በአትሌቲክስ ስፖርት ታላቁ ውድድር የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ሊጀመር የሳምንታት እድሜ ብቻ ቀርተውታል፡፡ የአሜሪካዋ ኦሪጎን አዘጋጅ በሆነችበት በዚህ ውድድር በስፖርቱ ያላቸውን ብቃት ለማስመስከር እንዲሁም የአገራቸውን ስም በአሸናፊነት ለማስጠራት የስፖርቱ ከዋክብት በዝግጅት ላይ ይገኛሉ፡፡
በዚህ ውድድር ተጠባቂ ከሆኑት መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያም በውድድሩ ተሳታፊ የሚሆነውን ብሔራዊ ቡድኗን ያሳወቀች ሲሆን፤ አትሌቶቹ ከዛሬ ጀምሮ ተሰባስበው ወደ ሆቴል እንዲገቡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጥሪ አቅርቧል፡፡
በዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና በተለይ በረጅም ርቀት የመም እና የጎዳና ላይ ሩጫዎች ስኬታማ ከሆኑት መካከል የምትጠቀሰው ኢትዮጵያ በሁለቱም ጾታ፤ ከ800 እስከ 10ሺ ሜትር ተሳታፊ የሚሆኑ እጩ አትሌቶችን ከነተጠባባቂዎቿ አሳውቃለች፡፡ አትሌቶቹ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድር ሰዓቶች እንዲሁም በሄንግሎ የተካሄደውን(10ሺ ሜትር) የሰዓት መሟያ ውድድር መሰረት በማድረግም ተመርጠዋል፡፡ ቡድኑ እንደ አጠቃላይ ሲታይም በዓለም ቻምፒዮናው ማንጸባረቅ በሚችሉ ከዋክብቶች የተሞላ እንደሆነ ከስብስቡ ጥንካሬ መገመት ይቻላል፡፡
በወንዶች 800 ሜትር ሁለት አትሌቶች በቻምፒዮናው የሚካፈሉ ሲሆን፤ ኤርሚያስ ግርማ እና ቶሎሳ ቦደና ከመሐመድ አማን ቀጥሎ በርቀቱ ኢትዮጵያን ለመወከል አስፈላጊውን ሚኒማ ማሟላት ችለዋል፡፡ በ1ሺ500 ሜትርም በተመሳሳይ ሁለቱ አትሌቶች ሳሙኤል ተፈራ እና ሳሙኤል አባተ አገራቸውን ይወክላሉ፡፡ በዚህ ርቀት ወጣቱ አትሌት ሳሙኤል ተፈራ በዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና ለሁለት ጊዜያት ቻምፒዮን መሆን የቻለ አትሌት ነው፡፡ በርሚንግሃም እና ቤልግሬድ ላይ ብቃቱን ያስመሰከረው አትሌቱ 3:32.77 የሆነ ፈጣን ሰዓት አለው፡፡
የኢትዮጵያዊያን ብርቱ አቅም የሚታይበትና ድል እንደሚመዘገብባቸው ከሚጠበቁ ርቀቶች መካከል አንዱ የሆነው 5ሺ ሜትርም እንደተለመደው የዓለም ምርጥ አትሌቶችን አካቷል፡፡ በዶሃው የዓለም ቻምፒዮና በምርጥ ብቃት ቻምፒዮን የሆነውና ለዚህ ውድድር በቀጥታ ተሳታፊነቱን ያረጋገጠው ሙክታር እድሪስ ርቀቱን በፊታውራሪነት ይመራል፡፡ በተለያዩ የውድድር መድረኮች በመሳተፍ ልምድ ያካበቱት ወጣቶቹ አትሌቶች በሪሁ አረጋዊ፣ ዮሚፍ ቀጄልቻ እና ከሰሞኑ በተካሄደው የኦስሎ ዳይመንድ ሊግ አሸናፊ የሆነው ጥላሁን ኃይሌም በርቀቱ የተፎካካሪዎቻቸው ስጋት እንደሚሆኑ ይጠበቃል፡፡
ሌላኛው የኢትዮጵያዊያን ኩራት ምንጭ የሆነው 10ሺ ሜትርም፤ የቶኪዮ ኦሊምፒክ ቻምፒዮን እና ወጣት አትሌቶችን አጣምሯል፡፡ በርቀቱ ሰለሞን ባረጋ ቡድኑን ሲመራ፤ ወጣቶቹ አትሌቶች ታደሰ ወርቁ እና ሚልኬሳ መንገሻ በቻምፒዮናው አቅማቸው የሚፈተሽ አዳዲስ አትሌቶች ናቸው፡፡
በ3ሺ ሜትርም በተመሳሳይ የርቀቱ ምርጥ አትሌቶች ቡድኑን ይወክላሉ፡፡ በኳታሩ የዓለም ቻምፒዮና፣ በቶኪዮ ኦሊምፒክ እንዲሁም በቅርቡ በተካሄደው የቤልግሬዱ የቤት ውስጥ ቻምፒዮና የብር ሜዳሊያዎችን የሰበሰበው ለሜቻ ግርማ ቀዳሚ ተመራጭ ሲሆን፤ ኃይለማርያም አማረም በሁለተኛነት የታጨ አትሌት ሆኗል፡፡ ኦሊምፒክና የዓለም ቻምፒዮናን ጨምሮ በበርካታ ውድድሮች ተሳትፎ ልምድ ያዳበረው ጌትነት ዋለም ተጠባቂ አትሌት ነው፡፡
በሴቶች 800 ሜትር በተለያዩ ውድድሮች ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ሃብታም ዓለሙ፣ ድርቤ ወልተጂ እና ፍሬወይኒ ሃይሉ ይሳተፋሉ፡፡ በ1ሺ500 ሜትርም ሂሩት መሸሻ፣ አክሱማዊት እምባዬ እና አያል ዳኛቸው ተይዘዋል፡፡ በ5ሺ ሜትር ደግሞ እጅጋየሁ ታዬ፣ ዳዊት ስዩም እና ጉዳፍ ጸጋዬ የተለመደውን ሜዳሊያ ለአገራቸው ለማስመዝገብ የሚፋለሙ እጩ አትሌቶች ሆነዋል፡፡ የቶኪዮ ኦሊምፒክ የነሃስ ሜዳሊያ ባለቤቷ ጉዳፍ በዚህ ቻምፒዮና የወርቅ ሜዳሊያ ታጠልቃለች በሚል ከሚጠበቁት መካከል ናት፡፡
ድልን የለመደው የ10ሺ ሜትር ርቀትም የኦሊምፒክ እና የዓለም ቻምፒዮና ባለድል እንዲሁም ወጣት አትሌቶችን አሰባስቧል፡፡ የዶሃ ዓለም ቻምፒዮና ብር እንዲሁም በቶኪዮ ኦሊምፒክ የብር ሜዳሊያ ባለቤቷ ለተሰንበት ግደይ ቡድኑን ትመራለች። ጠንካራዋ አትሌት የዓለም ቻምፒዮና ለመሆን የሚያስችላት አቋም ላይ እንደምትገኝም በውድድሮች ላይ የምታሳየው ብቃት አመላካች ነው፡፡ ቦሰና ሙላቴ እና ዳግማዊት ገብረእግዚአብሄርም በርቀቱ አገራቸውን የሚወክሉ ሲሆን፤ አትሌት አልማዝ አያና በተጠባባቂነት ተይዛለች፡፡ ኦሊምፒክን ጨምሮ እአአ ከ2013-2017 ድረስ በተካሄዱ የዓለም ቻምፒዮና እና ሌሎች ውድድሮች ምርጥነቷን ያስመሰከረችው አትሌቷ፤ ከወሊድና ጉዳት መልስ አገሯን ልታገለግል ተዘጋጅታለች፡፡
በ3ሺ ሜትር ደግሞ መቅደስ አበበ፣ ወርቅውሃ ጌታቸው፣ ዘርፌ ወንድማገኝ ሲያዙ፤ ሲምቦ አለማየሁ ተጠባባቂ ሆናለች፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሰኔ 13 /2014