ስለልዕለ ኃያሏ አሜሪካ ብዙ ሰዎች የሚሉት አንድ ነገር አለ፤ በሆነ ድንገተኛ አጋጣሚ የአገሪቱ መሪ ባይኖር አገሪቱ ምንም አትሆንም። እንዲህ ዓይነት ትንታኔዎች የበዙት በተለይም ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነው ከመጡ በኋላ ነበር።
ዶናልድ ትራምፕን ብዙዎች እንደሚሏቸው፤ እንኳን አገርን ያህል ነገር፣ አንድ ተቋም የመምራት ስብዕና የሌላቸው ናቸው። ሆኖም ግን ኃያሏን አሜሪካን ለአራት ዓመታት አስተዳድረዋል። ግን አገሪቱ አሜሪካ ስለሆነች በእንደ ትራምፕ ዓይነት ሰው ተመራች። ለምን? ሕዝቡ የሰለጠነ ስለሆነ።
ትራምፕ የአንዲት አፍሪካ አገር መሪ ቢሆኑ ብለን እናስብ። ያቺ አገር እስከዛሬ አትፈርስም ነበር? የዓለም አገራት መሪዎች ሌላ ያወሩ ነበር? ማዕቀብ በማዕቀብ አትሆንም ነበር? ዳሩ ግን ማዕቀብ ጣይና አንሽዋ አሜሪካ ስለሆነች በእንደ ትራምፕ ዓይነት ሰው ተመርታለች። እነሆ ሌላም ምስክር!
በአሜሪካ የምርጫ ሕግ መሠረት የትራምፕ ጊዜ ገደብ ተጠናቆ ምርጫ ሲደረግ ከጆ ባይደን ጋር የነበረው ፉክክር የዓለምን ቀልብ ስቦ ነበር። ትራምፕ ግን ገና ምርጫው ሳይደረግና የምርጫው ውጤት ሳይታወቅ ነበር ‹‹ተጭበርብሯል፣ እከሳለሁ›› የሚል ድንፋታ የጀመሩት።
በዚያን ወቅት የተለያዩ የዓለም መገናኛ ብዙኃን የሕዝብ አስተያየት እያሰባሰቡ ነበር፤ ‹‹እንዴት አሜሪካ ውስጥ ሆኖ ምርጫ ተጭበርብሯል ይላል! አስደፈረን!›› እያሉ በቁጣ የሚናገሩ ብዙዎች ነበሩ። እንዲህ ዓይነት ስብዕና ባለው ግለሰብ ስትመራ የቆየችው አሜሪካ ምንም ኮሽታ ሳይፈጠር ጣጣዋን ጨረሰች።
የአሜሪካን ነገር ያነሳሁት ስለአሜሪካ ለማውራት አይደለም። የሕዝብ መሰልጠንና ለአገር አሳቢነት ምን ያህል አገርን ሰላም እንደሚያደርግ ምሳሌ እንዲሆነን በሚል ነው።
እውነት እኛ የኢትዮጵያ ሕዝቦች እንደሚባልልን ስልጡንና የምንከባበር ነን? በአፋችን እንደምናወራው አገር ወዳድ ነን? እንዲያ ከሆነ ታዲያ እነዚህ በየጊዜው የምናያቸው ዘግናኝ ድርጊቶች ከየት የመጡ ናቸው?
ሕዝብ ነው የሚያደርጋቸው ለማለት አይደለም፤ ዳሩ ግን ለድርጊቶች መቀጣጠል ድንጋይ አቀባዮች ነን። የንትርክና የጥላቻ ዘመቻውን አቀጣጣዮች ነን። አሉቧልታና የሀሰት መረጃዎችን ብንጸየፍ እንዲህ አይሆንም ነበር።
በነገራችን ላይ መንግሥት ‹‹ድብቅ አጀንዳ ያላቸው›› የሚለው እውነት ነው። ምክንያቱም እንዲህ ዓይነት ጥፋት የሚያደርሱ ሰዎች በግልጽ አይታዩም። ያም ሆኖ ግን ‹‹ድብቅ አጀንዳ ያላቸው›› የምትለዋ የተለመደች አገላለጽ መንግሥትንም ከወቀሳ አታድንም። በኢህአዴግ ጊዜ በጣም የተሰለቸ አገላለጽ የነበረው ‹‹የእገሌ ተላላኪዎች›› የሚል ነበር። እነሆ አሁንም እየተባለ ነው። ጥፋቱን ያ የተባለው አካል ካደረሰው አስተዳዳሪው መንግሥት አይወቀስም ማለት ነው?
ሕዝብም እኮ እያለ ያለው መንግሥት ሕግ ያስከብርልን ነው እንጂ መንግሥት ራሱ ነው ጥፋቱን ያደረሰው አይደለም። ‹‹እገሌ ነው ጥፋቱን ያደረሰው›› ማለት ከተወቃሽነት አያድንም። ምክንያቱም እነ ‹‹እገሌ›› ጥፋት እንዳያደርሱ መጠበቅ የመንግሥት ኃላፊነት ስለሆነ። አሁን ያለው የአገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል። መንግሥት ሕግ የማስከበር ሥራ እየሠራ ነው።
አንድ የሚገርመኝ ነገር ግን የመንግሥት ችግር ተደጋግሞ ሲነገር የሕዝብ ችግር ደግሞ አለመነገሩ ነው። መንግሥትም ታዋቂ ሰዎችም አንድ ያስለመዱት ነገር አለ። ይሄውም ‹‹ሕዝብ ሁሌም ትክክል ነው›› የሚባለው ነገር። ሕዝብ ሁሌም ትክክል ነው ብሎ መደምደም አይቻልም። ሕዝብም ይሳሳታል። መንግሥት እርምጃ ሲወስድም ይወቀሳል፤ ባለመውሰዱም ይወቀሳል። ምናልባት ‹‹ሕዝብ ማለት የትኛው ነው?›› የሚለው ያወዛግብ ይሆናል። ምንም ይሁን ግን ሕዝብ ለሰላምና ለልማት ሆ ብሎ ቢነሳ ሰላም ማስፈን ይችላል። በአካባቢው የሚደርስን ጥፋት የማስቀረት ኃይል አለው። አካባቢውን የመጠበቅና ሰላም የማድረግ አቅም አለው።
የአገራችን ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት መድረክ ላይ የሚያደርጉት ንግግር ብዙ ጊዜ አሰልቺና የተደጋገመ ነው ተብሎ ይወቀሳል፤ ግን አይፈረድባቸውም። ምክንያቱም ከተለመደው ወጣ ያለ ንግግር ቢጠቀሙ ብዙ ፀጉር ሰንጣቂ አለና ሌላ ጣጣ ማምጣት ነው ብለው ይፈራሉ። እየሆነም አይተናል። የከፍተኛ ባለሥልጣናት ንግግሮች በማህበራዊ ገጽ አልፈው በጋዜጣና መጽሔቶች፣ በሬዲዮና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች መነጋገሪያ ሆነው ያውቃሉ። ይሄ ችግር አልነበረውም (እንዲያውም ሀሳባዊነት ነው ልንለው እንችላለን)። ችግሩ ግን ወደ ጥፋት እየተገባ ነው። ከውይይት ይልቅ እንደ ድንጋይ ዘመን ወደ ድንጋይ ለቀማ እየሄድን ነው።
በነገራችን ላይ ይሄኛውም ችግር ወደ መንግሥት ይወሰዳል። ‹‹በውይይት የሚያምን የሰለጠነ ሕዝብ መፍጠር የመንግሥት ኃላፊነት ነው›› የሚሉ ብዙዎች ናቸው። ግን ያ ደግሞ የእነዚያ የጠቢባን አባቶች ልጅ ሆኖ ከመንግሥት ብቻ መጠበቅም ትክክል አይደለም። መንግሥት እኮ ይቀያየራል፤ በቃ አንድ የሥርዓት ዓይነት ነው። ደርግ ሄደ ኢህአዴግ መጣ፣ ኢህአዴግ ሄደ ብልጽግና መጣ፤ ብልጽግና ሲሄድ ሌላ ይመጣል። በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን አገርና ሕዝብ አለ። አገርን ለትውልድ የሚያስተላልፈው አንድ ሥርዓት ብቻውን ሳይሆን ይሄ ሕዝብ ነው።
ፖለቲከኞች፣ ታዋቂ ሰዎች፣ ተራው ሕዝብ… መንግሥትን ምሩ። መንግሥት በሕዝብ ይመራል። አለበለዚያ መንግሥት በኃይል ይመራናል። መንግሥትን መምራት ማለት ሕግን ማክበር ነው። መንግሥትን መምራት ማለት ከመንግሥት ጋር መሥራት ማለት ነው። ይሄ ማለት መንግሥት እንደፈለገው ሲያበለሻሽ ዝም ማለት አይደለም። ዳሩ ግን ሁልጊዜ መንግሥትን መውቀስ ብቻ መፍትሔ ማስመሰል መንግሥት በራሱ ውሳኔ ብቻ እንዲመራን ማድረግ ነው። ምክንያቱም መሰማማት ከሌለ የሚሆነው ይኸው ነው።
የሕዝብ መሪነት፣ የሕዝብ ሉዓላዊነት፣ የሕዝብ የበላይነት የሚታወቀው ፀብ አጫሪዎች ጥፋት በሚያደርሱበት በእንዲህ ዓይነቱ ወቅት ነው። የውጭ መገናኛ ብዙኃን እየሠሩት ያለውን ዜና አይተናል። ገመናችን በዓለም አቀፍ ደረጃ እየታየ ነው ማለት ነው።
‹‹ጥፋት አድራሹ ጥቂት ቡድን ነው፤ ሕዝብ ምን ያድርግ?›› ይባል ይሆናል። ግድየላችሁም ጎበዝ መፍትሔው ከሕዝብ ነው። አንዱ በአንዱ ላይ ጥላቻ የሚያሳድር ነገር አንናገር። የእገሌ ሕዝብ ነው እኔ ምን አገባኝ አንበል! የዚህ ቋንቋ ተናጋሪ ነው በዚህ ቋንቋ ተናጋሪ ላይ ያደረሰው የምንል ከሆነ የጥፋቱ ተባባሪዎች ነን ማለት ነው።
ሌላው ደፈር ብለን ልንናገረው የሚገባው ነገር፤ መንግሥት ሕግ ያስከብር ብለን እንደወተወትነው ሁሉ፤ መንግሥት በጥፋተኞች ላይ እርምጃ ሲወስድ ‹‹በእገሌ ሕዝብ ላይ የተደረገ ዘመቻ›› ማለት የለብንም። ያልታጠቁ ንጹሃንን የሚጨፈጭፍ አረመኔ ማንንም ሕዝብ ሊወክል አይገባም!
በአጠቃላይ፤ ደረጃው ይለያይ እንጂ አገር የመምራት ኃላፊነቱ የሁላችንም ነው። አቀጣጣይ ነገሮችን አለመናገር ሰላምን እንደማስከበር ነውና ሁላችንም ኃላፊነታችንን እንወጣ!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሰኔ 15/2014