መንግሥት የነዳጅ ዋጋ በዓለም አቀፍ ደረጃ መናሩን ምክንያት በማድረግ በነዳጅ ዋጋ ላይ መጠነኛ ክለሳ ማድረጉ ይታወሳል። የተደረገውን መጠነኛ የሆነ የነዳጅ መሸጫ ዋጋ ክለሳን ምክንያት በማድረግ በእቃዎችና አገልግሎቶች ላይ ሰው ሰራሽ እጥረት የሚፈጥሩና በምርቶች ላይ ዋጋን የሚያንሩ አካላት ላይ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ የሚወሰድ ስለመሆኑም መንግሥት አስታውቋል። በቀጣይም ሐምሌ ወር የሚደረገውን የታለመለት የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ተከትሎ የኑሮ ውድነቱ እንዳይባባስ ቁጥጥር የሚደረግ እንደሆነ ነው የተገለጸው፤
ይሁን እንጂ ዜጎች በአገሪቱ ሲወጣ እንጂ ሲወርድ ያልታየው የኑሮ ውድነት የነዳጅ ዋጋ ጭማሪው በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዳይሆንበት ያላቸውን ስጋት ያነሳሉ። የኑሮ ውድነቱ እየተባባሰ የቀጠለ ስለመሆኑና በተለይም የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ሲሰማ በተለያዩ የሸቀጦች ዋጋ ላይ ከፍተኛ የሆነ ጭማሪ በመታየቱ ሰዎች መኖር ያልቻሉበት ደረጃ ላይ መደረሱን ጠቅሰው በቀጣይም የኑሮ ውድነቱ ተባብሶ የሚቀጥል እንደሆነ ያላቸውን ስጋት የዝግጅት ክፍላችን ያነጋገርናቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ይናገራሉ።
በአሁን ወቅት እየታየ ስላለው የኑሮ ውድነት ማውራት አስፈላጊ እንዳልሆነ በመጥቀስ በቀን አንድ ጊዜ በልተን ካደርን ተመስገን ብቻ ብለን ማደር አለብን የሚሉት ወይዘሮ ሰናይት ጋሻው ናቸው። ወይዘሮዋ በየጊዜው እየናረ ስለመጣው የኑሮ ውድነት ሲናገሩ ሁሉም ነገር ዕለት ዕለት “ጨመረ ጨመረ” እያልን ስናወራ እየባሰበት ስለመምጣቱና መንግሥት ምንም አይነት መፍትሔ መስጠት እንዳልቻለ በማንሳትም ዝምታ ይሻላል ይላሉ። ጨመረ ብሎ መጮህ የኑሮ ውድነቱን ይበልጥ እንዳባባሰውና ለውጥ እንዳልመጣ አንስተዋል። ‹‹ከዚህ የባሰ ቢመጣስ ምን ማድረግ ይቻላል?›› ብለው ላነሱት ጥያቄ ‹‹ምንም ማድረግ አይቻልም›› በማለት ምላሽ በመስጠት ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል።
ሌላኛዋ አስተያየት የሰጡን ወይዘሮ አያል ዘለቀ በተመሳሳይ ስለ ኑሮ ውድነት መናገር በራሱ ነገሩን ማባባስ እንደሆነና “የኑሮ ውድነቱን አልቻልነውም ከአቅማችን በላይ ሆነ” እያለ ላለው ህዝብ ምንም ጠብ የሚል መፍትሔ አልመጣለትም በማለት ሀሳባቸውን አካፍለውናል። እንደሳቸው ገለጻ፤ ዓለም አቀፍ የሆነው ጦርነትን ጨምሮ በአገሪቱ መቋጫ ያልተገኘለት ጦርነት ለኑሮ ውድነቱ አይነተኛ ሚና አላቸው። ይሁን እንጂ በአሁን ወቅት ደግሞ መንግሥት በነዳጅ ላይ ያደረገው ጭማሪም ሆነ በቀጣይ ሊያደርግ ያሰበው ጭማሪ የኑሮ ውድነቱን ይበልጥ ሊያባብሰው እንደሚችል ያላቸውን ስጋት ገልጸው ነዳጅ መደጎም እንዳለበት አንስተዋል።
በቅርቡ የማዳበሪያ እጥረት በመከሰቱና ዋጋ በእጥፍ በመጨመሩ ምክንያት ጤፍ ይወደዳል የሚል ስጋት ውስጥ ተገብቶ የነበረ መሆኑንም አስታውሰው ይሁንና እንደ ወሬው አለመሆኑን ጠቅሰው ለዚህም መንግሥት ማዳበሪያን ሊደጉም እንደሆነ ተሰምቷል። ነዳጅ ሲጨምር የንግድ ሥራ ከትራንስፖርት ጋር የተያያዘ በመሆኑ ሁሉም ነገር ይጨምራል። ለአብነትም አንድ ሻይ ቅጠል ከ15 ብር ተነስቶ በአሁን ወቅት 35 ብር መድረሱን አንስተው የዛሬ ወር ደግሞ ነዳጅ እንደተባለው ሲጨምር ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም። ስለዚህ ነዳጅ መደጎም አለበት ሲሉ ሀሳባቸውን አካፍለውናል።
የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን በበኩሉ በሐምሌ ወር የሚደረገው የነዳጅ ዋጋ ማስተካከያን ሰበብ በማድረግ የኑሮ ውድነቱ እንዳይባባስ ቁጥጥር የሚደረግ ስለመሆኑ አመላክቷል። የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን የነዳጅ ውጤቶች ግብይት ስታንዳርድ ጥናትና ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ለሜሳ ቱሉ እንደገለጹት፤ ነዳጅ በዋጋ ላይ ያለው ተጽዕኖ በራሱ ልክና ሚዛን መታየት ያለበት ሲሆን፤ ትክክለኛና ሳይንሳዊ ተፅዕኖው ምን ያህል እንደሆነ በፕላንና ልማት ኮሚሽን በተደረገው ጥናት ውስን ተጽዕኖ አለው። ነገር ግን ይህን እንደ ሰበብ በመውሰድ በተለያዩ የፍጆታ ዕቃዎች ላይ የሚደረገው ጭማሪ ልኩን ያለፈና ሊታረቅ የሚገባው እንደሆነ ነው ያመላከቱት።
ነዳጅ ላይ አምስት ብር ሲጨመር በሰበቡ ነጋዴው 15 ብር የሚጨምርበት ሁኔታ ስለመኖሩ ዳይሬክተሩ አንስተው፤ በነዳጅ ዋጋ ማስተካከያ ሰበብ የኑሮ ውድነቱ እንዳይባባስ 12 የሚደርሱ ባለድርሻ አካላት ቁጥጥር ይደረጋል። ለውጤታማነቱም በየደረጃው ያሉ የአስተዳደር፣ የፍትህና የጸጥታ አካላት በቅንጅት እንደሚሰሩ ነው የገለጹት። የነዳጅ ዋጋ መሸጫ ዋጋው ማስተካከያ የዓለም የነዳጅ ዋጋን ያገናዘበ በማድረግ በነዳጅ ግብይት ላይ የሚፈጸመው ህገ ወጥነትና ብክነትንም ለማስቀረት የሚያስችል እንደሆነና እየተሠራበት ስለመሆኑ ነው ያስረዱት።
የዋጋ ማስተካከያው በሚተገበርበት ወቅት አነስተኛ ገቢ ባላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ የጎላ ተጽዕኖ በማያደርስ መንገድ መፈጸም እንዳለበት የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ የነዳጅ ዋጋ ማስተካከያው አነስተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን የሚደግፍ እንደሆነም ነው የተናገሩት። ለዚህም ለሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎቶች በኩል ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ መመሪያ ወጥቶ ለተግባራዊነቱ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የከተማ አውቶብሶች፣ የሸገር ትራንስፖርት፣ ድጋፍ ሰጭ አውቶብሶች፣ ፐብሊክ ሰርቪስ፣ ከደረጃ አንድ እስከ ደረጃ ሦስት ያሉ በታሪፍ የሚሰሩ አገር አቋራጭ አውቶብሶች፣ ከ12 ሰው እስከ 40 ሰው የሚጭኑ መለስተኛ ተሽከርካሪዎች፣ የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ ሚኒባሶችና ባጃጆች የድጋፉ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ነው የተገለጸው።
ከዋጋ ጋር የተያያዘ፣ የነዳጅ መሰረተ ልማትና ሎጂስቲክስ፣ ከትራንስፖርት አሰራር፣ ክትትልና ቁጥጥር ጋር ተያይዞ የሚመጡ ችግሮች ተዳምረው በነዳጅ ግብይት ዙሪያ በርካታ ችግሮች መስተዋላቸውን ያነሱት ዳይሬክተሩ፤ በነዳጅ ላይ የነበረውን የቁጥጥርና የክትትል ስርዓት መልክ ለማስያዝ ከጉምሩክ ኮሚሽን ጋር በመነጋገር መመሪያ ወጥቶ ችግሩ እንዲቀረፍ እየተሰራ እንደሆነ ነው ያመላከቱት።
ይህ በሐምሌ ወር የሚደረገው የታለመለት የነዳጅ ዋጋ ማስተካከያ በነዳጅ ላይ ሲፈጸም የነበረውን ሕገ ወጥ ንግድን እና ብክነትን ማስቀረት ያስችላል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ የነዳጅ የችርቻሮ ዋጋ ከጎረቤት አገራት የችርቻሮ ዋጋ ከእጥፍ በላይ ልዩነት አለው፤ ኬንያ፣ ጅቡቲ፣ ሶማሊያና ሱዳን ነዳጅ የሚሸጠው በኢትዮጵያ ከሚሸጥበት ከእጥፍ ዋጋ በላይ በመሆኑ የኢትዮጵያን ነዳጅ መጠቀም መጀመራቸውን ነው የገለጹት።
ነዳጅ ወደ ጎረቤት አገራት እየወጣ ከመሆኑም ባለፈ አገር ውስጥም ለጥቁር ገበያ በር የከፈተ እንደሆነ በማንሳት ኢትዮጵያ ከምትፈልገው በላይ ተጨማሪ የነዳጅ ፍጆታ ፍላጎት የፈጠረ እንደሆነና አሁን ባለው ሁኔታ በኢትዮጵያ ነዳጅ የሚሸጠው በርካሽ ዋጋ ከመሆኑ የተነሳ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪና የነዳጅ ብክነት ማስከተሉንም አመላክተዋል።
መንግሥት የነዳጅ ግብይቱን ጤናማ ያደርገዋል፤ ብክነትንም ይቀንሳል በሚል በሐምሌ ወር በነዳጅ ዋጋ ላይ ሊያደርግ ያሰበው የዋጋ ጭማሪ ህዝቡን ስጋት ውስጥ የከተተው ስለመሆኑ አንስተን የህዝቡ ስጋትና መንግሥት የዋጋ ጭማሪው የኑሮ ውድነቱን እንዳያባብስ አስፈላጊውን ቁጥጥር አደርጋለሁ ስለማለቱ እንዲሁም መወሰድ ስላለበት ጥንቃቄ አንስተን ያነጋገርናቸው በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ምሁር ዶክተር ሞላ አለማየሁ ናቸው።
እንደሳቸው ማብራሪያ መንግሥት ያስቀመጠው አማራጭም ሆነ ህዝቡ ውስጥ ያለው ስጋት ሁለቱም ትክክል እንደሆነና በነዳጅ የገበያ ስርዓት ውስጥም ቢሆን ህገወጥ ግብይት መኖሩ የማይካድ ሀቅ እንደሆነ አንስተዋል። ይሁንና መንግሥት ሲያደርግ የነበረው ድጎማ ሲነሳና በሐምሌ ወር የነዳጅ ዋጋ ሲጨምር በሸቀጦች ላይ የዋጋ ጭማሪ እንደሚኖር ህዝቡን ጨምሮ የእርሳቸውም ስጋት እንደሆነ ነው የገለጹት።
ይሁንና መንግሥት ለህዝብ ትራንስፖርት ሊያደርግ ያሰበውን ድጎማ በጥንቃቄ ማድረግ ያለበት ስለመሆኑ የጠቆሙት ዶክተር ሞላ፤ አንዳንድ ጊዜ ህገወጥነትን ለመቀነስ ታስቦ ሊያስፋፋ የሚችልበት አጋጣሚ እንደሚፈጠር ያስረዳሉ። ለአብነትም በድጎማ የሚሰጣቸው የህዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት የሚሰጣቸውን የድጎማ ነዳጅ እንዴት እንደሚጠቀሙበትና ለሌላ ሶስተኛ ወገን ማስተላለፍ እንዳይችሉ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት አስረድተዋል። ይህን መከታተል ካልተቻለና እንደፈለጉ የሚቀዱ ከሆነ ህገወጥ ንግዱ በአገር ውስጥ እና በጎረቤት አገራት መሆኑ ቀርቶ በአገር ውስጥ ብቻ እንደሚሆን አንስተው ይህን ችግር ለመቅረፍም መንግሥት ስትራቴጂ ይኖረዋል የሚል ዕምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ አሁን ያለው የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ እየተባባሰ ለመጣው የኑሮ ውድነት በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሊሆን እንደሚችል ያነሱት ዶክተር ሞላ፤ ለዚህም አገሪቷ ውጤታማና ትላልቅ የሆኑ የባቡርና መሰል ትራንስፖርት አገልግሎት የተስፋፋ ባለመሆኑ የነዳጅ ጭማሪው ምርቶችን ከሚያጓጉዙ የትራንስፖርት አገልግሎት ጀምሮ አምራቾችም የዋጋ ጭማሪ እንዲያደርጉ ያስገድዳቸዋል። ይኸው ጫናም በመጨረሻ የሚያርፈው ተጠቃሚው ላይ ነው። ስለዚህ የነዳጅ ጭማሪው በኑሮ ውድነት ላይ ተጨማሪ ጫና መፍጠሩ የማይቀርና የሚጠበቅም ነው በማለት የማህበረሰቡ ስጋት ትክክል እንደሆነ አስረድተዋል።
ምንም እንኳን መንግሥት የነዳጅ ጭማሪውን ሰበብ አድርጎ የሚከሰት የዋጋ ንረት አይኖርም ካለም እቆጣጠራለሁ ቢልም አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ግን ግሽበቱን መቆጣጠር እንዳልተቻለ ነው። ስለዚህ መንግሥት የተለያዩ ስትራቴጂዎችን ነድፎ ከፍተኛ ችግሮች ያለባቸውን ዘርፎች በመለየት በቁርጠኝነት ወደ ሥራው መግባት ነው ያለበት። በተለይም የህዝብ ትራንስፖርት ላይ የሚኖረው ድጎማ ህገወጥ በሆነ መንገድ እንዳይቀለበስና ከታሰበው ዓላማ ውጭ እንዳይሆን ምን መደረግ አለበት በማለት ለይቶ ሊሠራ ይገባል።
የመንግሥት ቁርጠኝነትና ተነሳሽነት ወሳኝ እንደሆነ ያነሱት ዶክተር ሞላ፤ አሁን እየታየ ያለው የዋጋ ግሽበት እጅግ በጣም ከፍተኛ እንደሆነና በተመሳሳይ ደግሞ መንግሥት እየወሰደ ያለው እርምጃ ይህ ነው የሚባል እንዳልሆነና በተጨባጭ የሚታይ አለመሆኑን ይናገራሉ። ለአብነትም ፍራንኮ ቫሉታን በማንሳት በዚህ የግብይት ስርዓት ውስጥ የተሳተፉ አካላት የዋጋ ግሽበቱን እያባባሱት እንደሆነና ለዚህም የመንግሥት ቁጥጥር አለ ለማለት የማያስደፍር ነው ብለዋል።
የነዳጅ ዋጋ ጭማሪውን አስታኮ የኑሮ ውድነቱ ይበልጥ ይባብሳል በሚል ህዝቡ ቢሰጋም ተገቢነት ያለው ስጋት ስለመሆኑ ያነሱት ዶክተር ሞላ፤ ለዚህም ምክንያቱ መንግሥት እየወሰደ ካለው እርምጃ አንዱ ዋጋን በመቆጣጠር ከዚህ በላይ አትሽጡ ከሚል ያለፈ እንዳልሆነና ይህም ቁጥጥር ነው ማለት አያስችልም። የዋጋ ግሽበቱን ለመቆጣጠር የተለያዩ አማራጮችን ወስዶ በቁርጠኝነት መሥራትን ይጠይቃል። ካልሆነ ግን በቀላሉ እንደ ፍራንኮ ቫሉታ ሁሉ የነዳጅ ዋጋ ድጎማውም ከታሰበለት ዓላማ ውጭ በመሆን ሌላ ቀውስ ያስከትላል። ስለዚህ ኢኮኖሚው በሚፈልገው ልክና ተገቢ ሁኔታ ቁጥጥር ማድረግ ያስፈልጋል። አሁን ባለው ሁኔታ ግን መንግሥት በተገቢውና ትርጉም ባለው መንገድ የዋጋ ግሽበቱን መቆጣጠር አልቻለም በማለት ሀሳባቸውን ሲገልጹ ለአብነትም በየጊዜው እየጨመረ ያለውን የዋጋ ንረት መንግሥት በሚለው የቁጥጥር ሥርዓት ቢያንስ ባለበት እንዲቆም ማድረግ ያልተቻለ መሆኑን በማንሳት ነው።
በቀጣይም በሐምሌ ወር በነዳጅ ዋጋ ላይ የሚደረገው ጭማሪ ተግባራዊ ሲሆን የኑሮ ውድነቱ ይባብሳል የሚለው የማህበረሰቡ ስጋትም ሆነ መንግሥት በነዳጅ ዋጋ ላይ እያደረገ ያለው ጭማሪ ተገቢነት ያለው ነው። ያሉት ዶክተር ሞላ፤ መንግሥት ከምንም በላይ ለማህበረሰቡ ስጋት ክብደትና ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ እንዳለበት በመግለጽ ሀሳባቸውን ቋጭተዋል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሰኔ 8 /2014