የመንገድ መሰረተ ልማት እንደ ስሙ ለሁሉም ልማቶች መሰረት የሆነ ዘርፍ ነው:: ድህነትን ለመቀነስ፣ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ለማምጣት እንዲሁም ማህበራዊ አገልግሎቶችን ለማስፋፋትና ህዝቡን ተደራሽ ለማድረግ የመንገድ መሰረተ ልማት እጅግ አስፈላጊ ነው:: ከተሞችን ከምርት አካባቢዎች፣ የግብርና አካባቢዎችን ደግሞ ከገበያ ስፍራዎች ጋር በማገናኘት የአርሶ አደሩንም ሆነ የከተማ ነዋሪውን የጋራ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መንገድ ወሳኝ ነው:: ይህ ዘርፍ ለሁሉም ዘርፎች መሰረት እንደመሆኑ ዘርፉን ለማልማት ከፍተኛ ሀብት ይፈልጋል::
ለዚህም ነው ኢትዮጵያ ለዚህ ዘርፍ ከፍተኛ ሀብት በመመደብ የመንገድ መሰረተ ልማትን ለማስፋፋት በትኩረት ስትሰራ ነው የቆየችው:: ባለፉት ጥቂት አስርት ዓመታት ውስጥ በዘርፉ በተከናወኑ ስራዎች የሀገሪቱን የመንገድ ሽፋን በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደግ ተችሏል::
የመንገድ ልማቱ ግን ብዙ ፈተናዎችን አልፎ ነው ለአገልግሎት ሲበቃ የሚታየው:: ከመንገድ ግንባታ ጋር ተያይዞ በርካታ ችግሮችም ይነሱ ነበር፤ አሁንም እየተነሱ ናቸው:: ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ ባሉት ዓመታት በዘርፉ የታዩ ጥንካሬዎችን ለማስቀጠል እና ድክመቶችን ለማረም ርብርብ ሲደረግ ቆይቷል፤ የተጓተቱ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት ለማጠናቀቅ ተሰርቷል፤ ይሁንና ዛሬም ልማቱን እያጓተቱ የሚገኙ ችግሮች ይስተዋላሉ::
የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴርን የ2014 በጀት ዓመት የ10 ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ከትናንት በስቲያ ባዳመጠበት ወቅት ከምክር ቤቱ አባላት በርካታ ጥያቄዎች እና ማብራሪያዎች ከተጠየቀባቸው እና ምላሽና ማብራሪያ ከተሰጠባቸው ንዑስ ዘርፎች አንዱ የመንገድ መሰረተ ልማት ነው::
የሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸውን እና የተጠሪ ተቋማትን የአፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ባለፉት 10 ወራት በብዙ ችግሮች ውስጥ ሆኖም አመርቂ ውጤት አስመዝግቧል:: በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ለ2014 በጀት ዓመት የተያዙ የፊስካል ስራዎች 1 ሺህ 265 ኪሎ ሜትር ነባር መንገዶችን ለማጠናከር፣ የነባር መንገዶች ደረጃን ለማሻሻል፣ የአዲስ መንገዶች ግንባታን ለማከናወን፣ የፍጥነት መንገድ ግንባታን ለማካሄድ ታቅዶ 935 ኪሎ ሜትር መፈጸም ተችሏል:: ይህም እቅዱ 74 በመቶ ነው::
በሌላ በኩል 326 ኪሎ ሜትር መንገዶች ላይ ከባድ ጥገና ለማከናወን ታቅዶ 155 ኪሎ ሜትር ማከናወን መቻሉን ሚኒስትሯ ጠቅሰዋል:: ይህም ከተያዘው እቅድ 46 በመቶ ብቻ ነው:: በዚህ ዘርፍ የተመዘገበው አነስተኛ ነው:: ከአምናው አንጻር ሲታይም 11 በመቶ ቅናሽ ታይቷል:: ለዚህም ቅናሽ የኮምቦልቻና የነቀምት ዲስትሪክቶች ጥገና በግጭት ምክንያት መስተጓጎላቸው አፈጻጸሙ አነስተኛ እንዲሆን ማድረጉ ነው ተብሏል::
የ659 ኪሎ ሜትር ወቅታዊ መንገዶች ጥገና ለማከናወን ታቅዶ 523 ኪሎ ሜትር 79 በመቶ መከናወኑን የጠቀሱት ሚኒስትሯ፤ በዚህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጻር የ27 በመቶ ብልጫ መታየቱን ተናግረዋል:: በተጨማሪም የ8255 ኪሎ ሜትር መደበኛ ጥገና ለመስራት ታቅዶ 7204 ኪሎ ሜትር ጥገና መካሄዱን አስታውቀዋል:: በአጠቃላይ በመንገድ ግንባታና ጥገና የተመዘገበው አማካይ አፈጻጸም 84 በመቶ መሆኑን ነው ያመለከቱት::
ሚኒስትሯ ሪፖርቱን ለምክር ቤቱ ካቀረቡ በኋላ ከምክር ቤቱ አባላት በርካታ ጥያቄዎች እና ማብራሪያዎች ተነስተዋል:: ከአባላቱ ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል የመንገድ ፕሮጀክቶች ጥራታቸው በተጠበቀ መንገድ እንዲገነቡ ምን ያህል ጥንቃቄ እየተደረገ ነው? የሚለው ይገኝበታል:: ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ወጥቶ የሚገነቡ መንገዶች ከመሬት መንሸራተት፣ ከአፈር መደርመስ እንዲሁም የመንገድ ግንባታ ግብዓችን አይነት እና ባህሪይ ካለማጥናት የተነሳ ለብልሽት ሲዳረጉ ይስታዋላል:: ስለሆነም ሀገሪቱ ባላት ውስን ሀብት የምትገነባቸው የመንገድ መሰረተ ልማቶች ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሁም ለረጅም ጊዜ እንዲያገለግሉ የዘርፉን ውጤታማነት ለማሻሻል የተከናወኑ ሳይነሳዊ የምርምር ስራዎች እንዲሁም ስታንደርዳይዜሽን እና የቁጥጥር ስራዎች ምንድን ናቸው? የሚል ጥያቄ ተነስቷል::
በተጨማሪም የመንገድ መሰረተ ልማቶች በሚሰራባቸው አካባቢዎች ለሚካሄዱ የንብረት ግመታ፣ ካሳ ክፊያና ወሰን ማስከበር ችግሮች በወቅቱ መፍታት ባለመቻሉ የተጀመሩ የመንገድ ግንባታዎች በተያዘላቸው ጊዜና ጥራት እንዳይጠናቀቁ ማነቆ ከመሆኑም ባሻገር ለመንገድ ግንባታ ከሚውለው ወጪ ጋር ተቀራራቢ የሆነ ሀብት ለካሳ ክፊያ እየወጣ ነው:: ይህን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በክልሎች እና በከተማ አስተዳደሮች በባለቤትነት እንዲሰሩ ከማብቃት፣ ከመደገፍና የአሰራር እና የህግ ስርዓት አዘጋጅቶች ከማሳተፍ አንጻር ምን ተሰራ? በህግ ማስከበርና በጻጥታ ችግሮች ምክንያት የተቋረጡ የመንገድ ፕሮጀክቶችን ወደ ስራ በማስገባት ረገድ ጦርነቱ በአንጻራዊነት ከቆመ በኋላ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያከናወናቸው ተግባራት ካሉ ቢገለጹ? የሚሉ ጥያቄዎችም ቀርበዋል:: አማካሪዎች፣እያስተዳደሯቸውእና እየተቆጣጠሯቸው ያሉትን ፕሮጀክቶች አስመልክቶ ለሚነሱ ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ መስጠት፣ የተስተካከለና ትክክለኛ መረጃ አለመላክ፣ የሚልኳቸው ሰነዶችም ቢሆኑ የጥራት ጉድለት የሚስታዋልባቸው መሆን፣ የተሟላ ዲዛይን አለማቅረብና የዲዛይን መቀያየር ይንጸባረቃል:: ስለሆነም በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የአማካሪ ድርጅቶች በሙያዊ ስነምግባርና ተጠያቂነት መንፈስ ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ ምን የህግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቷል? በመንገድ ዘርፍ በ2014 በጀት ዓመት ከታቀደው እቅድ ውስጥ በአስር ወር ውስጥ የፊስካል ስራዎች በአማካይ 79 በመቶ ማሳካት እንደተቻለ ሪፖርቱ ያመላክታል:: ይሁን እንጂ በሁሉም በሀገሪቱ አካባቢዎች የመንገድ መሰረተ ልማት ሽፋን ከህዝብ ፍላጎት አንጻር ተደራሽ ለማድረግ ምን እየተሰራ ነው:: በተጨማሪም ታቅዶና በጀት ተይዞላቸው ወደ ስራ ያልገቡ የመንገድ ፕሮጀክቶች ምክንያት ምንድን ነው የሚሉና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎች ተነስተዋል::
ለተነሱት ጥያቄዎች የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ፤ የወሰን ማስከበር ችግር የመንገድ ግንባታ ዘርፍ ዋነኛው ማነቆ ሆኖ መቆየቱን አስገንዝበዋል:: በዋናነት የገንዘብ ፍሰት ችግር አንዱ ማነቆ መሆኑንም ጠቅሰው፣ በርካታ የወሰን ማስከበር ችግር ያጋጠማቸው ፕሮጀክቶች አሁንም እንዳሉ አስታውቀዋል:: ካለባቸው ወሰን ማስከበር ችግር አንጻር ግንባታቸው መቆም የነበረባቸው የመንገድ ፕሮጀክቶች ቢኖሩም ከነችግራቸውም ቢሆን ፕሮጀክቶችን ላለማቆም ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል::
እንደ ኢንጂነር ሀብታሙ ማብራሪያ፤ በትክክል የካሳ ተመን ተገምቶ ያልተከፈላቸው በርካታ ባለመብቶች አሉ:: ይህም የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኗል:: ከፍተኛ ሀገራዊ ችግር ውስጥ ተሁኖ ልማቱ እየተሰራ መሆኑን ህዝቡም ይገነዘባል::
የመንገድ ፕሮጀክት የፌዴራል መንግስት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ቢሆንም ባሉ ፕሮጀክቶች ልክ የገንዘብ ፍሰት የለም፤ የገንዘብ እጥረት አለ ያሉት ኢንጂነር ሀብታሙ፣ ለወሰን ማስከበር አንዱ ችግር ይህ የገንዘብ እጥረት መሆኑን አስታውቀዋል:: የሚጠየቀውን ከፍተኛ የካሳ ግምት መክፈል ለአስተዳደሩ አዳጋች እንደመሆነም ተናግረው፣ ሁሉም አካል ይህን አውቆ ልማቱ እንዳይቆም ሊተባበር ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል:: አንዳንድ ጊዜ ፍትሃዊ ያልሆኑ ካሳዎች ሲጠየቁ ይስተዋላል:: ይህ ሁኔታ ካልተቀየረ የፌዴራል የመንገድ ፕሮጀክቶችን ለማስቀጠል አዳጋች መሆኑንም ነው ኢንጂነር ሃብታሙ ያስገነዘቡት::
ክልሎች በሚያስገነቧቸው የመንገድ ፕሮጀክቶች ላይ መሰል ችግሮች ብዙውን ጊዜ ሲያጋጥም እንደማይታይ የጠቆሙት ኢንጂነር ሃብታሙ፣ የፌዴራል መንግስት ፕሮጀክቶችን ውጫዊ አካል ፕሮጀክቶች አድርጎ የማየት አዝማሚያዎች በመኖራቸው ችግሩ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል ይላሉ:: ወደፊት መሰል ችግር እንዳያጋጥም የወሰን ማስከበር ስራዎች በሚሰሩበት ወቅት የፌዴራል መንግስት ከክልሎች መንግስታት ጋር በቅንጅት ለመስራት የሚያስችል የአሰራር ማስተካከያ እና ማሻሻያ መኖር አለበት:: የባለድርሻ አካልት ትብብር የሚያስፈልግ ጉዳይ ነውም ብለዋል::
እንደ ኢንጂነር ሃብታሙ ማብራሪያ፤ የጸጥታ ችግሮች ባሉባቸው እና ዝናብ በብዛት በሚጥልባቸው አካባቢዎች ግንባታ ለማከናወን ፍላጎትና አቅም ያላቸው ተቋራጮች እየተገኙ አለመሆኑንም ተናግረዋል:: ይህም ችግር በአንዳንድ አካባቢዎች የሚገኙ ፕሮጀክቶች ግንባታ እንዳይፋጠን እንቅፋት እንደሆነም አስታውቀዋል::
‹‹ብዙ ስራ እና ብዙ ፕሮጀክቶች አሉ:: ከዚህ ቀደም ከተገነባው በላይ የአስፋልት መንገድ ስራ እየተሰራ ነው:: ነገር ግን በተለያዩ ችግሮች ምክንያት በቂ ተቋራጭ እየተገኘ አይደለም ሲሉም ተናግረዋል::
ሀገር ውስጥ ያሉ ተቋጮች ቁጥር እና አቅም ማነስ አንዱ ችግር ኢንጂነር ሀብታሙ ጠቅሰው፣ በሀገር ውስጥ የሚስታዋለው አለመረጋጋት የውጭ ሀገራት ተቋራጮች በብዛት ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይመጡ ተጽዕኖ እየፈጠረ መሆኑንም ጠቁመዋል:: በዚህ ምክንያት መጀመር የነበረባቸው በርካታ ፕሮጀክቶች ሳይጀመሩ መቆየታቸውን ኢንጂነር ሃብታሙ አንስተዋል::
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ጫልቱ ሰኒ በበኩላቸው በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ፤ በሀገሪቱ የተከሰተው የጸጥታ ችግር በብዙ የመንገድ ፕሮጀክቶች ላይ ከፍተኛ ውድመት ማድረሱን ጠቅሰው፣ ብዙ ማሽነሪዎች መዘረፋቸውንም አስታውቀዋል:: እነዚህን ማሽነሪዎች በግዥ እንተካ ቢባል ብዙ ጊዜ ሊፈጅ ይችላል ያሉት ሚኒስትሯ፣ ይህ ሁሉ የፕሮጀክቶች አፈጻጸም እንዲጓተት የሚያደርግ ነው ብለዋል:: አንዳንድ መጠነኛ ጉዳት በደረሰባቸው እና በአንጻራዊነት ሰላማዊ በሆኑ አካባቢዎች ከተለያዩ ፕሮጀክቶች ማሽነሪዎችን በማንቀሳቀስ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል::
ሚኒስትሯ እንዳሉት፤ የመንገዶች አስተዳደር በመንገዶች ቁጥጥርና ክትትል ዙሪያ የሚሰራቸውን ስራዎች ውጤታማነት ከፍ ለማድረግ ያልተማከለ አሰራር ዘርግቷል:: መንገዶች አስተዳደር ከዚህ ቀደም ከ200 በላይ የሚሆኑ ፕሮጀክቶችን ከማዕከል ነበር ክትትልና ቁጥጥር ሲያደርግ የነበረው:: ይህ በራሱ የአፈጻጸም ሂደቱን ያዘገየዋል:: የጥራቱን ክትትል እና ቁጥጥር አንዲደናቀፍ የራሱን ሚና ይጫወታል:: ይህንን ችግር ለመቅረፍ በእያንዳንዱ ዲስትሪክት የራሱን ፕሮጀክት ኦፊስ ማደራጀት ተችሏል:: እስከ ቀበሌ ያለውን የፌዴራል መንገድ ከአንድ ማዕከል ማስተዳደር ችግር ስለሚሆን ስትራቴጂክ በሆነ መንገድ የፕሮጀክት ጽህፈት ቤቶችን በማደራጀት ክትትል እና ቁጥጥር በቅርበት እንዲደረግ ትልልቅ ስራዎች ተሰርተዋል::
ከመንገዶች ጥራት ጋር ተያይዞ፤ የግንባታ ጥራት ሳይረጋገጥ የሚሰሩ ስራዎች፣ የሶስተኛ ወገን ማረጋገጥ የማይችልባቸው አሰራሮች የጥራት ችግር እንዲፈጠር ምክንያት እንደሚሆኑ ተናግረው፣ ይህን ችግር ለመፍታትም በአፍሪካ ደረጃ ሊጠቀስ የሚችል የምርምር ማዕከል ግንባታ ለማካሄድ ዝግጅቱ መጠናቀቁን አስታውቀዋል:: ማዕከሉ ለአብነት ያህል የግንባታ ግብዓቶችን መርምሮ ደረጃቸው ምን ይመስላል የሚለውን መለየት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል:: ግብዓቱ ከደረጃ በታች ነው ወይስ ደረጃውን ያሟላል የሚለውን የሚያረጋግጥ ይሆናል:: የመጣው ግብዓት ከደረጃ በታች ከሆነ ጥቅም ላይ እንዳይውል ይደረጋል ብለዋል::
እንደ ሚኒስትሯ ወይዘሮ ጫልቱ ማብራሪያ፤ የካሳ ክፊያ ለመንገዶች ግንባታ መዘግየት ዋነኛው መንስኤ እየሆነ ከመሆኑም ባሻገር በፌዴራል መንግስቱ ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ ነው:: ለካሳ ክፊያ ከ10 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ እየተደረገ ነው:: ካሳዎቹ ተገቢ ናቸው ወይ የሚለው ያጠያይቃል::
አንዳንዶች የካሳ ክፊያ ተገቢ ስለሆነ ጥያቄ ሲያነሱ፤ በሌላ በኩል በማይገባው መንገድ የፖለቲካ ቅርጽ በማስያዝ ለሌላ ዓላማ የሚጠቀምበትም አካል አለ ያሉት ሚኒስትሯ፣ ይህንን በየፈርጁ ማየት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል:: የፌዴራል መንግስት መንገድ በዚህ አቅጣጫ ያልፋል ከተባለ በአንድ ሌሊት ጎጆ የሚቀለስበት እና ካሳ የሚጠየቅበት ሁኔታ እንዳለም ጠቅሰዋል::
እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፤ የፌዴራል መንግስት ፕሮጀክቶችን በሌላ ሀገር መንግስት እንደሚገነባ ፕሮጀክት የማየት አዝማሚያ አለ:: አላግባብ ግምት ይጠየቃል:: እንዲህ አይነቶቹ ችግሮች ከከሳ አዋጁ ጋር የሚያያዙ በመሆናቸው የፌዴራል ፕሮጀክቶች የሚባሉት በቀጥታ ወደ ክልሎች እንዲወርዱ በማድረግ የህዝብ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ መንገድ መቀጠል ያስፈልጋል::
የመንገድ ፖሊሲ ማሻሻያ ማድረግ ስለሚያስፈልግ የመንገድ ፖሊሲ በማስጸደቅ ሂደት ላይ ነው:: ይህ ፖሊሲ የፌዴራል መንግስት ክልልን ከክልል፣ ሀገርን ከሀገር ጋር የሚያገናኙ መንገዶች ላይ ትኩረት እንዲያደርግ እንዲሁም ክልሎች ደግሞ ዞንን ከክልል፣ ዞንን ከወረዳ የሚያገናኙ መንገዶች ላይ ትኩረት እንዲያደርግ ይሰራል:: ይህም በአሁኑ ወቅት ከወሰን ማስከበር እና ከካሳ ክፊያ ጋር ተያይዘው የሚነሱ ችግሮችን ለመቅረፍ እንደሚያስችል ሚኒስትሯ ጠቁመዋል:: ፖሊሲው የባለቤትነት ስሜት እንዲኖር እንደሚረዳ ተናግረው፣ በእያንዳንዱ ፕሮጀክት አፈጻጸም ላይ የራሱ የሆነ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም አስታውቀዋል፤ የጥራት እና የመዘግየት ችግሮችን ይፈታል ይላሉ::
በተለያዩ ምክንያቶች የቆሙ የመንገድ ፕሮጀክቶችን ለማስቀጠል 9 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ዳግም መለቀቁን የጠቆሙት ሚኒስትሯ፣ መንግስት ይህን እርምጃ የወሰደው ፕሮጀክቶቹ በአስቸኳይ ማለቅ ያለባቸው በመሆናቸው ነው ብለዋል:: ለፕሮጀክቶቹ ዳግም ፈንድ መለቀቁ ሌሎች ፕሮጀክቶችን የሚገነቡ ተቋራጮች የዋጋ ማሻሻያ ይደረግልናል በሚል ስራዎችን እንዳያጓትቱ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ብለዋል::
የመሰረተ ልማትና ኮንስትራክሽን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ፤ በመጨረሻ የመንገድ ዘርፍን አስመልክተው በሰጡት ማጠቃለያ የመንገዶች አስተዳደር ከነበረው ሁኔታ አንጻር ሲታይ ፊስካል አፈጻጸሙ ጥሩ መሆኑን ጠቁመው፣ በርካታ ተስፋ ሰጪ የሪፎርም ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን በመስክ ምልከታ መታዘብ መቻሉንም አስታውቀዋል:: የተጀመሩ መልካም ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ያስገነዘቡት ሰብሳቢዋ፤ ከዚህ ጎን ለጎን በምክር ቤቱ በጀት ተይዞ እና ታቅዶ ወደ ስራ ያልተገቡ የመንገድ ፕሮጀክቶች፤ ከካሳ ክፊያ እና ወሰን ማስከበር በመሳሰሉ በተለያዩ መሰል ችግሮች ምክያቶች የቆሙ ፕሮጀክቶች በልዩ ሁኔታ ትኩረት ተሰጥቶ ከሚመለከታቸው ክልሎችና ከስራ ሀላፊዎች ጋር በመቀናጀት ፈጣን ምላሽ መሰጠት እንዳለበት አስገንዝበዋል::
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ሰኔ 4 /2014