በኢትዮጵያ ስፖርቶች ውስጥ ከሚስተዋሉ ችግሮች መካከል አንዱ ታዳጊና ወጣት ስፖርተኞች በተለያዩ አጋጣሚዎች በሚያገኙት እድል ተጠቅመው ለሚያሳዩት ብቃትና ተስፋ ቦታ ሰጥቶ ወደ ትልቅ ደረጃ ማሸጋገር በጉልህ ይጠቀሳል። በተለይ በእድሜ ገደብ በሚካሄዱ ውድድሮች ላይ ወጣት ስፖርተኞች ተስፋ ሰጪ ብቃት ቢያሳዩም ወደ ዋና ቡድን እንዲያድጉና በይበልጥ አቅማቸውን እንዲያሳዩ በማድረግ ረገድ ክፍተት መኖራቸው በስፖርት ቤተሰቡ ተደጋግሞ የሚነሳ ጉዳይ ነው። በሴቶች እግር ኳስ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታየ ያለው ሂደት ግን ለረጅም ጊዜ ሲነሳ የቆየውን መሰል ቅሬታ ለመቅረፍ አንድ ርምጃ ሆኖ ታይቷል።
ዩጋንዳ አዘጋጅ በነበረችበት የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ሀገራት የሴቶች እግር ኳስ ውድድር (ሴካፋ) ላይ በሉሲዎቹ ስብስብ ይህ ተስፋ ታይቷል። በዚህ ውድድር ላይ ዩጋንዳ የዋንጫ ባለቤት ስትሆን፤ ቡሩንዲና ኢትዮጵያ ደግሞ ሁለተኛና ሶስተኛ በመሆን ማጠናቀቃቸው ይታወሳል። ስምንት ሀገራት በሁለት ምድብ ተደልድለው ለአሸናፊነት በተፋለሙበት ውድድር ላይ ተካፋይ የነበረው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን (ሉሲዎቹ) በአዳዲስና ወጣት ተጫዋቾችን ከነባሮቹ ጋር አዋህዶ የተዋቀረ ተስፋ ሰጪ ስብስብ መሆኑን አስመስክሯል። ይህ ስብስብ እጅግ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴና ውጤት በጨዋታዎች ማሳየቱም በብዙዎች ተመስክሮለታል።
የሉሲዎቹን የዩጋንዳ ቆይታ አስመልክቶ በዋና አሰልጣኙ ፍሬው ኃይለገብርኤል አማካኝነት በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫም ለወጣትና ተተኪ ተጫዋቾች የተከፈተው በር ያለው ተስፋ ተንጸባርቋል። ቡድኑ ወደ ዩጋንዳ ከመጓዙ አስቀድሞ አሰልጣኙ እንዳሳወቀው፤ ከዚህ ቀደም ከ20 ዓመት በታች የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ሀገራት የሴቶች እግር ኳስ ውድድር (ሴካፋ) ዋንጫ ባለቤት በመሆን በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ እስከጫፍ መጓዝ ከቻለው የወጣት ቡድን በተውጣጡ ተጫዋቾች መገንባቱን ጠቁሞ ነበር። ይህ ለተተኪዎች በቀጥታ እድል በመስጠት ወደ ዋናው ቡድን የማሸጋገር ሂደትም ሉሲዎቹን የዋንጫ ባለቤት ባያደርግም አበረታች የሚባል ውጤት እንዳስገኘ አሰልጣኙ ተናግረዋል።
ተጫዋቾቹ ከተለያዩ ውድድሮች ተሰባስበው የብሄራዊ ቡድን ዝግጅት የጀመሩ ሲሆን፤ ከ11 ቀናት በኋላ ወደ ሴካፋ ውድድር መግባታቸው ይታወቃል። ይሁን እንጂ የውድድሩ መርሃ ግብር በአንድ ቀን ልዩነት መሆኑ የሉሲዎቹን የሴካፋ ጉዞ ከባድ ቢያደርገውም፤ ተጫዋቾቹ ከእድሜያቸው አንጻር የተካፈሉበት ውድድር እንዲሁም ያደረጉት ጥረት እጅግ የሚያስመሰግን መሆኑን አሰልጣኝ ፍሬው ተናግረዋል።
ሌሎች ቡድኖች አዋቂ ተጫዋቾችን ይዘው ሲቀርቡ ኢትዮጵያ ግን በወጣት በተገነባ ቡድን ውድድሩን ተካፍላ አበረታች ውጤት ማስመዝገቧም ለዚህ ማሳያ እንደሚሆን አስረድተዋል። የሉሲዎቹ ስብስብ ከ20 ዓመት በታች የሴካፋ ውድድር አሸናፊነት ወደ አዋቂዎች ቡድን ያደጉ ተጫዋቾችን በብዛት የያዘ መሆኑን ተከትሎም በርካታ ልምዶችን ማግኘት እንደተቻለ አሰልጣኙ በመግለጫቸው አስረድተዋል።
በተለይ አብዛኛዎቹ ተጫዋቾች ከ20 ዓመት በታች ቡድን ወደ ዋናው ብሄራዊ ቡድን ያደጉና ከዚህ ቀደምም ልምድ ያልነበራቸው በመሆኑ አዲስ ነገርን የተማሩበት ውድድር እንደነበር የተናገሩት አሰልጣኝ ፍሬው፣ ተጫዋቾች በሥነምግባር የታነጹ መሆን የሚገባቸው ከመሆናቸው ጋር በተያያዘ ከነባር ተጫዋቾች ጋር የነበራቸውን መከባበር በተግባር መመልከቱን አስረድቷል።
ተስፋ ያሳዩት ወጣት ተጫዋቾች በሜዳ ውስጥም ቢሆን በርካታ ልምዶችን ከአምበሏ ሎዛ አበራና ሌሎች ተጫዋቾች ሲቀስሙ መቆየታቸው ወደ ፊት የሉሲዎቹን ስብስብ ጠንካራ እንደሚያደርገው አሰልጣኙ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል። ቡድኑ በእድሜ ገደብም ይሁን በአዋቂዎች ተከታታይ ዓለም አቀፍ ጨዋታዎች ላይ ተሳትፎ ማድረጉ በቀጣይ ለሚኖረው ብቃት የሚጫወተው ሚና ቀላል የሚባል እንደማይሆንም አሰልጣኙ አክለዋል።
ቡድኑን ከ20 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን አባላት በመገንባቱና በውድድሩ ላይ በሚካፈሉ እንዲሁም አበረታች ውጤት ከማስመዝገቡ ባሻገር ወደ ፊት ለረጅም ዓመት ሊጫወት መቻሉ ተስፋ እንደሚሰጥ አሰልጣኙ ተናግረዋል።
በአዳዲስ ወጣት ተጫዋቾች የተዋቀረ ቡድንን ይዞ የቀረበው አሰልጣኙ ከዚህ ቀደሙ ቡድን ጥቂት ተጫዋቾችን ወደ ቡድኑ ሲያካትት ከጨዋታ ባሻገር በሌሎች ጉዳዮች ላይም እንዲያግዙት መሆኑን ጠቁማል። በተለይ እንደ ብርትኳን ገብረክርስቶስ ያሉ ምርጥ ተጫዋቾች ለቡድኑ አባላት ተምሳሌት መሆናቸውን አንስቷል።
ሌላኛዋ የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች ሎዛ አበራ በበኩሏ ከአዳዲሶቹ የቡድኑ ተጫዋቾች ጋር የነበራት መግባባትና ውህደት እንዲሁም ተጫዋቾችን በመምራትና በማነሳሳት ረገድ በሜዳ ውስጥ የነበረውን ስራ እንዳቀለለችለት አሰልጣኙ ጠቁሟል። ተጫዋቾቹ ከአሰልጣኞች ቡድን ባልተናነሰ ልምዳቸውን በማካፈል ላደረጉት አስተዋጽኦም ምስጋናውን አቅርቧል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሰኔ 10 /2014