ደምቆ ከሚታየው ሰፈር ራመድ ብሎ ከጠባቧ ግቢ ጎራ የሚል ቢገኝ ድንገት ከህሊናው ሊላተም ፣ ከማንነቱ ሊጣላ ግድ ይለዋል:: በእርግጥ ለእንዲህ አይነቱ እውነት በተፈጥሮ የሚቸር ዕዝነ- ልቦና ያስፈልግ ይሆናል:: እንደኔ ግን ሰው ሆኖ መፈጠር ብቻውን ለስሜቱ መጋባት በቂ ነው እላለሁ ::
ስድስት ኪሎ አካባቢ ተገኝተናል:: በተለምዶ ምስካየ ኀዙናን መድኃኒዓለም ከሚባለው ሰፈር:: አስፓልቱን ሻገር ብለን እንደነገሩ መለስ ያለች የአንዲት ግቢ በርን ከፍተናል:: እንደው ለወጉ ‹‹ግቢ›› እንበለው እንጂ ቦታው ሁለት ሰዎችን ጎን ለጎን አያራምድም :: ስፍራው ለመንገዱ ግርግር የቀረበ ቢሆንም ግቢው በሚያስደንቅ ጭርታ ተውጧል::
የአስፓልቱን ሁካታ ለጀርባችን ትተን በቀጭኑ ሸለቋማ መንገድ ወደውስጥ አለፍን:: ዓይኖቻችን በቁልፍ የተዘጉ ጎስቋላ ቤቶችን እያስቃኙን ነው:: ግድግዳውን እየታከክን ፊትና ኋላ ተራመድን :: ብዙ አልራቅንም:: ከአንድ የተከፈተ ቤት ደጃፍ ስንደርስ ባለንበት ልንቆም ግድ ሆነ:: በሩን አልፈን ወደውስጥ ለመግባት እግራችን ተገታ :: መግቢያው በዋዛ ዘው የሚባልበት አልሆነም:: ለመራመድ የሚፈትነውን የዝቅታ ደፍ በጥንቃቄ ማለፍ ያስፈልጋል::
ሁኔታው እያስደነቀን ወደውስጥ ዘለቅን:: ጠባቧና ጽዱ ክፍል ቁልጭ ብላ ታየችን:: አራት ማዕዘኗን ቤት ለአፍታ ቃኘናት:: በአንደኛው ግድግዳ የእጅ መዳፍ የምታክል መስኮት ቢጤ ተለጥፎላታል:: ለንፋስ መሆኑ ነው:: ይህች ጎጆና ባለቤቷ ለዓመታት አብረው ዘልቀዋል::
ጠባቧ ቤት ጎን ከማሳረፍ የዘለለ ለአሳዳሪዋ ማብላት ማጠጣት ይሉትን ወግ አታውቀውም:: ከጣራዋ በታች ውላ ለምታድረው አንዲት ነፍስ ውሀን ሳትለግስ ፣ ረሀብ ጥማት ሳታስታግስ ዓመታትን ገፍታለች:: በእነዚህ ጊዜያት በትኩስ ዕንባ የታጀቡ የመከራ ቀናት ተቆጥረዋል:: መከራው ፍፃሜ አልባ እስኪመስልም ከዘንድሮ ደርሷል::
በዚህች ቤት አሁንም ፍላጎት፣ ከተፈጥሮ እየተጋጨ፣ ፍጡር በተፈጥሮ እየተፈተነ ውሎ አዳሩ ቀጥሏል :: ለመኖር፣ እስትንፋስን ለማርዘም ባለው ትግል ግብግቡ አልተቋጨም:: የዚህ ቤት ሕይወት ከሌሎች ሁሉ ይለያል:: የማይቻለውን ችላ ቀኗን የምትገፋው ሴት በቤቷ በልቶ የማደር ወግን አልታደለችም:: ከራሷና ከተፈጥሮ መጋጨት ግዴታዋ ሆኗል::
ከጣራው ስር በየቀኑ ለሚፈሰው ትኩስ ዕንባ፣ ግድ የሚለው የለም:: በየዕለቱ ስለሚራበው ሆድና በውሀ ጥም ስለሚደርቀው ጉሮሮም አንዳች የሚደነቅ አልተገኘም:: አዎ! በቤቱ ሁሌም የምግብ ሽታ ያውዳል:: እንደወጉ እሳት ነዶ፣ እንደ ራስ አቅም ወጥ እንጀራው ይዘጋጃል::
ይህን ያደረጉ እጆች ግን ቀን ለዚህች ነፍስ አጉርሰው፣ አጠጥተው አያውቁም:: እነሱ መብላት ላማረው ሆድ፣ ጥም ላሳረረው ጉሮሮ ሊሆኑ አልታደሉም:: ይህን እንሞክረው ቢሉ እነሱም ከተፈጥሮ ይጋጫሉ:: በቤቱ እህል ውሀ ከአፍ አይደርስም:: ተበልቶ፣ተጠጥቶ‹‹ተመስገን ማለት አይታወቅም:: በየቀኑ ከሞሰቡ የሚያፈጡ ፣ዓይኖች በእንክርት ውለው ያድራሉ:: አይደበቄው እውነት ለጎጇዋ ባለቤት የተፈረደ ይመስላል:: እሷ እንደሰው ወግ ባትሆን በትካዜ ተውጣለች:: በትኩስ ዕንባ ተሸፍናለች::
ተመልስን ወደውጭ እየወጣን ነው:: ከበሩ ማሬ ደሴ ትጠብቀናለች:: ቁጭ ብለን ከማውጋታችን በፊት ገጽታዋ በትኩስ ዕንባ ተቀበለን:: ‹‹አይዞሽ! ›› ብሎ ማጽናናቱ ቀላል አልነበረም:: ይህን ቃል ማሬ ምናልባትም ለዓመታት ሰምታው ይሆናል:: በየቀኑ እንዲህ መባሉ ለእሷ ብርቅ አይደለም:: የማያባራ ትኩስ ዕንባ፣ ከልብ የማይወጣ ሲቃና ብሶት መገለጫዋ ሆኗል::
አሁንም በጉንጮቸዋ እየወረደ በአንገቷ የሚንቆረቆረው ዕንባ አላባራም:: እንደምንም አረጋግተን ታሪኳን እንድትነግረን ጠየቅናት:: ሳግ እያነቃት፣ ልታወጋን ተዘጋጀች:: አልቻለችም:: በዓይኖቿ የሞላው ትኩስ ዕንባ ቀደማት:: አልከለከለችውም:: ከልጅነት ማንነቷ ከሚቀዳው እውነት፣ እየኖረችው እስካለው የመከራ ሕይወት ትተርክልን ያዘች::
ልጅነቴ ማርና ወተቴ…
በቀዬው የሚጫወቱት የሰፈር ልጆች ቡረቃ አልቀዘቀዘም:: እየሮጡ ይፈነድቃሉ ፣ እየጮሁ ይደሰታሉ:: በመንደሩ መሐል የቆመው የድንጋይ ቤት እንደወትሮው ልጆቹን ቁልቁል እያስተዋለ ነው :: በዕድሜ ጠገቡ የካብ ቤት ዙሪያ ሕፃናቱ ጨዋታቸው ቀጥሏል::
የአስራ ሁለት ዓመቷ ማሬ ዛሬም ጓደኞቿ መሐል ተገኝታለች:: ገና በሶስት ዓመቷ እናቷን ያጣችው ታዳጊ ብቸኝነት ይሰማታል:: እህት ወንድሞቿ ባልታወቀ ምክንያት ተከታትለው ሞተዋል:: አሁን ከአባቷ በቀር ‹‹የኔ›› ትለው የላትም:: ኃዘንተኛው አባት የመጨረሻ ልጃቸውን በመንደሩ ትተው ከአካባቢው ርቀዋል::
ልጆቹ እየቦረቁ ይዘላሉ ፣ይሮጣሉ:: አሁንም አንጋፋው የድንጋይ ቤት ከላይ ሆኖ ቁልቁል ያያቸዋል :: ቤቱ ድንገት ሸርተት እንደማለት ሞከረ :: ሁኔታውን ያስተዋለው የለም :: የዓመሉ መለወጥ ያልገባቸው ሕጻናት ጨዋታውን አላቆሙም:: አሁን የካቡ ቤት ያለ ይመስላል:: ለአፍታ ተንገዳግዶ በቁመናው ተዘረገፈ:: ድንጋይ በድንጋይ ተቀባብሎ ከመሬቱ ሲያርፍ በመንደሩ አስደንጋጭ ድምጽ አስተጋባ:: ስፍራው በአቧራ ጭስ ፣ተሸፍኖ :: የልጆቹ ድምጽ በከባድ ነውጥ ተዋጠ::
ድንገት የቤቱን መደርመስ ያስተዋሉ ጩኸታቸው በረከተ:: ከደቂቃዎች በፊት በርከት ያሉ ልጆች ቤቱ ስር ይጫወቱ ነበር:: ሁሉም በዓይኖቻቸው ፈለጓቸው:: ‹‹ተመስገን ›› አብዛኞቹ ከጉዳት ነጻ ሆነዋል:: እፎይታን ተቀባበሉ:: አፍታ አልቆዩም:: ማሬን አስታወሷት:: ከተረፉት መሐል አልታየችም:: ተደናግጠው ፍለጋቸውን ቀጠሉ:: አላጧትም:: ልጅቷ ከተደረመሰው ካብ ስር ትልቅ ድንጋይ ተጭኗት ወድቃለች::
ሁኔታውን ጠጋ ብለው አስተዋሉ:: ሰዎቹ ክፉኛ የተጎዳችውን ልጅ ደፍረው ሊያነሷት አልሞከሩም:: አባቷ ከሄዱበት እስኪመለሱ ጠበቁ :: አባት እየሮጡ ከመንደሩ ደረሱ:: በሰላም የተዋት ልጃቸው አይሆኑ ሆናለች:: እግሮቿ፣ ተላቀዋል:: ወገቧ ተሰብሯል:: ዓይኖቿን እንጨት ወግቷቸዋል፡፤እጆቿ እየሠሩ አይደለም::
አባት ፈጥነው የወደቀች የሙት ልጃቸውን አነሱ:: ዕለቱን ሕክምና ማድረስ አልሆነላቸውም:: የገጠር ሕይወት የሀገር ቤት ኑሮ ቢያግዳቸው ቀናትን ቆጠሩ:: አንድ ቀን የማሬ አጎት ከቤት ደርሰው ሕክምና ሊወስዷት ቆረጡ:: ጉዞ ወደ አዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሆነ ::
አዲስ አበባ..
ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የደረሰችው ማሬ ሕክምና አግኝታለች:: ዕለት በዕለት የሚከታተሏት ሐኪሞች ጉዳቷ የከፋ መሆኑን አውቀዋል:: ማሬ በከባድ ስቃይ ሕይወትን ቀጥላለች:: አሁን መላ አካሏ እያገዛት አይደለም:: እጇቿ አይታዘዙም :: የእግሮቿ ጉዳት ከፍቷል :: አንደኛው ዓይኗ ጠፍቶ አንዱ ስጋት ላይ ነው:: ብሶተኛዋ ታዳጊ ብቸኝነትን ከስቃይ መቀበል ይዛለች::
ሐኪሞቹ ለማሬ ትጋታቸውን ቀጥለዋል:: ድካማቸው ፍሬ የያዘ አይመስልም :: ለወራት በእጃቸው የቆየችው ጉዳተኛ ሁኔታ ተስፋ ያስቆርጣል:: ለእግሯ ብረት አስገብተው በክራንች ሞክረዋል :: የወገቧ ጥልቅ ጉዳት አካሏን ማንቀሳቀስ አልቻለም:: አሁን ማሬ ቆሞ የመሄድ ሕልሟ ከስሟል :: ይህን ተከትሎ የአባቷን ሞት መስማቷ ልቧን ክፉኛ ሰብሮታል::
ኑሮ በዘመድ ቤት…
ማሬ ከሆስፒታል ከወጣች በኋላ በዊልቸር ልትጠቀም ግድ ብሏል:: ቀጣዩን ሕክምናና ማረፊያ ያገዛት የማዘር ትሬዛ ማዕከል ለአንድ አመት ተንከባከባት:: ጥቂት ቆይቶ ግን ከድርጅቱ ተሰናበተች :: ማሬ አዲስ አበባ ‹‹የኔ›› የምትለው ሰው የለም:: ደግነቱ ዘመዶቿ ሊቀበሏት ወደዋል:: አሁን አንድ ዓይኗ ጠፍቷል:: ሙሉ አካሏ ከእሷ አይደለም:: እንደልብ መውጣት መግባት አይሆንላትም:: ትናንት ስትሮጥ እንዳልነበር ዛሬ ከሰው እጅ ወድቃለች:: ይህን ችግር ይዛ ሌሎችን ማስቸገርና መቸገሩ በእጅጉ ይከብዳል:: ምርጫ አልነበራትም:: የዘመድ ቤትን ኑሮን ሳትወድ ተቀበለች::
ዘመዶቿ ብዙ ቤተሰብ አላቸው:: ልጆች ለማሳደግ ኑሮን ለማሸነፍ ይሮጣሉ:: ይህን የምታየው ማሬ በእንግድነቷ ተጨነቀች:: ያለሥራ፣ የልጆቹን እንጀራ መካፈሉ አሳቀቃት:: ሁሉም በእሷ የተማረሩ፣ የሰለቹ መሰላት:: ውሎ አድሮ ፍራቻዋ እውነት ሆነ:: ዘመዶቿ አፍ አውጥተው እሷን መያዝ፣ማኖር እንደማይችሉ ነገሯት:: ተምራ መለወጥ ለምትሻው ታዳጊ ውሳኔያቸው ከባድ መርዶ ሆነ::
ማሬ ግራ ገብቷታል:: ሀገር ቤት የምትመለስበት አንዳች ተስፋ የለም :: የዘመዶቿ ድንገቴ ውሳኔ እያስጨነቃት ነው:: አንድ ቀን ግን በአክስቷ ባል ጥረት የኑሮ መንገዷ ተቀየረ:: ተስፋ የዓይነስራውንና የአካልጉዳተኞቸ ማዕከልን በሥራ ተቀላቀለች:: ይህ መሆኑ ብቻ የማሬን ችግር አልፈታም:: አሁንም ቋሚ የመኖሪያ ቤት አላገኘችም::
ችግሯን የተረዱ አሠሪዎች በአንዲት ሻይ ቤት እንድታድር ፈቀዱላት:: ማሬ ማረፊያ ስታገኝ ፈጣሪን አመሰገነች:: እንዲህ መሆኑ ሌሎችን አላስደሰተም:: በድርጅቱ የሚሠሩ አንዳንዶች እገዛውን ከጥቅም ቆጥረው ተቃወሙ:: የማሬ ሕይወት ዳግም ከችግር ወደቀ:: በድንገት መጠጊያዋን እንድትለቅ ተወስኖ ከስፍራው ተባረረች::
ማሬ ግራ ተጋባች:: አሁን የቀድሞ ዘመዷቿን ከመለመን ውጭ ምርጫ አላገኘችም:: ሽሮሜዳን አልፋ አቀበቱን ወጣች:: ከግቢው ደርሳ ችግሯን አዋየች:: ዘመዶቿ ደግመው አልሰሟትም:: ወደመጣችበት እንድትመለስ ቁርጡን ነገሯት:: ባይተዋሯ ማሬ ሳግ እያነቃት ከግቢው ራቀች:: አሁን ተስፋዋ ተሟጧል:: ትሄድበት ትጠጋበት ጥግ የላትም:: ሆድ ብሷታል፣ ዕንባዋ በጉንጭ በአንገቷ ይወርዳል::
ማሬ ዊልቸሯን እየገፋች ከአንድ ፖሊስ ጣቢያ ደረሰች:: ታሪኳን ዘርዝራም እንደ ወንጀለኛ እጇን ሰጠች:: ችግሯን የተረዱ ኃላፊዎች ከበሩ ጥግ እንድታድር ፈቀዱላት:: ሕይወት ከፖሊስ ጣቢያ ደጃፍ ቀጠለ:: የዛሬን እንጂ የነገን የማታውቀው ማሬ የእለቱን እያመሰገነች ተኝታ ተነሳች:: የእንክርት ሕይወትን ለመደች:: አንድ ቀን ግን ከአንድ የሕግ ባለሙያ የሰማችው ምክር ከልቧ ገባ:: እሱ ያላትን ልትፈጽም ከራሷ ተስማማች::
በከንቲባው ፊት…
ማሬ በእጇ ያለውን ማመልከቻ ይዛ ወደ አዲስ አበባ አስተዳደር ቀረበች:: አጋጣሚ ሆኖ ደጅ አልጠናችም:: ከሚመለከተው ሰው በግንባር ተገናኘች :: በወቅቱ የከተማዋ ከንቲባ ኩማ ደመቅሳ ነበሩ:: ከንቲባ ኩማ ታሪኳን በወጉ አደመጡ፣ ችግሯን ከልብ ተረዱ:: ኃዘኗ ኃዘናቸው ሆነ:: አልዘገዩም:: ለማሬ አካል ጉዳት የሚመጥን ምቹ የቀበሌ ቤት እንዲሰጥ አስቸኳይ ትዕዛዝ አሳለፉ::
የጉለሌ ክፍለ ከተማና የሚመለከታቸው ሁሉ ለከንቲባው ትዕዛዝ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ሲተጉ ከረሙ:: ዊልቸር በወጉ የሚያስገባ፣ አመቺ መጸዳጃ ያለው ምቹ ቤት መኖሩ ተረጋገጠ:: ቤቱን ለማስረከብ በዕለተ ዓርብ ቀጠሮ ተይዞም ማሬ ተጠራች:: ፡ በተባለው ቀን ስፍራው ስትደርሰ አስረካቢዎቹ ቤቱን አሳይተው ‹‹እንኳን ደስ አለሽ›› አሏት::
እንደተባለው ቤቱ ለአካል ጉዳተኛ የሚመጥን፣ ለዊልቸር ጉዞ የሚያመች ነው:: ማሬ በደስታ ፈጣሪዋን አመሰገነች:: ቃል አክባሪ አስረካቢዎቿን ደጋግማ መረቀች:: ውል ለማሰር ለሰኞ ተቀጥራም ከግቢው ራቀች::
የነበረው እንዳልነበረ…
ለማሬ ዕለተ ሰኞ ሲያዘግም ደርሷል:: ይህ ቀን ለእሷ ከሌሎች ዕለታት የተለየ ሆኗል:: ቀጠሮዋን አክብራ የደረሰችው የቤት ባለቤት የሰዎቹን መምጣት እየጠበቀች ነው:: ቁልፉ ከእጇ ገብቷል:: የቀራት ቢኖር የውል ስምምነት ብቻ ነው::
ድንገት አጠገቧ የደረሰው አስረካቢ ገጽታው እንደቀድሞ አልሆነም:: ዓርብ ዕለት የሰጣት ቤት በስህተት መሆኑን ደጋግሞ እየነገራት ነው:: ቤቱ ለእሷ እንደማይገባ ያሳወቃት ሰው ይመጥናቸዋል ያላቸውን ተረካቢዎች አቅርቦ ቁልፉን ከእጇ ነጥቋል:: ማሬ በሁኔታው ደንግጣ መፍትሔ ጠየቀች :: ኃላፊ ተብዬው ለእሷ የምትመጥነውን ትንሽዬ ቤት እየጠቆመ ከዚህ በኋላ ዳግም እንዳትጠይቀው በቁጣ አስጠነቀቃት::
ማሬ የነበረው እንዳልነበረ መሆኑ ገብቷታል:: ዳግመኛ ቃል የማውጣት አቅም የላትም:: የተባለውን ቤት ለመረከብ ከስፍራው ደርሳ ከመንገድ ቆማለች:: በሩ ላይ ያለው የእንጨት ድልድይ ወደግቢው ለመግባት አያመችም:: ይህን ያዩ ልበ መልካሞች ከነዊልቸሯ ተሸክመው ከቤቷ ደጃፍ አድርሰዋታል::
ቀጭኑን ጭቃማ መንገድ በመከራ አልፋ ከጠባቧ ጎጆ የደረሰችው ማሬ በጭንቀት ተውጣለች:: ለእሷ ይበጃል የተባለው ቤት በእጅጉ ሆድ ያስብሳል:: የበሩ መግቢያ ገደል ነው:: በግቢው መብራት ፣ ውሀና መጸዳጃ የለም:: እንደምንም ከቤት ተንሸራታ ገባች:: በዋዛ መውጣት ሳትችልም ቀናትን በረሀብና ጥማት ገፋች:: ቀበሌ በምልልስ ደጅ ጠናች:: ስለቤቱ ተስፋ ተነፈጋት:: ‹‹ጆሮ ዳባ ልበስ›› ያሉት ኃላፊዎች እየተቀያየሩ ፊት ነሷት፣ ጀርባ አዙሩባት::
ዓመታትን በዕንባ…
እነሆ ማሬ ‹‹ላንቺ ይሁን›› በተባለው ቤት ኑሮን በሰቀቀን መግፋት ይዛለች:: በዚህ ቤት ያበሰለችውን መጉረስ ፣ የቀዳችውን መጠጣት አልተፈቀደላትም:: ከስራ መልስ ጎጆዋ ከገባች ተጠቅልላ ከመተኛት የዘለለ ምርጫ የላትም:: የጎረቤት ምግብ ቢሸታት፣ለአውደ ዓመት ጥሪ ቢደርሳት አንዲት ስኒ ቡና ፉት አትልም:: በቤቷ ካለው፣ ልቅመስ፣ ልጎንጭ ካለችም መፈጠሯን ትጠላለች፣ ከተፈጥሮ ትጋጫለች::
ማሬ ሁሌም በእጇ ያለውን እያየች ትራባለች፣ ትጠማለች:: ጠጥታ፣ላለመሽናት፣ በልታ ላለመጸዳዳት የወሰደችው ብቸኛ ርምጃ በረሀብ እየተሰቃዩ ፣በውሀ ጥም ማረር ሆኗል:: ከቤት ሆና ድንገት ሆዷ ቢንጓጓ ቀጥሎ የሚሆነውን እያሰበች ትጨነቃለች:: እንደሴት ልጅ ወግ ብዙ ያስፈልጋታል:: በቤቷ ገላዋን ብትታጠብ፣ ልብሷን ብታጥብ ትወዳለች:: ይህን ልሞክር ካለች ግን ችግሩ ይብሳል:: አንድም የአቅም ጉዳይ፣ ሌላም ወሀውን ትደፋበት ቦታ አታገኝም::
ማሬ ውላ ከምትገባበት፣ እንጀራ ቦታዋ ጉዳይዋን ጨርሳ ፣ከቤት ትደርሳለች:: የዓርብ ስንቋ እስከ ሰኞ ያዘልቃታል:: እህል ባፏ የሚዞረው ሥራ ስትገባ ነው:: በዚህ ስፍራ መጸዳጃ ታገኛለች :: እንደወጉ ትሆናለች:: ቤት የምትውልባቸው ቀናት ለዚህች ሴት የፈተና መሰላሎች ናቸው:: እየራባት የማትበላባቸው፣ እየጠማት የማትጠጣባቸው አስከፊ ቀናት:: ማሬ ከሁሉም በዘመነ ኮረና ያሳለፈችውን የጨለማ ጊዜ አትረሳም:: የዛኔ መሥሪያ ቤቷ በመዘጋቱ ከቤት የምትወጣበት ምክንያት አልነበረም:: በወቅቱ በረሀብ ተቆራምዳለች፣ጥቂት ብዙ ዋጋ ከፍላለች:: ለእሷ አሁንም ያለችበት ቤት የመቃብር ያህል ነው:: ያለሕይወት የሚጋደሙበት፣ያለተስፋ የሚያድሩበት የጨለማ ኑሮ ::
ኧረ ! መላ ምቱ…
ወዳጆቼ! ‹‹ኑሮ ካሉት›› እንዲሉ ሆኖ ከጣራው ሥር ሕይወት እንዲህ እየተኖረ ነው:: ቤት ብቻውን ትርጉም የለውም:: ፍቺው የሚታወቀው ገበናን ሸፍኖ በወጉ በልተው፣ጠጥተው ሲያድሩበት፣ ጭምር ነው:: አሁን ለዚህች የተጨነቀች ነፍስ አስቸኳይ መላ ያሻል:: ይህ ይሆን ዘንድ የመልካም ሰዎች ልብ፣ የቀበሌው አመራር ነን ባዮች ይሁንታ ያስፈልጋል:: ወገን ባለበት፣መንግሥት በቆመበት ሀገር ይህ መሰሉ ታሪክ ሊሰማ አይገባም :: በሮች ይንኳኩ ፣ዕንባዎች ይታበሱ::
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሰኔ 4 /2014