ከገነት ስፍራዎች አንዱን የሚመስል፣ የመላዕክት ስውር ሹክሹክታና ጽሞና የሚደመጥበት ከሰባቱ ሰማያት አንዱን የወረሰ፣ በአይን እየገባ ከነፍስ የሚያርፍ በደስታ እቅል የሚያሳጣ ቦታ፣ ነጭ አረፋውን እየደፈቀ በጌጣም ድንጋዮች ላይ የሚቦርቅ ፏፏቴ፣ እንደ ገረገራ በረድፍ በበቀሉት ዛፎች ላይ የሚዘምሩ አእዋፋት..በዚህ ሁሉ ውስጥ ለብቻዋ የተቀመጠች አንዲት ሴት። አይኗን ወደ ወንዙ፣ ጆሮዋን ወደ አእዋፍቱ፣ ቀልቧን ወደ ነፋሱ ሰዳ ከራሷ ጋር የጸሞነች። ወንዶች ያዩዋታል..በዛ ስፍራ ከእሷ ሌላ አይን ማረፊያ የሌለ እስኪመስል ድረስ። በዛ ስፍራ እሷ እንደ ጨረቃ ናት..እንደ ጀምበር። ሁሉም ወንዶች እሷን መሬት አድርገው የሚኖሩ ናቸው። ይሄ ያስጠላታል..ከወንዶች ሽሽት ያልደረሰችበት የብቸኝነት ጥግ የለም። ከወንዶች ሽሽት ያልቀለሰችው የብቻ ጎጆ የላትም። ግን ሁሉም ጽሞናዋ፣ ሁሉም የብቸኝነት ጎጆዋ በወንዶች የሚፈርስ ነው።
አጠገቧና ከአጠገቧ ራቅ ያሉ ጎርናና ድምጾች ይሰሟታል። ሁሉም ድምጾች ሴት ለማጥመድ፣ ሴት ለማሰናከል የሚያንሾካሹኩ ናቸው። እነኚህ ድምጾች ዘመኗን ሙሉ ስትሸሻቸው፣ ዘመኗን ሙሉ ስትጸየፋቸው የኖረቻቸው ናቸው ግን ሸሽተዋት አያውቁም። ባለችበት ሁሉ አሉ። ሀሳቧን ሳትጨርስ ወደ እሷ የሚደነቃቀፍ የወንድ ኮቴ ሰማች። ወዲያው በጥብቆዋ ያልተሸፈነ ገላጣ ማጅራቷ ላይ አንድ እጅ አረፈባት። ወደ ኋላዋ ስትዞር የሰማይ ስባሪ ከሚያክል ጎረምሳ ጋር ተገናኘች። ወጠምሻው በአይኑም፣ በጥርሱም እየሳቀ እጅ ነሳት። አስከትሎም ‹እርግጠኛ ነሽ የዚህ ግቢ ጠባቂ መላዕክት ነሽ?
‹አይደለሁም። መለሰችለት።
‹እሺ ከዘጠና ዘጠኙ ነገደ መላዕክት አንዷን ትሆኚ?
አይደለሁም።
‹ኪሊዮፓትራን አሊያም ደግሞ የዳቪንቺ ሞናሊዛ ነሽ እወራረዳለሁ?
‹አይደለሁም።
‹ኦ አወኩት! ይሄን ምሽት አብሮሽ የሚያሳልፍ እንደ እኔ ያለ ወንዳወንድ እየጠበቅሽ ነው አይደል?
‹አይደለም።
‹ይሄን ሁሉ ካልሆንሽ ታዲያ ምንድነሽ? መቶ ሃያ ሚሊዮን ሕዝብ ባላት ሀገር ላይ ብቻሽን ምን እየሠራሽ ነው?
‹‹ብቻዬን አይደለሁም..አየህ ብቻዬን እንዳይደለሁ እንኳን ማወቅ አልቻልክም። ልብ ቢኖርህ ኖሮ ብቻዬን እንዳልሆንኩ ትደርስበት ነበር።
በንግግሯ የበለጠ እየሳቀ ‹ታዲያ ከማን ጋር ነሽ? ከአንቺና ከክፍት ወንበርሽ በቀር እኮ አብሮሽ ማንም የለም›።
‹ሰው ብቻውን ሆኖ አያውቅም። እንደ ራስ ሙሉነት የለም። ከራስ ጋር እንደመሆን፣ ከራስ ጋር እንደማውራት በሰዎች መከበብ የለም። እኔም አሁን በራሴና በሀሳቤ፣ በጽሞናዬም የተከበብኩ ሴት ነኝ። ስለምን ብቻሽን ነሽ ትለኛለህ?
‹መግደርደሩን ተይና ቅረቢኝና ሴትነትሽን ሙሉ አድርጊ። አላት ጉራና ማን አለብኝነት በቀላቀለ ድምጽ።
‹እስካሁን ሙሉ ነኝ ይልቅ ከቀረብኩህ ነው የምጎለው..
‹ምን እያልሽ ነው? የትኛዋም ሴት እኔን ቀርባ ጎላ አታውቅም። እኚህ ሁሉ ሴቶች እኔንና የአንቺን እንቢ ማለት ነው የሚጠብቁት› አላት በዙሪያቸው ወዳሉት ሴቶች እየጠቆመ።
‹እንግዲያውስ ወደነሱ መሄድ ትችላለህ..አንድ ነገር ግን አስታውስ..እኔ ከነሱ ሌላ ነኝ፣ እኔ ካየሀቸው ሁሉ ሌላ ነኝ። እኔ በሕይወትህ ተመኝተህ ያጣሀት ሴት ነኝ። እኔ ማንም ፈልጎ የማያገኛት ሴት ነኝ። እኔ የትኛውም ወንድ ካለፍላጎቴ ምንም የማያደርገኝ ሴት ነኝ። እኔ ለእንዳንተ አይነቱ ከነውር ውጪ ምንም ለሌለው የሚሆን ልብ የሌለኝ ሴት ነኝ። እኔ በወንድ ልጅ መልክና ቁመና፣ ሀብትና ዝና ክብሬን አሳልፌ የማልሰጥ ሴት ነኝ። እኔ በሕይወትህ ባወኳትና በቀረብኳት ሚስቴም በሆነች ብለህ የተመኘሀት ሴት ነኝ። እኔ ሀብትህን መንዝረህ፣ እድሜህን ቆጥረህ የማትደርስባት ሴት ነኝ። እኔ የወንዶች ሁሉ ህልም ነኝ..ዳግመኛ እንዲህ እንደአሁኑ ፊቴ እንድትቆም እንኳን እድል አልሰጥህም› አለችው።
ሲያደምጣት በእልህ ነበር። የትኛዋም ሴት እንዲህ ብላው፣ እንዲህ ተናግራው አታውቅም። ወንድ አይደል የሆነ ሀሳብ መጣበት..ሴቶችን እንዴት መቅጣት እንዳለበት ያውቃል። ከእሷ ከምትበልጥ ሴት ጋር ወዳጅነት ፈጥሮ ሊያስቀናት ፈለገ እንዳሰበውም ፊቷ ብዙ አልቆየም ሸጋ ፍለጋ ወዲያ ወዲህ ጀመረ። አፍታ አልቆየም ግማሽ ደርዘን ሴቶችን ተዋወቀ። ከተዋወቃቸው ብዙ ሴቶች ጋር ፊቷ ላይ ብዙ ነገር ሆነ። ግን እንዳሰበው አልቀናችም..አለመቅናቷ ይበልጥ አበገነው። እኔ ስትል የተናገረችውን አምኖ መቀበል አልቻለም።
እሷ ረስታዋለች..ወደ ጽሞናዋ ከተመለሰች ዘመን የላትም። ወንዶችን ደግሞ ያለማሰብ ለነፍሷ ያስተማረቻት የልጅነት ጥበቧ ነው። አይደለም ደግማ ልታስባቸው አንድ ጊዜ የሚበዛባቸው የአፍታ ፍጥረታት ናቸው ትላለች። የቀረባት ሁሉ ግን ሳያስባት፣ ሳይሰልሳት ቀርቶ አያውቅም። ወንዶችን የመዠለጫ ትልቁ የበቀል በትሯ ይሄ ነው…
ሁሉም ሴቶች ዓለም አላቸው። ወንዶች የገቡበት ዓለም አንድ ቆንጆ ሴት ወንድ በሌለበት አንድ አጠገቧ ማንም ‹እንደዛሬ ውብ ሰማይ አይቼ አላውቅም..አንቺስ አይተሽ ይሆን? አንድ ድምጽ ተሰማት። የጽሞናዋ ውቅያኖስ ተናወጠ። ቀና ስትል በከሰዓት በኋላዋ ጀምበር ጥላው የረዘመ አንድ ወጣት ጎኗ ቆሞ ነበር። ‹ጸሐይ የሌለ ፈጋለች፣ ጨረቃም ያለልማዷ በቀን ወጥታለች፣ ክዋክብትም በጨረቃ ዙሪያ እያረገዱ አሸወይና ይላሉ። ንፋስም አናስገባም ሰርገኛ ሲል ያዜማል ማንን ሊድሩ ይሆን? እርግጠኛ ነኝ የቀረብሽ ሙሽራሽ እኔ ነኝ። ወንበሮቹም እኔን እየጠበቁ አሁንም ክፍት ናቸው› ሲል አጠገቧ አረፍ አለ።
ምንም አላለችውም። የሆነ ስህተት እንደሠራች ደረሰችበት። ይሄን ወንድ ጎትተው ያመጡት እነዛ ባዶ ወንበሮች እንደሆኑ አልጠፋትም። ስለ ወንበሮቹ ሲያወራት ነበር አጠገቧ ሰው የሚፈልጉ ሁለት ባዶ ወንበሮች መኖራቸው ትውስ ያላት። ስህተት ሠርታለች። መቀመጥ የነበረባት አንድ ወንበር ላይ ወይም ደግሞ ሌሎችን ሰዎች በማይጋብዝ ስፍራ ላይ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ችግሮቻችንን ራሳችን ነው የምንፈጥራቸው። እነዛ ባዶ ወንበሮች ማሰብ ለማይችሉት ወንዶች ሰው እፈልጋለሁ ብቻዬን ነኝ ከማለት ሌላ ትርጉም አልነበራቸውም። ላያቸው ሁሉ መልዕክታቸው ያ ነው። ሰው ጤናማና ደስተኛ መሆን ከፈለገ ዘሪያውን ማጽዳት አለበት። እሷ ዙሪያዋን ሳታጸዳ ነበር ከወንዶች ሽሽት የጀመረችው። ከዚህ በፊት ለወንዶች የሚያጋልጣትን ውበቷን፣ ሰውነቷን፣ አይንና ተክለ ቁመናዋን ስትወቅስ ነበረች። አሁን ደግሞ ሁለት ወጠምሻ ወንዶችን ይዘውባት የመጡትን እነዛን ባዶ ወንበሮች ተቀየመቻቸው። ቢሆንም ግን የራሷ ፈላጭ ቆራጭ ራሷ ናት። ውበቷም ሆነ ሌሎች ነገሮች በእሷ ውሳኔ በኩል ሕልውና የሚያገኙ ናቸው።
አጠገቧ የተቀመጠው ወጣት ሊያማልላት የባጥ የቋጡን መለፍለፍ ጀመረ። በአንድ ጊዜ ጠላችው። ራሱን ያልሆነ ሰው አትወድም። ሰው መቼ ነው የሚያምረው ላላት ራሱን የሆነ ቀን ስትል የምትመልሰው መልስ አላት። ለሴት ልጅ ክብር ያለውና እውነተኛ ማንነቱን ይዞ የሚቀርባትን ወንድ እስክታገኝ ድረስ የራሷ ናት። ለምትወደው የሚሆን ብዙ ፍቅር፣ ብዙ ክብርና ብዙ እውነት ያላት ሴት ነበረች። ሴት የራሷ ስትሆንና ሌላ ሁለተኛ ሰው በነፍሷ ላይ ስትሾም ሌላ ሁለት ዓለም ናት ትላለች። ሴት በሥርዓት፣ ወንድ በማሰብ ሲኖር ፍቅር ማለት ያ ነው ትላለች። ሴት ከገንዘብ ስትልቅ፣ ወንድ ከነውር ሲሸሽ አብሮነት ማለት ያ ነው ትላለች። ሴት ክብሯን ስትጠብቅ፣ ወንድ በጎነት ሲማር ጋብቻ ማለት ያ ነው ትላለች። ሴት ከውበት ስትርቅ፣ ወንድ ራሱን ሲሆን ትዳር ማለት ያ ነው ትላለች። ጨዋዋ ሴት።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ሰኔ 3 /2014