በምቾት፣ በድሎት ያደገ ሁሉ በከፍታው ላይዘልቅ ላይቀጥል ይችላል። ዝቅ ፣ ጎንበሰ ተብሎም ይኖሩበት አጋጣሚ ይከሰታል። በልጅነቱ ተቀማጥሎና ሞልቶለት ያደገ ሁሉ መጨረሻው ያምራል ማለት አይደለም። በትምህርቱም ሆነ በሀብቱ የት ይደርሳል የተባለ ሕይወቱ እንደታሰበው አልጋ በአልጋ የማይሆንበት አጋጣሚ የበዛ ነው።
በአብዛኛው እንዲህ አይነቱ በሕይወት ተስፋ አይቆርጥም። ለውጥ ባያገኝበትም እዚህም፣ እዛም እየተንቦራጨቀ ዕድሉን መሞክሩ የግድ ነው። ያም ሆኖ እንዳሰበው ካለበት የከፍታ ማማ መውረድ እንጂ በቀላሉ መውጣት አይሳካለት ይሆናል። ሕይወቱ እስካለች ግን ዛሬን ለማደርና ነገን ለመኖር የሚያደርገውን ጥረትና የኑሮ ፍልሚያ አይቋረጥም።
ዛሬ የሕይወት ተሞክሮዋን የምናካፍላችሁ ማዕከላዊት እሳቱም ከነዚህ ሰዎች አንዷ ናት። ማዕከላዊት ‹‹ግሩም ናት ድንቅ ናት ለምለሟ አገሬ ፣ የአክስቶቿ ብዛት፣ ድማማይ›› በሚሉና በብዙ ተደማጭና ተወዳጅ ዘፈኖቹ የሚታወሰው የድምፃዊ እሳቱ ተሰማ ልጅ ናት። ተወልዳ ያደገችው አዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ ሰድስት ኪሎ መነን እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ነው።
ማዕከላዊት አባቷ ያሳደጋት ያለ እናት ነው። እናቷ በወቅቱ መልከ መልካምና በአቋሟ ማራኪ ነበረች። ከአባቷ ባለመግባባታችው በወለደቻት በ15 ቀኗ ጥላት ሄደች። ይህኔ አባት ሞግዚት ቀጥሮ ይንከባከባት ገባ። ጥቂት ቆየና እቴቴ የምትላት እንጀራ እናቷ አባቷን አግብታ ተቀበለቻት። ትምህርቷ ላይ ብቻ ትኩረት ታድርግ በሚል በስስት አቀማጥላ አሳደገቻት።
ይህች ሴት ልብሷን ቀርቶ መሀረብ አሳጥባት አታውቅም። እሳቱም ቢሆን ቀበጥና ባለጌ ልጅ አይወድም። ልጆቹን በሥርዓት አሳድጎ የሚያሻቸውን የሚያደርግ ደግ አባት ነው። እሷና ከእንጀራ እናቷ የተወለዱት እህትና ወንድሞቿ የፈለጉትን የሚጠይቁት እቴቴን ነበር።
ማዕከላዊት ለእንጀራ እናቷ የተለየ ፍቅር አላት። እንደሷ አባባል ወላጅ እናቷና እንጀራ እናቷ አብረው ቢወድቁ ቀድማ የምታነሳው እንጀራ እናቷን ነው። እሷ በስመ እንጀራ እናት መልካም እናቶችን በሙሉ ክፉ እያሉ የሚፈርጁትን አጥብቃ ትቃወማለች። ወይዘሮ ወርቅነሽ ደምሴን አሁን ድረስ ‹‹እቴቴ›› እያለች በፍቅርና በቁልምጫ ትጠራታለች። እቴቴን እንጀራ እናትሽ ሲሏት አትወድም። ፊቷ በቁጣ ይለዋወጣል።
ማዕከላዊት እናቷ በ15 ቀኗ ጥላት ብትሄድም፤ የእንጀራ እናቷ እጅ መልካም ሆኖ ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል በስኬት አጠናቃለች። እንጀራ እናቷ ከራሷ ልጆች ይበልጥ ለማዕከላዊት ታደላ ነበር። ከእነሱ አስቀድማም ትምህርቷን በግል ትምህርት ቤት እንድትማር አድርጋለች። እንደታሰበው ግን የማትሪክ ውጤት መልካም አልሆነም።
የእሷም ሆነ የቤተሰቦቿ ፍላጎት ፤ በትምህርት ልቆ መሄድ ቢሆንም ዩኒቨርሲቲ መግባት የሚያስችል ነጥብ አልመጣላትም። በትምህርት ገፍቶ ለመሄድ በነበራት ጽኑ ፍላጎት የ12ኛ ክፍል መልቀቂያን ዳግም መውሰድ ፈልጋ ነበር። ሆኖም የአባቷና ፤ የወላጅ እናቷ የብቻ ኑሮ ሃሳቧን አላሳካውም። የግልዋ መፍጨርጨር ብቻውንም ውጤት አላመጣም። በወቅቱ እናትና አባቷ የየራሳቸውን ሕይወት ይመሩ ነበር። እሷ ግን ከማናቸውም ጥገኛ መሆንን አትሻም። ራሷን ለማውጣት ስትፍጨረጨር ኖራለች።
የ12ኛ ክፍል ትምህቷን ካጠናቀቀች በኋላ ድል ባለ ሰርግ ተዳረች። ጎጆ ወጥታ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች መሸጫ ከነበረው ባለቤቷ ጋር ለዓመታት ኖረች። ከትዳሯም አንዲት ሴት ልጅን አፈራች። ልጅቱ አሁን ከአባቷ ቤተሰቦች ጋር እየኖረች ነው። ዜግነቱ ሱማሌያዊ የሆነ አንድ የ10 ዓመት ወንድ ልጅም ወልዳለች። በአባቱ እጅ በአገረ እንግሊዝ ይኖራል።
ማዕከላዊት ሁሌም ከፍታን የምትፈልግ ሴት ነበረች። ማደግ መለወጥን አብዝታ ትሻለች። ወደከፍታው ማማ ለመውጣት የአባቷ ታዋቂነት ሳይገድባት ዝቅ ብላ ብዙ ሥራዎችን ሰርታለች። ከሰል እስከ መሸጥም ደርሳለች። ለትዳሯ መፍረስ ምክንያት ከሆነው አንዱ በዚህ ጥረቷ መካከል የተፈጠረው አጋጣሚ ነበር። ከቀናት በአንዱ ዕለት ባለቤቷ ከእሷ በፊት ከሚያውቃት ሴት ጋር የፍቅር ግንኙነት እንዳለው አወቀች። ከዚያ በኋላ የእሷ ወደ ከፍታ ለመውጣት በትዳሯ ዋጋ መክፈል ትርጉም እንደሌለው ሲገባት። ከባሏ በፍቺ ተለያየች።
ከትዳሯ ፍቺ በኋላ ሕይወት እንደቀድሞ ቀጠለ። ማዕከላዊት መነን አካባቢ ወደሚገኘው የወላጆቿ ቤት ስትመለስ ፊት አልነሷትም። በተለይ እንጀራ እናቷ የበሉትን በልታ አብራቸው እንድትኖር ተማጽናት ነበር። ‹‹በጄ›› አላለችም። ወደ ካዛንቺስ አቅንታ መኖርን መረጠች። አንዳንዴ ማዕከላዊት የአቅሟን ታንጎራጉራለች። የአባቷን ሙያ ግን በወጉ መውረስ አልቻለችም።
ጥበብ እንዳሰበችው ባልጠራቻት ጊዜ የድምፃዊ አባቷን የእሳቱ ተሰማን ጓደኞችና የሚያውቁትን ሁሉ፣ በተለይም ዝነኞቹን ድምፃዊያን እየዞረች ተማልዳለች። ጽዳት እንኳን እንዲያስቀጥሯት ስትል በሀገር ፍቅር ፣ብሄራዊና ሌሎች ቲያትር ቤቶች ደጃፍ ተመላልሳለች። አልተሳካላትም።
ስለ አባቷ ስታስታውስ ከልብ ታዝናለች። እሳቱ ታዋቂ ዘፋኝ ነበር። በሙያው ብዙ አበርክቷል። ለአገሩም በተፈለገ ጊዜ ዘምቷል። ሆኖም ስም እንጂ ሀብት አላወረሳቸውም። የራሱ ቤት እንኳን ስለሌለው አሁን ድረስ ባለቤቱና ልጆቹ በኪራይ ቤት ይኖራሉ። እግሩን ሪህ ሲያመው ቆይቷል። እስከ ዕለተሞቱ ግን በሥራ ላይ ነበር።
እሳቱ በታመመ ጊዜ ድምፃዊ መሐሙድ አህመድ ድጋፍ ቢያደርግለትም ሌሎቹ የሙያ አጋሮቹ ረስተውታል። ለራሳቸው በኪነ ጥበብ ምሽትና በሌሎች ዝግጅቶች ይደጋገፉና ይታወሳሉ ‹‹ሌላው ቀርቶ ሚዲያ ላይ ዘፈኖቹ እንደሌሎቹ ተደጋጋግመው ሲቀርቡ አይስተዋልም። ቀደምቶቹን የሙያ አጋሮቹ በየምክንያቱ እየተነሱ ሲያስታውሱና ሲዘክሩ እሳቱን የዚህች አገር የእንጀራ ልጅ የሆነ ይመስል የተዘነጋበት እውነት ሁሌም ያበሳጫታል።
እሷ እንደምትለው በሕይወት ያለፉ አርቲስቶች ልጆች የሚደግፉበት፣ የሚታገዙበት አጋጣሚ የበዛ ነው። ለእሳቱ ቤተሰቦቹ ግን የማንም እጅ አልተፈታም። ሁሉም ነገር ቲፎዞ ይፈልጋልና ማዕከላዊትም ድጋፍ የሚያደርግላት አላገኘችም። ይህኔ ተስፋ ቆርጣ ቆየች ‹‹አማራጭ ባጣች ጊዜም ከጎዳና ወጣች። በጎዳና ሕይወት ብዙ ስቃይና መከራዎች ተፈራርቀውባታል። የምትበላውና የምትጠጣው እንዲሁም የምታድርበት አልነበራትም። ሆኖም በአለባበስም ሆነ በንጽሕና ራሷን በመጠበቋ ጎዳና የወጣች አትመስልም።
አዳዲሶቹን ዘመናዊ ሆቴሎች ጨምሮ በቀደምቶቹ በነጊዮን፣ ሂልተንና ሆቴሎች ጎራ ስትል ይደረግላት የነበረው የክብር አቀባበልም ፕሮቶኮሏን በመጠበቋ ነበር። እሷ ዘመናዊነትን በመውደዷ ዛሬም ድረስ ከፍ ያለ ነገርን ትወዳለች። አራት መቶ ብር በእጇ ካለ አንድ ማክያቶ የሚታዘዝበት ባለ አራት ሆቴል ገብታ ዘና ፈታ ማለት ምርጫዋ ነው።
በጎዳና ላይ በቆየችበት ጊዜ አልጋ ይዛ የምታድርበት ብር እስክታገኝ መዞር ግድ ይላት ነበር። በዚሁ ምክንያትም የሴት አዳሪነትን ሕይወት ገብታ ሞክራዋለች። የዛሬን አያድርገውና ከአስፋልት የምትቆመው ሞዴል መስላ፣ በእጅጉ ተውባ ነበር።የ ዛኔ ፈላጊዎቿ የበረከቱ ፣ ናቸው። ‹‹ገንዘብ በ20 ዓመት ልብ በ40 ዓመት›› እንዲሉ ሆኖ እንጂ ከቀረቧት አብዛኞቹ የጠየቀችውንና ከጠየቀችውም በላይ ገንዘብ አስታቅፈዋታል። የዛኔ ታዋቂ የሚባሉት ሳይቀር በደንበኝነት ከእሷ አይለዩም። ማዕከላዊት ከስሟ ጀምሮ ማንነቷን ደብቃ አታውቅም። አትደብቅም። ማነሽ ምንድነሽ ሲሏት የእሳቱ ተሰማ ልጅ መሆኗን ሳትፈራና ሳታፍር ትናገራለች።
ስራዋን ከሚያውቁት በርካቶቹ በሚሰሙት እውነት ይደነግጣሉ። የወታደር ልጅ ወታደር መሆኑ የሚገባቸው ደግሞ በቆመችበት ስራ ይሸማቀቃሉ። አንዳንዶች በሶማሌ ወረራ ጊዜ ዳር ድንበሩን ለማስከበር ካራማራ ዘምቶ ይሙት ይቁም የማይታወቀውን ወንድሟን ያስታውሳሉ። ደፈር ብለውም ይጠይቋታል።
ይፋጃል እሳቱ የሚባል ወንድም አለሽ? አዎ አለኝ ስትላቸው ደንግጠው ከእስዋ የተነጋገሩበትን ብር ከፍለው የሚሄዱበት ጊዜ ጥቂት አልነበረም። ማዕከላዊት አስቂኝም አሳዛኝም ገጠመኖች አሏት። በሴተኛ አዳሪነት ሕይወቷ እንደዋዛ የማይነገሩ በርካታ ፈተናዎችን አልፋለች። ከመኪና ተገፍትሮ ከመጣል ጀምሮ ጥርሷን እስከመስበር አደጋ ገጥሟታል። የተቀበለችውን ብር በጉልበት አስፈራርቶ ከሚነጥቅና ብሎም ከሚደበደብ ጨካኝ ጋር ማሳለፍም ልምዷ ነበር። የሴተኛ አዳሪነት ሥራ በይፋ ስለማይፈቀድ የሕግ ከለላ አይደረግላትም። አንዳንዴ ደግሞ ለሴትነቷ ክብር የሚሰጡ፣ አብልተው፣ አጠጥተው፣ ተንከባክበው፣ በጥሩ ገንዘብ አንበሽብሸው የሚሸኙ ገጥመዋታል።
ደጋግማ እንደምትለው በሴት አዳሪነት ኑሮ ማንም ሴት ወዳ አትገባም። አማራጭ በማጣት እንጂ። አንዳንዶች ደግሞ እንጀራቸው ቢሻግት ይጥሉታል እንጂ ለእንዲህ አይነቷ ሴት እርቧት ይሆናል ብሎ የሚሰጡ አይደሉም። ለሴተኛ አዳሪዎች ሕይወት የሚጨነቅና ያገባኛል ሲል የሚቆም አካልም የለም።
ማዕከላዊት በሴተኛ አዳሪነት ሕይወት ያጋጠሟትን ወጣት ሴቶች ሁሌም ከመምከር አትመለስም። በዚሁ ስራ ተሰማርታ ከዓመታት በፊት በኤችአይቪ የሞተችን የእናቷን ልጅ ዋቢ አድርጋ ታስተምራለች። በዚህ መንገድ ሌሎች እንዳይቀጥሉም የራሷን ሕይወት እየጠቀሰች የስራውን ክፋት ትጠቁማለች
በአረብ አገራት ለዓመታት ተቀምጠው የተመለሱና አስፓልት ከመውጣት ያለፈ አማራጭ የሌላቸውን ሴቶች ታውቃለች። በየቡና ቤቱ እየዞረች ስታስተምር ዊዝ ድሮል ሞልታ ቡና ቤት የገባች የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማንጅመንት ተማሪም አጋጥማታለች።
አምስት ልጆቿን ምሸት ከመንገድ ቆማ በምታገኘው ገቢ የምታሳድግ እናትንም አግኝታለች። በቆይታ እንደታዘበችው ባብዛኛው ወደ ስራው የሚገቡት ሴቶች እንደ እሷ በሮች የተዘጋጉባቸውና የተቸገሩት ናቸው። ምንም አይነት መመዘኛ የማይጠይቅ ክፍት የሥራ ቦታ መሆኑኑን የተረዱ ሌሎችም እንደዋዛ የሚገቡበት ሕይወት መተዳዳሪያቸው ሆኖ ይቀራል። እሷም በዚህ ሕይወት ለዘጠኝ ዓመታት መዝለቋ ከባድ ዋጋ አስከፍሏታል።
አንዳንዴ ማዕከላዊት ብሩን ስታገኝ አልጋ ይዛ ለብቻዋ ታድር ነበር። በአልጋ በኩል ካዛንቺስ በግ ተራ አካባቢ በተለምዶ ትንሿ ቤት ተብላ የምትጠራው ሆቴል ባለቤት አቶ ገብሩን ከልብ ታመሰግናለች። እሳቸው ለረጅም ጊዜ የረዷት ባለውለታዋ ስለመሆናቸው ፈጽሞ አትረሳም። ሰውየው ሁሌም እንደልጃቸው ያቀርቧታል። ያለችበት ሕይወት እንደሚለወጥና ከሴተኛ አዳሪነት ሕይወት መውጣት እንደሚኖርባትም ይመክሯት ነበር። ገብሩ ስታገኝ ትከፍያለሽ እያሉም ጎዳና እንዳታድር ለብዙ ጊዜ ያለክፍያ አልጋ ሰጥተዋታል።
በቅርብ ጊዜ አንዲት ክፍል የቀበሌ ቤት አግኝታለች። ቤቷ ከአንድ አልጋና ከአንድ የከሰል ማንደጃ በላይ አትይዝም። በጊቢው መፀዳጃና ውሃም የለም። በግድግዳው የሰፈሩ ሰው የየራሱን ዘመናዊ ቆጣሪ ሲያስገባ የረሳው የዱሮ መብራት ቆጣሪ አለው። ‹‹መድሃኒዓለም ክብሩ ይስፋና አሁን ላይ ከፍቼ የምገባባትና ቆልፌ የምወጣው ቤት አለኝ›› ስትል ፈጣሪዋን ታመሰግናለች።
የማዕከላዊት ቤት ጠባብና ምቹ ባትሆንም ለኑሮዋ መለወጥ ሰበብና ምክንያት ሆናታለች። እንደዋዛ ከገባችበት ሴተኛ አዳሪነት ያላቀቀቻት በመሆኑም ትኮራበታለች። ቀደም ሲል በወረዳ 8 አካባቢ ሁለት በአራት የሆነች የሀገር ባህል ልብስ መሸጫ ተሰጥቷት ስትሰራ ቆታለች። በቅርብ ጊዜ ግን አምስት ዓመት ሞልቶሻልና ልቀቂ በመባሏ ሃሳብ ይዟታል። ቀጣይ ሕይወቷ ምን እንደሚሆን ባታውቅም በአባቷና በእንጀራ እናቷ ስም የሚሰየም እንደ አገር ተግባሩን ወደ ልማት የሚለውጥ ራዕይ ሰንቃ መንቀሳቀስ ከጀመረች ዓመታት አስቆጥራለች።
ያለምንም ድጋፍ በራሷ ወጪና ተነሳሽነት በየቡና ቤቱና በየጎዳናው እየዞረች ግንዛቤ ታስጨብጣለች። ሃሳቧን የሚደግፍላት ካገኘችም በርካቶችን አስተባብራ የትኛዋም ሴት በዚህ ሥራ እንዳትሰማራ የሚያስችል የልማት ተቋም መመስረት ነው።
የማከላዊት ዕቅድና ሃሳብ የሰፋ ነው። በሴተኛአዳሪነት ሕይወት ያሉትንና ልጆቻቸውን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችለውን ፕሮፖዛል በወረቀት እያሰፈረችው ትገኛለች። የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አበቤ፣ እንደ አገርም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ በእሳቱ ተሰማ ስም የምትቀርጸውን ፕሮጀክት ደግፈው ህልሟን እውን እንዲያደርጉም አበክራ ትማፀናለች።
ለመኖር፣ ሕይወትን ለማሸነፍ በርካታ ውጣውረድን የተሻገረችው የእውቁ ከያኒ እሳቱ ተሰማ ልጅ፤ ነገን በብሩህ መንፈስ ታስበዋለች። ዛሬ ላይ ቆማ በአባቷ ስም በጎ ታሪክ ለማስፈርም ከትናንትናው ሕይወቷ የሚበጀውን ወስዳ ሴተኛ አዳሪነትን ‹‹ሕይወቴ›› ላሉ ወገኖች መንገዶችን መቀየስ ጀምራለች። ማዕከላዊት ሕይወትን በአማራጮች መኖር እንደሚቻል ለማሳየት ሩጫውን የጀመረችው በታላቅ ጽናትና በተለየ ጥረት ሆኗል። እሷ የእሳት ልጅ ዓመድ እንዳትባል የከያኔ አባቷን ስም አክብራ ማንነቷን ለማስከበር እንቅልፍ ይሉትን አታውቅም። እያሰበች፣ ታቅዳለች፣ እያቀደች ትሞክራለች፤ ትናንትና ሕይወትን እንዲያ ኖራው ብታልፍም፤ ነገን ደግሞ ‹‹እንዲህ ይኖራል›› ለማለት ሃሳቧ አይነጥፍም፣ ህልሟ አይከስምም፣ ሩጫዋ አይገታም።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ.ም