የምስራቅ አፍሪካ ጥበባትና ባህል ፌስቲቫል በተያዘው ሰኔ ወር በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ይታወቃል። ይህን መሰል ሁነት በቀጠናው ያለውን ባህላዊ፣ ኪነ ጥበባዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና አጠቃላይ ማህበራዊ ትስስር እንደሚያጠናክረው ደግሞ ባለሙያዎች ይናገራሉ። በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በሌሎች ጉዳዩ በቀጥታ በሚመለከታቸው አካላት አስተናባሪነት በአፍሪካ መዲና አዲስ አበባ የሚዘጋጀው ፌስቲቫሉ በርካታ ሁነቶችን እንደሚያስተናግድ ይጠበቃል። ይህ ሁነት ላለፉት ሶስት ወራት በመንግስት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት ዝግጅት ሲደረግበት ቆይቷል።
ይህን ጉዳይ አስመልክቶ የባህልና ስፓርት ሚኒስቴር የተለያዩ ሲያደርግ የቆየ ሲሆን፣ ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችም የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ቀደም ሲል አካሂዷል። በጉዳዩ ላይ ከፍተኛ የፌዴራል መንግስቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት መግለጫ ሰጥተውበታል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጀላ መርዳሳ ‹‹የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የጋራ ወንዞች፣ መልክአ ምድር፣ ብዝኃ ሕይወት ያስተሳሰሯቸው ፤ ተመሳሳይ የዘር ግንድ፣ የጋራ ታሪክ፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖትና ባህላዊ እሴት ያላቸው ሕዝቦች የሚኖሩበት ቀጠና ቢሆንም፣ የአውሮፓዊያን ቅኝ ገዥዎች በፈጠሯቸው ድንበሮች ምክንያት ሳይወዱ በግድ ተነጣጥለው እንዲኖሩ ተደርገዋል። ›› ሲሉ ገልጸው፣ ‹‹ ‹ከሩቅ ዘመድ የቅርብ ወዳጅ፤› እንደሚባለው ሀገራችን ኢትዮጵያ ጎረቤት መር በሆነ ግንኙነት ለሺ ዘመናት የዘለቀውን የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ግንኙነት በጥበብና በባህል በማስተሳሰር እና በማጎልበት በቀጣይ ቀጠናውን በኢኮኖሚ ለማስተሳስር ና የቀጠናውን ህዝቦች የጋራ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል መሰረት የሚጣልበት ፌስቲቫል አዘጋጅታለች ብለዋል።
የምስራቅ አፍሪካ የጥባባት እና የባህል ፌስቲቫሉን በይፋ በማስተዋወቅ መልዕክት ያስተላለፉት የኢፌዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በበኩላቸው የምስራቅ አፍሪካ የጥበባትና የባህል ፌስቲቫል ለቀጠናው ሰላም፣ የህዝቦች ትስስር እና ልማት ወሳኝ መሆኑን አስታውቀዋል።
የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር የባህል ዲፕሎማሲን በትኩረት መከወን ይገባል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹በውጭ ጉዳያችን በኩል ዋናው የምንረባረብበት የትኩረት ማዕከላችን የጎረቤት ሀገራትን መሰረት ያደረገ ግንኙነት መፍጠር ነው›› ብለዋል። ‹‹እንዳለመታደል ሆኖ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና የሚታወቀው በጦርነት፣ በድርቅ፣ በርሃብ እና በስደት ነው። ይህንን ገፅታ መቀየር የምንችለው ሕዝብና ሕዝብን በጥበባትና በባህል በማስተሳሰር ተፈጥሮ ያደለችንን ፀጋ ተጠቅመን ቀጠናውን ስናለማ ነው›› ሲሉ አስገንዝበዋል። ይህን ጠንካራ ትስስር ለመፍጠር ያለመ ፌስቲቫል በዚህ በያዝነው ሰኔ ወር ለማዘጋጀት ዝግጅቶች እየተጠናቀቁ መሆኑንም ይፋ አድርገዋል።
በቅርቡም የባህልና ስፖርት ሚኒስቴርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዝግጅቱ ላይ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል። ሚኒስትሩ አቶ ቀጄላ መርዳ በፌስቲቫሉ የኢትዮጵያ ክልሎች፣ የምስራቅ አፍሪካ ሀገሮች የባህልና ኪነጥበብ ስራዎቻቸውን እንደሚያቀርቡ ጠቅሰው፣ የባህልና የጥበባት ሁነቱ የቀጠናው ሀገሮችና የአፍሪካ ህዝቦች፣ ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ እድል እንደሚሰጥ፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ደረጃ ከሚዘጋጁ ተመሳሳይ ሁነቶች ላይ የገበያ ድርሻ እንዲኖራት ምቹ ሁኔታ አንደሚፈጥርም ጠቁመዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ፌስቲቫሉ በተለይ በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ረገድ ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፣ከትርኢቱ ባሻገር አንድ አፍሪካን ለመፍጠር እየታሰቡ ካሉት ሁነቶች አንዱ ጅማሮ መሆኑን ገልጸዋል። ባህልና ጥበብን በመጠቀም የቀጠናውን ህዝቦች እርስ በርስ የበለጠ ለማቀራረብና ለማጠናከር ወቅታዊ ፓለቲካዊ ሁኔታዎችን ለማሻሻል ፣የገጽታ ግንባታ ለማካሄድ ያስችላል ይላሉ።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አለማየሁ ጌታቸው ለዝግጅት ክፍላችን የፌስቲቫሉን አስፈላጊነትና ዋንኛ አላማ ሲገልፁ እንዳሉት፤ አጠቃላይ ዓላማው ባህል እና ጥበባትን በመጠቀም የሚዘጋጀው ፌስቲቫል የቀጠናውን ህዝቦች ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነትን ማጎልበት ነው። በዝርዝር ደግሞ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ባህሎቻቸውን እንዲያስተዋውቁና ማህበራዊ ትስስራቸው እንዲጎለብት በማድረግ ዘላቂ ቀጠናዊ ሰላም መፍጠር፣ በሀገራት መካከል የብዝሃ ባህልና አብሮነት የተመለከቱ የልምድ ልውውጦች እንዲፈጠሩ ማድረግ፣ የቀጠናው ሀገራት ህዝቦች የባህል መገለጫዎች እና የኪነጥበብ ስራዎችን በመጠቀም ያለንን የባህል ሀብት ለገጽታ ግንባታ እንዲሆኑ ማስቻል ነው። ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ጋር ያለንን የመሰረተ ልማት ትስስር ማጠናከርና የኢንቨስትመንት ማስፋፋት፤ በባህልና በኪነ ጥበብ ምርትና አገልግሎት ዘርፍ በአምራቾችና በተጠቃሚዎች መካከል ቀጣይነት ያለው የጠናከረ የገበያ ትስስር እንዲፈጠርና የገበያ ተወዳዳሪነትን ማሳደግ፤ የዘርፉን ባለሙያዎች የእውቀትና ክህሎት እንዲሁም ተግባራዊ ልምምድ የሚገኘበትን ዕድል በመፍጠር አቅማቸውን ማሳደግ የሚሉትም የፌስቲቫሉ ፋይዳዎች ናቸው።
“የምስራቅ አፍሪካ የጥበባትና ባህል ፌስቲቫል በውስጡ አራት ዋና ዋና መርሀ-ግብሮችን ያካተተ” የሚሉት የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተሩ፤ እነርሱም ዐውደ ጥናት፣ ዐውደ ርዕይ፣ የኪነ ጥበባት እና ስፖርታዊ ዝግጅቶች እንደሆኑ ይናገራሉ። በሁነቱ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በርካታ ባለድርሻ አካላት እና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ በመጥቀስም እንዲህ ዓይነቱ ሁነት ከእቅድ ጀምሮ ቅድመ ሁነት፣ ጊዜ ሁነት እና ድኅረ ሁነት ወቅቶች ለሚከናወኑ ሥራዎች ሰፊ ጊዜ፣ ከፍተኛ በጀት፣ በርካታ የሰው ሀብት እና ቁሳቁስ እንደሚጠይቅ ይገልፃሉ። ይህንኑ መሰረት በማድረግ በተቀናጀ ዕቅድ እና አመራር የታለመለትን ውጤት ለማምጣት ከዚህ በታች የተዘረዘሩ ዝግጅቶች እንደሚቀርቡ ያስረዳሉ።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ አውደ ጥናቱ የምስራቅ አፍሪካን ትስስር ማጠናከር “Cultivating East African Integration” በሚል ስያሜ ይካሄዳል። በቀጠናው ህዝቦች ጥቅም ላይ የሚውሉ የጋራ ባህላዊ ሀብቶች፣ እሴቶች፣ ቋንቋ እና ኪነ ጥበብ ለጋራ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትና ተጠቃሚነት ባላቸለው ፋይዳ ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ ፅሁፎች የሚቀርቡበት እና ልምድ የሚቀሰምበት መድረክ ነው።
የዕደ ጥበባት ዓውደ ርዕዩ ደግሞ የምስራቅ አፍሪካውያን የባህል ተምሳሌት እና መገለጫ “East Africans Cultural Symbol and Expression” በሚል ስያሜ የሚካሄድ ነው። ይህ ዝግጅት የባህል መገለጫ የሆኑ ምግቦች እና መጠጦች፣ የእደ ጥበብ ምርቶች፣ የስዕልና ቅርጻ ቅርጽ ስራዎች ለዕይታ የሚቀርቡበት መሆኑንም ገልጾልናል።
የመጻሕፍት ዐውደ ርዕይም ምስራቅ አፍሪካ ታንብብ “Let East Africa Read” በሚል ስያሜ ይካሄዳል። ይህ ዝግጅት በየሀገራቱ የታተሙ ታሪካዊ መጻሕፍት ለዕይታ የሚቀርቡበት ነው።
የሙዚቃ ፌስቲቫልም ይካሄዳል። ይህም የምስራቅ አፍሪካ ሙዚቃ ቃና!! ‘’Rhythms of the East Africa’’ በሚል ስያሜ የሚካሄድ ነው። የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን ባህላዊ ሙዚቃዎች፣ ትርዒቶች፣ ሰርከስ፣ ዳንስ፣ ኮሜዲ እና ስነ ጽሁፍ የሚያሳይ ልምድ የሚቀሰምበት ድግስ በመድረክና በተለያዩ የዕይታ ቦታዎች ለታዳሚ ይቀርብበታል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የፊልም ፌስቲቫል ይካሄዳል። ፌስቲቫሉ ሀገራትን ማስተዋወቅ እና ማገናኘት! “Promoting and bridging the nations” በሚል ስያሜ ነው የሚካሄደው። የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ የሚያስተሳስሩ የባህል ትስስርን የሚያሳዩ ስለቀጠናው የሚናገሩ ታሪካዊ ፊልሞች ለዕይታ ይቀርባሉ።
የስዕልና ቅርጻ ቅርጽ ፌስቲቫል የሚካሄድ ሲሆን፣ የምስራቅ አፍሪካ ቀለም “East African Colors” በሚል ስያሜ የሚካሄድ ነው። የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ሰዓሊያን ስራቸውን በተለያየ የዕይታ ቦታዎች ለታዳሚ የሚያቀርቡበት ነው።
ባህልና ቀጠናዊ ትስስር
ዳይሬክተሩ እንደሚሉት፤ ባህልና ጥበባት ሰዎች እርስ በርስ በሚኖራቸው ግንኙነት እና ማኅበራዊ መስተጋብር ለዘመናት ያፈሯቸውን እሴቶች እና የአኗኗር ዘይቤዎች ለአካባቢያቸው እና ለሌሎች ህዝቦች የሚያጋሩበት እና የሚያስተዋውቁበት አንደኛው መሳሪያቸው ነው። በመሆኑም ባህልና ጥበባት ለሀገረ መንግስት ግንባታ እና ማህበራዊ ሀብት ክምችት (Social Capital development) ያላቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑ በተለያየ ጥናቶች የተረጋገጠ ነው። በመሆኑም ብዝሃ ባህል እና እሴቶች ለተጀመረው የሀገረ መንግስት ግንባታ ያላቸውን ሚና ለማጎልበት የጥበባትና ባህል ፌስቲቫሎችን ማዘጋጀት እና መሰል ሁነቶች በስፋት በማቀድ ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል። በተጨማሪም ጥበብ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት እንዲሁም ለህዝቦች ትስስር ገር ሀይል (soft power) በመሆኑ ይህንኑ ፀጋ በመጠበቅ፣ ማልማትና ጥቅም ላይ የሚውልበትን መንገድ መቀየስና ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል።
የክፍለ አህጉራዊ አደረጃጀቶች እና ኢንሼቲቮች ማህበረ ምጣኔ ሀብታዊ እድገትን ለማፋጠን በጎ አስተዋፅኦ እንዳላቸው ይታመናል። ይህንኑም ዳዊት አለምነህ (2007) Economic Integration in East Africa: The Case of Ethiopia and Kenya’ በሚል ርዕስ ባካሄዱት ጥናት በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት መካከል የሚኖር በቀጠናዊ የፀጥታ እና ደህንነት ጉዳዮች እንዲሁም የኢኮኖሚ መሰረቶች ማለትም በኃይል አቅርቦት፣ በመንገድ መሰረተ-ልማት እና ንግድ የሚኖር ግንኘነት ለቀጠናዊ ትስስር ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።
በተጨማሪም East African Outlook (2019) በአፍሪካ ልማት ባንክ ቡድን አዘጋጅነት “የቀጠናዊ ትስስር ፓለቲካል ኢኮኖሚ” በሚል ባወጣው ጽሁፍ እንደተመለከተው፤ የቀጠናው ሀገራት በንግድ፣ መንገድ እንዲሁም በቴሌኮም አገልግሎቶችና ኃይል አቅርቦት በመተሳሰር ለአጠቃላይ ዕድገት መጠቀም የሚችሉበትን ዕድል እንዳልተጠቀሙ አሀዛዊ መረጃዎችን ጭምር አስደግፎ ያትታል። በቀጣይም ሁለንተናዊ የመሰረተ- ልማት ትስስር እና ምጣኔ ሀብታዊ ፋይዳ ያላቸው የፖሊሲ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥና ተግባራዊ በማድረግ ተወዳዳሪና እድገት ያለው ምጣኔ ሀብት በቀጠናው መገንባት እንደሚገባ ምክረ-ሀሳብ አቅርቧል።
በሀገራት መካከል በጋራ ጥቅም ላይ የሚመሰረት የመሰረተ-ልማት ትስስርን ለማምጣት የሚደረግ ጥረት በህዝቦች መካከል በሚደረጉ የባህል እና ጥበባት ስራዎችና መድረኮች ቢታገዝ የበለጠ ውጤታማ ሊሆን ይቻላል። ይህንንም ከምስራቅ አፍሪካ ህዝቦች ቀደምት ታሪካዊ፣ ስነ-ምህዳራዊ ተመሳስሎና ተቀራራቢ ባህል አንጻር የህዝቦችን የጋራ ማንነት የሚያጎለብቱ የባህል ፌስቲቫሎች በማዘጋጀት ለቀጠናዊ ትስስር የሚውሉበትን ስልት በመቀየስ ለቀጠናው ዘላቂ ሰላምና ልማት እንዲውል መጠቀም ያስፈልጋል። የዲፕሎማሲ ተልዕኮን ወደ ተግባር በመቀየር የህዝቦችን ማህበራዊ ትስስር ለማጠናከር ባህል ወሳኝ ሚና ይጫወታል።
በተጨማሪም በሀገራችን መሰል ኩነቶች መዘጋጀታቸው በዘርፍ ተሻጋሪ ጉዳዮች ላይ የሚኖረው ሚና ከፍተኛ ለመሆኑ በርካታ ማሳያዎች ሊጠቀሱ ይችላሉ። የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም በሚወሰዱ የፖሊሲ አቅጣጫዎች፣ በተፈጥሮ ሀብት ስራዎች እና የተለያየ የቢዝነስ ተቋማት ከሀገራችን ውጪ በቀጠናው ሀገራት የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ ያላቸውን የገበያ ድርሻ እና ተሳትፎ በማጎልበት የምጣኔ ሀብትና የንግድ ትስስርን ለማጎልበት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።
የፌስቲቫሉ ለምስራቅ አፍሪካ ያለው ፋይዳ
እንደ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተሩ ገለፃ ፤ በኢትዮጵያና እና በምስራቅ አፍሪካ ደረጃ የጥበባት እና ባህል ፌስቲቫል መዘጋጀቱ ከአጭር ጊዜ አንጻር ማለትም እስከ አንድ ዓመት ባለ ጊዜ ውስጥ ማህበራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ እና ፖለቲካዊ ፋይዳ አንጻር ከፍተኛ አበርክቶ ይኖረዋል። በሀገራችን እና በቀጠናው ሀገራትና ህዝቦች መካከል በሚፈጠረው መስተጋብር በቀጠናው ህዝቦች መካከል እርስ በእርስ የበለጠ መቀራረብና መተማመንን በማጠናከር በሀገራችን እንዲሁም ጥበብና ባህልን በመጠቀም በምስራቅ አፍሪካ የሚስተዋለውን ወቅታዊ ፖለቲካዊ ሁኔታዎችን ለማሻሻል እና በጎ ያልሆኑ እይታዎች ለማለዘብ የሚረዱ የገጽታ ግንባታ ስራዎች ለመስራት ያስችላል።
“የመድረኩ መዘጋጀት በርካታ ማህበራዊ ፋይዳዎች አሉት የሚሉት አቶ አለማየሁ፤ ህዝቦችን ከማቀራረብና ከማስተሳሰር አንጻር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ይላሉ። በቀጠናው ያሉ ህዝቦች ካላቸው የመልከዓ ምድር፣ የባህል ፣ ቋንቋ እና የስነ ልቦና ተዛምዶ አንጻር ህዝቦች እርስ በርስ የበለጠ እንዲተዋወቁ፣ እንዲደናነቁ እና ግንዛቤ እንዲጨብጡ የሚያስችሉ ዝግጅቶች የሚቀርቡበት መሆኑን ይገልጻሉ። ይህም በጥበባትና የስፖርት ዝግጅቶች ደስታና ተዝናኖትን ከመፍጠር ባሻገር ውስጣዊ ግንኙነት ከማጠናከር አልፎ ነጻና አሳታፊ የባህል እና ጥበባት አቅርቦት እንዲኖር ያግዛል። በተጨማሪም ሲምፖዚየምና ልዩ ልዩ ዝግጅቶች፣ የተሞክሮ መለዋወጫ መድረኮች መኖራቸው ለተማሪዎች ፣ ተመራማሪዎች፣ ለትምህርት ተቋማት፣ ምርምርና ፈጠራ በማጎልበት ለዘርፉ ባለሙያዎች ዕውቀትና ተግባራዊ ልምድ በመፍጠር የአቅም ግንባታ ስራዎችን ለመስራት ያስችላል ብለዋል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ሰኔ 5 ቀን 2014 ዓ.ም