
አዲስ አበባ፡- የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ዘላቂ ሰላምና ልማት እንዲጠናከር ቻይና ድጋፍ እንደምታደርግ ገለጸች። የመጀመሪያው የቻይናና አፍሪካ ቀንድ ሀገራት የሰላም፣ የአስተዳደርና የልማት ኮንፈረስ ተካሂዷል።
ሰላምና ልማት ላይ ትኩረቱን ያደረገው የመጀመሪያው የቻይናና አፍሪካ ቀንድ ሀገራት ኮንፈረንስ ትላንት በአዲስ አበባ ከተማ መካሄድ ጀምሯል። በመድረኩም በቻይና ፍላጎት መሠረት የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ዘላቂ ሰላምና ልማት እንዲጠናከር እየተሠራ እንደሆነ፤ ቻይና ለቀጠናው ሀገራት መጠናከር ሙሉ ትብብር እንደምታደርግ ገልጻለች።
በአፍሪካ ቀንድ የቻይና ልዩ መልዕክተኛ ዡ ቢንግ በመድረኩ እንደገለጹት፤ ቻይና የአፍሪካ ቀንድ ሀገራትን በሰላም፣ በልማትና በአስተዳደር ዘርፍ ለመደገፍ ቁርጠኛ ናት። በቀጠናው ያሉት ሀገራት አንድነት እንዲጠናከር ከሀ ገራቱ ጋር በጋራ ለመሥራት ከፍተኛ ፍላጎት አላት።
የአፍሪካ ቀንድ በሁሉም መስክ ትልቅ አቅም ያለው ሥፍራ እንደሆነ የጠቀሱት ልዩ መልዕክተኛው፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ በሠላምና ደህንነት እንዲሁም በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ቀጣናው እየተፈነ መሆኑን ጠቁመዋል። የአካባቢውን ሕዝብ ሰላም ማስጠበቅና በዘላቂ ኢኮኖሚ ማበልጸግ እንደሚገባም ገልጸዋል። ለዚህ ደግሞ ቻይና ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ እንደሆነች አስታውቀዋል።
ቻይና የቀንዱ ሀገራት ወዳጅ እንደመሆኗ፤ በተለይም በጸጥታው ዘርፍ፣ በስደት፣ በድርቅና መሰል የቀጠናው ሀገራት ተግዳሮቶች የሆኑ ጉዳዮች ላይ መፍትሔ ሊሠጡ የሚችሉ ድጋፎችን እንደምታደርግ ነው ልዩ መልዕክተኛው የተናገሩት። ይህ ደግሞ የወደፊት የቻይና-አፍሪካ ማኅበረሰብን ለመጠናከር መነሳሳትን ይፈጥራል ብለዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፤የአፍሪካ ቀንድ በቁጥር በርካታ አምራች ዜጎች ያለው ቢሆንም፤ በሰው ሠራሽና ተፈጥሮአዊ አደጋዎች ሲታመስ መቆየቱን ገልጸዋል። ኮንፈረንሱ የቀጠናው ሀገራት በአንድነት ተቀምጠው ችግሮቻቸውን እንዲፈቱ ያስችላል በማለት፤ በተለይም የቻይና መንግሥት በልማትና ሰላም ጉዳይ ለቀንዱ ሀገራት እያደረገ ያለውን ትብብር አድንቀዋል።
ቀጠናው አቅሙን በመጠቀም፣ ሰላምና ጸጥታውን በማሻሻል፣ እንዲሁም የታሪክና የባህል እሴቱን በማጠናከር በጋራ መለወጥ እንደሚችልም አምባሳደር ሬድዋን አስታውቀዋል።
ቀጠናው እየተፈተነ ባለባቸው ጉዳዮች ላይ የቻይናን ድጋፍ በአዎንታዊ መልኩ እንደሚያዩና የተቀናጀው ተግባር ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል ተናግረዋል።
ቻይና የጋራ ጥቅምን መሠረት ያደረጉና ከአፍሪካ ጋር እያከናወነቻቸው ያሉ የትብብር ሥራዎችን አጠናክራ እንድታስቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።
ዛሬም ቀጥሎ በሚካሄደው ኮንፈረንስ ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ ቀንድ አገራት ተወካዮችና የቻይና ልዑካን እየተሳተፉ ይገኛሉ። የሀገራቱ ተወካዮች ቻይና በአፍሪካ ለምታደርገው ሁለንተናዊ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
ኮንፈረንሱ የአፍሪካ ጉዳይ በአፍሪካዊ መንገድ በአፍሪካውያን መፈታት እንዳለበት የሚደግፍ ሀሳብ የሚራመድበት ሲሆን፤ ለዚህ ደግሞ ቻይና ግንባር ቀደም ሚና ትወጣለች ተብሎ ይጠበቃል።
አዲሱ ገረመው