ትዝታና እውነታ፤
በኅዳር ወር 1989 ዓ.ም የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ፈጣሪ የተባሉ የ23 ሀገራት መሪዎች የተካተቱበትን አንድ ሴሚናር በአሜሪካዋ የሐዋይ ክፍለ ግዛት በማዊ ደሴት ለመካፈል ዕድል አጋጥሞት ነበር:: ተሳታፊዎቹ በሙሉ ከዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በስተቀር በየሀገራቸው በከፍተኛ የአመራር ሥልጣን ላይ የነበሩ የአንቱታ ባለጸጎች ነበሩ:: የሴሚናሩ አተገባበር ከፕሮፌሰሮቻችን ወደ ተካፋዮች የሚፈስ የአንድ አቅጣጫ ሌክቸር (One way communication approach) ሳይሆን እያንዳንዱ የሴሚናሩ ተካፋይ የሀገሩን መልከ ብዙ የአመራር ተሞክሮ በሚመደብለት ሰዓት መጥኖ ማቅረብ ይጠበቅበት ነበር::
በዚሁ መሠረትም ይህ ጸሐፊ ተራው ሲደርስ ይመጥናል ያለውን ዝግጅቱን አቅርቦ ካጠናቀቀ በኋላ ለተሳታፊዎቹ የአስተያየትና የጥያቄ እድል ለመስጠት ገና መድረኩን ለውይይት ክፍት ከማድረጉ በሌሎች ሀገራት አቅራቢዎች ባልተስተዋለ መነቃቃት በርካታ የሴሚናሩ ተሳታፊዎች “በእኔን አስቀድመኝ” ፉክክር እየተሽቀዳደሙ እጃቸውን እንደ ችቦ አንጨፈረሩ:: ለምን በኢትዮጵያ ጉዳይ ያን ያህል ጠያቂ ሊበዛ እንደቻለ ግራ የተጋባው ይህ ጸሐፊ ብቻ አልነበረም:: በወቅቱ አሜሪካን ሀገር በስደት ላይ የነበሩትና ያንን ሴሚናር እንዲያስተባብሩ እድል ቀንቷቸው ኃላፊነቱን የተረከቡት ብርጋዴር ጄኔራል ታዬ ጥላሁንም በሁኔታው መገረማቸውን ከሴሚናሩ በኋላ ጉዳዩን አንስተን ስንወያይ ስሜታቸውን አጋርተውኛል::
ጄኔራል ታዬ ጥላሁን ከቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ እስከ ወታደራዊ የደርግ አገዛዝ ዘመን በአየር ኃይል ውስጥ እስከ አዛዥነት፣ በባሕር ኃይልም እንዲሁ በሁለተኛ ረድፍ የሥልጣን እርከን ላይ፣ በመከላከያና በሀገር አስተዳደር ሚኒስቴር መ/ቤቶች ውስጥም በሚኒስትርነት ማዕረግ ሀገራቸውን በቅንነትና በታማኝነት ያገለገሉ ታላቅ ሰብዕና የነበራቸው ጎምቱ ኢትዮጵያዊ ወታደር ናቸው:: በመጨረሻም ለአራት የስካንዲኔቪያን ሀገራት (ስዊድን፣ ኖርዌይ፣ ዴንማርክና ፊንላንድ) የኢትዮጵያ አምባሳደር በመሆን አገልግለዋል:: በመጨረሻም የወታደራዊ መንግሥትን አስተዳደር ተቃውመው ስደትን በመምረጥ በአሜሪካ ሀገር ይኖሩ ነበር:: ዛሬ ወደ ሀገራቸው ገብተው በሰላም እየኖሩ ይገኛሉ::
ለማንኛውም፡- ይህ ጸሐፊ በሴሚናሩ ተሳታፊዎች የተጠየቃቸው ዋና ዋና ጥያቄዎች የሚከተሉትን ይመስሉ ነበር:: እናንተ ኢትዮጵያውያን ለምን ጦርነት ወዳድ ሆናችሁ? ለምንስ በረሃብ መቀጣትን ተለማምዳችሁ ለመኖር ወሰናችሁ? ሁልጊዜ የስንዴ ልመና አላሰለቻችሁም? ለምንስ ተፈጥሮና ፍጡር ፊታቸውን አዞሩባችሁ? የበቀደሙ አደጋ ራሱ ለሀገራችሁ የፖለቲካ አመራር ደካማነት ጥሩ ማሳያ ሊሆን አይችልም? መሪዎቻችሁ በጠብመንጃ አፈሙዝ ብቻ ሥልጣን ለመያዝ ከሚሞክሩ ለምን የዲሞክራሲ ባህልን አትለማመዱም? ወዘተ. ከብዙዎቹ ጥያቄዎች ጥቂቶቹ ነበሩ::
ሁሉም ጥያቄዎች የወቅቱ የሀገራዊ እውነታዎቻችን መገለጫዎች ስለነበሩ ከጠያቂዎቹ ጋር እንካ ሰላንትያ በመግጠም መሟገቱና መከራከሩ ፋይዳ አልነበረውም:: የነበረኝ ምርጫ እንደምንም ጥያቄዎቹን አለሳልሶና አድበስብሶ ለማለፍ ጥረት ማድረግ ነበር:: እውነትም በወጥመድ እንደተያዘች ድኩላ ከወዲያ ወዲህ መዝለሌ የተመደበውን የውይይት ጊዜ እምሽክ አድርጎ ስለበላው “ሰዓትህ አልቋል” ስባል የተነፈስኩት ከአጣብቂኝ መውጣቴ አስደስቶኝ “ቁና፣ ቁና” እየተነፈስኩ ጭምር ነበር:: እውነትን ሐሰት ነው ብሎ መሟገት ምንም ውጤት ስለሌለው::
“የበቀደሙ አደጋ” ተብሎ በጥያቄው ውስጥ የተጠቀሰው ክስተት የተፈጸመው ይህ ጸሐፊ ያንን ሴሚናር ይካፈል በነበረበት ወቅት፤ ኅዳር 14 ቀን 1989 ዓ.ም፤ የበረራ ቁጥሩ ኢቲ 961 የሆነ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 767 አውሮፕላን በዓላማ ቢስ ጠላፊዎች ክፉ ጭካኔ በኮሞሮስ ደሴት ላይ ተከስክሶ ከ175 ተሳፋሪዎችና የአየር መንገዱ ሠራተኞች መካከል 125ቱ ሕይወታቸውን ሲያጡ 50 ያህሉ በፈጣሪ ተዓምር መትረፋቸውን በማስታወስ ነበር:: በዚህ አደጋ ምክንያት ሕይወታቸውን ካጡት መካከል የጸሐፊው የቅርብ የሥራ ባልደረባ የነበረው የኢትዮጵያና የሕዝቧ ወዳጅ እንግሊዛዊው ሚ/ር አንዲ ሚከንስ እና ሌላ አንድ ወዳጁ ይገኙበት ነበር:: በተዓምር ከተረፉት መካከልም አንዱ የቅርብ ጎረቤቱ ዶ/ር ይስሐቅ ነበሩ:: እኒህ ሰው ከአደጋው ከተረፉ በኋላ ዕድሜ ተጨምሮላቸው ለዓመታት ከኖሩ በኋላ በተፈጥሮ ሞት የተለዩን ከጥቂት ዓመታት በፊት ነበር::
ወደ ሴሚናሩ ትዝታ እንመለስ:: ከሥልጠናው መጠናቀቅ በኋላ እያንዳንዱ ተሳታፊ ወደ ሀገሩ እንደተመለሰ መሻሻል አለበት ብሎ በሚያምንብት የሀገሩ ሁለንተናዊ የአመራር ስልት ዙሪያ እንደ አንድ አደራ ተቀባይ የተማረውን ለወገኖቹ ለማስተላለፍ ቃል ኪዳን መግባት ይጠበቅበት ነበር:: አንድም ተመሳሳይ ሴሚናር በማዘጋጀት ከተባባሪ ወገኖችና ተቋማት ጋር በማበር አደራውን በትጋት መወጣት ወይንም በአመራር ዙሪያ መጽሐፍ መጻፍ ከአማራጮቹ መካከል ጥቂቶቹ ነበሩ::
ይህ ጸሐፊም እንደሌሎቹ ተሳታፊዎች ቃል የገባው ሁለቱንም አማራጮች እተገብራለሁ በማለት ነበር:: የተማረውን በሥልጠና ለማካፈልና በአመራር ዙሪያ ቢያንስ አንድ መጽሐፍ ለመጻፍ:: “ቃል የእምነት ዕዳ ሆኖበትም” ኪዳኑን አክብሮ በ2001 ዓ.ም “የአመራር ጥበብ” በሚል ርዕስ መጽሐፍ ጽፎ ለአንባቢያን እንዲደርስ አድርጓል:: የአጋጣሚ ጉዳይ ሆኖም መጽሐፉ በከፍተኛ ሁኔታ ተወዳጅነት በማትረፉ ተደጋግሞ ለመታተም በቅቷል::
ከገጠመኞቹ ጋር በማዋዛት በአጭሩ በዚህ ጽሑፍ ለመቃኘት የሞከረውም ከስልጠናው በኋላ የቀመረውን ሦስት የሀገራዊ የአመራር ተግዳሮቶቻችንን ከዛሬ እውነታችን ጋር በመፈተሽ በወፍ በረር ቅኝት ለመዳሰስ በማሰብ ነው:: ሦስቱ የተባሉት ተግዳሮቶች የሚከተሉት ናቸው፡- መሪነትን ማን ይጠላል? መመራትስ መች ይወደዳል? ያለ መሪስ እንዴት መኖር ይቻላል? ዛሬያችን ላይ ጫን በማለት ጥያቄዎቹን ተራ በተራ እንፈትሻቸው::
ሀ. መሪነትን ማን ይጠላል? መልሱ ብዙ ምርምር አይጠይቅም:: መሪነትን ማንም አይጠላም:: ይህ ጥያቄ ስለ ውጤታማ መሪነት ብዙ ጉዳዮችን እንድንዳስስ ያበረታታናል:: በርግጥም መሪ መሆን፤ አቅም ይኑርም አይኑር፤ የሚጠላ አይደለም:: ምክንያቱም የመሪነት ፍላጎት ተፈጥሯዊ እንጂ ከቀን በኋላ የሚጎናጸፉት ክህሎት አይደለም:: በማንኛውም የሕይወት እንቅስቃሴ ውስጥ ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች አንድ የጋራ ዓላማ ለማስፈጸም ሲሰባሰቡ ከመካከላቸው አንዱ ቀዳሚ መሪ ሌሎች ተከታይ እንዲሆኑ የግድ የሚለን ሰብዕናችን ጭምር ነው::
ለምሳሌ፡- የዕለት ተዕለት የሕይወታችን እንቅስቃሴ ልብ ብለን እናስተውል:: ቡሄ ጨፋሪ ልጆች፣ የ“አበባ አየሽ ወይ” ባህላዊ ከዋኝ ልጃገረዶችና የጨርቅ ኳስ ተፋላሚ ቡድኖች ሳይቀሩ ወደ ባህላዊ ጨዋታቸው ከመግባታቸው አስቀድሞ መጀመሪያ የሚወስኑት ተቀዳሚ ተግባራቸው የቡድን አለቃቸውን ወይንም ካፒቴናቸውን መምረጥ ነው:: የወጣቶችና የጎልማሶች የገና ጨዋታም የገና አባት ሊኖረው ግድ ይላል:: ሙሽራና ሙሽሪይቱም ቀዳሚና አስተባባሪ ሚዜዎች መሰየም ይጠበቅባቸዋል:: የእናቶችና የአባቶች ማኅበርም “ሙሴ” አለው ወዘተ. “መሪነትን የሚሹ” በርካታ መሰል ተሞክሮዎችን መዘርዘር ይቻላል::
መሪ፣ አለቃ፣ አስተባባሪ፣ ዳኛ፣ ሹም፣ ሥራ አስኪያጅ፣ የኮሚቴ ወይንም የቦርድ መሪ፣ ጠቅላይ ሚኒስትርም ይሁን ፕሬዚዳንት የተለያየ ስያሜ ይምሰሉ እንጂ ጽንሰ ሃሳባቸውና ተልእኳቸው በየደረጃቸውና በሥልጣን ክልላቸው ልክ ሌሎቹን በመምራት፤ ወይንም ፊት ቀድሞ በመታየት ተከታዮችን በማስተባበር ተልዕኮን ማሳካት ነው:: በአጭሩ መሪነት ነው:: እንኳን የሰው ልጆች ቀርተው መላእክትም ቢሆኑ መሪ አለቃ እንዳላቸው በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ “የመላእክት አለቃ ሚካኤል” ተብሎ ተጠቅሷል:: ስለዚህም ነው መሪነት ተጠልቶ የሚገፈተር አይደለም የሚባለው::
እርግጥ ነው መሪነት እንደምናስበው ቀለል ተደርጎ ብቻ የሚበየን እንዳልሆነ አይጠፋንም:: ብቃቱና አቅሙ ያለው ባለ ራዕይና ለውጤት የጨከነ መሪ መልካም ተመሪዎችን መፍጠሩ እውነት ነው:: በአንጻሩም መልካም ተመሪም መልካም መሪን ለመፍጠር እድሉ የሰፋ ነው:: የውጤታማ መሪን ባህርያትና መርሕ በዝርዝር ለመተንተን የገጹ ውስንነት ስለሚገድበን ከዚህ በላይ ብዙም አንልም::
የሀገራችንን ወቅታዊ ሁኔታዎች ጠለቅ ብለን ስንፈትሽም ደረጃው ቢለያይም የችግሮቻችን ዋነኛው ማጠንጠኛ ከመሪነት ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ አያከራክርም:: ፖለቲከኞች የሚያምሱን ለምንድን ነው? እኔ ብቻ ካልመራሁ፣ የእኔ ሃሳብ ብቻ ካልተደመጠና ሥራ ላይ ካልዋለ በማለት አይደለምን? ጫካ ተሸሽገው የሚወጉን፣ በአሸባሪነት ተፈርጀው “ሀገርን ካላፈረስን” እያሉ ጦር የሚሰብቁት ምክንያታቸው ምንድን ነው? የመሪነት ወንበር ላይ ለመፈናጠጥ አይደለምን? አንዳንድ አክቲቪስት ተብዬዎችስ ችግራቸውና መንፈራገጣቸው ከምን ጋር የተያያዘ ነው? የእኔ ሃሳብ ብቻ ይምራ፤ እኔ ብቻ ልደመጥ፣ የእኔ ሃሳብ የሁሉም ችግሮች መክፈቻ ቁልፍ ካልሆነ፤ በሚል የቅዠት ባህር ውስጥ ስለሚዋኙ አይደለምን? ከያኒውንም፣ ነጋዴውንም ሆነ ሌላውን የማኅበረሰብ ክፍል በዚህን መሰሉ ወንጠፍት ብንፈትሸው መዳረሻው “እኔ ካልመራሁ፣ እኔ ቀድሜ ካልታየሁ፣ እኔ፣ እኔ ብቻ…” ከሚለው ምኞት የሚዘል ሆኖ አናገኘውም:: ስለዚህም ነው መሪነትን ማንም አይጠላም የሚባለው:: ምክንያቱም ውጤት ሲገኝ ዝና ይኖራል፣ ክብር ይገኝበታል፣ ጥቅምም አይጠፋውማ:: ብሂላችንስ “መሪ የሌለው ጨንባሳ፤ ምርኩዝ የሌለው አንካሳ” ብሎ ማረጋገጫውን ይሰጠን የለ::
ለ. መመራትስ መች ይወደዳል? እርግጥ ነው ካልቸገረ በስተቀር ማንም ሰው መመራትን አይወድም:: አሁንም የመከረኛዋን ሀገራችንን አሳር ልብ ተቀልብ ሆነን ብንፈትሽ “የመመራት ጥዩፍነት” አንዱ፤ ምናልባትም ተቀዳሚ ሀገራዊ ችግራችን ሳይሆን እንደማይቀር ይታመናል::
የፖለቲካ ፓርቲዎቻችን ለምን ህመምተኛ ሆኑ? የማኅበረሰብ አንቂዎች ተብዬዎችስ ከሃሳብ አፍላቂነት ይልቅ ለምን “ጦር ሰባቂነትን” መረጡ? ከወታደራዊ ክፍሎች በስተቀር በአብዛኛው መንግሥታዊና ሕዝባዊ ተቋማት ውስጥ የሚስተዋለው የመሪና ተመሪ መናናቅ መንስኤው ከምን የመነጨ ነው? መብትና ግዴታ መልካቸው ጠይሞ ግራ መጋባት ላይ የደረስነው “ለመመራት አለርጂ” የሆኑ “ደመወዝተኞች” ወይንም ጥቅመኞች እንደ አሸን በመፍላታቸው ምክንያት አይደለምን? “ሆድ ያባውን…” እንዳይሆን እንጂ፤ ብዙ ጉዳዮችን መዳሰስ ይቻል ነበር::
ሐ. ያለመሪስ እንዴት መኖር ይቻላል? “መሪ የሌለው ሕዝብ፤ አውራ የሌለው ንብ” እንዲል ምሳሌያችን፤ አለመሪ እኖራለሁ ማለት ውጤቱ እንደ ብሂሉ መንጋነት ነው:: “በመንጋ አስተሳሰብ” ሆ! በማለት ብቻ ያለ መሪ ለመኖር መኖር አይቻልም:: ብዙዎች የሚፋንኑት፣ “እንዳሻን እንሁን ልቀቁን” በማለት ሀገርና ሕዝብ ጤና የሚያጣው፤ “እሽ አትበሉን የንጉሥ ዶሮ ነን” እያሉ አዛዥ ናዛዥ አንፈልግም የሚል የመንጋ አስተሳሰብ ባላቸው ዜጎች አይደለምን? ሆድ ይፍጀው!
ማጠቃለያው እንዲህ ነው:: መሪነትን መመኘትና መጓጓት መብትም ነው፤ ሰብዕናችንም ይፈቅድልናል:: ቢሆንም ግን ለመምራት የራዕይ ጽንስ፣ የማስፈጸም ብቃት፣ ለተመሪዎች ፍቅርና ርህራሄ፣ ከራስ ምቾት ይልቅ ለተከታዮች አክብሮትና ለኅሊና ተገዥ መሆን ቀዳሚ መስፈርቶች ናቸው:: አምባገነንነት ለጭቆና እንጂ ለመሪነት ፋይዳ የለውም:: በተመሪዎች ጭንቅላት ላይ የባቢሎን ግንብን እየገነቡ ወደ ሰማየ ሰማየት ለመክነፍ የሚሞከርበት የአመራር ዘዴ ትርፉ በራስ ላይ ፈርዶ እንዳልሆኑ መሆን ነው::
እርግጥ ነው መሪነትን የሚጠላ የለም ብለናል:: መመራትም ላይወደድ ይቻላል:: ያለ መሪ ለመኖር መወሰን ግን እብደትም፤ መታወርም ነው:: “ላብ ደምን ያድናል” የሚል የተለመደ ወታደራዊ አባባል አለ:: ውጤታማ መሪ የዕይታ አድማሱ ሩቅ ነው:: ግቡም የተመሪው ስኬት ነው:: መዳረሻ ውጤቱ “የላብና የደም ግብርን” ቢጠይቅ እንኳን ራሱን መስዋዕት አድርጎ ለማቅረብ አያመነታም:: ልቡም ነፍሱም ለግቡ ስኬትና በተመሪዎች ፍቅርና አደራ የታሰረ ነው:: እንዲህም ቢሆን ግን መሪው መሞገስንም ሆነ መነቀፍን፣ መተቸትንም ሆነ መመስገንን በልበ ሰፊነት ለማስተናገድ ጫንቃው መደደር አለበት:: የውጤታማ መሪ ኒሻኑና ሜዳሊያው የተከታዮቹ ደስታ ነው:: በዘመናት ውስጥ የመሪ ያለህ ጩኸት የበረከተውም ይህን መሰሉን ጸጋ ለመጎናጸፍ ከመትጋት ይልቅ እንደ ባህላዊው የሀገራችን የ“ሆያ ሰለሜ” የሙዚቃ አጃቢ ትርዒት ጅራፍን ለሰልፍ አስከባሪነት መጠቀም ሲጀመር ነው:: ከተመሪው አንጻር ካየነውም መመራትን ጠልቶ ያለ መሪ ካልኖርኩ በሚል ራስ አምላኪነት ፍልስፍና ሕግን ማስለቀስ ሲጀምር “እመቤት ሆይ ፍትሕ” (Lady Justice) ሰይፏን ለመሪው ለማዋስ የዐይኗን መሸፈኛ ጥቁር ቱቢት ብትገልጥ አግባብ አይደለም ብሎ ለመሟገት ያዳግታል:: መሪነትን ማን ይጠላል? መመራትስ መች ይወደዳል? ያለመሪስ እንዴት መኖር ይቻላል? ትዝታዬና እውነቱ ይህን ይመስላል! ሰላም ይሁን!
በ(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ሰኔ 4 /2014