ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የዘጠኝ ወር አፈፃፀም ሪፖርት ባዳመጡበት ወቅት የሰጡት የሥራ መመሪያ ነበር። በወቅቱ ሁሉም የሥራ ኃላፊዎች እታች ድረስ በመውረድ የነዋሪውን ችግር በቅርበት በመረዳት መፍትሄ መስጠት እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል። ታዲያ የሥራ ኃላፊዎቹ ሥራቸውን እንዴት እየሠሩ ነው? የሚለውን ለመመልከት በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ተገኝተናል። ከቂርቆስ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ዘመኑ ደሳለኝ ጋር የነበረን ቆይታ እነሆ።
አዲስ ዘመን፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የሰጡትን የሥራ መመሪያ በምን መልኩ እየተገበራችሁ ነው?
አቶ ዘመኑ፡- መመሪያው ከተሰጠ በኋላ በከንቲባ አዳነች አቤቤ በመምራት ሁለንተናዊ ለውጥ ለማምጣት በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው። ከእነዚህም መካከል ቤቶች የማደስና የመገንባት ሥራ አንዱ ነው። በቅድሚያ የሕዝቦችን አንገብጋቢ ጥያቄዎች የሚመለስበት ሁኔታ የተመቻቸ ሲሆን እንደ ክፍለ ከተማው አስተዳደር የ60 ቀናት ዕቅድ አውጥተን በርካታ ሰው ተኮር ተግባራትን እያከናወንን ነው።
በ60ዎቹ ቀናት ይሠራሉ ተብለው የተያዙ 9 ፕሮጀክቶች አሉ። ከእነዚህ መካከል የመኖሪያ ቤት ግንባታ፤ የትምህርት ቤት ግንባታና የኮንዶሚኒየም ዙሪያ አጥር ጥያቄዎችንም ከሚመለከተው አካል ጋር ተነጋግረን በአፋጣኝ ምላሽ እንሰጣለን፡፡ ሌሎች የያዝናቸውን ሰው ተኮር ተግባራት በማጠናቀቅም የሕዝባችንን አንገብጋቢ ችግሮች ለመፍታት እየሠራን እንገኛለን።
በአስተዳደሩ የአገልግሎት ቀንን ለተገልጋይ ብቻ በማዋል የሕዝብ ሮሮን ለመቀነስ ብሎም በተገልጋዮች የሚነሱ አንገብጋቢ ጥያቄዎችን በአግባቡ አድምጦ ለመመለስ በሁሉም ጽሕፈት ቤቶች አገልግሎትን በአንድ ማዕከል መስጠት ጀምረናል፡፡ የአገልግሎት ዕለት በሆነው በዕለተ ረቡዕ እንደተለመደው በሁሉም ጽሕፈት ቤቶች የጽሕፈት ቤት ኃላፊዎችና የሚመለከታቸው የቡድን መሪዎች ባሉበት ሕዝብን ዝቅ ብለው እያገለገሉ ሲሆን ይህም ቀጣይነት እንዲኖረው ትኩረት ተሰጥቶት ይሠራል።
አዲስ ዘመን፡- ከሥራ ዕድል ፈጠራ አንፃር በክፍለ ከተማው ምን ምን ተግባሮች ተከናውነዋል?
አቶ ዘመኑ፡- ከ60 ቀናቱ የሰው ተኮር ተግባራት መካከል አንዱ የሆነው የሥራ ዕድል ፈጠራ ነው። በክፍለ ከተማው የተለያዩ የሥራ ዕድሎች ተፈጥረዋል። በአመቱ 27 ሺ የሥራ ዕድል ይፈጠራል ተበሎ ነበር። አመቱ ሳይጠናቀቅ ለ31 ሺ ወጣቶች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል።
የሥራ ዕድል ሲባል አሁን ከተማዋን አረንጓዴ ለማድረግ በሚሠራ ሥራ ላይ የሚሳተፉት ወጣቶች፤ በሸገር ዳቦ ላይ ዳቦ ከሚሸጡት አካላት በተጨማሪ እዛው ቤት ላይ ክፍል ተከፋፍሎ ፍራፍሬ የሚሸጡ፤ ፈጣን ምግቦችን የሚያቀርቡ ወጣቶች እንዲሠሩ እና እንዲጠቀሙ ተደርጓል። የሸገር ዳቦ መሸጫ ቤቶችን በማሻሻል ሌሎች ተጓዳኝ ሥራዎችም እንዲሠሩ ተደርጓል።
ከጀርመን ተራድኦ ድርጅት ጋር በመተባበር 115 ወጣቶች የተደራጁ ሲሆን ግማሹን በሻማ ማምረት ሥራ፤ በሳሙና ማምረትና በዘይት ማምረት ደረጃ እንዲሠሩ ስልጠና ወስደው በቂ ብድር ተመቻችቶላቸው በሙከራ ደረጃ ሥራ ተጀምሯል።
በክፍለ ከተማው ዳቦ ማምረቻም የተቋቋመ ሲሆን፤ የካናዳ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን አማኞች ወደ ሰባት ሚሊዮን ብር የሚገመት አንድ የዳቦ ማሽን ለግሰዋል። ያ የዳቦ ማሽን ሲተከልም 30 ለሚሆኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን፤ ማሽኑን ክፍለ ከተማው እያስተዳደረ ወጣቶች ዳቦ በማምረትና ወደ ገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ ሆነዋል።
የተለያዩ የቤት ግንባታዎች ሲደረጉ ለወጣቱም የሥራ ዕድል የሚፈጠር ሲሆን፤ ወጣቶቹ ወደ ሥራቸው ሲገቡ ሙሉ ትኩረታቸውን ወደ ሥራው አድርገው በታማኝነት የሚሠሩ ወጣቶች ናቸው። ወጣቶቹ የሥራ ዕድል ከማግኘታቸውም በላይ አገር ለማሳደግ የተዘጋጁ ለዜጎች ታማኝ የሆኑ የአገር ፍቅር ስሜት በውስጣቸው የተፈጠረና ለኢኮኖሚውም ጠብ የሚል ነገር ሊያበረክቱ የሚችሉ ወጣቶች ተፈጥረዋል።
አዲስ ዘመን፡- በብዙ ክፍለ ከተሞች ሥራ አጥ ወጣቶች እያሉ በአቋራጭ ለሌላ የሚሰጥበት ሁኔታ እንዳለ ይነገራል። በእናንተ ክፍለ ከተማ አሠራሩ እንዴት ነው? ለመሆኑ እንዲህ ዓይነት ችግሮችን የምትከታተሉበትና እርምጃ የምትወስዱበት ሁኔታ አለ?
አቶ ዘመኑ፡– እውነት ለመናገር ከዚህ በፊት ብዙ ጊዜ የሥራ ዕድል የሚፈጥረው በትውውቅ ነው፡፡ እኛ የሥራ ዕድል ስንፈጥር ትኩረት እያደረግን አልነበረም፡፡ ትኩረት ያለማድረግ አስተሳሰብን በመስበር የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበርና የአዲስ አበባ ሴቶች ማህበር ሙሉ ተሳታፊ እንዲሆኑ አድርገናል፡፡ አሁን የአካባቢው ማኅበረሰብ ድረስ በመውረድ ቤት ለቤት በመለየት ምዝገባ ይደረጋል። በኮሚቴ እየታየ ምዝገባ ከተደረገ በኋላ ደግሞ በተለያየ መንገድ የማጣራት ሥራ ይሠራል።
ከላይ እንዳልነው ከተደራጁት 115 ወጣቶች መካከል አጭበርብረው የገቡ ሁለት የነበሩ ሲሆኑ እነሱን በክትትል ማስወገድ ተችሏል። ወደ ማኅበረሰቡ የወረደ የሥራ ዕድል ለመፍጠር የተሠራው ሥራ ሙሉ ለሙሉ የፀዳ ነው ባይባልም፤ ትክክለኛ አካሄድን በመከተል ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- አካባቢው እንደ ሚታወቀው ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ያሉበት አካባቢ ነው፡፡ የሕዝቡን ኑሮ ቀለል ለማድረግ ምን እየተሠራ ነው?
አቶ ዘመኑ፡– በክፍለ ከተማው የድህነት ደረጃው አስከፊ የሆነበት፤ በዚያው ልክ ደግሞ ከፍተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚገኙበት አካባቢ ነው። አብዛኛውን ጊዜ በድህነት የሚጠራው ቂርቆስ አካባቢ ሳይቀር የሚገኘው በዚሁ ክፍለ ከተማ ውስጥ ነው። ይህን አስከፊ ድህነት ለመቅረፍ እየተሠራ ይገኛል።
አካባቢው መሃል ከተማ እንደመሆኑ ብዙ ልማት የሚከናወንበት ብዙም ድህነት ያለበት አካባቢ ሲሆን፤ ለውጥ ለማምጣት እየተሠራ ይገኛል። የምገባ ማዕከላት እንዲኖሩ ተደርገዋል። ከዚህ ቀደም አንድ ብቻ የነበረውን የምገባ ማዕከል ወደ ሦስት እያሳደግነው ነው፡፡ ከ100 በላይ አቅመ ደካሞችና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ነዋሪዎች ቀጣይነት ያለው የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብር ተከናውኗል፤ በመከናወን ላይም ይገኛል። ይህንን ድጋፍ በአካባቢው ከሚገኙ ባለሀብቶች ጋር በማስተሳሰር ተከታታይነት እንዲኖረው ለማድረግ ተሠርቷል።
ሌላው የእሁድ ገበያን ለማኅበረሰቡ ተደራሽ ማድረግ ነው። በዚህም ስድስት የእሁድ ገበያ ማዕከሎችን በማዘጋጀትና የመሸጫ ዋጋም ተመጣጣኝ እንዲሆን ቀጥታ ከገበሬው ጋር ንግግር ይደረጋል። በሌላ በኩል ለድጎማ መቶ ሚሊዮን ብር የተሰጠ ሲሆን፤ በዚህም በቂ የጤፍ አቅርቦት እንዲኖር ተደርጓል።
የዘይትና አንዳንድ ነገሮችን በክፍለ ከተማው እየተሞከረ ሲሆን፤ ዘይት እንዴት እንደሚመረት ለወጣቶች ስልጠና ሰጥቶ በአገር ውስጥ ግብአት የተመረተ ዘይት ለሸማቹ የአገር ውስጥ ምርት እንዲደርስ እየተሞከረ ነው። 115 የሚጠጉ ወጣቶችን ከጀርመን ተራድኦ ድርጅት ጋር በማስተሳሰር ሥራ ለማስጀመር ታስቧል።
የአቅመ ደካሞችን ቤት በማንሳት አዳዲስ ዘመናዊ ብሎኮችን የመሥራት፤ ባለሀብቶችን በማስተባበር ከአካባቢው ነዋሪዎች ተጨማሪ ለሌሎችም የሚሆን ቤት የመገንባት ሥራም ተሠርቷል። የሚሠሩ ሥራዎች በሙሉ የዜጎችን የድህነት መጠን ማዕከል ያደረገ ነው። በሁሉም አካባቢ የሥራው ባለቤቶች አሉ፡፡ ሁሉም በየሥራ ኃላፊነቱ ሥራውን እንዲሠራ መስመር የማስያዝ ሥራዎችም እየተሠሩ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- እነዚህ የሚሠሩት የምገባ ማዕከላት የድሃውን ማኅበረሰብ ችግር ከማቃለል አንፃርስ ምን ያህል ውጤታማ ናቸው?
አቶ ዘመኑ፡– ከዚህ በፊት የአንድ ሺህ ሰው ምገባ ይካሄድ ነበር። ፑሽኪን አዲሱ አስፓልት መንገድ የተሠራበት አካባቢ፤ ቄራ የሚባለው አካባቢ አንድ ሺ ሰው ለምሳ የተለያየ ፕሮግራም ወጥቶለት በለጋሽ ድርጅቶች አማካኝነት ምገባ እየተካሄደ ነበር። ይሄ በመሆኑ ዕድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ የሆኑ መሥራት የማይችሉ እና አንዳንድ ልጆቻቸው ቀን ትምህርት ቤት ተመግበው ማታ ‹‹ለልጆቻችን ምን እናብላቸው?›› የሚሉት በሳህን ይዘው መሄድ እንዲችሉ ተደርጓል፡፡ ይህ ብዙሃኑ የዕለት ጉርስ እንዲያገኙ ያደረገ ፕሮግራም ነው።
ከዚህ በፊት ከነበረው በተጨማሪ ሁለት የምገባ ጣቢያዎች እየተገነቡ ሲሆን፤ አንዱ ቂርቆስ አካባቢ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ጥላሁን ገሰሰ አደባባይ የሚባለው አካባቢ እየተሠራ ነው። ከማዕከላቱ መካከል አንዱ በአቶ በላይነህ ክንዴ ድጋፍ የሚሠራ ሲሆን፤ አንደኛው ደግሞ ሚኪ የተባለ በጎ አድራጊ እየሠራው ይገኛል።
በበላይነህ ክንዴ የሚሠራው ላይ አንድ ሺ ሰዎች የሚመገቡ ሲሆን፣ ሁለተኛው ላይ አምስት መቶ ሰዎችን ለማስተናገድ እንዲችል ተደርጎ እየተሠራ ነው። በተጨማሪ ይህ የምገባ ማዕከል በመኖሩ ለሚያበስሉ እናቶች የሥራ ዕድል ይፈጥራል። ከዚህም በተጨማሪ የማዕድ ማጋራት ሥራውን ከአካባቢው ባለሀብቶች ጋር አስተሳስረን እየሠራን እንገኛለን።
አዲስ ዘመን፡- የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ የከተማ ግብርናም አንዱ አማራጭ ተደርጎ በስፋት ወደ ሥራ ተገብቷል። በእናንተ ክፍለ ከተማ ያለው እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?
አቶ ዘመኑ፡– በክፍለ ከተማ ወረዳ 02 በተለምዶ 41 ኮንዶሚኒየም አካባቢ በግል ሥራ የሚተዳደሩ አንድ ነዋሪ የግል ሥራ ቢኖራቸውም ትርፍ ጊዜያቸውን በከንቱ ማባከን አልፈለጉም። በከተማ ግብርና እሳቤ ውስጥ በመግባት እጃቸውን ከመሬት አገናኝተው እጅግ ድንቅ የጓሮ አትክልት ያለማሉ። በአንድ ግለሰብ የተሠራው ይህ ተሞክሮ፤ ሰፋ ቢደረግ ምን ያህል ውጤታማ ይሆናል? የሚለውን በመቀመር በክፍለ ከተማው ያሉ ቦታዎችን የመለየት ሥራ ተጀመረ።
የከተማ ግብርና፤ በከተማ አስተዳደሩ ትኩረት ተሰጥቶት በግለሰቦች መኖሪያ ግቢ፤ በመንግሥት ተቋማት በሚገኝ ክፍት ቦታና መሠል ክፍት መሬት በተገኘበት ሥፍራ ሁሉ በንቅናቄ መልክ ተጀምሯል። ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች በመደጎም ትኩስ የአትክልት ውጤቶችን ለተጠቃሚ በማድረስ ተጨባጭ ውጤት እያመጣ ነው።
በክፍለ ከተማው ቅጥር ግቢ ውስጥ በጠባብ መሬት ላይ የተቀናጀ የከተማ ግብርና ተግባራዊ እየሆነ ነው። በአጭር ጊዜ ጥቅም ላይ የሚውሉ የጓሮ አትክልቶችን ማልማት ተችሏል። በክፍለ ከተማው ባሉ አስር ወረዳዎች ልማቱ ሲካሔድ አብዮት ቅርስና ኡራኤል ትምህርት ቤቶችን የማልማት ሥራ ይካሔዳል። በአብዮት ቅርስ ትምህርት ቤት ከሃምሳ በላይ ላሞችን በማርባት ለተማሪዎች ወተት ማቅረብ ብሎም ለገበያ ለማቅረብ እየተሠራ ይገኛል። ይህም ከወሬ ባለፈ በተግባር እየተተገበረ ያለ ጉዳይ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የጎርፍ ተጋላጭ አካባቢ የሚኖሩ ነዋሪዎችን ስጋት ለመቀነስ ምን እየተሠራ ነው?
አቶ ዘመኑ፡– በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 03 እና 05 በተለምዶ ጎርጎሪዮስ እና 09 እየተባሉ በሚጠሩ አካባቢዎች በአብዛኛው ጎርፍ ያጠቃቸዋል ተብለው የሚታሰቡ ናቸው። ቦታዎቹ ከፍተኛ የጎርፍ ውሃ የሚወርድባቸው በመሆኑ ክረምት በመጣ ቁጥር ለዜጎች ሕይወት መጥፋትና ስጋት እንዲሁም ለንብረት መውደም ምክንያት እየሆኑ ኖረዋል። በመንግሥት በኩልም ችግሩ በተፈጠረ ቁጥር መፍትሔ ለመስጠት ቢሞከርም በዘላቂነት ችግሩን መቅረፍ አልተቻለም።
የክረምት ጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን በዘላቂነት መፍትሔ በመስጠት የነዋሪውን ስጋት ለመቀነስ በልዩ ትኩረት እየተሠራ ሲሆን፤ በጥናት ላይ የተመሠረተ መፍትሔ በአፋጣኝ እየተሰጠ ነው። ዜጎች በመኖሪያ አካባቢያቸው በምንም ዓይነት ሁኔታ በስጋት መኖር የለባቸውም። ከዚህ በፊት ችግሩን ለመቅረፍ በመንግሥት በኩል የተደረገው ጥረት እንደተጠበቀ ሆኖ አሁን ግን ዘላቂ መፍትሔ በመስጠት ኅብረተሰባችንን ከስጋት ነፃ ለማድረግም ርብርቡ ቀጥሏል።
አዲስ ዘመን፡ – በክፍለ ከተማው ያለው የአገልግሎት አሰጣጥስ ምን ይመስላል? ቀደም ሲል ይታዩ የነበሩ ክፍተቶችን ለማስተካከል ምን ተሠራ?
አቶ ዘመኑ፡- የማኅበረሰቡን ሮሮ ለመቀነስ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው። ከእነዚህም መካከል ሠራተኛው የሥራ ሰዓትን አክብሮ እንዲሠራ በቅርቡ ክብርት ከንቲባዋ በተገኙበት የአሻራ ቴክኖሎጂ አገልግሎት መስጠት ተጀምሯል።
ይህም ሠራተኞች የሥራ ሰዓት ማርፈድ፤ በሥራ ሰዓት በትክክል ሥራ ገበታ ላይ አለመገኘት፤ ሁለት ቦታ ተቀጥሮ ደመወዝ መብላት እና ሥራ ላይ የሚያደርጉትን ትኩረት ለማሻሻል በቴክኖሎጂ ታግዞ ክትትልና ድጋፍ ለማድረግ የጣት አሻራ ፊርማ ተጀምሯል፡፡ የጣት አሻራው ሠራተኛው በቀን ሦስት ጊዜ ይፈርማል። ሠራተኛው ጠዋት ቢሮ ሲገባ፤ ቀን ምሳ ሲወጣና እንዲሁም ማታ ከሥራ ሲወጣ ይፈርማል፡፡
ይህን በቴክኖሎጂ የተደገፈ የፊርማ አሠራር ሠራተኛው ስንት ሰዓት እንደሠራ ክትትል የሚደረግ በትና በቆየባቸው የሥራ ሰዓት የሠራቸውን ሥራዎች ውጤታማነት የሚለካበት ሥርዓት አንድ ላይ አጠቃሎ የያዘ ነው፡፡
የሕዝቡ አንገብጋቢ ችግሩ እስኪፈታ ድረስ በትጋት፣ በታማኝነትና በቅንነት ወደ ሕዝቡ ቀረብ ብለን ማገልገላችንን እንቀጥላለን። በቀጣይም ዜጎች የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል ዘመናዊ አሠራር ለመዘርጋት ከተማ አስተዳደሩ ከመቼውም ጊዜ በላይ በቁርጠኝነት እየሠራ ነው።
በሥራ አስፈፃፀም ደረጃም ረቡዕና አርብ ባለጉዳይ የሚስተናገድበት ቀን በማድረግ ለእያንዳንዳቸው ችግሮች መፍትሄ ለመስጠት የሚሠራበት አካሄድም ተፈጥሯል። ከታች ጀምሮ እስከ ላይ ድረስ በየደረጃው ክትትል እየተደረገ ሥራዎችን በትኩረት የሚሠሩ አገልግሎት ሰጪዎችን መፍጠር ችለናል።
አዲስ ዘመን፡- ከተማዪቱን ውብና አረንጓዴ ከማድረግ አንፃር ምን ተሠራ? በቅርቡ ብዙኃኑን እያነጋገረ ያለው የአዲስ አበባ ሕንፃዎች ቀለም ጉዳይ በእናንተ ክፍለ ከተማ እንዴት ተስተናገደ? የደህንነትና ጸጥታ ሁኔታስ?
አቶ ዘመኑ፡– በክፍለ ከተማ የሚገኘውን ከኡራኤል ወሎ ሰፈር እንዲሁም እስከ ፑሽኪን አደባባይ ያለውን መንገድ በአረንጓዴ የማስዋብ ሥራ እየተከናወነ ነው። ፕሮጀክቱ በ60 ቀናት ከሚተገበሩ ሰው ተኮር ተግባራት መካከል አንዱ ሲሆን ዜጎች በንፁህና አረንጓዴ ስፍራ የመኖር መብት ለማስጠበቅ እየተሠራ ነው። አዲስ አበባን እንደ ስሟ አዲስ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት መላው የከተማው ነዋሪዎች፣ ባለሀብቶችና በጎ ፍቃደኞች ከአስተዳደሩ ጎን መቆማቸውም ሥራውን ውጤታማ እያደረገው ነው።
አዲስ አበባን የማሳመር ደረጃዋን የጠበቀች የማድረግ ሥራ በተለያየ መልኩ ይሠራል። ከተማዋ ስትታሰብ የራሷ የሆነ መገለጫ ስለሌላት እስታንዳርድ ወጥቶ ወጥነት ያለው ይሆን ዘንድ በቀለሞች ይመሳሰሉ ሲባል ሰው ሁሉ አዲስ አበባ ግራጫ ልትሆን ነው እያለ ነበር። ነገር ግን አስራ ሦስት ዓይነት የቀለም አማራጮች የፈለገውን ዓይነት ቀለም መርጦ መቀባት ይችላል።
ለምሳሌ ነጭ፤ ብርቱካናማ፤ ግራጫ፤ ጠቆር ያለና በርካታ አማራጮች የተቀመጡ ሲሆን፤ የከተማዋን ውበት በአረንጓዴ ልማት ብቻ ሳይሆን ደረጃውን የጠበቀ ውበት እንዲኖራት የራሷ መለያ ያላት ከተማ እንደ ስሟ አበባ እንድትሆን ለማድረግ እየተሠራ ነው።
ክፍለ ከተማችን ላይ ያለው የፀጥታ ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ነው። ከደህንነት አንፃር የቀን ክትትል ሪፖርቶች ሲታዩ የፀጥታ ሁኔታው ተሻሽሏል። ይህም የሆነበት ምክንያት አንዱ በህልውና ዘመቻው ጊዜ የተደራጁ በጎ ፈቃደኞች ነበሩ። በየጊዜው ተከታታይ ስምሪት ይወጣል፤ በአጋጣሚም የወንጀል ክስተቶች ቢኖሩም ወዲያው እርምጃ የሚወሰድበት ሁኔታ አለ።
ባሳለፍናቸው ሁለት ወሮች በክፍለ ከተማው ምንም ዓይነት የፀጥታ ችግር አላጋጠመም። ማታ ላይ ስምሪቶችን የመከታተል ሥራ ይሠራል፡፡ የፀጥታ መዋቅሩና ኅብረተሰቡ በጋራ በመስራቱ ምንም ወንጀል ተፈፀመ ባይባልም በጣም በተለየ መልኩ ግን ፀጥታው የተጠበቀና ሰላማዊ ክፍለ ከተማ ሊሆን እየቻለ ነው። ሕዝባዊ ሠራዊቱ የራሱ የሆነ የመለያ ልብስ ያለው ከፖሊስ ጋር በጋራ ተባብሮ የሚሠራ መሆኑ የጸጥታውን ሁኔታ የተሻለ ደረጃ ላይ አድርሶታል።
አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻ ማስተላለፍ የሚፈለጉት መልዕክት ካለ ዕድሉን ልስጥዎት?
አቶ ዘመኑ፡- ሰላም የሆነ አካል ስለፈለገ ሳይሆን ሰላም የሚሆነው ለሰላም የሚሆን መደላድል መፍጠር ከእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ይጠበቃል። በሁሉ አካባቢ በየደረጃው ያለው ሰው እያንዳንዱ ሰው ኃላፊነት አለበት። ወደ እዚህ ምድር የመጣነው በፈጣሪ ፍቃድ ነው፡፡ ማንም ፈልጎ ወዶ አልመጣም ። ወደምድር ከመጣን በኋላ ግን የእኔን ሀሳብ ሌላው ይቀበለኝ ብሎ ከመጫን፤ በመቻቻል ለመኖር መነሳት መፍትሄ ነው። ከብሔርተኝነት፣ ከጎጠኝነት በላይ ሰውነትን ማስቀደም እና ታላቅ አገርን የመፍጠር ሀሳብ ሊቀድም ይገባል። አብዛኛው ሰው ሰውነትን ካስቀደመ ‹‹የሰላም ባለቤት እኔ ነኝ›› ብሎ ካሰበ አገር እንደ አገር መቆም ትችላለች።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተማዋን በባለቤትነት ቀይሩ ካሉ በኋላ ባለን ኃላፊነት ከተማዪቱን ውብ ለማድረግ የመትጋት ባህላችን ጎልብቷል። ሁሉም አመራር ሙሉ ቀን የሠራውን ሌሊት ከክቡር ከንቲባዋ ጋር በቴሌ ኮንፍረንስ ያስገመገማል። የሥራ ባህሉ በዚህ ልክ ከሄደ ደግሞ እጅ ለእጅ ተያይዞ ወደ ከፍታ ለመሄድ የሚያዳግት ነገር አይኖርም። ለሁሉም ነገር ለውጥ ግን የአንድነት አስተሳሰብን አሳድጎ፤ መረዳዳት እና መቀራረብ ያስፈልጋል። ሁሉም በተቀራረበ ሀሳብ ወደ ከፍታ ለማደግ አገርን ለማሻገር መነሳት አለበት።
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ።
አቶ ዘመኑ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አሥመረት ብሥራት
አዲስ ዘመን ሰኔ 16/2014