የማስታወቂያ ሥራዎች አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በክልል ከተሞች ሳይቀር የከተሞችን ገጽታ በማበላሸት እንዲሁም በማቆሸሽ ስማቸው በእጅጉ ይነሳል:: ማስታወቂያዎቹ ወቅት ሲያልፍባቸው የሚያስወግዳቸው ካለመኖሩና በሥርዓት የሚመሩ ካለመሆናቸው ጋር ተያይዞ ከትንሹ ማስታወቂያ አንስቶ እስከ ትላልቆቹ ቢልቦርዶች ድረስ የከተሞች ችግሮች መሆናቸው አይካድም:: ይህ ሁሉ ችግር የሚያመለክተው ማስታወቂያውን የሚመራ አካል በሚገባ ኃላፊነቱን አለመወጣቱን ብቻ አይደለም፤ የማስታወቂያ ስራ እየዘመነ አለመሄዱም ጭምር ነው::
የማስታወቂያ ሥራ አሁን አሁን እየዘመነ መጥቷል፤ ምስጋና ለኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ፣ በርካታ ማስታወቂያዎች በማኅበራዊ ድረ ገጾችና በመሳሰሉት ለፈላጊዎቻቸው እንዲደርሱ እየተደረገ ነው:: ይህም ማስታወቂያዎች በቆየው አሠራር በየቦታው ቢለጠፉ በከተሞች ላይ ሊደርስ የሚችለውን መቆሸሽ እያስቀረው ነው:: ቢልቦርዶችና የመሳሰሉትም ዘመኑ በወለደው ቴክኖሎጂ ተውበው የሚቀርቡ አንደመሆናቸው የከተማም ውበት መሆን እየቻሉ ናቸው::
አሁንም ቢሆን በአገሪቱ የማስታወቂያና የሕትመት ሥራ ገና ብዙ ያልተሰራበት ዘርፍ መሆኑን በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ:: በዛሬው የስኬት ገጻችንም በማስታወቂያና የሕትመት ሥራ እንግዳ ይዞ ቀርቧል:: አቶ ደረጄ እያሱ ይባላሉ:: የስካይ ማተሚያ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ናቸው::
አቶ ደረጄ በትምህርት ዝግጅታቸው በኢኮኖሚክስ ትምህርትን የተማሩ ሲሆን በማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ ለስምንት ዓመታት ሠርተዋል:: አቶ ደረጄ በመንግሥት ሥራ የሚያገኙት የወር ደመወዝ ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን በማስተዳደር ረጅም ርቀት ሊያስኬድ እንደማይችል በማመን ሌሎች ተጨማሪ ሥራዎችን ለመሥራት ይወጥናሉ:: ራሳቸውን ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ጋር ማዋሀድን ‹‹ሀ›› ብለው በመጀመር ወደ ግል ሥራ ያመራሉ::
የቴክኖሎጂውን ዕውቀት በተለያዩ አጫጭር ኮርሶች በማዳበር በቀጥታ ወደ ኮምፒዩተር ጥገና አገልግሎት ያመሩት አቶ ደረጄ፤ የማስታወቂያና የሕትመት ሥራውም በዚህ ወቅት የተወለደ ስለመሆኑ ነው የሚያስታውሱት:: የኮምፒውተር ጥገና ሥራውን ዘር በማድረግ ተረግዞ የተወለደው የማስታወቂያና ሕትመት ሥራ ዛሬ 13 ዓመታትን አስቆጥሯል::
ጠንካራ የሥራ ባህልን ባህሪያቸው ማድረግ በመቻላቸው የግላቸውን ሥራ ለመሥራት መንገድ ጠረገላቸው:: ለሥራ ያላቸው ፍላጎትና ፍቅር ለአዲሱ ሥራቸው ትልቅ አቅም ሆናቸው:: ከኮምፒውተር ጥገናው በተጨማሪ አንዳንድ የዲዛይን ሥራዎችን በመሥራት ዘርፉን ለማስፋት መውተርተር ጀመሩ::
የመንግሥት ሥራቸውን በመልቀቅ ወደ ግል ሥራ የገቡት አቶ ደረጄ፤ ባለቤታቸውን ይዘው ወደ ሥራው ገቡ፤ አቶ ደረጄ ሥራውን ተፍ ተፍ ብለው ከበር ሲያደርሱት ባለቤታቸው ወይዘሮ ሰናይት ደግሞ የመጣውን ሥራ ሙያቸውን ተጠቅመው ደንበኞቻቸው በሚፈልጉት መልኩ የዲዛይን ሥራውን ያቀላጥፉትና ወደ ሌሎች ማተሚያ ቤት በመውሰድ አሳትመው ለደንበኞቻቸው ማቅረቡን ተያያዙት:: እንዲህ እንዲህ እያለ የተጀመረው የማስታወቂያና የሕትመትና ሥራ መሠረት እየያዘ ከእድገት ጉዞው ሊያጨናግፈው የቻለ የለም::
ከአንድ ብርቱ ሁለት መድኃኒቱ እንዲሉ ለዛሬው የስኬት ጉዞ ባለቤታቸው ወይዘሮ ሠናይት ዓለሙ የነበራቸው ሚና ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዝ አሁንም በብርቱ የሚተጋገዙ ጥንዶች ስለመሆናቸው አቶ ደረጄ ተናግረው አይጠግቡም::
ይህን ሁሉ አርገው አቶ ደረጄ አልረኩም፤ በኮምፒዩተር የሠሯቸውን ዲዛይኖች ደንበኞቻቸው ወደ ማተሚያ ቤት በመውሰድ ሲያሳትሙ ያስተውላሉ፤ በዚህም ሥራው ቅብብሎሽ ያለው መሆኑን አረጋገጡ:: ይሄኔ አንድ ሀሳብ የአዕምሯቸውን ጓዳ ደጋግሞ አንኳኳ፤ ለጥሪው ምላሽ ለመስጠት ሳያመነቱ ማተሚያ ቤት መክፈት እንዳለባቸውና ዲዛይኖቻቸውን በራሳቸው ማተሚያ ቤት ማሳተም እንደሚችሉ ለራሳቸው ቃል ገቡ፤ አቅማቸው አሟጠው በመጠቀም ሀዋሳ ከተማ ላይ ስካይ ማተሚያ ቤትን አቋቋሙ::
በዘርፉ ያላቸውን ዕውቀትና ከፍተኛ ፍላጎታቸውን መሠረት በማድረግ ሁለት ሆነው የጀመሩት የማተሚያ ቤት ሥራ መነሻ ካፒታሉ ስድስት መቶ ብር ብቻ ነበር:: ስድስት መቶ ብሩም ቢሆን አንድ ወንበርና አንድ ጠረጴዛ ተገዝቶበት በ150 ብር የቤት ኪራይ ነው ወደ ሥራው የተገባ::
ወቅቱ ለዘርፉ የሚመጥን የተሻለ ቁሳቁስና ገንዘብ ይዘው ነገር ግን ገበያውን መፍጠር ያልቻሉ በርካቶች የነበሩበት መሆኑን ያስታወሱት አቶ ደረጄ፤ እርሳቸው ግን በወቅቱ ካፒታሉ ሳይኖራቸው በዘርፉ ያላቸውን የካበተ ልምድና ዕውቀት እንዲሁም ከፍተኛ ፍላጎትን መሠረት በማድረግ በገበያው ውስጥ ያለውን ክፍተት ለመድፈን ታትረዋል:: ወደ ሥራው ሲገቡ ምቹ ሁኔታዎች አልነበሩም:: ይሁንና በሚሰጡት ጥራት ያለው አገልግሎት፣ ትዕግስትና ቁርጠኝነት ሁሉንም ፈተናዎች ማለፍ ችለዋል::
በአሁኑ ወቅትም ከ150 ብር ኪራይ ቤት ወጥተው በሀዋሳ ከተማ 500 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ማተሚያ ቤት ማቋቋም ችለዋል:: ከማስታወቂያና የሕትመት ሥራቸው ጎን ለጎን የታሸገ ውሃ የማከፋፈል ሥራም ይሠራሉ:: ለዚሁ ሥራቸውም ከማተሚያ ቤታቸው አጠገብ 500 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ መጋዘን ገንብተዋል::
አሁን በማስታወቂያ የሥራ ክፍላቸው ዘመኑ የዋጃቸውን ማሽኖች ጨምሮ አጠቃላይ ከሰባት የሚበልጡ ማሽኖች አሉ:: ከእነዚህ ማሽኖች መካከልም በዋናነት የቢል ቦርድና የስቲከር ማስታወቂያዎችን ጨምሮ የቲሸርት ሕትመቶች፣ የሌዘር፣ የጣውላ፣ የማይካ እንዲሁም በኤምዲኤፍ የሚሠሩ የተለያዩ የማስታወቂያው ሥራዎች ማሽኖች ይገኙበታል:: ኤምዲኤፍና ጣውላን በመጠቀም ሲኤንሲ በተባለው ማሽን የተለያዩ ቅርጻ ቅርጾችንና ፊደላትን በመቅረጽ ቲሸርቶች፣ ኮፍያ፣ ብርጭቆና የተለያዩ የስጦታ ዕቃዎችን የማስታወቂያ ክፍሉ ያመርታል::
በሕትመቱ ዘርፍም ከጀርመን አገር ከቀረጥ ነጻ ባስገቧቸው ዘመናዊ የወረቀት ማሽኖች በመጠቀም የተለያዩ የወረቀት፣ የጋዜጣና የመጽሔት ሥራዎችን ማተሚያ ቤቱ ይሠራል:: በተለይም የሠርግ፣ የልደት ካርዶችን ጨምሮ በመጽሔት ዘርፉ የምርቃትና ሌሎች መጽሔቶችን እንዲሁም የተለያዩ የልቦለድ መጽሐፍቶችንና የዩኒቨርሲቲ ጥናታዊ ጽሑፎችንም ያትማል::
በማስታወቂያ ሥራቸው ትምህርት ሰጪ ቢልቦርዶች፣ የሙዚቃ ኮንሰርቶችና እንደ ቴሌኮሙኒኬሽን አይነት ወቅታዊ ማስታወቂያዎችን በተለያየ ቦታ ይተክላሉ:: ከዚህ በተጨማሪም የትራፊክ ምልክት መብራቶችን ይሠራሉ::
የሥራ መነሻቸውና የማምረቻ ፋብሪካቸው ሀዋሳ ከተማ ላይ ቢሆንም፣ አዲስ አበባ ላይም ሰፊ ገበያና ፍላጎት ያለ በመሆኑ ቅርንጫፍ በመክፈት ጥሩ ሥራ እየሠሩ ይገኛሉ:: ከቻይና በሚገቡ በሶላር የሚሰሩና ኤልዲዎችን በመጠቀም የተለያዩ አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ምልክቶችን ለአብነትም የፍጥነት ምልክቶችን በአዲስ አበባ ከተማ በአራቱም አቅጣጫ ይሠራሉ:: በማይካ ሥራ የጠረጴዛ ምልክቶችን ጭምር ያመርታሉ::
አዲስ አበባ ላይ በሚሠሩት ሥራ በአብዛኛው አጀንዳ፣ ካላንደር መጽሔትና የተለያዩ ካርዶች ጭምር ወደ ውጭ አገር ተልከው ሲሠሩ መታዘብ የቻሉት አቶ ደረጄ፤ ይህን ለማስቀረትና በአገር ውስጥ ጥራት ያለውን ማንኛውንም የሕትመት ሥራ ለመሥራት ተዘጋጅተዋል:: ይህ ሳይሆን የቀረበት ዋናው ምክንያት በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይልና ዘመኑን የዋጁ መሣሪያዎች ባለመኖራቸው እንደሆነ በመረዳታቸው ይህን ክፍተት ለመሙላት ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን አቶ ደረጄ ይጠቅሳሉ::
ጥራት ያለው የማስታወቂያና የሕትመት ሥራ ለመሥራት ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው አቶ ደረጄ፤ በመፈለግ ብቻ የተወሰኑ አይደሉም፤ በግላቸው በተለያዩ አገራት ተዘዋውረው ልምድ ለመቅሰም ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል:: ተዘዋውረው የልምድና የዕውቀት ሽግግር ካደረጉባቸው አገራት መካከልም ጃፓን፣ ቻይና፣ ሕንድና ዱባይ በመሄድ ከዘርፉ ጋር የተያያዙ ባዛሮች ላይ ተሳትፈዋል:: በቀጣይም በእነዚህ አገራት ላይ የተመለከቷቸውን ዘመናዊና የረቀቁ ማሽኖችን ወደ አገራቸው በማምጣት የማስታወቂያና የሕትመት ሥራውን ለማዘመን አቅደዋል::
ለማስታወቂያና ሕትመት ሥራ የሚያገለግሉት አብዛኞቹ ግብዓቶች ውጭ ቀመስ እንደሆኑ የጠቀሱት አቶ ደረጄ፤ በአሁኑ ወቅት ጥሬ ዕቃውን በቀላሉ ለማግኘት ከፍተኛ ችግር እንደሆነም ነው የሚናገሩት:: ይህ መሆኑም በደንበኞች ላይ ዋጋው እንዲጨምር አድርጓል ይላሉ:: ‹‹ሰፊ የሰው ኃይል፣ የሥራ ፍላጎትና የምርት ተፈላጊነት በአገሪቱ አለ:: ዋናው ደግሞ ፍላጎት ነውና ዘርፉ ገና ያልተሠራበት እንደመሆኑ ብዙ መሥራት ይቻላል ይላሉ::
በአሁኑ ወቅት በባነር የሚሠሩት የማስታወቂያ ሥራዎች ቀርተው በስክሪን የሚሠሩ የማስታወቂያ ሥራዎች ተተክተዋል:: ስለዚህ ይህንኑ የኤል ዲ እና የኤች ዲ የማስታወቂያ ሥራዎች በስፋትና በጥራት በመሥራት የማስታወቂያውን ሥራ ማዘመን የግድ ነው የሚሉት አቶ ደረጄ፤ በተለይም የከተማን ውበት በመጠበቅ ዘመናዊ የማስታወቂያ ሥራዎቹ የጎላ ድርሻ አላቸው ይላሉ::
በባነርና በተለያዩ ወረቀቶች የሚሰቀሉ ማስታወቂያዎች ከተሞችን በማቆሸሽ ውበታቸውን እንደሚያጠፉ ጠቅሰው፣ በአሁኑ ወቅት ግን በተለያዩ ቦታዎች ላይ የሚሰቀሉ የማስታወቂያ ስክሪኖች ለከተሞች ውበት መሆን እንደቻሉ ይናገራሉ:: ማስታወቂያዎች የከተሞችን ውበት መጠበቅ እንዳለባቸው አስገንዝበው፣ባለቤት ሊኖራቸው ይገባልም ብለዋል::
አቶ ደረጄ ለሥራው ካላቸው ቅርበት፣ ዕውቀትና ፍላጎት የተነሳ ሥራውን ማስፋት ችለዋል፤ ለዜጎችም የሥራ አድሎችን አስገኝተዋል:: በአሁኑ ወቅት ለ52 ሰዎች በቋሚነት የሥራ ዕድል መፍጠር ችለዋል:: ሥራው ሁሌም የሚሠራና በተለያዩ ወቅቶች ደግሞ ሰፊ የሰው ኃይል የሚፈልግ መሆኑን ተናግረው፣ ይህ ሲሆን ከ100 እስከ 200 ሰዎችን በኮንትራት እንደሚያሠሩም ያብራራሉ::
አብዛኛው የማስታወቂያና የሕትመት ሥራ ሙያዊ ዕውቀት የሚፈልግ እንዳልሆነም ነው የሚናገሩት:: ብዛት ያላቸውን ሠራተኞች የሚቀጥሩት ከጎዳና ተዳዳሪዎች እንደሆነም አጫውተውናል:: ፍላጎት ላላቸው የጎዳና ልጆች ቅድሚያ በመስጠት ቀለል ባለ ስልጠና ወደ ሥራ እንዲገቡ ያደርጋሉ:: በተለይም በአካባቢያቸው ለሚገኙ የጎዳና ልጆች ይህን የሥራ ዕድል በማመቻቸት ከመደበኛው ክፍያ በተሻለ ክፍያ በማሠራት ገቢ ማግኘት እንዲችሉ እያደረጉ መሆናቸውን ይገልጻሉ::
ለአካል ጉዳተኞችም ስልጠና ሰጥተው ወደ ሥራ እንደሚያሠማሯቸው ተናግረው፣ ከ52 ቋሚ ሠራተኞቻቸው መካከልም አብዛኞቹ የአካል ጉዳት ያለባቸው መሆናቸውንም ይጠቁማሉ:: በቀጣይም ቢሆን የአካል ጉዳት ላለባቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች በራቸው ክፍት መሆኑን ነው አቶ ደረጄ ያመለከቱት::
በዘርፉ የሚሰጥ ስልጠና ባለመኖሩ ባለሙያዎችን ለማግኘት ችግር መሆኑን ጠቅሰው፣ የሚገኙዋቸው ሠራተኞች መደበኛ ባልሆነ ስልጠና የሰለጠኑና በልምድ የሚሠሩ መሆናቸውን ይገልጻሉ:: አቶ ደረጄ በስካይ ማተሚያ ድርጅት ውስጥ ለሠራተኞች ስልጠና በመስጠት ባሰለጠኗቸው ሙያተኞች ሥራውን ለመሥራት አቅደዋል:: የጎዳና ልጆችንና አካል ጉዳተኞችን ወደ ሥራ ከማሠማራት በተጨማሪ ማህበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አንጻር በተለይም የሀዋሳ ከተማ ገጽታን ማጉላትና አረጋውያንን በመርዳት ተሳትፎ ያደርጋሉ::
ለ13 ዓመታት በዘርፉ የቆየው ስካይ የማስታወቂያና የሕትመት ሥራ በጣም ትንሽ በተባለው ሲልክ ስክሪን ወጥሮ በቀለም ከማተም ተነስቶ፣ በአሁኑ ወቅት ቲሸርትን በዲጂታል ሕትመት እስከ ማምረት ደርሷል:: በማስታወቂያው ዘርፍም እንዲሁ በቀለም ቀርጸው ታቤላ ላይ ይሠሩት የነበረው ሥራ በዘመናዊ መንገድ በዲጂታል ቀይረው እየሠሩ ናቸው፤ በአሁኑ ወቅት የድርጅቱ ካፒታል አስር ሚሊዮን አምስት መቶ ሺ ብር ደርሷል::
ዘመኑ የውድድር እንደመሆኑ ሥራን በተሻለ ጥራት ሠርቶ ደንበኞችን ማስደሰት የግድ ስለመሆኑ ያነሱት አቶ ደረጄ፤ ድርጅታቸው ‹‹ደንበኛህን ለማስደሰት ሠራተኛህን ተንከባከብ›› በሚል መርሕ የሚመራ እንደሆነም አጫውተውናል:: ታድያ ሠራተኞቻቸውን ከማስደሰት ባለፈ ጤናማና ቤተሰባዊ የሆነ ግንኙነት ያላቸው አቶ ደረጄ፤ ይህም ለሥራቸው ስኬት ወሳኝ ሆኖ ያገኙት እንደሆነ አጫውተውናል:: በቀጣይም የተሠማሩበትን የማስታወቂያና የሕትመት ዘርፍ በማሳደግ በውጭ አገር የሚታተሙትን የሕትመት ውጤቶች በአገር ውስጥ በማተም ለዘርፉ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ማስቀረትን ዓላማ አድርገው ይሠራሉ:: እኛም እቅዳቸው እንዲሰምር በመመኘት አበቃን::
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሰኔ 4 /2014