ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ዘርፍ እምቅ አቅም ያላት አገር ናት። አገሪቱ አምራች ኃይል አቅም፣ ተፈጥሯዊ አቀማመጥ፣ ሕጋዊ ማዕቀፎችና ለዘርፉ እድገት አወንታዊ አስተዋፅዖ የሚያበረክቱ ሌሎች መልካም አጋጣሚዎችና አስቻይ ሁኔታዎችም አሏት። በኢንዱስትሪ ያላትን አቅም በመጠቀምና ከዚሁ ዘርፍ የሚገኘውን ገቢ በማሳደግ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ የምታደርገውን መዋቅራዊ ሽግግር እውን ለማድረግ ባለፉት ዓመታት በርካታ ተግባራትን አከናውናለች።
በዓይነትም ሆነ በብዛት በርካታ የሆኑት የዘርፉ ችግሮች፤ የመንግሥትን፣ የግሉን ዘርፍና በአጠቃላይ የሕዝቡን የተቀናጀ ጥረት የሚፈልጉ እንደሆኑ በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቷል። ለችግሮቹ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ብዙ ሙከራዎች ተደርገው የማይናቁ ውጤቶች ቢመዘገቡም፤ ከአገሪቱ አቅምና ከችግሮቹ ስፋት አንፃር ግን መፍትሄዎቹ የሚፈለገውን ያህል ውጤት ሊያስገኙ እንዳልቻሉ በተደጋጋሚ ተገልጿል።
ዘርፉ በግብዓት (ጥሬ ዕቃ)፣ በሰው ኃይል፣ በቦታ፣ በኃይል፣ በፋይናንስና በውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ችግሮች ተተብትቦ የተያዘ ነው። በዚህም ምክንያት ኢንዱስትሪዎች እያመረቱ ያሉት የአቅማቸውን ግማሽ ያህል ብቻ እንደሆነ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃዎች ያሳያሉ። በአሁኑ ወቅት የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ከአጠቃላይ ጥቅል አገራዊ ምርት የስድስት ነጥብ ስምንት በመቶ ድርሻ ያለው ሲሆን ይህን ድርሻ ወደ 17 ነጥብ ሁለት በመቶ ለማሳደግ ታቅዷል። ከዚህ በተጨማሪም አሁን ያለውን 50 በመቶ የኢንዱስትሪዎች የምርታማነት አቅም ወደ 85 በመቶ የማድረስ እቅድም ተይዟል።
መንግሥት የኢንዱስትሪው ዘርፍ ችግሮችን ለማቃለል እየተገበራቸው ከሚገኙ የመፍትሄ እርምጃዎች መካከል በቅርቡ ይፋ የተደረገው የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ሀገራዊ ንቅናቄ ተጠቃሽ ነው። የሀገራዊ ንቅናቄው ዋና ዋና ዓላማዎች የአምራች ኢንዱስትሪውን ችግሮች በጋራ በመፍታት ለዘርፉ ዘላቂ ልማትና ተወዳዳሪነት ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ዘርፉ ለኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ሽግግር የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲወጣ ማስቻል እንዲሁም በዘርፉ ያለውን የሥራ ባህል ማሻሻል ብሎም የኢንዱስትሪ ምርቶችን ጥራትና ተወዳዳሪነት በማሻሻል ገቢ ምርቶችን የመተካት ሽፋንን ማሳደግ ናቸው።
ንቅናቄው የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ምርትና ምርታማነት ለመጨመር ብሎም የዘርፉን ልማት ለመደገፍ እንዲሁም አምራች ኢንዱስትሪዎችን በጥራትና ቁጥር ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት የሚከናወኑበት ሲሆን የኢንዱስትሪ ዘርፉን ከተለመደው አሰራር በማሻገር ምርታማነትን ለመጨመር እንደሚያግዝ ታምኖበታል። በአሁኑ ወቅት ኢንዱስትሪዎች ለሀገር ውስጥ ምርት እድገት እያበረከቱት ያለውን አነስተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያሳድግም ተሥፋ ተጥሎበታል።
በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ አስቻይ ሁኔታዎችን በመፍጠር የዘርፉን የማምረት አቅም ማሳደግ፣ ለዜጎች ተጨማሪ የሥራ ዕድል መፍጠር፣ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ማሳደግ እና ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት የውጭ ምንዛሬን ማዳን ከ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› መርሃ ግብር የሚጠበቁ ውጤቶች ናቸው።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በንቅናቄው ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ለማሳደግ በአገር ውስጥ የማምረት አቅምን ማሳደግ እንደሚገባና የአገር ውስጥ ምርቶችን መጠቀም አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረው ነበር። ከዚህ በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያም፣ በ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ የኢንዱስትሪ ዘርፉን ምርታማነት ለመጨመር እየተሠራ እንደሆነ ገልፀዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ ኢንዱስትሪዎች የገጠሟቸውን ችግሮች በመፍታትና ለምርታማነታቸው ማደግ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር የኢንዱስትሪው ዘርፍ በአገራዊ ኢኮኖሚ የሚኖረውን ድርሻ ለማሻሻል ታቅዶ መተግበር እንደተጀመረ በንቅናቄው ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ መግለፃቸው የሚታወስ ነው።
አቶ መላኩ በቅርቡ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ባዘጋጀው የድሬዳዋው የውይይት መርሃ ግብር ላይ ስለንቅናቄው ምንነትና ፋይዳዎች ገለፃ አቅርበው ነበር። የአምራች ዘርፉ እድሎችንና የመንግሥትን ትኩረት በተመለከተው በዚሁ ገለፃቸው ላይ አገሪቷ ያላትን ትልቅ የዘርፉን እምቅ ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም ይቻል ዘንድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ ተሞክሮዎችን በመቀመር በቅርቡ የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ መጀመሩን ጠቁመው፣ የዚህ ንቅናቄ ምሠሦዎችም ባለድርሻ አካላትን ማሣተፍ፣ ዘርፉን በጥናትና ምርምር መደገፍ፣ ለዘርፉ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ማድረግ እና የአገር በቀል ምርቶችንና አመራረትን ማሳደግ መሆናቸውን አብራርተዋል።
የውጭ ምንዛሪ እጥረት ችግርን ለመፍታት የመጀመሪያውና መሠረታዊው መፍትሄ የአገር ውስጥ ምርትን ማሳደግ እንደሆነ ያስረዱት አቶ መላኩ፣ ከዚህ አንፃር ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል። ‹‹ኢትዮጵያን ከኢንዱስትሪ ውጭ ማሰብ አይቻልም›› ያሉት አቶ መላኩ፣ መንግሥት የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን በመደገፍ ዘርፉን ለማጠናከር በ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ የአቅም ማጠናከር ሥራ እያከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።
በአጠቃላይ ንቅናቄው ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ የሆኑ የኢንዱስትሪ ምርቶችን አምርቶ ለመሸጥ እንዲሁም ከውጭ የሚገቡ የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን በአገር ውስጥ ለመተካትና የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለመቅረፍ የምታደርገውን ጥረት ወደ ወሳኝ ምዕራፍ የሚያሻግር ተግባር እንደሆነም ገልፀዋል።
አገሪቱ ያላትን የኢንዱስትሪ አቅም ገቢራዊ ለማድረግ የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን መደገፍና ተወዳዳሪ ማድረግ ይገባል። የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን መደገፍ ዘርፍ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት። የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን የመደገፍና ተወዳዳሪ የማድረግ ጉዳይ በምጣኔ ሀብት ትብብርና በእርዳታ ስም የሚደረግን የሀብታም አገራትንና የተቋሞቻቸውን ጣልቃ ገብነት በማስቀረት ሉዓላዊነትን እስከማስከበር ድረስ የዘለቀ ትርጉምና ፋይዳ አለው።
የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ጀማል አህመድ በበኩላቸው በድሬዳዋው የውይይት መድረክ ላይ የግሉ ባለሀብት በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ስላለለው ተሳትፎ፣ ስላበረከተው አስተዋፅዖ እና ስላሉበት ችግሮች ባቀረቡት ገለፃቸው፣ መንግሥት የአገር ውስጥ አምራቾች እንዲበረታቱ ለዓመታት ያከናወነው ሥራ በተለያዩ ዘርፎች የግል ባለሀብቱ እንዲጠናከር አቅም መፍጠሩን ተናግረው፣ በሕዝቡም ሆነ በመንግሥት በኩል የአገር ውስጥ ምርት በመጠቀም ረገድ ያሉ ክፍተቶችን ማስተካከል እንደሚገባ ገልጸዋል። ለዚህም ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› የተሰኘው ንቅናቄ ትኩረት ተሰጥቶት በትክክል ከተተገበረ ትልቅ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ጠቁመዋል።
በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህርና በ‹‹ፍሮንቲየርአይ (Frontieri)›› ጥናትና አማካሪ ድርጅት ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ሞላ አለማየሁ ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› የተሰኘው ንቅናቄ አንድ አገር ባላት እምቅ ሀብት ላይ ተመስርታ ማምረት እንደሚገባት የሚጠቁም መርሃ ግብር እንደሆነ ያስረዳሉ።
‹‹በርካታ አገራት ዜጎቻቸው፣ ባለሀብቶቻቸውና የሌሎች ሀገራት ባለሀብቶችም በሀገራቸው እንዲያመርቱ ጥረት ያደርጋሉ። የኢትዮጵያም ጥረት ከዚህ የተለየ አይሆንም። ‹ኢትዮጵያ ታምርት› ሲባል አገራዊ የማምረት አቅሟን በማሳደግ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርቶች የመተካት ተግባሯን ከማጠናከር ጋር ትስስር አለው›› ይላሉ።
እንደርሳቸው ገለፃ፣ ‹ለማምረት ምን ያስፈልጋል?› ለሚለው ጉዳይ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል። የግብዓት እጥረት የአገሪቱ ኢንዱስትሪዎች ከግማሽ በታች በሚሆነው አቅማቸው እንዲያመርቱ ስላስገደዳቸው የማምረት አቅምን ለማሳደግ የግብዓት አቅርቦትን ማመቻቸት ይገባል። ንቅናቄው የአገር ውስጥ ባለሀብቶችም ሆኑ የውጭ ኢንቨስተሮች በኢንቨስትመንት ሥራዎች ላይ እንዲሰማሩ ያስችላቸዋል። በተገቢው የፖሊሲ ማዕቀፍ እና በተቀናጀ ጥረት ከታገዘ ምርታማነትን ለማሳደግ እንዲሁም የውጭ ምንዛሬ እጥረትንም ለማቃለል አማራጭ መፍትሄ መሆን ይችላል።
ንቅናቄው ካስገኛቸው ውጤቶች መካከል አንዱ ማምረት ያቆሙ ኢንዱስትሪዎችን ወደ ሥራ እንዲመለሱ ማገዙ ነው። በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ማምረት አቁመው ከነበሩ ፋብሪካዎች መካከል በንቅናቄው ትግበራ ከ118 በላይ የሚሆኑት ወደ ሥራ መመለሳቸውን የኢንዱትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ተናግረዋል።
በእርግጥ የንቅናቄው ውጤታማነት በመንግሥት ጥረት ብቻ የሚሳካ አይሆንም። አምራች ኢንዲስትሪው ለዘላቂ ልማት ዋነኛ ሞተር የመሆኑ እውነታ ላይ የጋራ መግባባት መፍጠር ያስፈልጋል። ከዚህ አንፃር አቶ መላኩ ከመንግሥት ጥረት ባለፈ ባለሃብቱም ተገቢውን የኢንዱስትሪ አስተዳደር ስርዓት ተግባራዊ በማድረግ ምርታማነትን ማሳደግ እንዳለበትም ተናግረዋል። ‹‹የሕግና የፖሊሲ አፈፃፀሞችን መከታተል እንዲሁም ከዚህ ቀደም የተተገበሩ አሰራሮችን መገምገም ያስፈልጋል፤የአመለካከት ችግሮችን የሚፈቱ ሥራዎችን ማከናወንም ያስፈልጋል›› ብለዋል።
ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት ዓመታት በኢንዱስትሪው ዘርፍ ለማሳካት የያዘችውን እቅድ ከግብ ለማድረስ ሚና እንደሚኖረው የታመነበት ይህ ንቅናቄ ዓላማውን እንዲያሳካ የተቀናጀ ተግባር እንደሚያስፈልግ ዶክተር ሞላ ይናገራሉ። እርሳቸው እንደሚሉት፤ ለመርሃ ግብሩ ስኬት የመንግሥት፣ የባለሀብቱና የሕዝቡ ድርሻ በግልፅ ሊታወቅ ይገባል። ንቅናቄው የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግብና ለዘላቂ መፍትሄ አጋዥ እንዲሆን በተገቢ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች መደገፍ ይኖርበታል።
መንግሥት ንቅናቄውን እንዲሁም ዘርፉን ውጤታማ የሚያደርጉ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በማዘጋጀት ምቹ የኢንዱስትሪ ከባቢን መፍጠር ይጠበቅበታል። የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራትና የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን ለመደገፍ ትኩረት መስጠት ይኖርበታል። መንግሥት ማበረታቻዎችን ሲያደርግም ማበረታቻዎቹ ለታለመላቸው ዓላማ መዋላቸውን ማረጋገጥ አለበት። ከዚህ በተጨማሪም መንግሥት የመርሃ ግብሩን አፈፃፀም እየተከታተለና እየገመገመ ማስተካከያዎችን በማድረግ የአመቻችነት ሚናውን ሊወጣ ይገባል። ባለሀብቶችም አዳዲስ አሰራሮችን በመተግበር አቅማቸውን ማሳደግና ከመንግሥት የሚደረጉላቸውን ማበረታቻዎች በጥንቃቄ መጠቀም እንደሚኖርባቸውም ዶክተር ሞላ ይናገራሉ።
ኅብረተሰቡ ስለሚኖረው ሚና ደግሞ ‹‹ከሀገር ውስጥ ምርቶች ይልቅ ለውጭ ምርቶች የተሻለ ትኩረትና ፍላጎት የመስጠት አመለካከትን መቀየር ይገባል። የሀገር ውስጥ ምርቶችን በተጠቀምን ቁጥር የአምራቾቹን አቅም እያጎለበትን እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል›› ይላሉ።
የአገሪቱን የምጣኔ ሀብት መዋቅር ከእርሻ መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለማሸጋገር የሚያግዙ በርካታ መልካም አጋጣሚዎችና እድሎች እንዳሉ አይካድም። ይሁን እንጂ እነዚህን መልካም አጋጣሚዎች በመጠቀም የኢኮኖሚውን መዋቅራዊ ሽግግር ለማሳካት የተከናወኑ ተግባራት አገሪቱ ካላት አቅምና ፍላጎት በብዙ ርቀት ላይ የሚገኙ በመሆናቸው ለወቅቱ የሚመጥን ተግባራዊ ምላሽ መስጠት እጅግ አስፈላጊ ነው። ለዚህ ደግሞ አገራዊ የማምረት አቅምን በማጎልበት የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ፣ ተጨማሪ የሥራ እድሎችን ለመፍጠርና ተወዳዳሪ አገራዊ ምጣኔ ሀብት ለመገንባት ያስችላል ተብሎ የታመነበት የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ ከፍተኛ ትኩረት የሚሻ አማራጭ የመፍትሄ አቅጣጫ ነው።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሰኔ 9/2014