ስራ ስትገባና ከስራ ስትወጣ አይኖቿ አንድ ሰው ላይ ማረፋቸው ግድ ነበር። የመስሪያ ቤታቸውን ሽንጠ ረጅም አጥር ተደግፎ የሚኖር አንድ ሰውን። ይህ ሰው በህይወቷ አብዝታ ያየችው ሰው ነው። ነፍሷ ብትጠየቅ እንደዚህ ሰው ፊት የምታስታውሰው ምንም አይኖራትም።
ሳቂታና አሳዛኝ ፊቱ እዛ የግንብ አጥር ላይ ተስሎ እስኪበቃት አይተዋለች። ግን ተጠግታው አታውቅም። አንድ ቀን ከዚህ ሰው ጋር ምሳ እበላለሁ ብላ አሰበች.. እንዳሰበችውም ወዳለበት ሄዳ አብረኸኝ ምሳ እንድትበላ እፈልጋለው አለችው።
በደንብ አስተዋላት.. በርቀት የሚያውቀው ፊቷ አጠገቡ ቆሞ ሲያየው ጸሀይ ከህዋ አካላት ላይ ተገንጥላ ፊቱ የተዘረጋች መሰለው። ፊቷ ምድር ሆኖ አይኖቿ እንደ ከዋክብት ለምድር ሁሉ ብርሃን እየረጩ መሰለው። በሰማይ ርቃን ላይ የሚያያቸው እነዛ የብርሃን ዛጎሎች በእሷ ፊት ላይ ተስለው ብርሃን ሲወልዱ አስተዋለ። ብርሃን ተሸክማ የምትዞር ብርሃናማ እንስት መሰለችው። የእሷ መምጣት በሕይወቱ ለአንድ ጊዜ ብቻ የሚስተናገድ መሰለው። በዝምታ ባረፈበት ከአንዲት ውብ ሴት ነፍስ ውስጥ የሚፈልቅ የብርሃን ጎርፍ ምድረ በዳ ሕይወቱን አጥለቀለቀው። ብርሃኗን መቋቋም ሲያቅተው ባትመጣብኝ ሲል አሰበ…
‹ምነው ዝም አልክ? ፊቱ ላይ እንደቆመች ጠየቀችው።
‹እንደራበኝ እንዴት አወቀች እያልኩ እያሰብኩ ነው። ለዘመናት በስሬ ስታገድም አንዴም እንብላ ያላለችኝ ሴት ዛሬ መራቤ እንዴት ገባት ስል ራሴን እየጠየኩ ነው› ሲል ፈገግ አለላት።
ፈገግታው ነፍሷ ውስጥ ነበር ያረፈው። ፊት እንደዛ ጸዳል በለበሰ መልኩ ሲፈግ አይታ አታውቅም። ጠይም ጺማም ፊቱ ፈገግታ ሲጎበኘው ጽልመት ላይ ያረፈ የመብረቅ ብልጭታ ይመስል ነበር። ጥያቄውን በፈገግታው ዘነጋችው። እሱም መልሶ ሳይጠይቃት እሷም መልሳ ሳትቆዝም ግብዣዋን ተቀብሎ ፊቷ ቆመ። ጎን ለጎን እየተራመዱ ወደ አንድ ካፌ አቀኑ። እሷን ከእሱ ጋር ያዩ መንገደኞች ምድር ላይ ተአምር የሆነ እስኪመስል ድረስ አዩዋቸው።
‹ዛሬ ምድር አዲስ ነገር አብቅላለች..!
‹እንዴት?
‹አታይውም እኔን አንቺ ጎን ያየኝ መንገደኛ እንዴት እንደሚሆን?
ቀድማ የታዘበችው ነገር ስለሆነ ብዙም አልገረማትም።
‹የእየሱስ የውልደት ቀን እኮ ነው የሚመስለው። ሰው ግን አይገርምሽም…አዲስ ነገር አያውቅም። በዙሪያው ብዙ አዲስ ነገር እያለ ተራ በሆነ ነገር ይደነቃል።
‹እስኪ ለአንተ አዲስ ነገር ምንድነው? ስትል ጠየቀችው።
‹ለእኔ አዲስ ነገር መኖር ነው.. ከዛሬ ወደ ነገ መሄድ። በዚህ የሕይወት እርምጃ ውስጥ ደስታና ነጻነት አብረውኝ ካሉ አዲስ ነገሬ ያ ነው › ።
‹የሚገርም ነው! አለች። ማንንም ብትጠይቅ ከዚህ የተሻለ መልስ እንደማይሰጣት ታውቃለች።
‹የአንቺ አዲስ ነገር ምንድነው? ሲል በተራው ጠየቃት።
‹እውነት ለመናገር አዲስ ነገሬን አላውቀውም። ኮረጅሽ ካላልከኝ ግን መኖር ይመስለኛል እና ደግሞ ፍቅር።
‹ያንቺም አስደናቂ ነው..ፍቅርን በህይወቱ ውስጥ ያኖረ ሁሉ አዲስ ነው›። አለ።
‹ታዲያ ለምን ፍቅርን አጉድለህ ደስታና ነጻነት አልከኝ? ስትል ድንገት የጠየቀችው። ከጠየቀችው በኋላ ነበር ትክክለኛ ጥያቄ እንደጠየቀችው ገባት።
‹ከዛሬ ወደ ነገ ተራማጅ ነኝ ብዬሽ የለ..እስካሁን ፍቅር ላይ አልደረስኩበትም። የምወደው እንጂ የሚወደኝን አላገኘሁም። ድሃ ስትሆኚ ታሪክ አይኖርሽም። ድሃ ስትሆኚ የምትከተይው እንጂ የሚከተልሽ አይኖርም። ለዛም አይደል የአንቺ እኔን መከተል አስገርሞት ሰው ሁሉ ቆሞ የሚያየን›።
ትክክል የመሰላት ጥያቄ አሁን ልክ እንዳልነበር ገባት። እንዲህ መጠየቅ አልነበረብኝም ስትል አሰበች። ባልተገባ ጥያቄዋ የፍቅር ርሃብተኛ እንደሆነ ደረሰችበት። አሳዘናት.. ሳታውቀው እጁን በእጇ ያዘችው። በዚያ ሰዓት እሷም እሱም የፍቅርን ቅኔ እየተቀኙ ነበር። ተጠግታው ስለነበር መጥፎ ጠረኑ አፍንጫዋን ሞገታት..ፍቅር የራባት ነፍስ እድፍ እድፍ ሸተተቻት።
‹እንደ ሰው ርሃብ ሞት የለም። የሰው ርሃብ ነፍስ ላይ ነው ማረፊያው። ድህነት ማለት የገንዘብ ማጣት አይደለም..ድህነት ማለት ነፍስ ሰው ሲርባት ነው። ነፍስ የኔ የምትለው ስታጣ ነው። የሰው ረሃብ ደግሞ የፍቅር ርሃብ ነው። ፍቅር ሲርብሽ መሞት ትጀመሪያለሽ። እኔም እየሞትኩ ያለሁት በፍቅር ርሃብ ነው› አላት።
ሲያወራት ላለማልቀስ ከስሜቷ ጋር እየታገለች ነበር። ይሄን ሁሉ ዘመን ስትወጣና ስትገባ ይሄን ሰው ችላ ማለቷ ትልቅ ጥፋት እንደሆነ አሁን ነው የተገለጠላት። እሷም እኮ አባት የላትም አባት ማጣቷ በህይወቷ ውስጥ ያጎደለባትን ስታብ ሰው ማጣት ምን ያክል ህመም እንዳለው ተረዳች። በዙሪያዋ በፍቅር ርሃብ ለመሞት የሚያጣጥሩትን ህያዋን ስታስብ ያመቀችው እንባዋ ገንፍሎ ወጣ..
‹ፍቅር ሞትን መግደያ ጥበባችን ነው። ሰው ፍቅርን ካላወቀ ምንም ቢያውቅ መሃይም ነው። በልቡ ላይ ፍቅርን የያዘ ሰው እንደ ሙሴ ነው.. በመንገዱ ሁሉ ተአምር የሚሰራ። በበትሩ ባህር የሚከፍል፣ በገባውን ሰማይ ጸሀይን የሚያቆም፣ በሀይሉ ደመናን የሚሰውር። ሰው ሙሉ ሆኖ ለመኖር ፍቅር ያስፈልገዋል። ሰው በፍቅር መከራውን መግደል ካልቻለ ለመኖር አቅም አያገኝም። አቅም ያጣነው የመውደድ ሃይላችንን ለጥላቻ አሳልፈን ስለሰጠን ነው። ዓለም ላይ አብዛኞቹ ሞቶች የፍቅር ሞቶች ናቸው። አብዛኞቹ ስቃዮች ሰው የማጣት ስቃዮች ናቸው። አብዛኞቹ ጉስቁልናዎች ራስን ብቻ የማፍቀር ጣጣዎች ናቸው። አብዛኞቹ እንግልቶች የራስ ወዳድነት ጽንሶች ናቸው›። ሲል ተናግሮ ዝም አለ።
ፍቅር ነው ጎዳና ያወጣኝ፣ ሰው ማጣት ነው ብቸኛ ያደረገኝ እያላት እንደሆነ አልጠፋትም። እስካሁን ይሄን ሰው ተጠግታ ያጣችው የለም። ያልደረሰችበትን የሕይወት ከፍታ እያሳያት ነው። እጁን እንደጨበጠችው ከእሱ ጋር ብዙ ህልም አለመች። ብዙ ነገዎችን ተመኘች። ካፌ እስኪደርሱ ድረስ ከሃሳቧ አልወጣም ነበር።
ሳይተዋወቁ ሩቅ የዘለቀ በሚመስል የወዳጅነት ስሜት ለእሷም ለእሱም የጣፈጠ ድንቅ የሆነ ምሳ ተመገቡ። ከምሳው በኋላ ‹ስምሽን እኮ አልነገርሽኝም? አላት።
‹አንተም እኮ አልነገርከኝም..›
‹ዛሬ አንቺን የማደምጥበት ጊዜ ነው..ባይሆን ነገዬን አወርስሻለው› ሲል መለሰላት።
‹እንደዛ ከሆነ መቅደላዊት እባላለሁ› አለችው።
‹ስምሽ ያምራል!
‹ስሜ እንኳን አያምርም አትዋሽ። የኦሪቷ ዝሙተኛ መሆኔን ረሳህ እንዴ?
‹እየሱስ እግር ላይ አጎንብሶ ቀና እንደማለት ሴትነት ያለ አይመስለኝም። እንዳውም ስምሽ ሌላ ቢሆን ኖሮ የዚህን ያክል ብርሃን ባለበሽ ነበር። በልክሽ የተሰፋ ስም ነው ያለሽ› አላት ከልቡ ነበር ማንንም እንዲህ እውነት በሆነ ስሜት ተናግሮ አያውቅም።
አስደነገጣት.. ስህተት ሆኖ አይታው ታውቅም። ካገኘችው ሰዓት ጀምሮ እያስገረማት ነው። ይሄ ሰው ማረፊያዋ ሆነ..ከእንግዲህ ፍቅር እየመገበች በልቧ ውስጥ ታሳድገዋለች እንጂ ስትወጣና ስትገባ እያየችው አታልፈውም። ዓለም ለነፍሷ የተገባ ከእሱ የተሻለ ሰው እንደማትሰጣት ገብቷታል። ቀና ብላ አየችው..አይኖቹን አይኖቿ ላይ አገኘቻቸው።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵያ)
አዲስ ዘመን ሰኔ 10 /2014