በማሳየት ጠንካራ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በጸጥታው ምክር ቤት ሀገራችን ተከሳ በቀረበች ጊዜም በኒውዮርክ ጎዳና ላይ የተቃውሞ ሰልፍ በመውጣት፣ በተለያዩ ሀገራት የሚኖሩ ዲያስፖራ ወገኖቻችን ለየሀገራቱ ዲፕሎማቶች ግድባችን ለፍትሐዊ ተጠቃሚነት እየተገነባ መሆኑን በፒቲሽን እና ሰላማዊ ሰልፎች ጭምር በመግለጽ፣ እነዚህና ሌሎችም ድጋፎች በዲያስፖራው ሲደረግ ቆይቷል፡፡
ከፐብሊክ ዲፕሎማሲው በተጨማሪ የግድቡን የግንባታ ደረጃ ቀን ከሌት ነቅቶ ይከታተላል።የግድቡ የግንባታ ደረጃን ተከትሎ በሐምሌ 2012 የመጀመሪያ የግድቡ ውሃ ሙሌት ተከትሎ ግድቡ ለመጠናቀቁ ሙሉ ለሙሉ መተማመን በመፍጠሩ በ2013 በጀት ዓመት ከመቼውም ጊዜ በላይ በወኔና ደስታ ድጋፉን በማጠናከር 134 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ በስጦታና በቦንድ ግዢ ፈጽሟል፡፡
የታላቁ ህዳሴ ግድብ እውን ሆኖ የማየት ፍላጎቱ ከፍተኛ በመሆኑ ዛሬም ድጋፉን አጠናክሮ እንደቀጠለ ነው።በዘንድሮ ዓመት ከተለያዩ ሀገራት ዲያስፖራ ምክር ቤት አባላት እና የኮሙኒቲ ተወካዮች ሀገር ቤት በመምጣት በገንዘብ እና የተለያዩ ሥራዎችን ( የስዕል ሥራዎችን) ለጽሕፈት ቤቱ በማበርከት ድጋፋቸውን ገልጸዋል። ለአብነት የደቡብ እና ደቡብ ምዕራብ ጀርመን ዲያስፖራ ኮሚቴ አባላት ጽሕፈት ቤታችን ተገኝተው 18ሺ ዩሮ ለግድቡ በስጦታ አበርክተዋል።
በ2014 ዓ/ም ሀገሪቱ ባለችበት ወቅታዊ ሁኔታ ውስጥ ሆናም ባለፉት 10 ወራት ከሐምሌ 1/2013 ዓ/ም እስከ ሚያዝያ 30/2014 ዓ/ም በቦንድ ሽያጭ እና በስጦታ የተደረገ ድጋፍ ያለበት ደረጃ ስንመለከት ዲያስፖራው 257 ሚሊዮን ብር በላይ በቦንድ ግዢና በስጦታ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድጋፍ አድርጓል።
ይህ የዲያስፖራው የ10 ወራት ድጋፍ የሚያሳየው ድጋፉ በየዓመቱ ተጠናክሮ የቀጠለ መሆኑን ነው። በዓለማችን ካሉት የዲያስፖራ አባላት ብዛት አኳያ ሲታይ በእርግጥ ድጋፉ በቂ ነው ለማለት ባያስደፍርም ዲያስፖራው ለታላቁ ህዳሴ ግድብ እያደረገ ያለው አስተዋጽኦ ዛሬም እንዳልነጠፈ ፤ በቀጣይም ግድቡ እስከሚጠናቀቅ እንደሚቀጥል ማሳያ ነው።
ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ያሳየው ሁለንተናዊ ተሳትፎ ከዚህ ቀደም ያልታየ እና በመላው ዓለም ያለውን ኢትዮጵያዊ እና ትውልደ ኢትዮጵያዊ እንዲሁም ወዳጅ የሆኑ የሌላ ሀገር ዜጎች በአንድ ያሰለፈ፣ ከገንዘብ እና ከዕውቀት ድጋፍ በላቀ መልኩ በዓለም ሕዝቦች ዘንድ ሰፊ ስፍራ የያዘ ታላቅ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ትግል በታላላቅ የዓለማችን ከተሞች አደባባይ በመውጣት የታየበት ድንቅ ሀገራዊ ድጋፍ ነው።
በዲያስፖራው ያላሰለሰ ሕዝባዊ ተሳትፎ በሀገር ውስጥ ካለው ንቅናቄ ጋር ተናቦ እና ተዳምሮ ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ በሕዝባዊ ዲፕሎማሲ ጎልታ እንድትታይ እና ለመደበኛው ዲፕሎማሲ እገዛ ያደረገ፣ በዓለም አቀፍ ተቋማት እና ሀገራት ላይም የተ.መ.ድ. ፀጥታው ምክር ቤት እና ግብጽ ላይ ጭምር ተጽዕኖ የፈጠረ ሰላማዊ ትግል ተካሂዷል፤ ድል በድል እየሆን ተራምደናል።
ይሁን እንጂ አሁንም ግድቡ ተጠናቆ በቂ ውሃ እስኪይዝ ድረስ ልናልፋቸው የሚገባ እንቅፋቶች አሉ።እነዚህን እንቅፋቶች ተሻግረን ለትውልድ ደማቅ ታሪክ ማውረስ ይጠበቅብናል። ለዚህም የበለጠ እጅ ለእጅ በመያያዝ በተለይ ዲያስፖራው በሚኖርበት ሀገር የታላቁ ህዳሴ ግድብ አርበኛ ሆኖ መቀጠል ይገባዋል፡፡
ዲያስፖራው በግድቡ ዙሪያ ያሳየውን ጠንካራ ተጋድሎ ለግድቡ ግንባታ በሚያደርገው የገንዘብ ድጋፍም ሊደግመው ይገባል። በርግጥ የገንዘብ ድጋፉ ከዓመት ዓመት እየተጠናከረ የመጣ ቢሆንም ከሚጠበቀው አንፃር ብዙ ይቀራል። ያለፉት ዓመታት የዲያስፖራውን ድጋፍ ከሀገር ውስጡ ጋር ብናነጻጽር ልዩነቱ በጣም ሰፊ ነው። ለማሳያ ያህል በሬሾ 1 ለ14 ይሆናል። ይህም ዲያስፖራው በተደራጀ እና በተጠናከረ መልኩ የገንዘብ ድጋፉን አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አመላካች ነው ።
ግድቡ ለሀገር ያለውን ጠቀሜታና ለተፋሰሱ ሀገራት የሚያስገኘውን ጥቅም ከግንዛቤ በማስገባት ሰፊ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ሥራዎችን እንዲያከናውን፤ ኢትዮጵያ በራሷ አቅም እንደ ታላቁ ህዳሴ ግድብ አይነት ግዙፍ ፕሮጀክቶችን መገንባት መቻሏ ለሌሎች ሀገራት ትርጉም ባለው መልኩ ሊነገር እና ሊተነተን ይገባል። ልክ እንደ ዓድዋ ድል ታላቁ የህዳሴ ግድብም የአፍሪካውያን ብቻ ሳይሆን የዓለም ድሃ ሀገራት ሕዝቦች ድህነትን እና ተመጽዋችነትን ከጫንቃቸው ለማላቀቅ ምሳሌ አድርገው እንዲወስዱት የሚያስችል ሥራ መሠራት አለበት።
በርግጥ አሁን አሁን አንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት መንግሥታት እና አክቲቪስቶች ‹‹ግድቡ የአፍሪካ ህዳሴ ግድብ ነው›› ብለው መከራከር መጀመራቸው ዲያስፖራው በዚህ ላይ ተጨምሮ ቢሠራ ውጤታማ መሆኑን ያመላክታል።
የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ያደረገው ተሳትፎ በታሪክ ማህደር በአባይ ወንዝ ሰማያዊ ቀለም ተጽፎ ለትውልድ የሚተላለፍ ወርቃማ ገድል ነው። ይሁን እንጂ ግንባታውን ማጠናቀቅና ለተፈለገው ዓላማ ማዋል ሀገራዊ ክብራችንን ሊመልሱ ከሚችሉ ሥራዎች እንደ አንዱ መሆኑን ወስዶ አሁንም ርብርቡን አጠናክሮ መቀጠል ይጠበቅበታል፡፡
ግድቡ ከልማት አስተዋፅኦም በላይ ትርጉም ያለውና ኢትዮጵያ ግዙፍ ግድብ መገንባት አትችልም ለሚሉ አካላት እንደምትችል ያሳየንበት ፕሮጀክት በመሆኑም ለኢትዮጵያውያን የፈጠው የመንፈስ ኩራት ከፍተኛ ነው።
ወደፊትም ዲያስፖራው የግድቡ ግንባታ የሚያስገኘውን የልማት ትሩፋት መቋደስ መብቱ በመሆኑ እስከ ግድቡ ግንባታ ፍጻሜ ድጋፉን ይበልጥ አጠናክሮ ፤ ግድቡ ውሃ ሞልቶ ኃይል ሲያመነጭ ለማየት እና በሐይቁ ላይ ፈልሰስ ብሎ ተዝናንቶ ለመመለስ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ተቀናጅቶ እና ተናቦ ድጋፉን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። ዲያስፖራው ለሀገሩ ግድብ ድጋፍ ድንበር አያግደውም ርቀትም አይገድበውም።
በይገደብ ዓባይ