የሚኒስትሮች ምክር ቤት የፌዴራል መንግስቱ የ2015 በጀት አመት ረቂቅ በጀት 786 ቢሊዮን ብር እንዲሆን በቅርቡ አጽድቆ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወያይቶ አንዲያጸድቀው ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መምራቱ ይታወሳል፡፡ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴም ባለፈው ማክሰኞ በተካሄደው ስድስተኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንደኛ አመት የስራ ዘመን 11ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ረቂቅ በጀቱን አቅርበዋል፡፡ በዛሬው የኢኮኖሚ አምዳችንም ሚኒስትሩ በቅድሚያ ኢኮኖሚውን አስመልክተው የሰጡትን ማብራሪያ ከዚያም ያቀረቡትን ረቂቅ በጀት ይዘን ቀርበናል፡፡
ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች
የገንዘብ ሚኒስትሩ በቅድሚያ ባለፉት አመታት በሀገሪቱ ኦኮኖሚ ላይ በአጠቃላይ የታዩ ዋና ዋና ጉዳዮችን በማንሳት ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ተግባራዊ በመደረጋቸው ምክንያት በአገሪቱ የተከሰተውን የተዛባ የማክሮ ኢኮኖሚ በማስተካከል ተስፋ ሰጪ የኢኮኖሚ ውጤቶች መታየታቸውንም አስታውቀዋል፡፡ ለዚህም በርካታ የገንዘብና የፊስካል ፖሊሲ፣ የውጭ ምንዛሪ፣ የፋይናንስ፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች እንዲሁም የመዋቅራዊና የዘርፍ ማሻሻያዎች ተግባራዊ መደረጋቸውን ጠቅሰው፣ ይህን ተከትሎም በትክክልም የማክሮ ኢኮኖሚው የመሻሻል አዝማሚያ ማሳየት እንደቻለና በኢኮኖሚው ላይም ለውጦች እንደነበሩ ጠቁመዋል፡፡
ፈተናዎች
ከ2012 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ዘርፈ ብዙ ፈተናዎች እንዳጋጠሙትም ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል፡፡ እነዚህም በማሻሻያዎቹ ትግበራ ውጤት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድረዋል ነው ያሉት ሚኒስትሩ፡፡
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ጨምሮ በርካታ ተግዳሮቶች አጋጥመዋል፡፡ በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች የተከሰተው ድርቅ፣ የአንበጣ መንጋ፣ የጎርፍ አደጋና በሰሜኑ የአገሪቷ ክፍል የተከሰተው ጦርነትና ተያያዥ አለመረጋጋቶችን እንዲሁም በሩሲያና በዩክሬን መካካል የተቀሰቀሰው ጦርነትም እንዲሁ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ካሳረፉት ዋና ዋና ችግሮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ እነዚህ ችግሮችም በቀጣይም ጫናዎችን እያስከተሉ ናቸው፡፡
ከ2011 እስከ 2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ዕደገት በአማካኝ በሰባት ነጥብ አንድ በመቶ ማደግ መቻሉንም የገንዘብ ሚኒስትሩ አስታውሰው፣ አፈጻጸሙ ግን ከዕቅድ በታች መሆኑን መረጃዎች አመላክተዋል ብለዋል፡፡
ሚኒስትሩ የጠቅላላ ኢንቨስትመንት አፈጻጸምን በተመለከተ በ2011 በጀት ዓመት ከነበረው የ35 ነጥብ ሶስት በመቶ ድርሻ እየቀነሰ በመምጣት በ2013 ዓ.ም ወደ 28 በመቶ ዝቅ ማለቱን ጠቅሰው፣ የዜጎች የነፍስ ወከፍ ገቢም በ2013 በጀት ዓመት ወደ አንድ ሺ 92 የአሜሪካ ዶላር ከፍ ማለቱን መረጃዎች እንደሚያመለክቱ ተናግረዋል፡፡
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት የበርካታ ዓለም አገራት ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በከፍተኛ መጠን ቀንሰዋል፤ ከዜሮ በታች ዕድገት ያስመዘገቡ ሀገሮችም ነበሩ፡፡ ከዚህ አንጻር በአገሪቱ ተግባራዊ የተደረጉ መጠነ ሰፊ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች የተከሰቱትን ተጽዕኖዎችና ተግዳሮቶች ለመቋቋም የሚያስችል አቅም መፍጠር ማስቻላቸውን ከአፈጻጸሙ መረዳት ይቻላል፡፡
ዋጋ ንረትን በተመለከተም ባለፉት ዓመታትና በተያዘው በጀት ዓመት የዋጋ ንረት ባለሁለት አሃዝ ዕድገት በማሳየቱ የኢኮኖሚ ፈተና ሆኖ ቀጥሏል፡፡ በኢኮኖሚው ማሻሻያው አመርቂ ውጤት የልታየበት የዋጋ ንረት በታህሳስ ወር 2011 ዓ.ም ከተመዘገበው 10 ነጥብ አራት በመቶ ጀምሮ በተከታታይ ጭማሪ በማሳየት እየተጠናቀቀ ባለው 2014 በጀት ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ የ36 ነጥብ ስድስት በመቶ የዋጋ ንረት ተመዝግቧል፡፡ የዋጋ ንረቱ የመነጨው ከምግበና ምግብ ነክ ባልሆኑ ምርቶች ላይ ሲሆን ከአቅርቦትና ፍላጎት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ለዋጋ ንረቱ መንስኤ መሆናቸውን የተካሄዱ ጥናቶች አመላክተዋል፡፡
እየተገባደደ ላለው የ2014 በጀት ዓመት ባለፈው አመት የፌዴራል መንግሥት ተጨማሪ በጀትን ጨምሮ የ675 ቢሊዮን ብር የወጪ በጀት ማጽደቁን ያስታወሱት ሚኒስትሩ፤ ይህን ወጪ ለመሸፈንም ብር 436 ቢሊዮን ከታክስ፣ ታክስ ካልሆኑና ከውጭ እርዳታ ታቅዶ እንደነበረ ተናግረዋል፡፡ የታቀደውን የበጀት ጉድለት ብር 38 ቢሊዮን ከውጭና 190 ቢሊዮን ብር ከአገር ውስጥ የተጣራ ብድር በመውሰድ ለመሸፈን ታቅዶ አንደነበርም አስታውሰው፣ በተከሰተው ጦርነት ምክንያት ተጨማሪ የወጪ ፍላጎት ከመታየቱም በላይ ከታቀደው አጠቃላይ የፌዴራል ገቢ ውስጥ እስከ 25 በመቶ የሚሆነው የታክስ ገቢና የውጭ እርዳታ የማይሰበሰብ መሆኑን ማወቅ ተችሏል ብለዋል፡፡
የጦርነቱ ጉዳትም በተያዘው በጀት ዓመት ብቻ ሳይሆን በቀጣዮቹ ዓመታትም ከፍተኛ የፊስካል ጫና እና ስጋትን የሚያስከትል መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትሩ ጠቅሰው፣ የቀጣዮቹ ዓመታት የመንግሥት በጀት ዝግጅት ዋናው ትኩረት ከዚህ ቀደሙ በተለየ በጦርነት የደረሰውን ጉዳት መልሶ መገንባትና የሰብአዊ ድጋፍ እንዲሁም የዕዳ ክፍያ ላይ ትኩረት የሚያደርግ መሆን አመልክተዋል፡፡
የ2015 ረቂቅ በጀት
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወያይቶ እንዲያጸድቀው በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቆ የተመራለት የ2015 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግስት ረቂቅ በጀት 786 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ረቂቅ በጀቱ ካለፈው በጀት ዓመት በጀት ጋር ሲነጻጸር ከ111 ቢሊዮን ብር በላይ ልዩነት አለው፤ 16 በመቶም ዕድገት ያሳየ ነው፡፡ ወቅቱን ያገናዘበና ያለፉትን ዓመታት የኢኮኖሚ ሁኔታዎችን ታሳቢ ያደረገ ስለመሆኑ እንዲሁም በቀጣይ የሚመጣውን የኢኮኖሚ ሂደትም ከግምት ውስጥ ያስገባ በጀት እንደሚሆን ተገምቶ የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ምቹ ሁኔታዎችና የትኩረት አቅጣጫዎች
የገንዘብ ሚኒስትሩ አጠቃላይ አገሪቱ ከኢኮኖሚና ከፊስካል አፈጻጸም አንጻር ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ በማስረዳት፣ 2015 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግሥት ዓመታዊ በጀት የተመሰረተባቸውን ታሳቢዎችና የበጀቱን የትኩረት አቅጣጫዎችንም ለምክር ቤቱ አብራርተዋል፡፡
የቀጣዮቹ ዓመታት የማክሮ ኢኮኖሚ ትንበያን እንደ መነሻ በመውሰድ በቀጣይ ዓመት ሰላም ሰፍኖ የማክሮ ኢኮኖሚው እይታም ከተግዳሮቶች የተላቀቀ በመሆን ለቀጣይ የኢኮኖሚ ዕድገትና ማክሮ ኢኮኖሚ ዕድገት ምቹ ሁኔታዎች እንደሚፈጠር ታሳቢ መደረጉን ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡
የገቢ ምንጮች
በዝርዝር የቀረበው የ2015 ዓ.ም አጠቃላይ ገቢ የውጭ እርዳታን ጨምሮ 477 ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር እንደሚሆን መታቀዱን ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡ ከዚህም ውስጥ ከአገር ውስጥ ምንጭ የሚሰበሰበው ገቢ 92 በመቶ የሚሆነውን ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝ ገልጸዋል፤፤ ከታቀደው የአገር ውስጥ ገቢ ብር 400 ቢሊዮን ብር ወይም 84 በመቶ የሚሆነው ከታክስ ገቢ ለመሰብሰብ የታቀደ መሆኑም ተገልጿል፡፡
ታክስ ካልሆኑ የገቢ ምንጮች የሚሰበሰበው ገቢ ሌላኛው የፌዴራል መንግሥት የወጪ በጀቱን ለመሸፈን የታቀደ የገቢ አይነት ሲሆን፣ በዚህም መሰረት በ2015 ዓ.ም ታክስ ካልሆኑ ምንጮች 38 ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዷል፡፡ ከዚህ ምንጭ የሚሰበሰበው ገቢ በዋናነት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ከሌሎች ተቋማት የሚገኝ ገቢ ነው፡፡ ይህም በ2014 በጀት ዓመት ከተያዘው የ10 በመቶ ጭማሪ እንደሚነረው ተጠቁሟል፡፡
ከገቢ አንጻር ለ2015 በጀት ዓመት መሸፈኛ የሚውለው የገቢ ምንጭ ከውጭ እርዳታ ምንጭ እንደሚገኝ የታቀደ ገቢ ሲሆን፣ ከዚህ ምንጭ ጠቅላላ ብር 38 ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር ለማግኘት ታቅዷል፡፡ ከዚህም ውስጥ ብር ሰባት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር በቀጥታ ወደ መንግስት ማዕከላዊ ቋት የሚፈስ ሲሆን፣ ቀሪው ብር 31 ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር ለተወሰኑ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ በእርዳታ የሚገኝ እንደሆነም ተጠቅሷል፡፡
የመደበኛና የካፒታል በጀት
በረቂቅ በጀቱ ላይ ከተመለከተው ጠቅላላ የወጪ በጀት ውስጥ ለመደበኛ ወጪ ብር 345 ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር ለካፒታል ብር 218 ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር እንዲሁም ለክልል መንግስታት ድጋፍ ብር 213 ቢሊዮን እና ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ብር 14 ቢሊዮን ተደግፎ ቀርቧል፡፡
አጠቃላይ ተደግፎ ከቀረበው የፌዴራል መደበኛና ካፒታል በጀት ውስጥ 37 ነጥብ አምስት በመቶ ለመንገድ፣ ለትምህርት፣ ለውሃና ኢነርጂ፣ ጤናና የከተማ ልማትና የግብርና ዘርፎች የተመደበ ነው፡፡ ለእነዚህ ዘርፎች በ2014 በጀት ዓመት ከተደለደለው በጀት ድርሻ አንጻር የበጀት ድርሻው ቅናሽ ያሳያል፡፡ ለዚህም ዋናው ምክንያት ለዕዳ ክፍያ፣ ለመከላከያ፣ ለመልሶ ማቋቋም፣ ለዕለት እርዳታ እንዲሁም ለማዳበሪያና ለስንዴ ድጎማ የተመደበው የበጀት ድርሻ በመጨመሩ ሲሆን፣ ለእነዚህ የተመደበው በጀት መጠንም ብር 239 ቢሊዮን ወይም የጠቅላላ መደበኛ በጀቱ 69 በመቶ ነው፡፡
በአጠቃላይ ለመደበኛ ወጪ ከተደለደለው በጀት ውስጥ ብር 75 ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ወይም 218 በመቶ ለደመወዝ፣ ለአበልና ለልዩልዩ ክፍያዎች እንዲውል የታቀደ ሲሆን፣ ብር 271 ነጥብ አምስት ቢሊዮን ወይም 78 ነጥብ ሁለት ደግሞ ለሥራ ማስኬጃ የተደገፈ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ለበጀት ዓመቱ ከተያዘው በጀት ውስጥ 213 ነጥብ 4 ቢሊዮን የተጣራ የበጀት ጉድለት እንደሚገጥመው የተተነበየው ይሄው ረቂቅ በጀት በአገር ውስጥ እና በውጭ በሚወሰድ ብድር እንዲሸፈንም ታቅዷል። በሁለት አሃዝ ባደገ የዋጋ ንረት የታመመው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከ 2011 እስከ 2013 ዓ.ም በነበሩት ሦስት ዓመታት ውስጥ ከእቅድ በታች የሆነ የሰባት ነጥብ አንድ በመቶ አማካይ ዕድገት ማሳየቱም ተገልጿል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሰኔ 3 /2014