የሰው ልጅ ከሌላው ፍጡር የሚለየው እና እንደ መለያ ሆኖ የሚታወቅበት ባህሪ እርስ በርሱ በመረዳዳትና በመተጋገዝ የሚኖርና ፤ራሱን የቻለ ማሕበራዊ መስተጋብር ያለው በመሆኑ ነው። ይህ የመተጋገዝና የመረዳዳት እሴት በሃገራችን ለረጅም ጊዜ የቆየና አሁንም ድረስ ያለ የሚከበር ባህላችን ነው።
ይህ ማህራዊ ሕይወት ሳይበላሽ እና ሃገርም እንደሃገር እንድትቀጥል ያለመታከት የሚሰራና የሕይወት መስዋዕትነት ጭምር በመክፈል ሃገሩን የሚጠብቅ ኃይል ደግሞ የሃገር መከላከያ ሰራዊት ነው። እኔም ስለኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና ቤተሰቦቹ እንዲሁም የአብራኩ ክፋይ ልጆቹ ትንሽ ላካፍላችሁ ወደድኩ።
መቀሌ ውስጥ ኲሐ ክፍለ ከተማ ተብሎ በሚጠራው ጥንታዊ የወታደሮች ካምፕ ፤ማሰልጠኛና መኖሪያ ስፍራቸው ሲሆን ከፊትለፊቱ የኲሐ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ይገኛል።ስለ ሀገርና ህዝብ ወዳዱ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ለመናገር በዚህ ትምህርት ቤት መማርና እዛ አካባቢ መኖር ፤ እንዲሁም ሰራዊቱ ሲወጣ ሲገባ ያየና ከማንም በላይ በተግባር የሚያውቅ ሰው ያውቀዋል።
ይህ ሰራዊት በአካባቢው ከተወለዱ ተጋሩ ጋር የተጋባና ልጆች የወለደ ከመሆኑም በላይ ፤ሌላ መኖሪያ ቀዬ የሌለውና እንደ ትውልድ ቦታው በመቁጠር የተሳካለት ቤት ሰርቶ የሌለው በአቅሙ ተከራይቶ የተረጋጋ ሕይወት በመመስረትና ከአካባቢው ባህልና ሁኔታ ጋር ተላምዶ የሚኖር ስርአት ያለው ሰራዊት ነው።
ይህ የሚያኮራ ታሪክ የሰራና ከመላው የኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰብ የተውጣጣ ሰራዊት ፤ ስልጣን ወዳዶች በፈጠሩት ሸፍጥና ሴራ ምክንያት ብዙዎችን የሕይወት መስዋዕትነት ያስከፈለና ከዚህም አልፎ በልጆቻቸውና ሚስቶቻቸው ላይ ለመናገር ኣዳጋች የሆነ ግፍና መከራ የፈጸመ ቢሆንም ፤የሚስቶቻቸው ጥንካሬና ወኔ ግን ወደፊት በተስፋ እንዲራመዱ የሚያደርግ ነው።
ከ50 በላይ የሚሆኑ የወታደር ሚስቶች ከህፃናት ልጆቻቸው ጋር ሁነው ከኲሐ አዲስ አበባ ድረስ አስቸጋሪ ጉዞ አልፈው የገቡ ሲሆን፤በየመንገዱ ያጋጠማቸው መከራ ድካሙና ርሃቡ ቀላል አልነበረም። እነዚህ ያላሰቡት መከራና ስቃይ የተቀበሉ ሴቶች አብዛኞቹ የትግራይ ተወላጆች (ተጋሩ) ናቸው።
ገሚሶቹ ተወልደው ያደጉት እዛው አካባቢ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ በተመሳሳይ ትግራይ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች ተወልደው ከባሎቻቸው ጋር ለመኖር እዛው የመጡ ናቸው፤ ከነዚህ ሴቶች መካከል የሶስት ልጆች እናት የሆነችው ወይዘሮ ፅጌ ወልደማሪያም አንዷ ናት። ባለቤትዋ የሻለቃ ጉደታ ደበላ ይባላል። ይህች እናት ከሰሜን እዝ ጥቃት በኋላ ባለቤትዋን በሞት ያጣችው ሲሆን ፤ይህን ተከትሎ እጅግ አሳዛኝ ሁኔታ ስላጋጠማት ሕይወቷንና የልጆቿን ሕይወት ለማትረፍ ብዙ መከራ በማለፍ አሁን እዚህ አዲስ አበባ ሸጎሌ የጋራ መኖሪያ ቤት ውስጥ ከመሰሎቿ ጋር ትገኛለች።
የሻለቃ ጉደታ ደበላ ባለቤት እጅግ ስሜትዋን የጎዳውን ነገር ስትናገር፤ ‹‹እኔ ተወልጄ ባደኩበት ስፍራ ፤ ከሀገሬ ውጪ ተብዬ ከልጆቼ ጋራ ተገፍቻለሁ፤ ነገር ግን ባለቤቴ በሕይወት እያለ ለትግራይ ህዝብና ለኢትዮጵያ ህዝብ ሲያገለግል የነበረ ጀግና ሻለቃ ነው፤ በድንገት በተፈጠረ ግጭት እኛ በማናውቀውና ተጠያቂ በማንሆንበት ነገር እንደ ወንጀለኞች ተቆጥረን እስርና ሞት ተፈርዶብናል፤ ብዙዎች በሚያሰቅቅ ሁኔታ ተገለው የት እንደገቡ አይታወቅም፤ ይህ የተደረገው ግን የመከላከያ ሰራዊት ሚስቶች ስለሆንን ብቻ በመሆኑ እጅግ ያሳዝነኛል ›› ትላለች።
ወይዘሮ ፅጌ እየቆጫት ስትናገር፤ባለቤቴን ጨምሮ አጠቃላይ የሰሜን እዝ አባላት ለትግራይ ህዝብ ሁለንተናዊ እገዛ በማድረግና ደጀን በመሆን ሲጠብቁት የነበሩና ፤እስከ መጨረሻዋ እለት ድረስ አረጋውያንን በማገዝና የገበሬውን ሰብል በማጨድ ፤እንዲሁም አምበጣ ሲመጣ በህብረት እያባረረ ቀን ከሌሊት ለህዝብ የቆመ ቅን ሰራዊት ልጆቹ ለግፍና መከራ እንዲዳረጉ ማድረግ እጅግ ያንገበግበኛል።
ሌላኛዋ ወይዘሮ እስከዳር ታደሰ ትባላለች ፤ተወልዳ ያደገችው እዛው ኲሐ ከተማ ሲሆን ፤በሰሜን እዝ ሆስፒታል እየሰራች ከባለቤትዋ ሻለቃ ባሻ ከድር ለ15 ዓመታት በትዳር የቆዩ ሲሆን ሁለት ልጆችም አፍርተዋል፤ ይህች ወጣት ሴት በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ለእስርና ለተለያዩ እንግልት እንደተዳረገች ትናገራለች።
‹‹የመከላከያ ሰራዊት እንደወጣ ቤታችንንና ንብረታችንን ጥለን በፍጥነት እንድንወጣ ታዘዝን፤ ልጆቻችንን ይዘን የት እንውደቅ ብለን ለመጠየቅ በወካዮቻችን አድርገን ዶክተር ደብረፅዮን ቢሮ ድረስ ሄደናል፤ ምንም ምላሽ አልተሰጠንም፤ ይባስ ብሎ የጠላቶቻችን ሚስቶች ስለሆናችሁ ከልጆቻችሁ ጋር እናጠፋችኋለን እያሉ ቀን ከሌሊት በማናውቀው ምክንያት እያስፈራሩ መኖሪያ አሳጡን ፤ ልጆቻችን በምግብ እጦትና በጭንቀት ታመሙብን ፤ይህ እየሆነ ያለው በገዛ ተወልጄ ያደኩበት ሀገሬ ነው›› እያለች ስትናገር እምባዋ ሃሳብዋን ሊያስጨርሳት አልቻለም።
ወጣት እስከዳር ቤተሰቦቿ እዛው ከተማ ውስጥ ስለሆኑ ሁለት ጎረቤቶቿ ከሷ ጋር እንዲቆዩ በማድረግ መኖሪያ ቤታቸውን ልቀቁ በተባሉት መሰረት ለቀው ሄዱ፤ ከዛ ቀጥሎ ቀስ በቀስ መውጫ መንገድ በማፈላለግ ክልሉን ለቀው በአማራ ክልል አድርገው አዲስ አበባ ሊገቡ ችለዋል።
ወይዘሮ ፈትለወርቅ አለሙና ወይዘሮ አልማዝ እሸቱ እያንዳንዳቸው የሁለት ልጆች እናቶች ናቸው።እነዚህ ተጋሩ እዛው ይኖሩ የነበሩ የወታደር ሚስቶች ሲሆኑ ፤በወቅቱ ብዙ ግፎች አይተናል ይላሉ፤ ግፈኞች እንደ ምክንያት የሚጠቀሙት ‹‹ከሌላ ብሄር ጋር ለምን ተጋባችሁ፣ ታሳፍራላችሁ፣ እናንተ የኛ ዘር አይደላችሁም›› እያሉ ብዙ ስድብ አውርደውብናል።
በተለይ ወይዘሮ ፈትለወርቅ የእስር ወረቀት ተዘጋጅቶላት ሊወስዷት ሲሉ የስድስት ወር ነብሰጡር ስለነበረች ጎረቤቶቿ እግራቸው ላይ ወድቀው በመለመን ሳትታሰር እንደቀረች ትናገራለች። እነዚህ ያለ ምንም በደል ከሰላማዊ ኑሯቸውና ከቀዬአቸው በግፍ ተሰደው የወጡ ተጋሩ ያሳለፉት መከራ ቀላል አይደለም።
እነዚህ እናቶች እንደ ሌሎች ኢትዮጵያውያን መከራ ተቀብለዋል፤ የሕወሓት ግፍ ደግሞ ማብቂያ የሌለው እና ጽንፍ የወጣ ጥላቻን የሚያንጸባርቅ ነው። ዛሬም ቢሆን ይህ ቡድን ዜጎችን ለሌላ ስቃይ ለመዳረግ እንቅልፍ አልባ ሌሊቶችን እያሳለፈ ይገኛል። አሁን የተሰጠውን የሰላም እድል ተጠቅሞ ራሱን ማዳን ካልቻለ ግን የሚደርስበት ቅጣት የከፋ መሆኑ አይቀሬ ነው።
ሄርሞን ፍቃዱ
አዲስ ዘመን ሰኔ 13 /2014